‹‹በሚገባው መልኩ ስላላስተዋወቅን እንጂ ከእኛ ከተሞችም የሚወሰዱ በርካታ ተሞክሮዎች አሉ››  -አቶ አንዱዓለም ጤናው የኢትዮጵያ ከተሞች ትብብር መድረክ ዋና ዳይሬክተር      

ከተሞች በሚያከናውኗቸው መሠረተ ልማቶች እና በሌሎች በተለያዩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ካሉ ከተሞች ጋር የእህትማማችነት ግንኙነት በመፍጠር ለጋራ ችግራቸው በጋራ ይሰራሉ። በኢትዮጵያም የከተሞች የእህትማማችነት ስምምነት በበቂ ሁኔታ ያደገ ባይሆንም፤ አዲስ አበባን ጨምሮ ሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ካሉ ከተሞች ጋር የእህትማማችነት ስምምነት ያደርጋሉ።

በተጨማሪም አዲስ አበባ እና ኪጋሊ ባለፈው ወር በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ፣ ከተማን አረንጓዴ ከማድረግ እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ በማተኮር የእህትማማችነት ስምምነት ማድረጋቸው ይታወሳል። ይህንን እና ሌሎች ከከተሞች የእህትማማችነት ስምምነትን በተመለከተ እንዲሁም ከተሞች አካባቢ ያሉ ችግሮች ምንድን ናቸው? መፍትሔው ምንድን ነው? በሚሉ እና በሌሎች ጉዳዮች አዲስ ዘመን ከኢትዮጵያ ከተሞች ትብብር መድረክ ዋና ዳይሬክተር አቶ አንዱዓለም ጤናው ጋር ቆይታ አድርጓል። መልካም ንባብ።

አዲስ ዘመን፡- የከተሞች ትብብር መድረክ የተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማ ምንድን ነው?

አቶ አንዱዓለም፡- የከተሞች ትብብር መድረክ ዋና ዋና የሚሰራቸው እና በተልዕኮ ደረጃ የተሰጠው፤ አንደኛ ለአባል ከተሞች እርስ በእርስ ልምድ መለዋወጫ መድረክ ሆኖ ማገልገል ነው። ይህ ማለት ለምሳሌ፤ አንድ ከተማ በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ጥሩ ተሞክሮ ካለው፤ ለሌሎች ከተሞች የሚያካፍልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው። ብዙ ጊዜ አባል ከተማ የሆኑ ከንቲባዎችን ለሶስት፤ ለአራት እና ለአምስት ቀን ወደ ከተማ በመጥራት ጥሩ ተሞክሮ እንዲወስዱ፤ በተግባርም እንዲያዩት ይደረጋል። ከተሞች ደግሞ ሁኔታው እንዴት እንደተፈጠረ ያላቸውን ተሞክሮ ያቀርባሉ። ስለዚህ ተቋሙ ተሞክሮ መለዋወጫ መድረክ ሆኖ ማገልገል አንዱ ተግባሩ ነው።

አዲስ ዘመን፡- በዘንድሮ ዓመት ተቋሙ ምን ዓይነት ሥራዎችን ሰርቷል?

አቶ አንዱዓለም፡- በዘንድሮ ዓመት በርካታ ከላይ የገልጸኳቸውን ሥራዎች አከናውኗል። ሌላው የስልጠና ፍላጎቶችን በተመለከተ ዳሰሳ በማካሄድ ወቅታዊ እና ችግሮቻቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ስልጠናዎችን እናመቻቻለን።

ስልጠናውም ሆነ የልምድ ተሞክሮ ሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ሀገሮች ከተሞች ማለትም ወደ ውጭም ከንቲባዎችን ልከን ተሞክሮ እንዲወስዱ እናደርጋለን። እንዲሁ ለማነጻጸር ያህል ባለፈው ዓመት ወደ 25 የሚጠጉ ከንቲባዎችን ወደ ተለያዩ ሀገሮች፤ በዘርፍ በዘርፍ የተሻለ ልምድ ወዳላቸው ከተሞች ልከናል። ተሞክሮ እንዲወስዱ ወደ አፍሪካም ሀገራት የላክናቸው አሉ። በተለይ ሞሮኮ፣ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ ልከናል። አሜሪካም ድረስ ልከናል። ወደ ኒዮዎርክ ከተማ አምስት ከንቲባዎች ልከናል። ሄደው አይተው ተሞክሮ እና ስልጠና አግኝተው መጥተዋል።

ስልጠናው እና የልምድ ልውውጡ እርስ በርስ ተመጋጋቢ ነው። አሠራሩ በሀገር ውስጥም ተመሳሳይ ነው። በሀገር ውስጥ በዘንድሮ ዓመት አንድ አራት ከተሞች የእህትማማችነት ስምምነት ተፈራርመዋል። በቅርቡ አዲስ አበባና አርባምንጭ ተፈራርመዋል። ሀዋሳ እና ጋምቤላ ተፈራርመዋል። ከላይ እንዳልኩት የሚፈራረሙበት ዘርፍ እንዲለዩ በማድረግ እንዲፈራረሙ እናደርጋለን። ከአዲስ አበባ ከተማ ጋርም ጥሩ ግንኙነት ጀምረናል። ዓለም አቀፍ እና ሀገር ውስጥ የግንኙነት ዴስክ አለ። ከዛ ጋር እኛም እገዛ ለማድረግ እንሞክራለን።

በእህትማማችነት ስምምነት ከሌሎች ሀገራት ጋርም እንሰራለን። በተለይ በጀርመን ከተቋማችን ጋር መሰል ተቋም አለ። ወደ መፈራረም አልተደረሰም እንጂ አብዛኛዎቹን ነገሮች በጋራ እየሰራን ነው። የሀገር ውስጥ ከተሞች እራሳቸውን አጭር ግለ ታሪክ እንዲያዘጋጁ እያደረግን ነው። በዛም በኩል የሚገኙ ከተሞች የሚገናኙት የራሳቸውን ታሪክ ይዘው መጥተው በዛ አማካኝነት ነው።

የእህትማማችነት ቡድን የሚፈፀመው አንደኛው የከተሞቹ ታሪክ ተመሳሳይ መሆን አለበት። እህትማማችነት የሚፈረመው ቢያንስ ከተሞቹ የተመሰረቱበት ዓመት፣ ባህላዊ አደረጃጀታቸው፣ ተቋማዊ አደረጃጀታቸው እና ፍላጎቶቻቸው ተመሳሳይ እንዲሆን ይመከራል። እነዚህን ነገሮች አስታርቆ መሄድ የግድ ነው።

ይህን ለማድረግ የኢትዮጵያ ከተሞች ሁሉም የራሳቸውን አጭር ታሪክ እንዲያዘጋጁ ሞክረናል። አንዳንዶቹ በሂደት ላይ ናቸው፤ አንዳንዶቹ ቶሎ ጨርሰው የላኩ አሉ። ስለዚህ ይህንን የማገናኘት ሥራ እንሰራለን። አንዱና ዋነኛው የሀገር ውስጥና የውጭ ከተሞችን የማጎዳኘት ሥራ መሥራት ነው።

አዲስ ዘመን፡- አዲስ አበባ እና ኪጋሊ የተፈራረሙትን የእህትማማችነት ስምምነት እንደ ተቋም እንዴት ይመለከቱታል?

አቶ አንዱዓለም፡- የእህትማማችነት ስምምነት በተመለከተ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የኢትዮጵያ ከተሞች ትብብር መድረክ የሚያበረታታው ነው። የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወደ ኪጋሊ ሄደው የእህትማማችነት ስምምነት መፈራረማቸው ይበል የሚያስብል እና ጥሩ ነገር ነው። ይህንን እናበረታታለን፤ ማበረታት ብቻ ሳይሆን ከተሞችም እንዲፈራረሙ የማነሳሳት ሥራ ይሰራል። ከተሞች በሀገር ውስጥ እርስ በርስ የእህትማማችነት የቡድን ግንኙነት እንዲፈጥሩ እናደርጋለን። ለእዛ ቡድን ደግሞ ቴክኒካል ድጋፍ እናደርጋለን።

የእህትማማችነት ቡድን ዝም ብሎ በጥቅል የሚቀርብ ነገር አይደለም። በሁሉ ነገር ላይ እንዲሁ ቡድን መፍጠር አይቻልም። ከዚህ በፊት ባሉ ልምዶች እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ነበሩ። የኢትዮጵያ ከተሞች ትብብር መድረክ ከሶስት ዓመት፤ በፊት ከተሞች ያላቸውን ቡድን፣ ከማን ጋር እንደሆነ እና በምን ጉዳይ ላይ እንደሆነ የዳሰሳ ጥናት ተሰርቶ ነበር። በውጤቱም አብዛኞቹ ከተሞች ያደረጉት ስምምነት ጥቅል ነው።

አሁን ግን የሚደረገው ስምምነት ምን መሆን እንዳለበት ከአንድም ሁለት ጊዜ አውደ ጥናት ተካሂዷል። ከዚህ አንጻር የአዲስ አበባ እና ኪጋሊ ስምምነት በእኔ እይታ በውስን ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው። በአረንጓዴ ልማት፣ ጽዳት፣ በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ እና በአንድ አራት ጉዳዮች ላይ ነው። ስለዚህ የከተማው አስተዳደርም ሆነ ፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ውስን ሆኖ፤ የሚመለከተውን ጉዳይ ማስኬድ ስለሚችሉ ጥሩ ስምምነት ነው።

ከንቲባዋ ሲገልጹት እንደነበረው፤ ብዙ ጊዜ የእሩቁ የእሩቁን ብቻ ማየት በቂ አይደለም ብለዋል ከአፍሪካም ብዙ ተሞክሮ የሚወሰድባቸው ከተሞች አሉ። በፊት የነበረ ቢሆንም በመሀል ተቋርጦ ስለነበር እንደ ተቋም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከደቡብ አፍሪካ ዋና ከተማ ጁሃንስበርግ ጋር እንዲፈራረም ጥረት ስናደርግ ነበር። ለአፍሪካዊያንም እርስ በእርስ ግንኙነት የሚፈጥር እንደመሆኑ የአዲስ አበባ እና የኪጋሊ ስምምነት ጥሩ ነገር ነው።

አዲስ ዘመን፡- በተደረገው ስምምነት መሠረት ከኪጋሊ ምን ዓይነት ትምህርት መውሰድ ይቻላል?

አቶ አንዱዓለም፡- ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ከተሞች ከኪጋሊ ተሞክሮ እንዲወስዱ ስናበረታታ ነበር፤ ልምድ እንዲያገኙ ልከን የወሰዱ ከተሞች አሉ። ባለፈው ዓመት እንደዚሁ የተወሰኑ ከተሞችን ልከን ልምድ አግኝተዋል። በእኔ እይታ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ኪጋሊ የተፈራረሙት ስምምነት ኪጋሊ ባላት ልክ ነው።

ኪጋሊ በዋናነት ያላትን አንድ ሶስት ነገር ማንሳት ይቻላል። አንደኛው ጽዳት ነው፤ ሁለተኛ ስማርት ነች። ስማርት ማለት ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶቿ በጣም ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ እና ለነዋሪዎቻቸው ተደራሽ ናቸው። ስለዚህ ከዚህ አንጻር ኪጋሊ አረንጓዴ ናት፤ ምንም ዓይነት የተዝረከረከ ደረቅ ቆሻሻ አይታይባትም፤ ከተማዋ ጽዱ እና ውብ ናት።

ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ፣ ስማርት መሆን እና ንጹህ መሆን ኪጋሊ ያላት ጸጋ ነው። ኪጋሊ እንደ አዲስ አበባ ትልቅ ከተማ አይደለችም። ቢሆንም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተሞክሮ ላገኝበት እችላለሁ ያለውን ዘርፍ መርጦ መፈራረሙ ጥሩ ነገር ነው። ከተማዋም ያላት ይሄ ነው።

ሌላው ምናልባት ኪጋሊ ከአዲስ አበባ ሰፋፊ መንገዶችን በተመለከተ መማር ትችላለች ብዬ አስባለሁ። ከዚህ በፊት የነበሩና አዲስ እየተሰሩ ያሉ አሉ። በቤት ልማት ፕሮጀክትም ቢሆን፤ የአዲስ አበባ በጣም አመርቂ ነው። ከነዋሪው ፍላጎት አንጻር ክፍተት ያለበት ቢሆንም፤ ለሌሎች ግን በጣም ትልቅ ተሞክሮ የሚሆን ነው።

ስፋት ባለው ሁኔታ የቤት ልማት ፕሮጀክቶች በሌሎች ከተሞች በስፋት አይታዩም። ኪጋሊም እንደዛው ነው። እንደውም ከአዲስ አበባ ቀደም ብላ የወሰደችው ነገር ያለ ይመስለኛል።

በቅርቡም ኬንያ ናይሮቢ ጥቂት ኮንዶሚኒዬም ቤቶች ሞካክረው አስጎብኝተውናል። ሄደን በምናይበት ጊዜ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ሲነጻጻር ጥቂት የሚባል ነው። ምናልባት በአራብሳ አካባቢ የተሰሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ያህል ቢሆን ነው። እራስን ያለ መግለጽ ችግር ነው እንጂ፤ ከእኛ ከተሞችም የሚወሰዱ ብዙ ተሞክሮዎች አሉ። እንደውም ከአዲስ አበባ ከሌሎች ሁለተኛ ደረጃ ከተሞች የሚወሰዱ ብዙ ተሞክሮዎች አሉ።

አዲስ ዘመን፡- በሁለቱ ከተሞች የተደረገው ስምምነት ውጤታማ መሆን የሚችለው እንዴት ነው?

አቶ አንዱዓለም፡- ትክክለኛ ጥያቄ ነው። መፈራረሙ በራሱ ወጤት አይደለም፤ እንደ መግቢያ በር ነው። ፊርማው ሁለቱ ከተሞች የሚማማሩበትን እና የሚደጋገፉበትን አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ነው። አመራሮቹ ከተፈራረሙ በኋላ፣ ከላይ እንዳልኩት ዘርፎቹ የጽዳቶቹ በጽዳት፣ በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ደግሞ የአዲስ አበባ ጽዳት አስተዳደር እንደዚሁ በሌሎቹም በተፈራረሙባቸው ዘርፎች የሚገኙ መሥሪያ ቤቶች ዝርዝር እቅድ ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል። ዝርዝር ካወጡ በኋላ በዛ በተስማሙበት እቅድ መሠረት ሁለቱም አንድ እቅድ ኖሯቸው፣ በአንድ እቅድ ላይ መመሥረት ይችላሉ። የተደረሰውን ስምምነት ሴክተር መሥሪያ ቤቶቹ ወደ ታች የማያወርዱ እና የጋራ እቅድ የማያዘጋጁ ከሆነ፣ ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን በእቅዱ መሠረት የማይተገብሩ ከሆነ ውጤቱን መለካት አይቻልም። ውጤት ማምጣትም አይቻልም። ስለዚህ የከተሞች ስምምነቶች ወደ መሬት የሚወርዱበት ሁኔታ ላይ በሰፊው እየተሠራ ነው።

አዲስ አበባ ቢያንስ ከ29 የውጭ ከተሞች ጋር የእህትማማችንት ስምምነት ተፈራርማለች። ግን አብዛኞቹ ተፈራርመው ቁጭ ያሉ ናቸው። የተደረገው ስምምነት ለውጤት ያለመብቃት ዋናው ምክንያት፤ አንደኛ የተደረገው ስምምነት በውስን ጉዳዮች ላይ አልነበረም። ስለዚህ አፈጻጸሙን ከንቲባዎች ለመከታተል የሚያስቸግር የሚሆንባቸው እና ለውጤት የማያበቃቸው ይሄ ነው።

ስለዚህ ሁለቱ የተፈራረሙ ከተሞች ከተደረገው ስምምነት ውጭ የጋራ ዝርዝር እቅድ ያስፈልጋቸዋል። በዛ እቅድ መሠረት ከተሞቹ ልምድ ይለዋወጣሉ፤ የአቅም ግንባታ ስልጠናም ከሆነ ስልጠና እንዲሰጥ ያደርጋሉ። ለአንድ ሳምንት ባለሙያዎችን ወደ ኪጋሊ በመላክ ያለውን ነገር አይቶ ድጋፍ እንዲደርግ ማድረግ ይቻላል። ከአዲስ አበባም በኩል ወደ ኪጋሊ ልኮ ድጋፍ እንድታገኝ ሲደረግ፤ በትክክል ቡድኑ ውጤት አመጣ ማለት ይቻላል። ካልሆነ ስምምነት ሆኖ ይቀራል ማለት ነው።

አዲስ ዘመን፡- እስከ አሁን በተደረጉ ስምምነቶች ጥሩ ተሞክሮ ምንድነው? በተጨማሪ ስምምነቶችን ወደ ተግባር ለመቀየር ችግሮች ምንድናቸው?

አቶ አንዱዓለም፡- አብዛኞቹ ስምምነቶች የሚፈጸሙበት መንገድ ለውጤት የማያበቃቸው ይመስለኛል። እኛ እንደተቋምም ያለን ግምገማ እንደዛ ነው። የእህትማማችነት ስምምነት መፈጠሩ መልካም ነገር ነው። አንደኛ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት፤ ሁለተኛ የሁለቱን ከተሞች እኩል ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆን አለበት።

ገና ከመጀመሪያው የከተሞች ስምምነት እኩል የመጠቃቀም መርህ ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት። እኩል ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ስምምነት ከሆነ ስምምነቱን ውጤታማ ማድረግ ከባድ አይሆንም ማለት ነው። ለምሳሌ በፈረንሳይ ሊዮን የምትባል ከተማ ከአዲስ አበባ ጋር ስምምነት ተፈራርማለች። ፈረንሳዮች ከእኛ ምንም አይፈልጉም የሚል አስተሳሰብ ሊኖር እና ስምምነት ላይ ሊፈረም አይገባም። ሊዮን ከተማ ከአዲስ አበባ ከተማ የምትማረው ብዙ ነገር አለ። አብዛኞቹን የአውሮፓ ከተሞች ብናይ አጋጣሚው ፈጥሮላቸው ከቀኝ ግዛት በተገኘ ሀብት እና የሰው ኃይል ከተሞች ቀድመው ተገንብተዋል። አሁን መገንባት ቢፈልጉም ቦታ የላቸውም። አውሮፓ መሬት ላይ አንድ ምልክት ተቀብራ እናያለን። 1960፣ 16ኛ ፣17ኛ መቶ ክፍለ ዘመን የሚሉ ነገሮች ይታያል። ይህም በቀኝ ግዛት ዘመን የተሠራ መሆኑን ያሳያል። እነሱ የሚኖሩት አሁን በተሠራ ነገር ላይ ነው።

የተሠሩ ነገሮች ሕንፃም ሆነ መንገድ የማደስ እና የማሻሻል ሥራ ይሠራሉ። ሌሎች ተጨማሪ ነገሮችን ይጨመራሉ እንጂ መሠረታዊ ነገሮቻቸው የተሟላ ነው ማለት ይቻላል። ምናልባት እነሱ ጋር ገንዘብ ስላለና የእኛ ደግሞ ገና የመልማት ፍላጎቱ ከፍተኛ ስለሆነ፤ እኛ ከእነሱ ገንዘብ የማግኘት ሃሳብ ብቻ ኖሮን ቡድን ከተፈጠረ መርህ ላይ የተመሠረተ አይደለም። ለምሳሌ እነርሱ ሀገር እና ከተማ በረዶ በሚሆንበት ጊዜ እኛ ሀገር ቢመጡ ምን ያህል ለአዕምሮም ለጤናም አስደሳች ነገር እንደሆነ መገመት ይቻላል። ስለዚህ ቱሪስት ሆነው ከመምጣት በእህትማማችነት ስም ቢመጡ ያለው ክብርና አገልግሎት በገንዘብ የሚሰላ አይደለም።

ስለዚህ መጀመሪያ በእህትማማችነት ስምምነት እኩል ተጠቃሚ መሆን ቀዳሚው ጉዳይ እንደሆነ መታሰብ አለበት። ከዛ በኋላ ወደ ውስን ጉዳዮች መሄድ ያስፈልጋል። የሚደረገው ስምምነት በቤት ጉዳይ ከሆነ፣ በባህል፤ በአረንጓዴ ልማት፣ በጽዳት ወይም ለዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከሆነም በትክክል ዘርፉ መለየት እና መታወቅ አለበት።

ከፌዴራል መንግሥት ውጭ ከተሞች በራሳቸው ዲፕሎማሲያው ግንኙነት መፍጠር ባይችሉም፤ በጋራ ችግሮች አብረው ለመሥራት እና በሌሎች በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ሊስማሙ ይችላሉ። ለምሳሌ የጎንደር ከተማ ከአንድ የውጭ ሀገር ከተማ ጋር በቤተመንግሥት እድሳት ብቻ ላይ ተፈራርሞ የፋሲል ቤተመንግሥት ጨምሮ ሌሎች አብያተ መንግሥታትን ማደስ ይችላል። ስለዚህ እንደ ኢትዮጵያ ከተሞች ትብብር መድረክ በሀገሪቱ ከተሞች የእህትማማችነት ጅምሮች ቢኖሩም፤ ዘርፉን ከመጠቀም አኳያ ቀሪ ሥራዎች አሉ።

አዲስ ዘመን፡- አጭር የግል ታሪካቸውን አዘጋጅተው የላኩት እስካሁን ምን ያህል ከተሞች ናቸው?

አቶ አንዱዓለም፡- በርከት ያሉ ከተሞች ልከዋል እስከ 20 ከተሞች የሚደርሱ የላኩ አሉ። ግን አይተን በዚህ መንገድ ቢሻሻል ብለን የላክናቸው አሉ። መልሰን ከላክን በኋላ ቶሎ ያለመመለስ ሁኔታ አለ። ያው እንግዲህ አንዳንድ ከተሞች በጣም በሥራ ይወጠራሉ፤ በደንብ ያለ መረዳት እና ትኩረት ያለ መስጠትም ሁኔታ ይኖራል። እኛ ግን በዚህ ነገር ላይ ትኩረት አድርገን እንሰራለን። መጀመሪያ በርከት ያሉ ከተሞች ልከውልን የነበረ ቢሆንም፤ እንደ መመሪያ ከላክነው ይዘት ውጭ ሰርተው የላኩ ከተሞች ነበሩ።

ስለዚህ ያ በትክክል ለእህትማማችነት የምንፈልገውን ቡድን ማስገኘት ስለማይችል፣ በተቀመጠው የአሠራር ይዘት በድጋሚ ለከተሞቹ ተመላሽ ይሆናል። ቀይራችሁ አሻሽላችሀ አምጡት እንላቸዋለን። ስለዚህ በዚህ ዓይነት መንገድ አጭር ታሪክ የማዘጋጀቱ ተግባር ሂደት ላይ ነው።

በርግጥ የአሠራር መመሪያውን መላክ ከጀመርን እና ስልጠና መስጠት ከጀመርን አንድ ዓመት ሆኖናል። ግን ያው የእኛ ሀገር ነገር ይታወቃል። አንዳንድ ነገሮች ብዙ ጊዜ የሚሰሩት ቀስ ተብለው ነው። ፈጥነው የላኩትን ለሌሎች ሀገሮች ልከን ምላሽ እየጠበቅን ነው።

አዲስ ዘመን፡- 20ዎቹ አጭር የከተሞችን ታሪኮች የፃፉ ተቀባይነት ያገኙ ናቸው ወይስ የተቀነሰ አለ?

አቶ አንዱዓለም፡– ተቀባይነት አገኙ የሚባለው ሲፈራረሙ ነው። 20 ሁሉ ወደ ውጭ ተልከው የተፈራረሙ ስላልሆኑ ውጤት ያመጡ ናቸው ማለት አይቻልም። ወደኛ የተላኩ ቢሆኑም አብዛኛዎቹ መዳበር የሚፈልጉ ናቸው።

አዲስ ዘመን፡- ለምሳሌ እስካሁን የላኩ ከተሞች እነማን ናቸው?

አቶ አንዱዓለም፡- ቀሪ ሥራዎችን የሚፈልጉ ያላለቁ ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ የተላከው አጭር ታሪክ በድጋሚ ምንም ዓይነት ነገር የማይፈልግ ቢሆን መግለጽ ይቻል ነበር። ይመጣል ታይቶ የሚጎለው ነገር ሲኖር ይላካል። አሁንም የሚቀር ነገር ሲኖር ተመልሶ ይላካል። ግን በዚህ ዓይነት መንገድ ፍለጋችንን እንቀጥላለን።

አዲስ ዘመን፡- በአባልነት የተመዘገቡት ምን ያህል ከተሞች ናቸው?

አቶ አንዱዓለም፡- በእኛ የከተሞች ትብብር መድረክ በዚህ ዓመት እስከ የካቲት ወር መጨረሻ ድረስ 89 ከተሞች ነበሩ። አሁን አንድ ከተማ ተጨምሮ 90 ደርሰዋል።

አዲስ ዘመን፡- ከንቲባዎችን ወደ ባህር ማዶ ስልጠና እንዲሚወስዱ እና የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ እንደሚላኩ ገልጸዋል። በዚህ ዓመት በዘጠኝ ወራት ምን ያህል ከንቲባዎች ለስልጠና ተልከዋል?

አቶ አንዱዓለም፡- እስከ አሁን ባለው በዘጠኝ ወር ውስጥ ለተሞክሮ የሄዱት 16 አካባቢ ናቸው። ከግንቦት አራት እስከ 15 ድረስ 15 ከንቲባዎችን ወደ ኒዘርላንድ ለመላክ ዝግጅታችን ተጠናቋል። ከንቲባዎች እንደመሆናቸው የጊዜ መጨናነቅ እና አንገብጋቢ ሥራ ካልገጠማቸው 15 የሚሆኑ ከንቲባዎችን ልከን በስማርት ሲቲ፣ ማህበረሰብን በማሳተፍ እንዴት ከተማን ማሳደግ እንደሚቻል በኒዘርላንድ አንድ አምስት ከተሞችን በማየት ተሞክሮ ለመውሰድ እቅድ ይዘናል።

የታቀደው 30 ሰው ለመላክ ነበር። በተለያዩ ሥራዎች ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል። በሚያዝያ ወር አራት ከንቲባዎችን ወደ ኒዮዎርክ በመላክ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ ተሳትፈው፤ ከተማዋን አይተው ልምድ እንዲያገኙ ታቅዶ ነበር፤ አስቸኳይ ሥራ በመብዛቱ ምክንያት ሳይሄዱ ቀርተዋል።

በሀገር ውስጥ የልምድ መለዋወጫ መድረኮች ጋር ተያይዞ በርካታ መድረኮች ተዘጋጅተዋል። በተለያ ደግሞ ኋላ ቀርተው በነበሩት የትግራይ ክልል ከተሞች አባል የሆኑትንም ያልሆኑትንም ጨምሮ ሶስት ዙር የልምድ ልውውጥ መድረኮች የተዘጋጁ ሲሆን፤ አራተኛውን ለማዘጋጀት ከተማውን እና ጊዜውን ወስነው እንዲነግሩን ለክልሉ ጥያቄ አቅርበናል።

አዲስ ዘመን፡- እስካሁን በሰራችኋቸው ሥራዎች በኢትዮጵያ ከተሞች ምን ዓይነት መሻሻሎች ታይተዋል?

አቶ አንዱዓለም፡– እስካሁን ከሰራናቸው ሥራዎች በተለይ በሁለቱ በስልጠናው እና በልምድ ልውውጡ የምናያቸው ነገሮች አሉ። ለምሳሌ የሀዋሳ ከተማ ተሞክሮ በብዛት በሌሎች ከተሞች ተስፋፍቶ እናያለን። ከተሞችን አረንጓዴ እና ንጹህ ማድረግ አብዛኞቹ ከተሞች እንደ ጥሩ ተሞክሮ ወስደው ከንቲባዎች እራሳቸው በተገኙበት ከተማዎችን የማጽዳት ተግባርን አሠራር አድርገዋል።

ይሄ ለሀዋሳ ስድስትና ከዛ በላይ ዓመት የወሰደ ተሞክሮ ነው። አሁን ይህንን ሌሎች ከተሞች በተጨባጭ እንደ አሠራር ወስደው ሲተገብሩት እያየን ነው። አካባቢውን እንዲጠብቅ እና እንዲያጸዳ ማህበረሰቡን የማንቃት ሥራ እየተሠራ ነው። ሌላው በእቅድ መተግበር ዙሪያ ልክ አሁን በአዲስ አበባ የኮሪደር ልማቱ እንደሚሠራው፤ ባለፈው ዓመት በሀዋሳ ከተማ የእግረኛ መንገድ ልማት ተጀምሯል። ይህም ቀድሞ የተጀመረው የአዲስ አበባን ተሞክሮ በመውሰድ ነው። ቸርቸር ጎዳና ከለማ በኋላ ሀዋሳም ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አሮጌው አውቶቡስ ተራ፣ አቶቴ የሚባለውን እና ሌሎች ሰፈሮች ማልማት ችላለች።

በተጨማሪ ከሀዋሳ ተሞክሮ ወስደው ሌሎች ከተሞች እየሠሩ ነው። አርባ ምንጭን ፣ ጅግጅጋን እና ሌሎች ከተሞችን ብናይ ተመሳሳይ ነገሮች ማየት ይቻላል። ከእጽዋት አንጻርም አንዱ ከተማ ለአንዱ ከተማ የሚሰጥበት ሁኔታ አለ። ከተሞችን ውብ እና ምቹ ጽዱ ከማድረግ አንጻር ውጤት የተገኙባቸው ናቸው። ግን እኛ መሠረተ ልማቶችን ብቻ ሳይሆን ከተሞች እንዲሰሩ የምንፈልገው፣ በዋናነት ለነዋሪዎች የሚሰጡት አገልግሎት የተሳለጠ እንዲሆን ነው።

አማራሪ የሆነው አገልግሎት አሰጣጥ እንዲቀር፣ ስማርት ሲቲ ላይ ከተሞቹ በደንብ አስበው እንዲንቀሳቀሱ እየሠራን ነው። ስልጠናም እየሰጠን ነው። ይህ ሀዋሳ ተጀምሯል። በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው። አዳማም የተሻለ ከተማ ነው፣ ባህርዳርም ጅምር ቢሆንም እንደዛው ጥሩ ነው።

ሌሎች ከተሞችም እየመጡ ያሉ አሉ። ከመሠረተ ልማት በዘለለ በአገልግሎት አስጣጥጥ ከመታወቂያ አሰጣጥ ጀምሮ እንዲዘምን እና ፈጣን እንዲሆን እየሠራን ነው። አንዳንድ ፕሮጀክቶች ላይም ንድፎችን በመጻፍ፣ የልማት አጋር በመሆን እንሰራለን። ለአብነት ያህል በይርጋለም ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ገቢ ለማሳደግ ባለፉት ሶስት ዓመታት የሙከራ ፕሮጀክት ተጀምሮ ነበር።

በፕሮጀክቱ የታክስ ገቢ ሳይጨምር በማዘጋጃ ቤቶች በሚሰጥ አገልግሎት በዓመት 9 መቶ ሺህ የነበረው ገቢ፤ በዚህ በሶስተኛው ዓመት ላይ እስከ 30 ሚሊዮን ብር እንዲደርስ አድርገናል።

በቅርቡ ሥራውን ለመገምገም ሀዋሳና ይርጋለም ሔደን ነበር፤ በተጨባጭ መንገድ ወደ ሌሎች ከተሞች እንዲስፋፋ እየተገበርን እንገኛለን። ካለው ፍላጎት አንጻር በቂ ነው የሚባል ባይሆንም በተለያዩ ከተሞች በተሠሩ ሥራዎች ውጤቶች እየተመዘገቡ ናቸው።

አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ እጅግ አመሰግናለሁ።

አቶ አንዱዓለም፡- እኔም አመስግናለሁ።

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ግንቦት 22/ 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You