አካዳሚው በተለያዩ ርቀቶች የተሰጥኦ ልየታ ማዕቀፍ ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የ5ሺ ሜትርና የ3ሺ ሜትር መሠናክል የተሰጥኦ (ታለንት) ልየታ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ይፋ አደረገ። አካዳሚው 9ኛውን ሃገር አቀፍ የስፖርት ሳይንስ ጥናትና ምርምር ጉባኤውን በቢሾፍቱ ከተማ ትናንት አካሂዷል፡፡

ታዳጊ ስፖርተኞችን በመመልመል በሳይንሳዊ ስልጠና ለክለቦችና ብሄራዊ ቡድኖች የሚያበቃው የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ፤ ውጤታማነቱን በውድድሮች ላይ በሚያሳትፋቸው ስፖርተኞቹ አረጋግጧል። ከእነዚህ ስፖርቶች መካከል አትሌቲክስ ተጠቃሽ ሲሆን በ5ሺ ሜትር እና 3ሺ ሜትር መሰናክል ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስኬታማ አትሌቶችን አፍርቷል። ይህንንም ተከትሎ በዘርፉ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለውጤታማነት የሚያበቃ ማዕቀፍ በማዘጋጀት አስመርቋል።

ማዕቀፉ የምልመላ ስታንዳርድ፣ የአሰለጣጠን ዘይቤ፣ ምዘና እና ልኬትን አካቷል። አካዳሚው ውጤታማ የሆነበት ይህ ሞዴል በተግባር የተፈተሸ በመሆኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ ስፖርቱን ሊጠቅም እንደሚችልም ታምኖበታል። በቀጣይም በእግር ኳስ እና ሌሎች ስፖርቶች የሚዘጋጅ ይሆናል።

ከተቋቋመባቸው ዓላማዎች መካከል የስፖርት ጥናትና ምርምር ማካሄድ አንዱ የሆነው አካዳሚው ዓመታዊ ጉባኤው ላይም የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር አመራሮች፣ ክልሎች፣ የስፖርት ማህበራትና ተቋማት፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተወጣጡ የስፖርት ሳይንስ ምሁራን እንዲሁም የስፖርት ሙያተኞች ተካፍለዋል፡፡ “ከቤተሙከራ ወደ መስክ፥ ስፖርትን በምርምር መቀየር” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው ጉባኤ የተለያዩ ጥናታዊ ስራዎች ቀርበዋል።

በአካዳሚው የጥናትና ምርምር ማማከር ምክትል ዳይሬክተር አመንሲሳ ከበደ (ዶ/ር)፤ አካዳሚው በዘርፉ የአደረጃጀት ማሻሻያ በማድረግ በጥናትና ምርምር ዘርፍ ግምባር ቀደም ለመሆን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ጥናቶቹ ከአካዳሚው ሙያተኞች ባለፈ ከሀገርና የውጪ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን እየተከናወነ ሲሆን፤ ትኩረቱንም በስፖርት ችግር ፈቺ ጥናቶችና አሰራሮች ላይ አድርጓል። በአትሌቲክስ ስፖርት የምልመላና ምዘና ሞዴል ሲያዘጋጅ በቀጣይም በእግር ኳስና ቅርጫት ኳስ ስፖርቶች ላይ መሰል ስራዎችን የሚያከናውን ይሆናል። ከስፖርት ተቋማት ጋር በመሆንም መሰል ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

አካዳሚው ከምስረታው አንስቶ ባለፉት 13 ዓመታት 207 የሚሆኑ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ማሰራጨቱን የሚገልጹት የአካዳሚው ዳይሬክተር አቶ አምበሳው እንየው፣ አካዳሚው ከራሱ አቅም ባለፈ ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን የተሰሩት እነዚህ ጥናቶች መድረክ እንዲያገኙ፣ እንዲሰራጩና ተግባራዊ እንዲሆኑ ይደረጋል ብለዋል። ከዚህ ባለፈ ቤተሙከራዎችን በማደራጀትና በማበልጸግ የታዳጊ ሰልጣኞችንና ሌሎች ቡድኖችን ልኬቶችንና ግምገማ በማከናወን ላይ መሆኑንም አብራርተዋል።

በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በበኩላቸው፤ የጥናትና ምርምር ስራዎች በየትኛውም ዘርፍ ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን ጠቁመዋል። በስፖርቱ የሚሰሩ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን ተግባራዊ በማድረግና የፖሊሲ አካል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም አብራርተዋል። የአካዳሚው ዓላማ ከግብ እንዲደርስም ሳይንሳዊ ጥናቶችን አጠናክረው መቀጠልና ዘመናዊው ስፖርት በሚፈልገው ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። ለዚህም ባለድርሻ አካላት ተሳትፏቸውን ማሳደግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ከተቋቋመባቸው ዓላማዎች ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊ ወጣቶች በመመልመልና በማሰልጠን ለሃገርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ምርጥ ስፖርተኞችን ለማፍራት፣ የስፖርት ባለሙያተኞችን አቅም ለመገንባት እንዲሁም በስፖርቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን የሚፈታና ለስፖርት እድገት አስተዋጽኦ ሊያደርግ የሚችል ጥናትና ምርምር ማካሄድ ናቸው፡፡ ከአካዳሚው ባለሙያዎች ባለፈ በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባለሙያዎች የሚደረጉ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን በማሰራጨት የሃገሪቱ ስፖርት ልህቀት ማዕከል የመሆን ዓላማንም አንግቧል፡፡

ይህንን ዓላማ ለማሳካትም አካዳሚው ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ የስፖርት ጥናትና ምርምር ጉባኤውንም በየዓመቱ በማካሄድ ችግር ፈቺ የጥናት ውጤቶች መድረክ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ጥናቶቹ መድረክ ከማግኘት ባለፈ እንዲታተሙ በማድረግ የስፖርት ማህበራት፣ የማሰልጠኛ ማዕከላት እንዲሁም የስፖርት ተቋማት ተደራሽ ሆነው ተግባር ላይ እንዲውሉም ይደረጋል፡፡ ካለፈው ዓመት ጀምሮም ይፋ በሆነው ድረገጽ አማካኝነት ጥናቶቹን በመለጠፍ የዘርፉ ባለሙያዎች በቀላሉ ተጠቃሚ በመሆን ላይ ናቸው፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You