‹‹የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተያዘው ዓመት በሰባት ነጥብ ዘጠኝ በመቶ እንደሚያድግ ማሳያዎች አሉ›› – ፍጹም አሰፋ (ዶክተር ) የፕላንና ልማት ሚኒስትር

ኢትዮጵያ በ2016 በጀት ዓመት በ7ነጥብ 9በመቶ ለማደግ ዕቅድ አስቀምጣ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ትገኛለች። ሀገሪቱ ያስቀመጠችው እቅድ እንደሚሳካም የዓለም የገንዘብ ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትም መደገፋቸው የሚታወስ ነው። ከዚህ አንጻር ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያለው አፈጻጸም ምን ይመስላል? በግብርና፤ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፉስ ያለው ክንውን ምን ደረጃ ላይ ይገኛል የሚሉትን ነጥቦች በማንሳት የፕላንና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ ለጋዜጠኞች መረጃ ሰጥተዋል። መልካም ንባብ።

 

 ጥያቄ፡- ዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር ኢትዮጵያ በ2016 በጀት ዓመት 7ነጥብ 9 እንደምታድግ ተንብየዋል። ይህ ምን ያህል ይሳካል ብለው ያስባሉ?

ዶክተር ፍጹም፡– ከኢኮኖሚ ዕድገት አኳያ ትልቁ መለኪያ የምናውቀው ጥቅል ሀገራዊ ምርት የምንለው(GDP) ነው። ከዚህ አኳያ የ2016 ዓ.ም ጥቅል የኢኮኖሚ ዕድገት ተጠቃሎ የሚወጣው መስከረም ከተጠናቀቀ በኋላ ቢሆንም እንደምናስታውሰው፤ በ2016 በጀት ዓመት ሲጀምር የዓመቱ የኢኮኖሚ ዕድገት 7ነጥብ 9 በመቶ ሆኖ ሊሳካ እንደሚችል ትንበያ ተቀምጧል። ይህ ትንበያ እንግዲህ በሌሎች የዓለም አቀፍ ተቋማትም ጭምር የተደገፈ ነው።

ኢትዮጵያ በብዙ ፈተናዎችም ቢሆን ባለፉት ዓመታት 2015 ዓ.ምን ጨምሮ ጠንካራ የኢኮኖሚ ዕድገት ስታስመዘግብ ቆይታለች፤ እንግዲህ ይሄ ጠንካራ የኢኮኖሚ ዕድገት በ2016 ዓ.ም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ዓለም አቀፍ ተቋማት በተለይ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም (IMF) ጭምር የታመነበት ነው።

ጥያቄ፡- ኢትዮጵያ ያስቀመጠችውን የ7ነጥብ 9 በመቶ እድገት ከማሳካት አኳያ ያለፉት ዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ምን ይመስላል?

ዶክተር ፍጹም፡– የ7ነጥብ 9 የኢኮኖሚ ዕድገትን ከማሳካት አኳያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያሉ አመልካቾች አዝማሚያዎች ምን ይመስላሉ? የሚለውን መመልከቱ ጥሩ ነው። ከግብርና አኳያ በተለይ በዋና ዋና ሰብሎች ብቻ ከመቶ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ከአምና ተመሳሳይ ጊዜ ተጨማሪ ምርት ተገኝቷል።

ለምሳሌ ስንዴን ብቻ ብንመለከት ስንዴ በመሬት ሽፋን ብቻ ብንመለከተው አምና በመኸርና በበጋ መስኖ ወደ አራት ሚሊየን ሄክታር አካባቢ በዘር ተሸፍኖ ወደ 47 ሚሊዮን ኩንታል ተሰብስቦ ነበር። ዘንድሮ ወደ 6ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በማረስ በዘጠኝ ወራትም ከሰማንያ ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ተችሏል።

ሌላው በስንዴ መጠን በሀገር ውስጥ መተካት አለብን ተብሎ ሥራ የተጀመረው በሩዝ ልማት ላይ ነው። ከሩዝ አኳያ አምና ከስምንት ሚሊዮን ኩንታል ያልበለጠ ነበር የተመረተው ዘንድሮ 38ሚሊዮን ኩንታል ማምረት ተችሏል። ቡናም እንደዚሁ ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማምረት ተችሏል።

በተመሳሳይ በእንስሳት ሀብት ላይ የተገኘውም ውጤት አበረታች ነው። ከዚህ አንጻር በክቡር ጠቅላይ ሚንስትራችን የተጀመረው የሌማት ትሩፋት ከፍተኛ እርካታ ካሳዩ ዘርፎች አንዱ ነው። የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ ከተጀመረ በኋላ በተለያዩ የፖሊሲ ድጋፎች በግብዓት፣ በኤክስቴንሽን ሥራዎች፣ በፋይናንስ በከፍተኛ ሁኔታ ትኩረት ተሰጥቶት ድጋፍ በመደረጉ ከፍተኛ ውጤት ተገኝቷል። በዚህም በወተት ዘርፍ አምና በዚህ ሰዓት ከተመረተው ሁለት ቢሊዮን ሊትር ተጨማሪ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ማምረት ተችሏል። እንቁላልን ብንመለከት አምና ከተመረተው ወደ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ተጨማሪ በዘጠኝ ወራቱ ተመርቷል።

ቀይ ሥጋን ስንመለከት አምና ከነበረው ወደ ሁለት መቶ ሺህ ቶን ተጨማሪ የሥጋ ምርት ተገኝቷል። ማርን እንደዚሁ ስንመለከት አምና ዘጠኝ ወር ተመርቶ ከነበረው ተጨማሪ 110 ሺህ ቶን በላይ ምርት ተመርቷል። ስለዚህ በግብርናው ዘርፍ ለሀገራዊ ጠቅላላ ምርት (GDP) የሚኖረው አስተዋጽኦ አምና ከነበረው ተጨማሪ አለው ማለት ነው። ስለዚህ 7.9 የኢኮኖሚ ዕድገት ብለን ያስቀመጥነው ትንበያ በግብርና በኩል አዝማሚያው የሚያሳየው የሚሳካ መሆኑን ነው።

የኢንዱስትሪ ዘርፉም ሌላው ለጥቅል ሀገራዊ ምርት አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው። ከዚህ አኳያ ኢንዱስትሪ ዘርፉም ዘንድሮ ከአምና በተሻለ አፈፃፀም ላይ እንዳለ የሚያሳዩ አመላካቾች አሉ። የማምረት አቅም አጠቃቀም አንዱ የኢንዱስትሪ ዕድገት አመላካች ነው። በየስድስት ወሩ ባለው ልኬት የማምረት አቅማችን 56 በመቶ ደርሷል። ሆኖም 70 በመቶ ድረስ አቅማቸውን የሚጠቀሙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ተፈጥረዋል።

ይሄ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በተለይ ለሀገራዊ ጥቅል ምርት ያለው ድርሻ የተሻለ እንደሚሆን አመላካች ነው። በዚህ ዓመት የሚያመለክት ነው። የኢንዱስትሪዎችም የኃይል አጠቃቀም አድጓል። ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሁለት ቢሊዮን ኪሎዋት በሰዓት የጨመረ ሲሆን ለአምራች ኢንዱስትሪዎች በሰዓት የተሸጠው ኃይል በዘጠኝ ወሩ ከአራት መቶ ሚሊየን ኪሎዋት በላይ ነው።

ሌላኛው ሲሚንቶ ስንመለከት አጠቃላይ ከአንድ ሚሊየን ቶን በላይ ተጨማሪ ተመርቷል። በአጠቃላይ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያለው ዕድገት ከአምና የተሻለ መሆኑን ቁጥሮች ያመለክታሉ። ከፋይናንስ አኳያ አምና ለብድር ከተሰጠው ውስጥ ለአምራች ኢንዱስትሪው የተሰጠው ብድር አስራ ሁለት በመቶውን ብቻ ነበር። ዘንድሮ ወደ አስራ ስድስት በመቶ ከፍ ብሏል ማለት ነው።

ሌላው ለሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው የአገልግሎት ዘርፉ ነው። የአገልግሎት ዘርፉ የተለያዩ ንዑስ ዘርፎች ያሉት ሲሆን ከንግድ የወጪ ንግድና የገቢ ንግድ መጠን ስንመለከት ከአምና ዘጠኝ ወር ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።

በዘጠኝ ወራት ውስጥ ወደ ሶስት መቶ ሰባ አራት ቢሊዮን ብር ገቢ ተሰብስቧል። ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከአስራ አምስት በመቶ በላይ ያደገ ገቢ ተገኝቷል። ነው የሰበሰብነው። በተለይ የሀገር ውስጥ ገቢን ስንመለከት ከአምናው በሃያ ሁለት በመቶ ያደገ ገቢ አለው።

ሌላኛው እንደ አዲስ ከለውጡ ወዲህ በሪፎርም ወደ ሥራ ተገብቶበት በተለይ የክልሎችን የገቢ አቅም ከማሳደግ አኳያ ትልቅ ሚና የተጫወተው የጋራ ገቢ መሰብሰብና ማስተላለፍ ነው። ከዚህ አንፃር ዘንድሮ በዘጠኝ ወር ወደ አምሳ አራት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር የጋራ ገቢ የተሰበሰበ ሲሆን ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲወዳደር የሃያ ዘጠኝ በመቶ ጭማሪ አለው።

ሌላው የመንግሥት ወጪ ምን ይመስላል የሚለው ነው። ከወጪ አኳያ እስከ አሁን ድረስ በዘጠኝ ወራት አራት መቶ ዘጠና አምስት ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል። ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲወዳደር የስምንት በመቶ ጭማሪ አለው። አብዛኛውም ወጪ የወጣው ካፒታል ላይ ሲሆን በተለይ አምራች ዘርፉ እና በኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ የሆኑ ለማህበራዊ ዕድገት ወሳኝ የሆኑ ዘርፎች ላይ ነው። በተለይም ለካፒታል ፕሮጀክቶች የወጣው ወጪ ጭማሪ ማሳየቱ ከኢኮኖሚ ዕድገት አኳያ ትልቅ እንድምታ ያለው ነው።

ከዚህ አኳያ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲወዳደር የካፒታል ወጪ በአስራ አምስት ነጥብ አምስት በመቶ ዕድገት አሳይቷል። አምና በዘጠኝ ወር መቶ አስር ቢሊዮን ብር ወጪ ለካፒታል ወጪ ወጥቶ የነበረ ሲሆን ዘንድሮ ወደ መቶ ሃያ ሰባት ቢሊዮን ብር አድጓል።

ከዚህ ውጭ ከትራንስፖርት አንጻርም ከፍተኛ እመርታ አለ። በተለይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባጓጓዛቸው መንገደኞችና ዕቃዎች አንጻር ከአምናው ሃያ አምስት በመቶ ዕድገት አሳይቷል። ሌላኛው የቱሪዝም ዕድገት አንዱ ማሳያ ነው። ከቱሪስት ፍሰት አኳያ አምና በዘጠኝ ወር ከመጣው የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ተጨማሪ መቶ ሺህ ቱሪስቶች ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል።

የዲጂታል ዘርፉም ውጤት ካመጡት ውስጥ ነው። በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የዕድገት ምንጮች ተብለው ከተለዩት ውስጥ የፖሊሲ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ካለው ዘርፍ ውስጥ አንዱ የዲጂታል ኢኮኖሚው ዘርፍ ነው።

የዲጂታል ኢኮኖሚው ዘርፍ በአንድ በኩል እንደ መሠረተ ልማት ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎችን አፈፃፀም በማሳለጥ የራሱን ሚና የሚጫወት ቢሆንም በራሱ ደግሞ ትልቅ ሚና አለው። ከክፍያ አኳያ በዲጂታል መንገድ የተከፈሉ ክፍያዎች አምና በዘጠኝ ወር ከተከፈለው ዘንድሮ አራት ትሪሊዮን ተጨማሪ ገንዘብ ሊተላለፍ ችሏል። ይህ በጣም ትልቅ እመርታ ነው።

ሌላኛው በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ወሳኝ አመላካች የዲጂታል ብድር አገልግሎት ነው። ከዚህ አኳያ ማይክሮ ብድሮችን በመስጠት በቴሌ ብርና በሌሎች አማራጮች አምና በዚህ ሰዓት ከተሰጠው ብድር በሶስት ቢሊዮን ብር ያደገ ወይም ተጨማሪ ብድር መስጠት ተችሏል። ሌላኛው በዲጂታል ዘርፉ የተገኘው ውጤት ቁጠባን የሚመለከት ነው። ባለፉት ዘጠኝ ወራትም ከአራት ቢሊዮን የበለጠ ቁጠባ ተከናውኗል።

ሌላኛው ከማክሮ አፈፃፀም አኳያ የሚታየው የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ልማት ነው። የፋይናንስ ዘርፉ ጤናማነትን የሚያመለክቱ በርካታ አመላካቾች አሉ፤ ከዚህ አኳያ ብዙ አመላካቾችን ማንሳት የሚቻል ቢሆንም በዋናነት ለምሳሌ የባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ ዕድገት ከፍተኛ የሆነ ዕድገት አስመዝግቧል።

በዘጠኝ ወር የባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ ሁለት ነጥብ አራት ትሪሊዮን አካባቢ ደርሷል። በዘጠኝ ወራቱ ባንኮች የለቀቁትን ብድር ስንመለከት ወደ ሰላሳ ሰባት ነጥብ አራት በመቶ የሚሆነው ለግብርናና ለአምራች ኢንዱስትሪ የተሰጠ ነው።

ጥያቄ፡- ከውጭ ንግድ የተገኘው ገቢስ ምን ይመስላል ?

ዶክተር ፍጹም፡- የውጭ ንግድና ምንዛሬን በተመለከተ መሻሻሎች አሉ። ከውጭ ምንዛሬ ግኝት አኳያ የመጀመሪያ የሚሆነው የሸቀጦች የወጪ ንግድ ነው። ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከሸቀጦች የወጪ ንግድ አኳያ ወደ ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል። ይህ እንግዲህ ከአጠቃላይ ከእቅድ አኳያ ዝቅ ያለ ቢሆንም በአፈፃፀም ከአምናው የተቀራረበ አፈፃፀም መሆኑን ማየት ይቻላል።

በተለይ በዚህ ዓመት ከዚህ ቀደም ዝቅተኛ አፈፃፀም ሲያስመዘግብ የነበረው የማዕድን ዘርፍ በተለይ በወርቅ የወጪ ንግድ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የሰማንያ ሶስት በመቶ ዕድገት አለው። አምና በዘጠኝ ወር ከወርቅ ተገኝቶ የነበረው ገቢ መቶ አምሳ ሚሊየን ዶላር ሲሆን ዘንድሮ ሁለት መቶ ሰባ አምስት ሚሊየን ዶላር ለመድረስ ችሏል። የቅባት እህሎችን በተመለከተ 264 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል። ይህም ከአምናው አንጻር ወደ አምሳ በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። እንደዚሁም ጥራጥሬ ከአምና በአስራ ሁለት በመቶ እድገት አምጥቷል።

ሌላው የውጪ ምንዛሪ ግኝት የአገልግሎት ገቢ ምንጭ ነው። 75 በመቶ በላይ የሚሆነውን ገቢ የሚሸፍነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው። አምና በዘጠኝ ወር ያገኘነው 5 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ነበር። ዘንድሮ በ7 ነጥብ 3 በመቶ አድጎ፤ 5 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር ማግኘት ችለናል። ሌላኛው የውጪ ምንዛሪ ምንጫችን የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ነው። አምና በዘጠኝ ወር 2 ነጥብ 68 ቢሊየን ዶላር ያገኘን ሲሆን፤ ዘንድሮ ይሄ በአራት በመቶ ጨምሮ 2 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር ማግኘት ችለናል።

የውጪ ሃዋላ አንዱ የወጪ ንግድ ገቢያችን ነው። ይሄ ማለት በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ውስጥ የሚልኩት ገንዘብ ነው። ከዚህ አኳያ አምና በዚህ ጊዜ በዘጠኝ ወር 3 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ተገኝቶ ነበር። ዘንድሮ ይህ 7 ነጥብ 4 በመቶ ዕድገት አሳይቶ፤ 3 ነጥብ 65 ቢሊየን ዶላር ማግኘት ችለናል።

ስለዚህ በአጠቃላይ በዘጠኝ ወር የውጭ ምንዛሪ ግኝታችን በሸቀጦች ኤክስፖርት ከአምና ተመጣጣኝ ነው። በአገልግሎት የተገኘው ደግሞ በ7 ነጥብ 3 በመቶ አድጓል። የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከአምናው በአራት በመቶ ጨምሯል። የውጭ ሀገር የሃዋላ ፍሰትም ከአምናው 7 ነጥብ 4 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። ይህም አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሁኔታው የተሻለ እንደሆነ የሚሳይ ነው።

ጥያቄ፡- በዚህ መጠን ኢኮኖሚው ካደገ የሥራ ዕድል ፈጠራው ምን ያህል መሻሻል አሳይቷል?

ዶክተር ፍጹም፡– በዘጠኝ ወራት ውስጥ ወደ 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ዜጎች በሀገር ውስጥ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል። ይሄ ከአምናው ጋር ሲወዳደር ቀንሷል። ከአጠቃላይ ከዕቅዳችን አንፃርም ውስን ነው። በዚህ ምክንያት በሥራ ዕድል ፈጠራ የተሠሩ በርካታ ሥራዎች ቢኖሩም፤ በየዓመቱ ወደ ገበያ የሚገባው ሥራ ፈላጊ ከፍተኛ ከመሆኑ አኳያ ትልቅ ሥራ የሚጠይቅ ዘርፍ ነው።

ከሥራ ዕድል ፈጠራ አኳያ በጣም ትልቅ እመርታ ያሳየው፤ የውጭ ሀገር ሥራ ሥምሪት ነው። ሀገራትን በማስፋት እና ስምምነቶችን ወደ ውጤት በመለወጥ የተሠሩ ሥራዎች በጣም ትልቅ ለውጥ የታየባቸው ናቸው። ለምሳሌ አምና በዘጠኝ ወር ወደ ውጭ የተላኩት ሰዎች 78ሺ 260 ብቻ ነበሩ። ዘንድሮ በውጭ የሥራ ዕድል 278ሺህ 198 ዜጎች የሥራ ዕድል በውጭ ሀገር ተፈጥሮላቸዋል። ይህ ከአምናው ጋር ሲወዳደር፤ የ255 በመቶ ጭማሪ አለው። በአስር ወሩ ከዚህም የተሻለ ቁጥር ያመላክታል። በቀጣይም በተለይ በስፋት የሠለጠኑ ዜጎችን የተሻለ ክፍያ የሚከፈላቸው ዜጎችን ጨምሮ ለውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት በማዘጋጀት እና የሥራ ሥምሪት ሀገራትንም በማስፋት ተጨማሪ ሥራ ለመሥራት፤ ዘርፉን የሚመራው ተቋም ተጨማሪ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል።

ጥያቄ ፡- የዋጋ ንረትን በተመለከተ ምን ይላሉ?

ዶክተር ፍጹም፡– ከዋጋ ንረት አኳያ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አንድም ሆነ፤ እርሱ ተጠናቆ በአዲስ መልክ የመጣው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሁለት ትልቁ የሀገር ማክሮ ኢኮኖሚ ተግዳሮት ብሎ ካስቀመጣቸው እና መፈታት አለባቸው ብሎ ካመነባቸው ተግዳሮቶች ውስጥ አንዱ የዋጋ ንረት ነው።

ከዚህ አኳያ በተለይ በርካታ ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ የዋጋ ንረትን ሊያባብሱ የሚችሉ ጉዳዮች ያጋጠሙን ቢሆንም፤ የዋጋ ንረቱ ከእጅ ወጥቶ በጀመረበት ሁኔታ በጣም ከፍ ብሎ እያደገ እንዳይሔድ የተሠሩ ሥራዎች ለውጥ ማሳየት ጀምረዋል። ከእነዚህ የተሠሩ ሥራዎች ውስጥ አንዱ በተለይ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ በተለይ የግብርና ዘርፍ ላይ የተሠሩ ሥራዎች ተጠቃሾች ናቸው።

በተለይ በእንስሳት ሀብቱም ሆነ በሌማት ትሩፋት የታዩት ለውጦች የተለያዩ ምርቶችን ወደ ገበያ በማስገባት የምርቶቹ ዋጋ እንዲቀንስ ወይም ቢያንስ ባሉበት እንዲቀጥል በማድረግ በኩል ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ለምሳሌ በሌማት ትሩፋት በከተማችን በእንቁላል ምርት የሚታይ ለውጥ ማምጣት ተችሏል። በቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች በአትክልት ምርቶች ለውጥ እያየን ነው።

ሌሎችም እንዲሁ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የተሠራው ሥራ የዋጋ ንረትን ምጣኔ እየቀነሰ ወይም ባለበት እንዲሄድ የራሱን ሚና ተጫውቷል። በሚያዝያ ወር ያለው የዋጋ ንረት ወደ 23 ነጥብ 3 በመቶ መቀነሱ የሚታወቅ ነው። ከዛ ውስጥ ደግሞ ምግብ ነክ የሆኑት፤ አሁንም ትኩረት የሚፈልግ እና 27 በመቶ የታየበት ነው። ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች የዋጋ ንረት ከፍተኛ ቅናሽ አሳይቷል። ወደ 18 በመቶ ወርዷል። ይሄ የሚሳየው የተሠሩ ሥራዎች ለውጥ እያመጡ መሆናቸውን ነው።

የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ከምርትና ምርታማነት ባሻገር ጥብቅ የገንዘብ እና የፊሲካል ፖሊሲ በዚህ ዓመት ተተግብሯል። ከላይ እንደገለጽኩት የብድር ጣራ ለንግድ ባንኮች ተቀምጦ፤ የባንኮቹም ብድር በብሔራዊ ባንክ በተቀመጠው ጣራ መሠረት ከአምናው ከ14 በመቶ በላይ እንዳይሆን ተደርጎ ተተግብሯል። በተለይ በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ገንዘብ በመገደብ የዋጋ ንረቱ እንዳይባባስ የራሱን ሚና ተጫውቷል። ሌላው ገበያ ማዘመን እና የገበያ መሠረተ ልማቶችን የማስፋፋት ሥራ ተሠርቷል። ከዚህ አኳያ የቅዳሜ እና እሁድ ገበያ ያለው ሚና የሚታወቅ ነው። በተጨማሪ ሌሎች የገበያ ሠንሰለቶችን የማሳጠር፤ ያለ አግባብ በገበያ ውስጥ ያሉ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ የዋጋ ንረቶችን የሚያባብሱ፤ ጭማሪዎችን የሚያደርጉ የገበያ ተዋንያን ላይ ርምጃ የመውሰድ እና ያንን የማስተካከል ሥራዎች ሲሠሩ ቆይቷል።

ይህ ሁሉ ቢሠራም አሁንም የዋጋ ንረት ከፍተኛ በመሆኑ የከተማ ነዋሪውን ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የመንግሥት ሠራተኞችን የዋጋ ንረቱ እየፈተነ በመሆኑ ከዛ በተጨማሪ መንግሥት ድጎማዎችን እያደረገ ይገኛል። አንዱ የነዳጅ ድጎማ ነው። ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ወደ 29 ቢሊየን ብር የሚጠጋ የነዳጅ ድጎማ ተደርጓል። በተጨማሪ የማምረቻ ዋጋን በመቀነስ ገበያ ላይ የሚመጡ ምርቶች ዋጋቸው የተሻለ እንዲሆን ከማድረግ አኳያ የማምረቻ ግብዓቶች ላይ የተደረገ ድጎማ ነው። ዋናው ማዳበሪያ ነው። ማዳበሪያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዋጋ መጨመሩ ይታወቃል። ይህንን ዋጋ ሙሉ ለሙሉ ለአርሶ አደሩ ቢተላለፍ መጨረሻ ላይ ተመርቶ ከአርሶ አደሩ የሚመጣው ምርት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምር ታሳቢ በማድረግ መንግሥት ከ16 ቢሊየን ብር በላይ ለማዳበሪያ ድጎማ አድርጓል።

ሌላው ከውጭ ለሚገቡ ሸቀጦች በተለይ መሠረታዊ የሚባሉትን ከቀረጥ እና ግብር ነፃ እንዲገቡ በማድረግ የዋጋ ንረት ለማረጋጋት የራሱን ሚና ተጫውቷል። ዘይት፣ ሩዝ፣ ስኳር፣ የሕፃናት ወተት እና የሕፃናት ምግብ ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ በማድረግ መንግሥት በሌሎች ዘርፎች ከወሰዳቸው ርምጃዎች በተጨማሪ የዋጋ ንረቱ ከዚህ እንዳይባባስ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

በማክሮ እና በዋና ዋና ኢኮኖሚ ዘርፎች ያለው አፈፃፀም ይህንን ቢመስልም፤ በዚህ ጉዳይ ላይ አሁንም ኢኮኖሚያችንን እየፈተኑ ያሉ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ሳላነሳ አላልፍም። ከላይ እንዳልኩት የሥራ ዕድል ጉዳይ፤ ሥራ አጥነት ዓለም አቀፍ ፈተና ነው። ሌላኛው ተግዳሮት የዋጋ ንረት ነው። የዋጋ ንረትን በከፍተኛ ሁኔታ የመቀነስ ሥራ መሠራት አለበት። ከላይ እንደገለጽኩት ተጋላጭ ዜጎች ማለትም ገቢያቸው የተወሰነ የሆኑ ዜጎች በከፍተኛ ሁኔታ የዋጋ ንረት ስለሚያስቸግራቸው ትልቅ የኢኮኖሚው ተግዳሮት ነው። ስለዚህ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራ እንደሚገባ አያጠያይቅም።

ጥያቄ ፡- የውጪ ዕዳን በተመለከተ ምን ይላሉ?

ዶክተር ፍጹም፡- እንደሀገር የውጪ ዕዳ ተጋላጭነት አለ። ይህንን የዕዳ ተጋላጭነት በተለይ በሁለተኛው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በተቀመጠው መሠረት ቀጣይ ሥራዎች ከልማት አጋሮች ጋር የሚሠራ ሲሆን፤ ትብብሮችም ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል። ዕዳን ከማሸጋሸግ እና ዕዳን ከማሰረዝ ጎን ለጎን የውጪ ምንዛሪ ፍሰትን በማሻሻል ዕዳዎቻችንን በአግባቡ መክፈል የምንችልበትን ሁኔታ መፈጠር ይኖርበታል። ከዚህ አኳያ የተበደርናቸውን ብድሮች ያለምንም ማቆራረጥ እየከፈልን ሲሆን ባለፉት አምስት ዓመታት ከአስር ቢሊየን በላይ ዶላር ዕዳ መክፈል ተችሏል።

አሁን በቀጣይም ያሉ መከፈል ያለባቸው ዕዳዎች አቅም ፈጥሮ መክፈል ያስፈልጋል። ነገር ግን ከሁሉ በላይ ከዓለም አቀፍ ተቋማት እና ከልማት አጋሮች ጋር አጠቃላይ የዕዳ ሁኔታችንን እና ጫናዎቻችንን ለመቀነስ በትብብር የማሻሻል ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።

ሌላው የኢኮኖሚ ተግዳሮት የዘርፎች ተወዳዳሪነት እና ምርታማነት አሁንም ትልቅ ሥራ የሚፈልግ መሆኑ ነው። በግብርና እና በሰብል ምርት በጣም ከፍተኛ መሻሻሎችን አይተናል። በምርታማነትም ቀላል የማይባል በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት ምርታማነት መሻሻሉን ማየት እንችላለን። ግን አሁንም ከዓለም የምርታማነት ደረጃ ስናወዳድረው ብዙ ክፍተት አለ። ስለዚህ ምርታማነትን በየዘርፉ በአምራች ኢንዱስትሪው፣ በግብርና በሌሎችም ዘርፎች ምርታማነትን በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር ይኖርብናል። ይሄ አሁንም ተወዳዳሪነት እና ምርታማነት የሀገራችን ኢኮኖሚ አሁንም ትልቅ ሥራ የሚጠይቅ ተግዳሮት ነው ብለን እናያለን።

የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ሁኔታ ተለዋዋጭነት በእኛ ኢኮኖሚ ላይ ያለው አንድምታ ቀላል አይደለም። ከዚህ አኳያ በተለይ የልማት አጋርነት መቀዛቀዝ አንዱ ፈተና ነው። በሌሎች የጎረቤት ሀገሮችም ሆነ ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገሮች የልማት አጋርነት እና የልማት ድጋፍ በከፍተኛ ሁኔታ ተቀዛቅዟል። በሌሎች በሚያጋጥሙ ሰው ሠራሽም ሆነ የተፈጥሮ አደጋዎች አጠቃላይ የአቅርቦት እና የሎጀስቲክ ሰንሰለት መቆራረጥ በኢኮኖሚያችን ላይ ከፍተኛ ተግዳሮት የሚፈጥር መሆኑን በቅርብ እንኳን በቀይ ባህር ላይ የተፈጠረው ችግር የምናውቀው ነው። አንደኛ የሎጀስቲክ ወጪን መጨመር ሲሆን፤ ግብዓቶች ሸቀጦች በአግባቡ በጊዜ ወደ ሀገር እንዳይገቡ በማድረግ፤ የምንልካቸውን እና በኤክስፖርት የምንሸጣቸውን ዕቃዎች ደግሞ በሰዓቱ ወደ ውጭ እንዳይሔዱ በማድረግ የራሱን አሉታዊ ሚና የሚጫወት ነው።

እነዚህ ተግዳሮቶች በተለይ ዓለም አቀፍ ፈተናዎችን በቻልነው መጠን ተንብየን ሌሎች አማራጮችን የመጠቀም ፈተናዎችን የምንቀንስበት ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅብናል። የአገልግሎት አሰጣጣችን አሁንም መሻሻል አለባቸው። አሁንም ብልሹ አሠራሮች አሉ። ይሄ እንደ ትልቅ የኢኮኖሚያችን ተግዳሮት ሆኖ በተለያየ መድረክም የተገመገመ ነው። ይህ መሻሻል ይኖርበታል። የንግድ እና የኢንቨስትመንት ከባቢያችንን ምቹ ከማድረግ አኳያ ብዙ ይጠበቅብናል። ይህም በተግዳሮትነት የሚነሳ ነው።

ጥያቄ፡- መሠረተ ልማት እና የፕሮጀክቶች አፈፃፀምን በተመለከተ ምን ይላሉ?

ዶክተር ፍጹም፡- እዚህ ላይ ሁላችንም ዓይናችንን ጥለንበት የምንሠራው የሕዳሴ ግድባችን ነው። ከዚህ አኳያ በዓመት ውስጥ መሠራት ያለበት ሥራ በአግባቡ እየታቀደ እና እየተከናወነ፤ የሕዳሴ ግድብን ከማጠናቀቅ አኳያ አፈፃፀሙ በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው። ሌሎች የመንገድ መሠረተ ልማቶች፣ ድልድዮች ጥሩ አፈፃፀም እየታየባቸው ናቸው። በቅርቡ የተመረቀው እና ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው፤ በጥራትም በትልቅነትም በሚሰጠው የአገልግሎት ዓይነትም ከፍተኛ ደረጃ ያለው በዓባይ ላይ የተሠራው ድልድይ አንዱ ማሳያ ነው።

የከተማ መሠረተ ልማትን ከማስፋት እና ከተሜነትን የተሻለ ከማድረግ አኳያ በማዘመን በኩል በተለይ በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደር ልማት በሚታይ ፍጥነት እና ጥራት ቀን ከሌሊት እየተሠራ ነው። በተለይ በፕሮጀክት አፈፃፀም ላይ ትልቅ የባሕል ለውጥ ያመጣ ቀን እና ማታ 24 ሰዓት እየተሠራ ነው።

የቱሪዝም ዘርፍ ፕሮጀክቶች ላይም በተለይ በጠቅላይ ሚንስትሩ የተጀመሩት የገበታ ፕሮጀክቶች በጊዜያቸው በተቀመጠላቸው የጥራት ደረጃ እየተጠናቀቁ እና እየተመረቁ መሆኑን በዚህ ዘጠኝ ወር የመረቅናቸው እና ወደ ሥራ የገቡ፤ በመጠናቀቅ ወደ መጨረሻው ያሉ ፕሮጀክቶች የምናውቃቸው ናቸው።

የጨበራ ጩርጩራ ፣ የዝሆን ዳና ሎጅ፣ የወንጪ የቱሪዝም መዳረሻ እንደዚሁ በቅርብ ተጠናቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ የሚጠበቀው ወደ መጨረሻ የደረሰው የጎርጎራ ሪዞርትም እንደዚሁ ማለት ነው። ስለዚህ እነዚህ ሁሉ በገበታ ፕሮጀክቶች አፈፃፀማችንን በከፍተኛ ሁኔታ የቀየሩ፤ ጥራትን እና ትልቅነትን የምናይበት የአፈፃፀም ብቃትን ያየንባቸው ፕሮጀክቶች ናቸው። በአጠቃላይ ያለፉት ዘጠኝ ወራት የኢኮኖሚያችን አፈጻጸም ይህንን ይመስላል።

 እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You