‹‹ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የሚዲያው ሚና የማይተካ ነው›› – ጥበቡ በለጠ  የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚዲያ ፎረም ም/ሰብሳቢ

በየትኛውም ዓለም የፖለቲካ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ሽግግር ውስጥ የሚዲያ ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ሚዲያው በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለ ለሀገር ዕድገትና ለዜጎች ብልጽግና መጎልበት የራሱን በጎ አሻራ ማሳረፍ ይችላል። ባልተገባና ጥንቃቄ በጎደለው ሁኔታ ጥቅም ላይ ከዋለም ደግሞ በዛው ልክ የሚያስከትለው መዘዝ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም።

እንደ አገርም ሕዝብን ለልማትና ዴሞክራሲ በማነሳሳት ችግሮች ሲያጋጥሙም ተገቢ በሆነና አግባብነት ባለው መልኩ በመፍታት በኩል የበኩሉን ሚና መወጣት ይችላል። እስካሁንም ቀላል የማይባሉ የሚዲያ ውጤቶች በኢትዮጵያ ልማት እንዲፋጠንና ዴሞክራሲ እንዲተዋወቅ የማይተካ ሚና ተጫውተዋል፡፡

በሌላም በኩል ግጭትና አለመግባባትንም በመፍጠር የኢትጵያን ችግር የሚያወሳስቡ ሚዲዎችም በርካቶች ናቸው። ቀን ከሌት ግጭትና ብጥብጥን የሚሰብኩና ዜጎችን አብሮነት የሚያውኩ መረጃዎችን የሚለቁ በርካታ ሚዲያዎች አሉ። እነዚህ ሚዲያዎች ገንዘብ ያግኙ እንጂ የዜጎች በሰላም ውሎ ማደርና በሕይወት መቆየት አያሳስባቸውም። የሀገር ሕልውናና በሰላም መቆየት ግድ አይሰጣቸውም። ይህ ደግሞ በሌሎች ሀገራት እንደታየው ሁሉ ውጤቱ የከፋና በቀላሉም ለማረም የማይቻል ነው፡፡

እነዚህን ሁለት የሚዲያ ገጽታዎች በመገንዘብና በተቻለም መጠን በጎ ጎናቸውን ለሀገር ጥቅም እንዲያውሉት በማሰብ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምክክር ኮሚሽን ሚዲያው በሀገራዊ መግባባቱ ላይ የራሱን በጎ አሻራ እንዲያሳርፍ የበኩሉን ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ሚዲያ በሕግ የበላይነትና ዲሞክራሲ ግንባታ ላይ ወሳኝ ሚና እንዳለው ሁሉ አገርን ከአንድ ምዕራፍ ወደሌላ ምዕራፍ ያሻግራል ተብሎ በብዙ ታምኖበት በርካታ ባለሙያዎችና ምሁራን እውቀታቸውን ጊዜያቸውን አቅማቸውን ሁሉ አሟጠው እየተሳተፉበት ያለውን የምክክር ሂደትም ለሕዝብ በማድረስ እና የሕዝቡንም ተሳትፎ በማሳደግ በኩል ትልቅ የቤት ስራ የተሰጠው ሆኗል።

ሚዲያ በሀገራዊ ምክክር ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለውም እንዲሁም ሚናውን ይበልጥ በተጠናከረና በዳበረ መልኩ ይወጣ ዘንድ በጥቅምት ወር የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚዲያ ፎረም በሚል አንጋፋና ወጣት ባለሙያዎች ከግልና ከመንግስት ተቋም ተሰባስበው እንዲመሰረት ሆኗል።

ይህ ፎረም ኮሚሽኑ የሚሰራቸውን ስራዎች ወደ ሕህዝብ የማድረስ ብሎም ራሱ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ ለአገር ይጠቅማል ያለውን ሃሳብ ላይ አቅዶ በመስራት ብዙዎችን መንገድ ሲያሳይም ቆይቷል። ይህ ደግሞ ሚዲያዎች ለአገር ሊያበረክቱ ከሚገባቸው አስተዋጽዖ አንዱና ዋነኛውም ነው።

በምክከር ኮሚሽኑ የስራ እንቅስቃሴም ሆነ አገር ምክክር ላይ ያለች እንድትመስል በማድረጉ በኩል ሚዲያው እስከ አሁን የሰራው ስራ የሚናቅ ባይሆንም አሁንም ግን ስራው የተጠናቀቀ ባለመሆኑ ከፍ ያለ ተሳትፎን ማድረግም እንደሚጠበቅና እንደሚያስፈልግ ይነሳል።

ሚዲያዎቹ በቀጣይ ለሚመጡ ለውጦችም ይሁን እንደ አገር የጀመርነው የምክክር ሃሳብ ዳር ደርሶ እንደ አንድ አገር ሕዝቦች በአንድ አፍ ተናጋሪ በአንድ ልብ መካሪ እስክንሆን ድረስ ሚናቸው ይቀጥል ዘንድም የቤት ስራው እየተሰጣቸው ነው።

መገናኛ ብዙሃኑ ለሕዝብ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ በማቅረብ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ እንዲያጠናክሩም ምክክር ኮሚሽኑ የሚችለውን የሚዲያ ተቋማቱም በገንዘብ በሰው ኃይል በጊዜ ሊረባረቡም እንደሚገባቸው ይነሳል።

መገናኛ ብዙሃን በስራዎቻቸው በሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ስራዎችን እንዲያከናውኑና የሀሰት መረጃዎችን በመመከት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ያስፈልጋል። በቀጣይ የሚከናወነው ብሔራዊ ምክክር የተሳካ እንዲሆን መገናኛ ብዙሃን አወንታዊ ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ እየቀረበላቸው ነው።

በተለይም ጽንፈኝነትን እና አግላይነትን በማከም በኩል ባለፉት ጊዜያት የተሰሩት ስራዎች ጥሩ ቢሆኑም አሁንም ለሕህዝቡ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ በማቅረብ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር ያስፈልጋል።

በሀገር ግንባታ ሂደት የሕብረተሰቡን ተሳትፎ ሊያጎለብቱ የሚችሉ ስራዎች መስራት ከሚዲያ የሚጠበቅ ኃላፊነት ከመሆኑም በላይ የአገራዊ ምክክር ሂደትን ከሚያደናቅፉ ተግባራት በመቆጠብ ለስኬቱ አዎንታዊ ሚና መጫወት ያስፈልጋል። መገናኛ ብዙሃን የአገራዊ ምክክር ሂደትን ከሚያደናቅፉ ተግባራት በመቆጠብ ለምክክሩ ስኬት አዎንታዊ ሚና መጫወት አለባቸው የሚለው የሁሉም ሃሳብ ከመሆኑም በላይ በተለይም የተቋቋመው ፎረም ይህንን በማድረጉ በኩል ሚናው ከፍ ያለ ነው።

እኛም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚዲያ ፎረም ምክትል ሰብሳቢ የሆኑትን አቶ ጥበቡ በለጠን በእስከ አሁኑ የሚዲያው ተሳትፎ እንዲሁም በቀሩት ጥቂት ወራቶች ውስጥ ሊተገበሩ ስለሚገባቸው ጉዳዮች ቃለ ምልልስ አድርገናል።

አዲስ ዘመን – መገናኛ ብዙሃን ሀገራዊ ምክክሩን ውጤታማ በማድረግ በኩል ያለው ሚና እንዴት ይገለጻል

አቶ ጥበቡ በለጠ:- መገናኛ ብዙሃን ሰላምና ዴሞክራሲን በማስፈን እና ቀጣይነት ያለው ልማት እንዲረጋገጥ የማይተካ ሚና ይጫወታሉ። በተለይም በዜጎች መካከል የሃሳብ ልውውጥ እንዲኖርና የተግባባ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር በማድረግ በኩል ድርሻቸው የጎላ ነው፡፡

አሁን ያሉት አለመግባባቶች ተወግደው በፍቃደኝነት እና በመግባባት ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ምክክሩ የማይተካ ሚና አለው። ሀገራዊ ምክክሩ ከዘመን ወደ ዘመን ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን ለመፍታትና የመወያየትና የመነጋገር ባሕልንም ለማዳበር ይረዳል። በመወቃቀስ ላይ የሚያተኩረውንም የፖለቲካ ባህላችንንም ወደ መነጋገር፤ መተባበርና መደጋገፍ እንዲመጣ ያደርጋል። ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ ሚዲያው የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል።

ይህንን ሚናቸውን ለመወጣት ደግሞ መገናኛ ብዙሃን ኮሚሽኑ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ለሕዝቡ ተደራሽ በማድረግ፣ ሕብረተሰብን የሚያስተሳስር ድልድይ በመሆን ሚናቸውን ማሳደግ አለባቸው።

አገራዊ ምክክሩ የአገር ፕሮጀክት በመሆኑ መገናኛ ብዙሃን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ይህ ፕሮጀክት እንዲሳካ በኃላፊነት መስራት አለባቸው። በዚህም መገናኛ ብዙሃን የአገራዊ ምክክር ሂደትን ከሚያደናቅፉ ተግባራት በመቆጠብ ለምክክሩ ስኬት አዎንታዊ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል ፡፡

አዲስ ዘመን ፦ አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከሚዲያው ጋር በምን አይነት መልኩ ነው እየሰራ ያለው ?

አቶ ጥበቡ ፦ አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እንደተቋቋመ በርካታ ዘርፎች ነበሩት አንዱ ደግሞ የሚዲያው ዘርፍ ነው። ይህንን ዘርፍ ተባብሮ መስራት ከተቻለ ማሳደግ እንደሚቻል ታምኖበት በጥቅምት ወር 2016 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ላይ የመገናኛ ብዙሃን ስብሰባ ተደርጎ ስራውን በተቀናጀና በተናበበ መልኩ ያለመቆራረጥ የሚሰራ አንድ ስብስብ ሊኖር ይገባል በመባሉ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚዲያ ፎረም ተቋቋመ።

ፎረሙ ሲቋቋምም በዋናነት በአገሪቱ ትልልቅ የሆኑና ለሕዝብ ተደራሽነታቸውም ሰፊ የሆነ የመንግስትና የግል የሚዲያ ተቋማት እንዲካተቱበት ተደርጓል። ከስብስቡና ከምስረታው በኋላ ፎረሙ የተለያዩ የወረቀት ስራዎችን ሲያከናውን ነው የቆየው፤ በዚህም አንደ መገናኛ ብዙሃን የእኛ ሚና ምንድን ነው? ኮሚሽኑን እንዴት እናግዝ ? ሙያችንን በመጠቀም የዜግነት ግዴታችንን እንዴት እንዴት መወጣት እንችላለን ? የሚለውን ሃሳብ በብዙ ከተወያየንበት በኋላ እንደዜጋ በሙያችን የሚጠበቅብንን ማድረግ አለብን በማለት ስምምነት ተደርሶ ነው ወደ ስራ የተገባው።

ሚዲያው እንደ አንድ ትልቅ ተቋም ሰላም ላይ፤ አንድነትና መረጋጋት ላይ የመስራት ስነ ምግባራዊ ጉዳዮች ስላሉት በዛ መልኩ ሙያችን ላይ አተኩረን እንስራ በሚል ሚዲያዎችን የሚያስተባብር ሰነድ እንዲዘጋጅ ተደርጓል። በመቀጠልም ሚዲያው የሚተዳደርበትንና የሚገዛበትን ሕግ በማፅደቅ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡

ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ከሁሉም ሚዲያዎች የተውጣጡ ትልልቅ ኃላፊዎች ስለነበሩ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን አጀንዳ በደንብ እንዲሰራበት አድርጓል። በዚህም ከጥቅምት ጀምሮ የተሰሩት ስራዎች ሰፊ ተቀባይነትን አግኝተዋል።

አዲስ ዘመን፦ ከጥቅምት ወር ወዲህ በመገናኛ ብዙሃኑ በኩል ስለ ምክክር የተሰሩትን ስራዎች እንዴት ይገመግሟቸዋል?

አቶ ጥበቡ፦ እውነት ለመናገር ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል፤ የአብዛኞቹ ትልልቅ ሚዲያዎች ኃላፊዎችም በፎረሙ ውስጥ ስላሉ ኮሚሽኑ የሚያዘጋጀውንም ሆነ በራሳቸው እቅድ ይዘው የተለያዩ የዘገባ ስራዎችን በሚገባ ሰርተዋል። መስራትም ብቻ ሳይሆን ሞጋች የሆኑ ነገሮችንም በማንሸራሸር በኩል በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል። በተለይም የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲታረሙ በማድረግ በኩል በአደባባይ ሲጽፉም ሲናገሩም ነበር፤ ይህ ደግሞ ኮሚሽኑን ከማጠናከሩም በላይ ምን መስራት እንዳለበት ውጤትን በምን መልኩ እንደሚያገኝ ያመላከተ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡ – በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ችግሮች አሁን የተከሰቱ ሳይሆኑ ሲንከባለሉ የመጡ ናቸው። እነዚህን ችግሮች በማስገንዘብ በኩል የሚዲያው ሚና እንዴት ይገለጻል ?

አቶ ጥበቡ በለጠ፡- ኋላ ቀሩ የፖለቲካ ባኅላችን በርካታ ችግሮችን አስከትሎብናል። ከመነጋገር ይልቅ በር ዘግቶ መወቃቀስና አልፎ ተርፎም ነፍጥ እስከማንሳትና መገዳደል ድረስ አድርሶናል። ያለፈን ታሪክ በማንሳት መወቃቀስና አልፎ ተርፎም ወደግጭት መግባት የትም አያደርሰንም። ከዚያ ይልቅ ቁጭ ብሎ በመመካከርና በመነጋጋር የተፈጸሙ ችግሮች ካሉ እንኳን አስተካክሎ ካልሆነም ይቅር ተባብሎ ወደ ፊት መቀጠሉ ለሁሉም ወገን አዋጭ ነው። ይህንን እና ሌሎች የታሪካችን ጠባሳ የሆኑ ጉዳዮች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት እንዲያገኙ ሚዲያው ሲሰራ ቆይቷል፤ ወደፊትም መስራት ይጠበቅበታል።

በመሰረቱ የኢትዮዸያ ችግር ረጅም ዓመት ሲንከባለል ቆይቶ የመጣ ነው አሁን በሰራነው ስራም ብቻ ይፈታል ብሎ ማሰብም ቀልድ ነው፤ የሚሆነው ነገር ግን ሚዲያው የምክክር ኮሚሽኑን ስራ ለማገዝ እየተጋ ያለበትን ሁኔታ አጠናክሮ በመቀጠል እሱም አቅድ ይዞ በመስራትና በማሰራት ውጤት ማምጣት ይገባል።

ከዚህ ባለፈ ግን ከጥቅምት ወር ጀምሮ የተሰሩ ስራዎች በጣም ብዙ ውጤትም የታየባቸው ናቸው ማለት ይቻላል። እንደው እውነት ለመናገር ኮሚሽኑ ፈልጎት አልያም ሕብረተሰቡ ጋር መድረስ አለበት ተብሎ ታምኖ ያልተሰራ ስራ የለም። ከዚህ በተጨማሪ እንደውም ሌሎች ዋና ስራቸው አድርገው ፕሮግራም ቀርጸው የውይይት መስመሮችን እየከፈቱና ተወያዮችን እየጋበዙ ሰርተዋል። ይህ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡

አዲስ ዘመን፦ ጋዜጠኞች የስራውን ክብደት ምን ያህል ተገንዝበውታል ?

አቶ ጥበቡ ፦ በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው። ይህ ስራ በጣም ተፈላጊና ዘላቂ ከመሆኑ አንጻር ጋዜጠኞች ስለምክክርም ሆነ ስለ ምክክር ኮሚሽኑ በቂ እውቀትና ግንዛቤ ኖሯቸው ይሰሩ ዘንድ ሕጉን፤ ደንቡን፤ ዓላማውን እንዲረዱ ማድረጉ የሚጠበቅ ስራ ነው። እነዚህ በዚህ ልክ የተረዱ ባለሙያዎች ደግሞ ስለጉዳዩ የሚመለከተውን ሰው ቁጭ አድርገው ልክ እንደ ኢኮኖሚ፤ ፖለቲካ፤ማኅበራዊ ጤና ጉዳዮች የሚሞግቱ ጋዜጠኞችን ማፍራት አለብን።

በመሆኑም ከዚህ በኋላ በየቢሮው የሚሰጡ ስልጠናዎች ይህንን መሰል ባለሙያ ለማውጣት የሚያግዙ እንዲሆኑም ይሰራል። ምክንያቱም ምክክሩን ሁነቶችን እየፈለጉ ከመዘገብ ባሻገር በጥልቀት መስራት ከሕግና ከሌሎች ነገሮች ጋር እያዛመዱ መተንተንም ቀጣይ ሊኬድበት የሚገባ ጉዳይ ነው።

አዲስ ዘመን፦ ማኅበራዊ ሚዲያውን ጨምሮ ሌሎች በጋዜጠኝነት ስም የሚንቀሳቀሱ አካላት ሚናቸው ምን መሆን አለበት ?

አቶ ጥበቡ፦ ሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳካ የማድረጉ ጉዳይ ለእዚህ፤ ለእዚያ ተብሎ የሚተው አይደለም። የግልም ሆነ የመንግስት ሚዲያዎች ወይንም ማኅበራዊ ሚዲያው ላይ የሚሳተፉ አካላት በሙሉ ሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳካ መስራት አለባቸው። ሚዲያውም ሆነ ሌላው አካል ሊኖር የሚችለው ሀገር ስትኖር ነው፡፡

ሆኖም ሁሉም አካል በእኩል መጠን እተንቀሳቀሱ ነው ማለት አይቻልም። እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ይኖራሉ፤ በተለይም በማኅበረሰብ ትስስር ገጾች ላይ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን የሚሰብኩ፤ ከሰላም ይልቅ ጥላቻን የሚዘሩ ግለሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ። ምክንያቱ ደግሞ ማኅበራዊ ትስስር ገጹን የሚያንቀሳቅሱት ግለሰቦች በመሆናቸው ተቋም ስለሌላቸው ኤዲቶሪያል ፖሊስ ወይም ሌላ የሚገዛቸው ሕግ ስለማይኖራቸውና አንጻራዊ ነጻነትም ስላላቸው ከብሄራዊ ምክክሩ ዓላማ ያፈነገጡ ነገሮችን ሊሰሩ ይችላሉ። ነገር ግን በሂደት በተለይም የምክክር ኮሚሽኑን ዓላማና ግቦች በማስረዳት ማስተካከል የሚቻል ይመስለኛል። ደግሞ ልዩነትም መኖሩን መጥላት አያስፈልግም ዋናው ነገር ግን መሰረታዊውን ነገር አለመሳት ብቻ ነው።

አዲስ ዘመን፦ ኮሚሽኑ የስራ ጊዜውን ሊያጠናቅቅ አስር ያህል ወራቶች እንደቀሩት ይነገራልና እንደው በእነዚህ ወራቶች ውስጥ የሚዲያው ሚና ምን ሊሆን ይገባል እንዴትስ ነው መቀጠል ያለበት?

አቶ ጥበቡ፦ አዎ እንደተባለው የቀሩት ጊዜያት በጣም ጥቂት ናቸው። እነዚህን ጊዜዎች ደግሞ ለአገር የሚጠቅሙ ስራዎች የሚሰሩበት ነው ብዩ አምናለሁ። ምክክር ኮሚሽኑም ባለፉት ዓመታት የለፋባቸውን ነገሮች ዳር እንዲያደርስ የሚያግዙትን ስራዎች መስራት ይጠበቅብናል። እስከ አሁን ከመጣንበት በተለየ እና በተጠናከረ መንገድም መስራት ከሁሉም የሚዲያ አካላት የሚጠበቅ ኃላፊነትም ነው።

በሌላ በኩልም የምክክር ኮሚሽኑ ያስቀመጣቸው እቅዶች አሉ፤ እነሱን መሰረት በማድረግ ሕብረተሰቡ ጋር ሊደርስ የሚችል፤ ደርሶም ውጤት የሚታይበትን ስራ መስራት ያለባቸው ከመሆኑም በላይ ሚዲያዎች እስከ አሁን ከመጡበት አካሄድ ለየት ባለ ሁኔታ የራሳቸውን እቅድ ይዘው መስራት አለባቸው።

ለምሳሌ የኢትዮጵያ ችግር ምንድን ነው? የቱስ ጋር ነው? የቱ ጋር ነው የተበላሸነው? ለምን ሰላም አጣን? ለምንድን ነው እዚህም እዚያም ሰዎች በጦርነት የሚያልቁት? ለምን መነጋገር አቃተን? ምንድነው ችግሩ? እያሉ እየሰሩ ግን ደግሞ ወደዋናው የምክክር መድረክ የሚመጣበትን መንገድ ሁሉም ቁጭ ብሎ የሚነጋገርበትን አውድ መፍጠር የሚጠበቅ ነው።

ምክንያቱም ዛሬ ጋዜጠኛ ሆነን የተለያየ ቦታ እንደልባችን ሄደን ዘገባ የምንሰራበት ወቅት ላይ አይደለንም፤ ይህ ሁኔታ በራሱ ሚዲያው የምክክሩ አካል እንዲሆን ያስገድደዋል፤ በመሆኑም እነዚህ ነገሮች ሁሉ ከግምት ውስጥ በማስገባት በጣም በጥልቀት ሰርቶ የምክክር ኮሚሽኑን የሶስት ዓመት የስራ እቅድ በቀሩት አስር ወራት ውስጥ ስኬታማ ማድረግ ይገባል።

የምክክር ኮሚሽኑ የተሰጠውን ጊዜ ሊያጠናቅቅ የቀረው 10 ወራት ብቻ ቢቀሩትም በአግባቡ ከተጠቀምንባቸው እነዚህ አስር ወራት ለኢትዮጵያውያን ወሳኝ ጊዜያት ናቸው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡

ቀሪዎቹ አስር ወራት ከፍተኛ የሆነ ስራ የሚሰራባቸው ጊዜያት ናቸው። እስከ አሁን የነበረው ስራ ቢያንስ በምክክሩ የሚሳተፉ ሰዎችን የመለየት ነው። ይህ ሂደት በራሱ እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ መውረድን የሚጠይቅ በመሆኑና ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍሎች ወደፊት ማምጣት ስለነበረብን ረዘም ያለ ጊዜን ወስዷል። ሌላው ፓርቲዎችን ወደዚህ ምክክር ማምጣቱ በጣም አስቸጋሪ ሆኖ ስለቆየ ኮሚሽኑ ሰፊ ጊዜን ወስዶበታል። ከዚህ በኋላ ያሉትን ጊዜ በአግባቡ ለመጠቀም ሁሉም ዜጋ ለብሔራዊ ምክክሩ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በቀሪዎቹ ጊዜያት ከእያንዳንዱ ዜጋ ምን ይጠበቃል ?

አቶ ጥበቡ በለጠ፡- ኋላ ቀሩ የፖለቲካ ባህላችን በርካታ ችግሮችን አስከትሎብናል። ከመነጋገር ይልቅ በር ዘግቶ መወቃቀስና አልፎ ተርፎም ነፍጥ እስከማንሳትና መገዳደል ድረስ አድርሶናል። አሁን ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ግጭት፤ ጦርነትና መወነጃጀል ሳይሆን ውይይትና ምክክር ብቻ ነው።

ስለዚህም ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባሕልም እንደሀገር ሊጎለብት ይገባል። የስልጣኔም አንዱ መለኪያም ይኸው ነውና። በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ውስጥም ሆነ በሌሎች መስኮች የተሰማሩ ወገኖች፣ ለውይይት ቅድሚያ መስጠት አለባቸው። ሀገራዊ ምክክሩን እንደ ዕድል ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡

እንደ ሕዝብም የታሪካችን አንዱ ክፋይ ሆኖ ዘመናትን የተሻገረውን ጦርነትና ግጭትን ለማስወገድና የተረጋጋች፤ ሰላሟ የተጠበቀ እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመጭው ትውልድ ለማውረስ ሀገራዊ ምክክሩ ይዞ የመጣውን ዕድል መጠቀም ሀገርን የማሻገር አንዱ ተልኮ ነው፡፡ ስለዚህም በየትኛውም ጫፍ ያለ ኢትዮጵያዊ በዚህ የምክክር ሂደት መሳተፍና የመፍትሄው አካል መሆን ሀገርን ማዳን መሆኑን ሊረዳ ይገባል።

አካታች አገራዊ ምክክሮችን ማድረግ የተሻለ አገራዊ መግባባትን ይፈጥራል። ኢትዮጵያውያን በዘር፤ በሃይማኖት፤ በጾታና በአካባቢያዊ ርቀት ሳይገደቡ ስለሀገራቸው መጻኢ ዕድል ሊመክሩ ይገባል፡፡ ብሄራዊ ምክክሩ ከሞላ ጎደል ሁሉም ሃሳብ አለኝ የሚል የሕብረተሰብ ክፍል ሃሳቡን ያለምን ገደብ የሚሰጥበትና በመደማመጥ ጉዳዮች እልባት የሚያገኙበት ይሆናል የሚል ተስፋ መጨበጥ አለብን።

አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።

አቶ ጥበቡ፦ እኔም አመሰግናለሁ።

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2016 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You