የማይደክመው አቦሸማኔ

ይህ ሰው ድል ያላደረገበት የውድድር መድረክ፣ ክብረወሰኖችን ያላስመዘገበበትን ቻምፒዮናዎች ፈልጎ ማግኘት ይከብዳል። በ 25 ዓመታት የሩጫ ሕይወቱ ኦሊምፒክንና የዓለም ቻምፒዮናን ጨምሮ በሁሉም መድረኮች ደጋግሞ መንገስ ችሏል። ስፖርት የእድሜ ስራ ነው የሚለውን ሃሳብ ውድቅ ካደረጉ ጥቂት ስፖርተኞች ተርታ የሚያሰልፈውን እንቅስቃሴውን አሁንም አጠናክሮ እንደቀጠለበት ነው።

የረጅም ርቀት አትሌቲክስ ንጉሱ ቀነኒሳ በቀለ፤ በስፖርቱ ዓለም አስደናቂ ስኬቶችን ከተጎናጸፉና ከተዘመረላቸው ስፖርተኞች መካከል አንዱ ሊሆን ችሏል። አትሌቲክስን ከጀመረበት ወቅት አንስቶ በርካታ ጀብዱዎችን በመፈጸም የስፖርት ቤተሰቡን ቀልብ ገዝቷል። በአስደናቂ አሯሯጡና አጨራረሱ የሚታወቀው አትሌት፣ ሀገሩን በብዙ መድረኮች ወክሎ ለማመን የሚከብዱ ድሎችንም አስመዝግቧል።

በረጅም ርቀት ሩጫ ለመቁጠር የሚያዳግቱ ሜዳሊያዎችን አጥልቋል። በኦሊምፒክ ጨዋታዎች 3 ወርቆችን፣ በዓለም ቻምፒዮና 5 ወርቆችን፣ በዓለም ሀገር አቋራጭ ቻምፒዮና 11 ወርቆችን እንዲሁም በትልልቅ የዓለም ማራቶን ውድድሮች 2 ወርቆችን የግሉ አድርጓል። በ25 ዓመታት የአትሌቲክስ ሕይወቱ 26 የወርቅ ሜዳሊያዎችን ወስዷል። በእነዚህ ዓመታት በዓለም አቀፍ ተሳትፎ ወርቅን ጨምሮ ከ30 በላይ ሜዳሊየዎችን በመሰብሰብ ምትሃተኛ አትሌት መሆኑንም አስመስክሯል። በመም ውድድሮች ያሳየውን የአሸናፊነት ብቃት በጎዳና ውድድሮችም መድገም የቻለው አንጋፈው አትሌት፣ ምንም እንኳን ጉዳት ቢፈትነውም እጅ ሊሰጥ ግን አልፈቀደም።

ጉዳት አቅሙን እስከ መጨረሻው አውጥቶ እንዳይጠቀም ቢያደርገውም ቅሉ በተሰለፈባቸው ውድድሮች ግን ለማመን የሚከብዱ ድሎችን በማስመልከት ተወዳጅነትን ማትረፍ ችሏል። በእድሜ አንጋፋ ቢሆንም አሁንም ስራውን ሳይታክት እየሰራ ይገኛል። በቅርብ ጊዜ በተካሄዱ ውድድሮች የአሸናፊነት መንፈሱ አብሮት እንዳለም አስመልክቷል።

ከቀናት በፊት 42ኛ ዓመቱን የደፈነው አትሌቱ አሁንም ከፊቱ ለሚጠብቀው ትልቅ የዓለም ድግስ ራሱን በማዘጋጀት ላይ ተጠምዷል። በጥቂት ወራት ልዩነት በተሳተፈባቸው ማራቶኖች ባስመዘገበው ውጤት ኢትዮጵያን በፓሪስ ኦሊምፒክ በሚወክለው ብሄራዊ ቡድን ውስጥ በመካተቱ የትኩረት ማዕከል መሆኑን ቀጥሏል። ብዙ ክብረወሰኖችን በማሻሻል እና ሜዳለያዎችን የግሉ በማድረግ የብርታትና የጥንካሬ ተምሳሌት በመሆኑ ‹‹አንበሳ›› የሚለው ቃል መጠሪያው ሆኗል።

ውጤታማው የረጅም ርቀት ሯጭ፣ የአትሌቶች መፍለቂያ ከሆነችው በቆጂ ወጥቶ ዓለምን ጉድ አሰኝቷል። የአትሌቲክስ ሕይወቱን የጀመረው ገና በለጋ እድሜው ሲሆን በአስደናቂ ጽናት እና ታታሪነት በአትሌቲክሱ ነግሷል። በዚህም በዓለም አትሌቲክስ ከታዩት የምን ጊዜም ምርጥ የረጅም ርቀት ሯጮች ግንባር ቀደሙ ነው።

የ5 ሺ እና የ10 ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰኖችን ከ15 ዓመታት በላይ በእጁ ቆይቷል። የማራቶን ምርጥ ሰዓትን 2 ሰዓት ከ1 ደቂቃ ከ41 ሴኮንድ ማስመዝገብም ሶስተኛው ፈጣን አትሌት ነው። በአሌቲክስ ከ120 በላይ ውድድሮችን ያሸነፈ ሲሆን ለቁጥር የሚታክቱ ሜዳሊያዎችንና ዋንጫዎችን በማሸነፍ በዓለም አቀፍ ውድድሮችም በርካታ ድሎችን መጎናጸፍ ችሏል።

በሩጫ ዘመኑ ድንቅ ከሆኑ አትሌቶች ከባድ ፉክክር ቢገጥመውም ድንቅ አትሌት መሆኑን በተግባር ለዓለም ማስመስከር ችሏል። በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ አስደናቂ ድሎችን በመቀዳጀት ከምንጊዜውም የረጅም ርቀት ሯጮች አንዱ መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ።

አትሌቱ በመም ውድድሮች ካስመዘገበው አስደናቂ ስኬት በተጨማሪ በማራቶን የላቀ ውጤት በማስመዝገብ አሁንም ተስፋ እንዲጣልበት ማድረግ ችሏል። እኤአ በ2014ቱ የፓሪስ ማራቶን ውድድር 6ኛውን የማራቶን ፈጣን ሰዓት በ2፡05፡04 አሸንፏል። በርሊን ማራቶንን 2፡03፡03 በሆነ አዲስ የግል ምርጥ ሰዓት ሲያስመዘግብ፤ እአአ በ2019 እዚያው በርሊን ላይ ለዓለም ክብረወሰን እጅግ በቀረበ ሰዓት ድሉን ደግሞታል።

ቀነኒሳ በጉዳት ሳይሳተፍባቸው ከቀረባቸው መድረኮች በስተቀር ምርጥና የማይዋዥቅ ብቃቱን ለአትሌቲክስ ወዳጆች ማስኮምኮሙን ቀጥሏል። እድሜው አርባዎቹን ቢሻገርም በሚያስደንቅ ሁኔታ ላይ እንዳለ ተጨማሪ ድሎችን ለማስመዝገብ በጥረት ላይ ነው።

ቀነኒሳ ልደቱን ሲያከብር በፓሪስ ሀገሩን ወክሎ ሌላ ታሪክ ለመጻፍ የተለመደውን ዝግጅት እያደረገ ነው። የዓለም አትሌቲክስ የዓመቱ ምርጥ አትሌት፣ የትራክና የጎዳና ውድድሮች ምርጥ አትሌትና የኢትዮጵያ የዓመቱ በጎ ሰው የሚሉ ክብሮችን መቀዳጀት የቻለው ንጉሱ ታሪክን ለመጻፍ የአሸናፊነት መንፈሱን ይዞ የውድድሩን መጀመር ብቻ ይጠባበቃል።

አለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2016 ዓ.ም

Recommended For You