‹‹በክልላችን የሰለጠነ ፖለቲካ እንዲለመድና ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ መሰረት እየጣልን ነው›› – ፕሬዚዳንት ሙስጠፌ መሃመድ

የሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ከለውጡ በፊት የልማት እና የዲሞክራሲ ጥያቄ የሚነሳበት፤ የሰላም እና የጸጥታ ችግር የሚስተዋልበት ክልል ነበር፡፡ ክልሉ ሊታረስ የሚችል ሰፊ መሬት፣ ከፍተኛ መጠን ያለው የገጸ-ምድርና የከርሰ-ምድር ውሃ፣ የእንስሳት ሃበትና ማዕድናትን የያዘ ቢሆንም ይህን እምቅ ሃበት ወደ ኢኮኖሚ መንዝሮ የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ሥርዓት ባለመዘርጋቱ ክልሉ እያለው እንደሌለው ሆኖ፤ በልማትና እድገት ወደ ኋላ ተጎትቶ ዘመናትን አሳልፏል፡፡

ዛሬ ግን ሁኔታዎች ተለውጠዋል፡፡ እንደሀገር የመጣው ለውጥ ለሶማሌ ክልልም ተርፏል፡፡ የሶማሌ ክልል በሰላም፣ በዲሞክራሲና በልማት ፋና ወጊ ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞችም በመስክ ጉብኝታቸው ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡

በዋናነት ከክልሉ ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ ጋር ስለ ክልሉ ሰላምና ጸጥታ፣ አጠቃላይ በክልሉ ስለሚደረጉ የልማትና ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ-ግብሮች ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አጠናቅረን አቅርበንላችኋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

አዲስ ዘመን ፡- የሶማሌ ክልል ከለውጡ በፊትና በኋላ ያለበትን የሰላም፤ የልማትና የዴሞክራሲ ገጽታ እያነጻጸሩ በአጭሩ ቢነግሩን ?

ፕሬዘዳንት ሙስጠፌ ፡– በክልላችን በአብዛኛውን ጊዜ የፖለቲካ ሽኩቻዎች፣ ጎሳን መሰረት ያደረጉ ሽኩቻዎች የተለመዱ ነበሩ:: ብዙ ጊዜ የክልሉ አመራር ወደ ልማት ሳይሆን ወደ እርስ በእርስ ሽኩቻ የማድላት ባህሪ ነበረው::

ባለፉት ስድስት ዓመታት ይህን ችግር ቀርፈን የክልሉን አንድነት ባስጠበቀና እና ሕዝቡን ባስተሳሳረ መልኩ ሰላማችንን አስፍነን ወደ ልማት ገብተናል:: ለዚህም ነው ታች ድረስ ወርደን ለሕዝቡ አገልግሎት መስጠት የቻልነው:: ያም ሆኖ አሁንም በርካታ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ እናምናለን:: ዋናው የሰላም መሠረት ልማት ነው:: ስለዚህ በእኛ እምነት ልማትን ማቀላጠፍና ማሳደግ ከቻልን፤ የሕዝብ ጥያቄዎችን ከመለስን፤ የአመራሩን አንድነት ከጠበቅን፤ የሀገር ሽማግሌዎችን እና የሃይማኖት መሪዎችን ሚና እና ተሳትፎ ካሳደግን አሁን ያለው የሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ ይሄዳል እንጂ ወደኋላ ይመለሳል የሚል ሀሳብ የለንም::

በክልላችን ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያለን ቅርርብም እያደገ መጥቷል:: ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ጥሩ ውይይትና መቀራረብ አለ:: ስለዚህ በክልላችን የሰለጠነ ፖለቲካ እንዲለመድ፣ ነገሮች በውይይት እንዲፈቱ መሰረት እየጣልን ነው፤ የክልሉ ሰላም የጸና ነው፤ ጸንቶ እንደሚቀጥልም እምነት አለኝ:: የፉክክር መንፈስ ያላቸውም ጊዜውን ጠብቀው በምርጫ እንዲወዳደሩ መድረኩ ክፍት ነው:: እነዚህ ጉዳዮች በሙሉ ከለውጡ በፊት የሚታሰቡ አልነበሩም:: ለውጡ በሁሉም ረገድ ተስፋ ይዞ መጥቷል ማለት ይቻላል::

አዲስ ዘመን፡- ክልሉ በመሰረተ-ልማት ግንባታ አሁን ያለበት ሁኔታ እንዴት ይገለጻል?

ፕሬዚዳንት ሙስጠፌ ፡- እንደሚታወቀው ክልላችን ከሰላም እጦት ባሻገር ለረዥም ጊዜ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ብዙም ያልተሰሩበት ስለነበር ከፍተኛ የሕዝብ ሮሮ የነበረበት ክልል ነው:: ከለውጡ በኋላ በተገኘው ሰላም እና በፌደራልም ይሁን በክልል ደረጃ መንግሥት ከበጀት አቅርቦት ጀምሮ በሰጠው ትኩረት በተለያዩ ሴክተሮች በርካታ የልማት ሥራዎችን መሥራት ተችሏል:: ለምሳሌ መንገድን በተመለከተ፤ ክልሉ በጣም ሰፊ እንደሆነ ቢታወቅም የዚያን ያህል በአስፋልትም ይሁን በጠጠር መንገድ የተሸፈነ አልነበረም:: በአንዳንድ ክልሎች በወረዳ ደረጃ የአስፋልት መንገድ ተደራሽነት ሲነገር በእኛ ክልል በዞን ደረጃ እያሉ አስፋልት ያልደረሰባቸው ቦታዎች ነበሩ:: ይህን መሰረት በማድረግ የፌደራል መንግሥት ለሶማሌ ክልል ትኩረት በመሰጠቱ ተደማምረው ከ2ሺ ኪሎ ሜትር በላይ የሚሆኑ ከ17 በላይ የአስፋልት መንገዶችን መገንባት ተችሏል::

በእርግጥ በበጀት እጥረት እና በኮንትራክተሮች ድክመት ምክንያት በአንዳንድ ቦታዎች መጓተት የታየባቸው መንገዶችም አሉ:: ነገር ግን እነዚህ መንገዶች ሙሉ ለሙሉ ቢያልቁ የክልሉን የንግድ እንቅስቃሴና የሕዝብ አገልግሎት በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድጉ ናቸው ብለን እናምናለን:: ከዚህ በተጨማሪ በክልሉ በጀት የገጠር መንገድ ሥራ ተሠርቷል::

ክልሉ አጠቃላይ በነበረው 1ሺ 200 የሚገመት የገጠር መንገድ ላይ ሌላ 1ሺ ኪሎ ሜትር በመጨመር እስከ 2ሺ 200 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ተሠርቷል:: እነዚህም ቢሆኑ ሁሉም ተጠናቀዋል ማለት አይቻልም:: መንገድ በጣም ብዙ ገንዘብ ይፈልጋል:: በዚህ ምክንያት ቢያንስ በተያዘው በጀት ዓመት ሙሉ ለሙሉ እንዲጠናቀቁ እቅድ ተይዟል:: እስከ አሁን ግን ከ70 እስከ 80 በመቶ የጠጠር መንገዶች አልቀው አገልግሎት እየሠጡ ይገኛሉ::

የክልሉን ዋና ከተማ ጅግጅጋን ጨምሮ በከተሞች አካባቢ በጣም ከፍተኛ የመንገድ ችግር ነበር፤ ከከተማ ልማት አንጻር መንገዶች ወሳኝ መሆናቸው ስለታመነበት በአጠቃላይ ከ50 ኪሎ ሜትር በላይ አስፋልት ያስፈልጋቸዋል በተባሉ አራት ትላልቅ ከተሞች ማለትም በጂግጂጋ፣ በደጋሃቡር፣ በቀብሪደሃርና በጎዴ የውስጥ ለውስጥ የአስፋልት መንገዶች ተሠርተዋል::

የጂግጂጋ ከተማ ከለውጡ በፊት የነበረው መንገድ ከስምንትና ዘጠኝ ኪሎ ሜትር ያልበለጠ ነበር፤ በአሁኑ ጊዜ ወደ አርባ ኪሎ ሜትር ተሠርቷል:: ጎዴ እስከ 16 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ተሠርቶ ግማሹ ለአገልግሎት ክፍት ሲሆን ግማሹም በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል:: በቀብሪደሃርና ደጋሃቡርም ከ5 እስከ 6 ኪሎ ሜትር በላይ ተሠርቷል:: እነዚህ በቂ ናቸው ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ከነበረው በጀት አንጻር በጣም ጥሩ ጅምር እንደሆኑና ሕዝብና መንግሥትን ያቀራረቡ ሥራዎች እንደሆኑ እናምናለን፤ የክልላችንንም ገጽታ የቀየሩ ናቸው::

ወደ ንጹህ ውሃ አቅርቦት ስንመጣ በክልላችን ከለውጡ በፊት በአጠቃላይ የንጹህ ውሃ አቅርቦት ሽፋን የገጠሩም የከተማውም ተደምሮ በአማካይ 19 በመቶ ነበር:: በአሁኑ ሰዓት ይህንን ምጣኔ ወደ 47 በመቶ ማሳደግ ተችሏል:: በዚህ ሂደት ከ309 በላይ የጥልቅና መካከለኛ ጉድጓዶች ቁፋሮ ተከናውኗል፤ 15 መለስተኛ የውሃ ጋኖች ተሠርተዋል፤ ከ15 በላይ ደግሞ የበርካታ መንደሮች ውሃ አቅርቦት ሥራዎች ተሠርተዋል:: በእነዚህና በከተሞችም ጂግጂጋን ጨምሮ ጎዴ፣ ቀብሪደሃር ፣ ደጋሃቡር ፣ፊቅ ፣ ዋርዴር እና ሌሎችም የዞን ከተሞች የውሃ አቅርቦታቸው አድጓል:: ይህ በቂ አይደለም፤ በቀጣይም ከ47 በመቶ በላይ ለማድረስ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ::

ጤናን በተመለከተ በክልሉ ከለውጡ በፊት ሥራ ላይ የነበሩ ሆስፒታሎች ዘጠኝ ብቻ ነበሩ:: ከለውጡ በኋላ አሁን በጎዴና በጂግጂጋ እየተጠናቀቁ ያሉ የእናቶችና ሕጻናት ሆስፒታሎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 14 ተጨማሪ ሆስፒታሎች የተገነቡ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 12 የሚሆኑት ተጠናቀው ወደ ሥራ ገብተዋል:: በዚህም ከለውጡ በፊት በነበሩ ሆስፒታሎች ላይ ከመቶ ፐርሰንት በላይ አዳዲስ ሆስፒታሎችን በመገንባት ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ ተችሏል ማለት ነው::

በተለያዩ አካባቢዎች ባለፈው ዓመት እንዲሠሩ ታስበው በበጀት ምክንያት የቆሙ አሥር ሆስፒታሎችም ሥራቸው ይጀመራል ብለን እናምናለን:: ይሄ ሲሆን የዛሬ ሁለት ዓመት ክልሉ ከነበሩት ዘጠኝ ሆስፒታሎች ተጨማሪ 24 ተገንብተው አጠቃላይ የሆስፒታሎችን ቁጥር ወደ 33 ለማሳደግ እቅድ ተይዞ እየተሠራ ይገኛል:: ይህ ትልቅ እምርታ ነው::

ከዚህ በተጨማሪ ከ50 የማያንሱ ዘመናዊ የጤና ማዕከሎችም ተሠርተው በሆስፒታሎች አካባቢ የሚኖረውን ጫና ለመቀነስ እያገዙ ይገኛሉ:: አብዛኛውን ሰው መጀመሪያ ላይ በአካባቢው በሚገኘው ክሊኒክ የሚታከም ስለሆነ ወደ ሆስፒታል ሊመጣ የሚችለውን ሰው እዚያው እያስተናገዱ ይገኛሉ:: ከነዚህም መካከል አስር የሚሆኑት ዘመናዊ የጤና ኬላዎች በተለይም የወላድ እናቶችን ቀዶ ጥገናን ያከናውናሉ:: በገጠር አካባቢ የሚገኙ እናቶች ለመውለድ ሆስፒታል ድረስ መምጣት ሳይጠበቅባቸው፤ በጤና ኬላዎች የኦፕሬሽን ክፍል ተዘጋጅቶላቸውና ባለሙያ ተመድቦላቸው በቀዶ ጥገና እንዲወልዱ ተመቻችቷል:: በዚህም ምክንያት ይህ ተግባራዊ በሆነባቸው አካባቢዎች የእናቶችና ሕጻናት ሞት በከፍተኛ ደረጃ ቀንሶ ዜሮ በሚባል ደረጃ ላይ ደርሷል:: ይህንን ተሞክሮ በማስፋፋትና ሌሎችም ክሊኒኮች ተመሳሳይ ሥራ እንዲሠሩ በማድረግ በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥ ለማስመዝገብ እየተሠራ ይገኛል::

የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ሥርዓትን በተመለከተም ከለውጡ በፊት ክልላችን ምንም አልበረውም ማለት ይቻላል:: በአሁኑ ሰዓት ከ30 በላይ ወረዳዎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎትን ለሕዝቡ እንዲሰጡ ከጤና ሚኒስቴር ጋር ተዋውለን እየሠራን እንገኛለን:: ያም ሆኖ ከሀገር አቀፍ ስታንዳርድ እና ከሌሎች ክልሎች አፈጻጸም አንጻር ሲታይ ዝቅተኛ ነው::

ይህ ማለት ከ30 በመቶ በላይ በወረዳዎች እና በከተማ አስተዳደሮች የሚገኘው ሕዝብ የጤና ሽፋን እያገኘ ነው ማለት ነው:: በሚቀጥለው ዓመት ሽፋኑን 60 በመቶ ለማድረስም እየተሠራ ይገኛል::

የትምህርት ሴክተሩን በተመለከተ ከለውጡ በኋላ በተለያዩ አካባቢዎች ከ576 በላይ የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ከ90 በላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም 12 የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ተሠርተዋል:: የአዳሪ ትምህርት ቤቶቹ ገና ወደ አገልግሎት አልገቡም፤ አምስቱ በዘንድሮው ዓመት ሥራቸውን ይጀምራሉ ብለን እናስባለን፤ ሌሎቹም በሂደት ወደ ሥራ እንዲገቡ በጀት እያመቻቸን ነው::

ከመማሪያ ክፍሎችና ከተማሪዎች ምጣኔ አንጻር ከለውጡ በፊት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአንድ ክፍል እስከ 107 ተማሪዎች ይማሩ ነበር:: በአሁኑ ሰዓት በተሠሩት አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎች ምክንያት ጫናውን በመቀነስ በአንድ ክፍል ውስጥ የነበረውን የተማሪዎች ምጣኔ ወደ 70 ማውረድ ተችሏል::

የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ያየን እንደሆነ፤ በአንድ ክፍል ውስጥ በአማካይ ወደ 99 ተማሪ ነበር የሚማረው፤ በተሠሩ ሥራዎች ይህንንም ወደ 70 ማውረድ ተችሏል:: አሁንም በቂ ነው ማለት አይደለም፤ በስታንዳርዱ መሰረት ወደ 50 እና 40 ማውረድ ያስፈልጋል:: ነገር ግን ጥሩ ጅምር አለ ማለት ይቻላል::

በከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ላይ ለውጥ መጥቷል የምንለው ከጥራት አንጻር ኩረጃን ማስቀረት በመቻሉ ነው:: የትምህርት ጥራትን በተመለከት በተለይም በ12ኛ ክፍል እና በ8ተኛ ክፍል ፈተና ላይ በክልላችን ኩረጃ በመንግሥት ደረጃ የሚበረታታ እንደነበር ይታወቃል:: ወላጆችም፣ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ያሉ አመራሮችም፣ የፖለቲካ አመራሩም፣ ተማሪዎችን በገፍ ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ማሻገር ጥሩ ነው ብለው ስለሚያምኑ ኩረጃን ያበረታቱ ነበር:: ኩረጃ በከፍተኛ ደረጃ ተማሪዎች እንዳያጠኑ፣ እንዳይማሩ፣ የሚያልፍና የሚወድቅ ስለማይታወቅና በጥራት ላይ የተመረኮዘ ስላልሆነ ስንፍናን አብዝቶ ነበር:: ይህንን በማስቀረት ትምህርት ዋጋ እንዲኖረው፤ አመራሮች የተማሩ መሆናቸውን በማረጋገጥ፤ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ያላቸውን ከሥራ በማሰናበት፣ አንድ ሰው የእድገቴ መሰረት ትምህርት ነው ብሎ እንዲያምን በከፍተኛ ደረጃ ሥራ ተሠርቷል:: በተሠራው ሥራም በወጣቱ ዘንድ ለውጥ እየታየ መጥቷል::

ክልሉ በኤሌክትሪክ አቅርቦት እና ሽፋን ደረጃ ዝቅተኛ ነበር ማለት ይቻላል:: ከለውጡ “በፊት በፌዴሬሽን ምክር ቤት በተደረገ ጥናት የክልላችን የመብራት አቅርቦት ከሁሉም ክልሎች በጣም ዝቅተኛ ነው:: ያን መሠረት በማድረግ ጥሩ ሥራ ከሠሩ ተቋማት መካከል መብራት ኃይል አንዱ ነው:: ከለውጡ በኋላ በክልሉ ወደ 20 የሚሆኑ ወረዳዎች የ24 ሰዓት መብራት አግኝተዋል:: በነዚህ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ በጠቅላላው ሲደመሩ ከሰባ የማያንሱና በተለያየ ደረጃ ያሉ ከተሞችም የመብራት አገልግሎት አግኝተዋል:: ይህ ደግሞ ለኢንዱስትሪዎች መስፋፋት፣ ለሕዝቡ ኑሮ መሻሻል፤ ለእርሻ እና ለተለያዩ ተጓዳኝ ሥራዎች እድል ፈጥሯል::

አዲስ ዘመን፡- ክልሉ ከግብርና አንጻር ምን ምን ተግባራትን አከናውኗል? በተለይም የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ- ግብሩን ለማሳካት ግብርናው የሚጠበቅበትን ሚና እንዴት እየተወጣ ነው?

ፕሬዚዳንት ሙስጠፌ ፡-ግብርናን ያየን እንደሆነ፤ ክልሉ ካለው የመሬት ስፋት አንጻር ብዙ አልተሠራም ነበር፤ ክልላችን ከ10 ሚሊየን ሄክታር የማያንስ ሊታረስ የሚችል መሬት አለው፤ ከዚህ ውስጥ ከለውጡ በፊት ሲታረስ የነበረው ወደ 400ሺ ሄክታር ነበር:: በአሁኑ ጊዜ ወደ 900 ሺ ሄክታር ማልማት ተችሏል::

በሀገር አቀፍ ደረጃ በተያዘው በምግብ ራስን የመቻል መርሃ-ግብር ተጨማሪ 50ሺ ሄክታር በማልማት በአጠቃላይ ወደ 1 ሚሊዮን ሄክታር ለማሳደግ እየሠራን እንገኛለን::

በአጠቃላይ በክልላችን ይመረት የነበረው ምርት የተለያዩ ሰብል አይነቶችን ጨምሮ በዓመት ከ10 ሚሊዮን ኩንታል የማይበልጥ ነበር:: ከለውጡ በኋላ በተሠራው ሥራ በመካናይዜሽን፣ በመስኖ ተጨማሪ መሬት በማረስ ሕብረተሰቡ ወደ እርሻ እንዲገባ በማበረታታት በአሁኑ ጊዜ ወደ 26 ሚሊዮን ኩንታል የተለያዩ ምርቶችን ማምረት ተችሏል:: ከነዚህ ውስጥ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ማሽላ የሚጠቀሱ ሲሆን ክልሉ ኤክስፖርት የሚያደርገው ሽንኩርት እንዲሁም በበቂ ደረጃ የሚያመርተው ቲማቲምም ይገኙበታል::

ግብርና ሴክተሩ በዚህ ብቻ እንዳይታጠር ከ300 የማያንሱ ትራክተሮችና በሺዎች የሚቆጠሩ የውሃ ፓንፖች ተገዝተው ለኅብረተሰቡ ከተከፋፋሉ በኋላ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አንጻር የራሳቸውን የጎላ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ::

በዘንድሮ ዓመት በጎዴና ሲቲ ዞኖች በ3 ሺ ሄክታር ላይ የሩዝ ምርት ለማምረት በሙከራ ደረጃ እየተሠራ ነው:: ይህ እቅድ ከተሳካ በሀገር አቀፍ ደረጃ ድጋፍ እየተደረገልን ስለሆነ ከዚህም በላይ እስከ 20 እና 30ሺ ሄክታር መሬት በሩዝ የማንሸፍንብት ምክንያት አይኖርም:: ስለዚህ በግብርናው ዘርፍ እንዲህ አይነት እምርታዎች እየታዩ ይገኛሉ::

ከምንም በላይ የሚያስደስተው ግን ሕዝቡ ከአሁን በፊት በሰላም እጦት ምክንያት የማያርሰውን መሬት ማረስ መጀመሩ ነው:: በምግብ እርዳታ ላይ የተመረኮዘውን አስተሳሰብ ትቶ ኑሮው ከመሬት እንደሚገኝ በማመን ወደመሬት አጎንብሶ ሥራ እየሠራ ይገኛል:: የአስተሳሳብ ለውጥም አሳይቷል::

አዲስ ዘመን፡- በክልሉ የመስኖ ልማት እንቅስቃሴ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ምን ያህል ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው?

ፕሬዚዳንት ሙስጠፌ ፡- ክልሉ ካለው ሀብት አንጻር በመስኖ ልማት የሚፈለገውን ያህል ተሠርቷል ባይባልም ጥሩ ጅምር አለ:: ዋቤ ሸበሌ፣ ገናሌ፣ ዳዋ፣ ወይብን የመሳሳሉ አራት ትልልቅ ወንዞች በክልሉ ይገኛሉ:: ከእነዚህም በተጨማሪ በሲቲ ዞን አካባቢ በጣም በርካታ ክምችት ያለው የከርሰ ምድር ውሃ አለ:: ካለው ሀብት አንጻር ገና ብዙ መሥራትን ቢጠይቅም በመስኖ ልማት ጥሩ የሚባል ጅምር አለ:: ለምሳሌ በዘንድሮው ዓመት በፌደራል መስኖ እና ቆላማ ሚኒስቴር ድጋፍ ከስምንት ቢሊየን ብር በላይ የመስኖ ፕሮጀክቶች ተጀምረው እየተሠሩ ነው:: እነዚህ ተጠናቀው ወደ ሥራ ሲገቡ በክልሉ ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣሉ፤ ለሀገሪቱ የሚተርፍ ምርት ይመረታል ብለን እንጠብቃለን:: ለምሳሌ በጎዴ አካባቢ ሊታረስ ከሚችለው መሬት አብዛኛው እየታረሰ አይደለም፤ ይህ የአቅም ጉዳይ ነው፤ ካፒታል ወይም ገንዘብ ይፈልጋል:: በዚህ ምክንያት ያልተሠሩ ሥራዎች አሉ:: ነገር ግን ቀደም ሲል ከነበረው ሁኔታ አንጻር በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ መነቃቃት እና ጥሩ ጅምር እንዳለ ይሰማናል::

ከግብርናው ጋር ተያይዞ በእንስሳት ሃብትም በጣም ጥሩ እምርታ እየታየ ይገኛል:: በክልሉ ከ50 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ እንስሳት እንዳሉ ይገመታል:: ያልዳበረ የእንስሳት ገበያ አሁንም ማነቆ በመሆኑ ከውጭ ገበያ አቅርቦት አንጻር የሚቀሩ ሥራዎች አሉ:: ክልሉ በእንስሳት ሃበት የታወቀ ቢሆንም የእንስሳት ኳራንቲን ማዕከላትን ሠርቶ እንስሳት ጤናቸው ተጠብቆ ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ ከማድረግ አንጻር አሁንም ተግዳሮቶች አሉ::

አዲስ ዘመን፡- ክልሉ በርካታ የእንስሳት ሃበት እንዳሉት ይታወቃል፤ ድርቅ በሚከሰት ጊዜ እንስሳት የመኖ እጥረት እንዳይገጥማቸው ምን የተሠሩ ሥራዎች አሉ ?

ፕሬዚዳንት ሙስጠፌ፡– የእንስሳት ልማትን በተመለከተ ጥሩ ለውጥ እየታየበት ካለው አንዱ የመኖ አቅርቦት ላይ እየተሠራ ያለው ሥራ ነው:: በተለይም በመስኖ እና በመደበኛ ዝናብ ወቅት የእንስሳት መኖን እያመረቱ በማከማቸት በድርቅ ጊዜ ለእንሳስት በመስጠት፣ በድርቅ ለተጎዱ ለሌሎች ክልሎች ድጋፍ በማድርግና ለጎረቤት ሀገራትም በመሸጥ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ይቻላል:: ይህን ልምድ እያሳደግን ክልሉ ያለውን ሰፊ መሬትና የውሃ ሀብት በመጠቀም በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ለሚገኙ ጎረቤት ሀገራት ጭምር የእንሰሳት መኖ ለማቅረብ እየሠራን ነው::

አዲስ ዘመን፡ ከሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር አንጻር ክልሉ ምን ይመስላል?

ፕሬዚዳንት ሙስጠፌ፡-በሌማት ትሩፋት ፕሮግራም የእንስሳት ሃብትን ለማዘመን እና ምርታማነትን ለማሳደግ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል:: በተለይ ከአሁን በፊት ሕዝባችን ከግመል፣ ከቀንድ ከብት፣ ከፍየል እና በግ ውጭ ከሌሎች እንስሳት የሚገኘውን ምርት ትኩረት አያደርግም ነበር:: በአሁኑ ሰዓት በዶሮ እርባታ፣ በንብ እርባታ እና በዓሳ እርባታ ላይ በማህበር ተደራጅቶ ከፍተኛ ሥራዎችን እየሠራ በምግብ ራስን ከመቻልም አልፎ ሕዝቡ የተመጣጠነ ምግብ የማግኘት እድል እንዲኖረው እየተደረገ ነው::

አዲስ ዘመን፡- በክልሉ የተገኘው ሰላምና መረጋጋት ኢንቨስትመንትን እንዴት እያነቃቃው እንደሆነ ቢያብራሩልን?

ፕሬዚዳንት ሙስጠፌ ፡- ሰላም የሁሉ መሰረት ነው፤ ቀደም ሲል በክልላችን በኢንቨስትመንት ደረጃ ይህ ነው የሚባል ሥራ አልነበረም:: ለዚህም ምክንያቱ አንደኛ የሰላም እጦት ነበር፤ ሁለተኛ ኢንቨስተሩም ዋስትና ስለሌለው መምጣት አይፈልግም ነበር፤ በተጨማሪም የነበረው ሥርዓት ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ አልነበረም፤ በነዚህ ምክንያቶች ብዙ ኢንቨስትመንት አልነበረም::

ከለውጡ በኋላ ግን እንዳያችሁት ከጂግጂጋ ከተማ ጀምሮ በአገልግሎት ዘርፍ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፤ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተለያዩ አይነት ፋብሪካዎች (የአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ የቆርቆሮ ፋብሪካ፣ የመኪና መገጣጠሚያ፣ የእምነበረድ ፋብሪካና ሌሎችም በርካታ ፋብሪካዎች ተከፍተዋል::

ከለውጡ በፊት ክልላችን ወደ 85 የሚደርሱ አነስተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ ፋብሪካዎች ብቻ ነበሩት:: ከለውጡ በኋላ ግን ከ230 በላይ አዳዲስ ፋብሪካዎች ተከፍተዋል:: በአሁኑ ሰዓት በአጠቃላይ ከ318 በላይ ፋብሪካዎች በሥራ ላይ ይገኛሉ:: በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች በተለይም ወጣቶችም የሥራ እድል ፈጥረዋል:: በርካታ ካፒታልም ይንቀሳቀስባቸዋል:: ስለዚህ በክልላችን ከታዩት እምርታዎች በዋናነት መጠቀስ ያለበት የግል ሴክተሩ አስተዋጽኦ ነው:: የግል ሴክተሩ በከፍተኛ ደረጃ ኢኮኖሚ እያንቀሳቀሰ፣ የሥራ እድል እየፈጠረ፣ ምርት እያመረተ ይገኛል::

አዲስ ዘመን ፡- በክልሉ የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት መርሃ-ግብር እንዴት እየተከናወነ ይገኛል?

ፕሬዚዳንት ሙስጠፌ፡– አረንጓዴ ዐሻራ ለሀገራችን ያለው አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ በእኔ እምነት ከየትኛውም አካባቢ በላይ ለሶማሌ ክልልና ለቆላማ አካባቢዎች ወሳኝ ነው ብዬ አምናለሁ:: ምክንያቱም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በከፍትኛ ደረጃ ሕዝብ እየተጎዳ ይገኛል:: የእንስሳት ሀብቱ እየጠፋ ይገኛል፤ ድርቅ እየተመላለሰ ይገኛል::

በዚህም ምክንያት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር ሲጀምር ክልላችን ቁርጠኛ አቋም ይዞ ሠርቶበታል:: የአካባቢ ጥበቃ እና የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ በካቢኔ ደረጃ ቡድን አዋቅረን ሥራዎችን እየሠራን እንገኛለን:: ባላፉት ሶስት ዓመታት ከ11 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል:: በአንዳንድ ቦታዎች በመጽደቅ ላይ ችግሮች እንዳሉም ገምግመናል:: ስለዚህ በአሁኑ ሰዓት እንደስትራቴጂ የወስድነው በከተሞች አካባቢ ትኩረት ለማድረግ ነው፤ በዋናነት ችግሩ ያለው ሕዝብ በተሰበሰበባቸው ከተሞች አካባቢ ስለሆነና ለቁጥጥርም ስለሚያመች ከተሞች አካባቢ ላይ ትኩረት እናድርግ የሚል አቅጣጫ ይዘናል::

በገጠር አካባቢ ደግሞ ያለውን እንዳናጣ ጥረት ማድረግ የሚል አቅጣጫ ተይዟል:: ምክንያቱም ክልላችን ሰፊ ነው፤ በአብዛኛው የተለያዩ አካባቢዎች የቆላ ዛፎች አሉ፤ ያለንን ደን ጠብቀን በከተሞችና ሕዝብ በሰፈረባቸው አካባቢዎች ደግሞ ብንተክል አካባቢን መጠበቅ እንችላለን ብለን ስላመንን በዚህ ደረጃ ብዙ ሥራዎች ተሠርተዋል:: በእኛ እምነት ከዚህም በላይ መሥራት እንችላለን ብለን እናምናለን፤ ጅምሩም ጥሩ ነው:: ከዚህ አንጻር በጎዴ፣ በጂግጂጋ፣ በደጋሃቡር፣ በቀብሪደሃር እና በሌሎችም ከተሞች አበረታች የሆኑ የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራዎች ተሠርተዋል:: እነዚህ አካባቢዎች በአሁኑ ሰዓት ያላቸው የደን ሽፈን ከምን ጊዜውም የተሻለ ነው::

አዲስ ዘመን፡- በከተሞች አካባቢ የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመፍታት የተሠሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን አይተናል፤ እስከ አሁን የተሠሩት ምን ያህል አጥጋቢ ናቸው? በቀጣይስ ምን ለመሥራት ታቅዷል?

ፕሬዘዳንት ሙስጠፌ፡- በክልላችን የመኖሪ ቤት አቅርቦት ችግር በመኖሩ አቅመ ደካሞችን ወይም አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ሰዎች ለማገዝ ከመጀመሪያው ዓመት ጀምሮ ትኩረት ሰጥተን በሁሉም ዞኖች ብዙ ገቢ ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በጥሩ ስታንዳርድ ቤቶች እንዲሠሩ እንቅስቃሴ ተደርጓል::

በዚህም ምክንያት በአሥራ አንዱም የዞን ከተሞች በአጠቃላይ ከ1ሺ 200 በላይ የመኖሪያ ቤቶች ተገንብተዋል:: ይህንን በየዓመቱ ማስቀጠል ቢታሰብም የበጀት እጥረት በመኖሩ ምክንያት አልተቻለም:: ነገር ግን አሁን ከባንኮች ጋር በመተባባር በአዲስ መልክ ተጨማሪ ቤቶች መገንባት አለባቸው ብለን እናምናለን:: በክልሉ ኮንዶሚኒየምና አፓርታማዎች የሉም፤ የሕዝቡ ቁጥር እየጨመረ በመጣ ቁጥር የመኖሪያ ቤት ችግር ይስተዋላል:: በከተሞች አካባቢ መጨናነቅና የቤት ኪራይ በከፍተኛ ደረጃ ሕዝብን እያማረረ ስለሆነ ትኩረት ሰጥተን የቤት አቅርቦትን ለማሳደግ እየሠራን እንገኛለን:: ካለው ፍላጎት አንጻር እስከ አሁን የተሠሩት ሥራዎች በቂ ናቸው ማለት ባይቻልም ፤ ጥሩ ጅምር ናቸው ብለን እናምናለን::

አዲስ ዘመን ፡- ክልሉ ችግሮችን በውይይት ፈትቶ ወደ ልማት ገብቷል፤ ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብም ሰላሙን አረጋግጦ ወደ ልማት እንዲገባ ስለተጀመረው ሀገራዊ ምክክር ምን መልዕክት ያስተላልፋሉ?

ፕሬዚዳንት ሙስጠፌ፡- እንደሚታወቀው በሀገራችን ፖለቲካ ብዙ ጊዜ ችግሮችን የምንፈታው በጠመንጃ ነው:: የባለፉት መቶ ዓመታት የሀገራችን ታሪክ እንደሚያሳየው መንግሥታት የሚመጡት በጠመንጃ ነው፤ ስልጣን ላይ ያሉት የሚወርዱት በጠመንጃ ነው፤ ስልጣን ላይ የሚወጡትም በጠመንጃ ነው:: እንዲህ አይነት የፖለቲካ ባህል ለረዥም ዘመን አብሮን ኖሯል:: ይህን የፖቲካ ባህል ለመለወጥ መመካከርና መወያየት ያስፈልጋል::

የሚያከራክሩ ሀገራዊ ጉዳዮችን በውይይት መፍታት እንችላለን ተብሎ የተቀመጠው አቅጣጫ በጣም አበረታች ነው:: የተጀመረው ሀገራዊ የምክክር ሂደትም ይንን ባህል ይለውጣል ብዬ አምናለሁ:: በሁሉም ሀገራት ግጭቶች ይኖራሉ፤ ከጎረቤት ሀገራት አንጻር ሲታይ የእኛን ሀገር ትንሽ ለየት የሚያደርገው መብዛቱ ነው፤ ለሀገራችን እድገት ዋናው ማነቆ የሰላም እጦት ነው:: ረዥም ጊዜን በግጭት አሳልፈናል፤ ይህ መቆም አለበት::

ሕዝቡ በጣም ጨዋ ሕዝብ ነው፤ ምንም ችግር የለበትም:: በፈለግነው የሀገራችን አካባቢዎች ብንሄድ በጥሩ ሁኔታ ነው የምናስተናግደው:: ሀገራችን ሀብታም ነች፤ እዚህ ክልል ብቻ ያለው መሬትና መአድን ለሀገሪቱ ይበቃል:: በሁሉም ክልል ተመሳሳይ ሀብት አለ፤ የተማረ የሰው ኃይል አለ፤ እነዚህ ሁሉ ነገሮች እያሉን ይህቺ ሀገር የማትለወጠው ወደ ግጭት ስለምንገባ ነው:: ሰለዚህ ይህንን ለማስቀረት አሁን የተጀመረው የውይይትና የምክክር መድረክ የምናተርፍበት እንጂ የምንጎዳበት ባለመሆኑ ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት ሁላችንም የድርሻችንን እንድንሰጥ በዚሁ አጋጣሚ መልዕክቴን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ:: አመሰግናለሁ !

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You