‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገር ደረጃ የተሻለ የሕንፃ ግንባታ ኮዶች ፀድቀው ተተግብረዋል›› – አርክቴክት ብሥራት ክፍሌ

የከተማ ገጽታን የሚመጥን የኪነ ሕንፃ፣ የተሽከርካሪ እና የእግረኛ መንገድ፣ ለአንድ ከተማ አስፈላጊ ከሚባሉት መካከል ይጠቀሳል። ደረጃውን የጠበቀና የተሟላ መሠረተ ልማት ያላት ሀገር በቀላሉ የውጭ ኢንቨስትመንትን፣ ቱሪዝምን በመሳብ ኢኮኖሚ ለማመንጨት እንደሚያስችላትም የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በዚህ ዙሪያ የዕለቱ የዘመን እንግዳችን አርክቴክት ብሥራት ክፍሌ የተለያዩ ሃሳቦችን አካፍለውናል።

እንግዳችን በሙያቸው አርክቴክት እና የከተማ ፕላነር ናቸው። በከተማ ፕላን ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው። በቀድሞ ስሙ ሕንፃ ኮሌጅ፣ በአሁኑ ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ የአርክቴክቸር ሕንፃ ግንባታና ከተማ ልማት ኢንስቲትዩት ውስጥ በመምህርነት እያገለገሉ ነው።

በሙያቸው እስከ አሁን ስላበረከቱትም ሲናገሩ፤ ከመስቀል አደባባይ እስከ ማዘጋጃ ባለው ፕሮጀክት ሥራ ላይ መነሻ ዲዛይን በመሥራት፣ ግንባታውንም በመቆጣጠር አማካሪ ሆነው ሠርተዋል። ከተማሪዎቻቸውና ከሙያ አጋሮቻቸው ጋር አዲስ አበባ ከተማ ላይ ትኩረት ያደረገ ዘጋቢ ፊልሞችንም አዘጋጅተዋል። በግላቸውም መጽሐፍ ጽፈዋል።

የከተማ ዕድገት ከነዋሪዎች እድገት ጋር ተናብቦ እንዲሄድ፣ ነዋሪዎች በከተማ እድገት ላይ ሊኖራቸው ስለሚገባው አዎንታዊ ተሳትፎና ተያያዥ ጉዳዮችን ያካተተ የጥናት ሥራ እየሠሩ ነው። ይሄኛው ጥናታቸው መንግሥት አቅራቢ፣ ሕዝብ ደግሞ ተገልጋይ ሳይሆን ፤ አብረው አገልግሎት አቅራቢ የሚሆኑበትን መንገድ ይዳስሳል። ይሄ ትንሹ ሥራ ነው የሚሉት አርክቴክት ብሥራት፤ አዲስ አበባን በ2050 ዓ.ም በሚለው ጥናት ላይ ለመካፈል ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ ይናገራሉ። በሰፊ እቅድ ሥራ ውስጥ በመሳተፍ የበኩላቸውን ሙያዊ አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆኑም ይገልፃሉ። እንደ አንድ መምህርና እንደዜጋ ንቁ ተሳታፊ በመሆን፤ በከተማ ልማት ላይ አስተዋጽኦ ማድረግም ይፈልጋሉ። ከእኚሁ አርክቴክት ጋር ሥራዎቻቸውን እና የከተማ ፕላንን በተመለከተ ቆይታ አድርገን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል። መልካም ንባብ፡-

አዲስ ዘመን፡- በቅድሚያ የከተማ ፕላንን አስመልክቶ ስለወጣው ሕግ ይገለጹልን?

አርክቴክት ብሥራት፡- የመንገድ አጠቃቀምን፣ ስፋትን እንዲሁም የሕንፃ ዓይነትና አጠቃቀምን በተመለከተ የሚያስገድድ ሕግና መመሪያ አለ። በተለያየ ጊዜም በተለያዩ ከተሞች የጥናት ሥራዎች ተሰርተዋል፤ እየተሠራም ነው። ለአብነት አዲስ አበባ ከተማን ብንጠቅስ፤ መዋቅራዊ ፕላን (ስትራክቸራል ፕላን) በሚል በየአስር ዓመቱ እየተሻሻለና እየተከለሰ ሲሠራ ቆይቷል። በከተማ ደረጃ የመንገድ ስፋትና ዓይነት ምን መሆን እንዳለበት፣ የቤቶች አገነባብ፣ የአረንጓዴ ስፍራዎች በከተማ ደረጃ የሚካሄዱ ጥናቶች ይወስኑታል ማለት ነው።

ሕጉን የሚያስተገብረው ደግሞ የከተማ አስተዳደሩና በሥሩ ያሉ የተለያዩ ተቋማት ናቸው። በከተማ ደረጃ ፕላንና ልማት ኢንስቲትዩት አለ። ኢንስቲትዩቱ የከተማዋን ፕላን፣ እድገት… ወዘተ በተመለከተ የጥናት ሥራዎች ይሠራል። እነዚህ በተለያዩ መመሪያዎችና ዝርዝር ደንቦች ወደ ትግበራ የሚገቡበትን ሁኔታም ይዘጋጃል። አስፈጻሚ አካላት ደግሞ የክፍለ ከተማ አስተዳደሮች፣ ወረዳ ወይም በማዕከል ደረጃ እንደአስፈላጊነቱ የተቋቋሙ ተቋማት ሊሆኑ ይችላሉ።

አዲስ ዘመን፡- ሊያሠራ የሚያስችል ሕግ ካለና አስፈጻሚ ተቋማትም ከተደራጁ የግንባታ ልማቶች በምን ሁኔታ እየተካሄዱ ናቸው?

አርክቴክት ብሥራት፡- ሕጉን ለመተግበር ከፍተኛ ጥረት እየተደረገና እየተሠራበት ነው። ይህ ሲባል ግን ተግዳሮት የለውም ማለት አይደለም። አንዳንዴ የከተማው እድገትና ፍላጎት አሁን በሥራ ላይ ያሉት እና እየተተገበሩ ከሚገኙት ሕግና መመሪያዎች ጋር አለመጣጣም ወይም መጣረስ ይፈጠራል። በቀላል ምሳሌ ለማስረዳት፤ አንድ አካባቢ ለመኖሪያነት ብቻ እንዲውል ይወሰንና ቦታው ለሌላ ተግባር የሚውልበት ሁኔታ አለ። ይሄ የሚያሳየን ፕላኑና ነባራዊው ሁኔታ አለመጣጣማቸውን እና ሕጉም አለመተግበሩን ነው።

አዲስ ዘመን፡- የተቀመጠውን ሕግ ለመተግበር የማይቻልበት ምክንያት ምንድነው?

አርክቴክት ብሥራት፡- ፕላንን በእሳቤ ደረጃ ስናስቀምጠው፤ አሁናዊ ነገር ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ አይደለም። ወደፊት ሊሆን የሚችልን መተንበይ፣ ማሰብ፣ መገመት ማለት ነው። ወደፊትን ስናስብ ብዙ ነገሮችን ለማሳካት እንጂ ጉድለት አይኖርም ማለት አይደለም። ምክንያቱም ፍፁም የሆነ ፕላን ማስቀመጥ ከባድ ነው። ከተማን አንድ ሕይወት እንዳለው አካል አድርገን ልናስበው እንችላለን። ምክንያቱም ያድጋል። የከተሞች እድገትና ሂደት ልክ እንደ አካል በሂደት ችግሮች ይገጥሙታል።

ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ቁጥር እድገት ይመጣል። ወይም ሥራ አጥነት ይስፋፋል። በተቃራኒው ደግሞ ጠንካራ ኢኮኖሚ ይፈጠርና ከታሰበው በላይ እድገቱ ይጦዛል። ቀድሞ የተቀመጠው ፕላን ይህንን ሁኔታ መቋቋም የማይችልበት ሁኔታ ይፈጠርና ከተማ ከፕላን ውጭ የሚሄድበት ሁኔታ ይፈጠራል።

አዲስ ዘመን፡- እስኪ አዲስ አበባ ከተማን መነሻ በማድረግ በከተማዋ እየተከናወኑ የግንባታ መሠረተ ልማቶች ሕግን የተከተሉ ናቸው?

አርክቴክት ብሥራት፡- ከተማዋ የምትመራበት የፀደቀ መዋቅራዊ ፕላን አለ። አብዛኛው ሥራም የሚሰራው በፕላን መሠረት ነው። ሆኖም ግን አንዳንድ ልዩ ፕሮጀክቶች ይመጣሉ። ፕሮጀክቶቹ በከተማ ደረጃ ወይም ሀገራዊ የሆነ ትልቅ ፋይዳ ይኖራቸዋል ተብሎ ሲታሰብ የፀደቀው ፕላንም ቢሆን ይህንን እድል ይፈቅዳል። ለሕዝብና የመንግሥት የጋራ ጥቅም ወዘተ… እያለ ፕላኑ ክፍተቶች አሉት። እሱን በመተግበር ሂደት ለምሳሌ የመንገድ ስፋት ማሻሻል፣ ወይም አንዳንድ ቦታዎችን ለአረንጓዴ ልማት ማዋል፤ ወይም በላዩ ላይ ግንባታ እንዲካሄድ መፍቀድ ማለት ነው።

በጥብቅ ለአረንጓዴ ልማት የተፈቀደ ቦታ ይጠቅማል ተብሎ አሳማኝ የሆነ ምክንያት ከቀረበና በቂ ጥናት ከተደረገ ማሻሻያዎች ይደረጋሉ። ማንኛውም ሀገር የሚመራበትን ሕገ መንግሥት ለማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ሕጉን ተከትሎ እንዲሻሻል እንደሚደረግ ሁሉ የከተማ ፕላንም በተመሳሳይ ሕጉን ተከትሎ ይሻሻላል።

ግን መጠየቅ የሚኖርብን ማሻሻያዎቹ ከተለመደው፣ ወይም ከደረጃውና ከተጠናው ውጭ የምንሰራቸው ነገሮች በቂ የሆነ ጥናትና እይታ ተደርጎባቸዋል? ብሎ መጠየቅ እንጂ ለምን ማሻሻያ ተደረገ ይደረጋል ማለት አይቻልም።

አዲስ ዘመን፡- በግንባታ መሠረተ ልማት እንደ አንድ ባለሙያ የእርስዎ ትዝብት ምንድነው?

አርክቴክት ብሥራት፡- እንደ አንድ ባለሙያና በከተማ ውስጥም እንደ ነዋሪነቴ ስታዘብ፤ የከተማ ፕላን ሕጎች፣ የሕንፃ ግንባታ ደንቦችና መመሪያዎች በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ ይቀያየራሉ። ተለዋዋጭ እየሆኑ መጥተዋል። እነዚህ ነገሮች በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ተገማች መሆን ይኖርባቸዋል። የከተማ ፕላኑ ለምን ተቀየረ ማለቴ አይደለም። ሰዎች ጥሩ መኖሪያ ይሆናል ብለው ገንብተው ገና ሳይኖሩበት መንደሩ ወደ ገበያነት ከተቀየረ፤ ሰዎቹ የሠሩትን ቤት ለንግድ አከራይተው ወደ ሌላ ሰፈር ለመሄድ ይገደዳሉ።

ስለዚህ የመሬት አጠቃቀማችን፣ የሕንፃ ግንባታ ሕግና መመሪያዎች፣ ለከተማ የሚወጣው ደረጃ፣ ዝርዝር ጥናቶች፣ ፍጹም ትክክለኛ የሆነ እይታ እንኳን መፍጠር ባይችሉ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል እሳቤ በባለሙያ ቢያንስ መተንበይ አለበት። አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ፍጹም የመኖሪያ ሰፈር ለማግኘት አዳጋች ሆኗል። ምክንያቱም አብዛኛው ሰፈር ወደ ቅይጥ እየተቀየረ መጥቷል። ይሄ የራሱ የሆነ መንስኤ አለው። ከተማን ፕላን ሲደረግ መኖሪያ፣ የሥራ ቦታ፣ ማምረቻ፣ የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎችንም አገልግሎቶችን ያማከለ መሆን ይኖርበታል።

እነዚህ ነገሮች በትክክል ተሰባጥረው ካልተቀመጡ ሰው ክፍተቱን በራሱ አቅም ለመሙላት ጥረት ያደርጋል። ለምሳሌ ሱቅ በሌለበት መንደር ውስጥ መኖሪያ ቤታቸውን ለንግድ አገልግሎት ያከራያሉ። ነጋዴውም ፍላጎት መኖሩን አይቶ ይከራያል። ክሊኒክ፣ ባንክ እየተከፈተ ንግዱ ይስፋፋል። እንዲህ ያለው ነገር በማህበረሰቡ በራሱ ከሚጀመሩ ቀድሞውኑ በከተማ ደረጃ እስከታች የቀበሌ አስተዳደር የማስፈፀም አቅም ተፈጥሮ በየመኖሪያ መንደሮች የሚያስፈልጉ አገልግሎቶች እንዲካተቱ የከተማ ፕላኑ ማስፈጸም ቢችል ከተማውን እንዳሰብነው ልናገኘው እንችላለን።

የከተማ ፕላኑ በእሳቤ ደረጃ እንዲህ ያለውን ነገር የያዘ ቢሆንም፤ አተገባበር ላይ ግን ክፍተት አለ። በግሌም የምለው ችግሩ የከተማ ፕላኑ ላይ ሳይሆን፤ ክፍተቱ ማስፈጸም ላይ የተፈጠረ ነው። የከተማ ፕላኑ ያነሳቸውን ነጥቦች ሁሉ አካትቷል። በወረዳ ደረጃ የወጣት ማዕከል፣ መዋዕለ ሕፃናት፣ ትምህርት ቤት፣ የእምነት ተቋማት የሚሉትን አካቷል። ነገር ግን እነዚህ በሂደት ለሌላ አገልግሎት ውለዋል። ምናልባት የተወሰኑት ሊኖሩ ይችላሉ። ሌላው ሊሆን የሚችለው ደግሞ ያልታሰበበት ቦታ ግንባታዎች ተከናውነው ተጠቃሚው አነስተኛ ይሆናል። የከተማ ፕላን ክፍተት ሊኖረው ይችላል። እሱን እያሻሻልን እንሄዳለን። ነገር ግን ያሰብናቸውን ነገር ደግሞ ማውረድ፤ የተቀናጀ፣ የተናበበ ውጤት ይሰጠናል።

አዲስ ዘመን፡- የከተማ ፕላን ሕግና መመሪያዎች ላይ የሚታየው ክፍተት የአንድ ከተማ ችግር ተደርጎ ነው የሚወሰደው ወይስ በሀገር ደረጃ የሚታይ ነው? በአግባቡ ተፈጻሚ መሆን አለመቻላቸው እንደ ሀገር ምን አሳጣ?

አርክቴክት ብሥራት፡- ክፍተቱ የሚገለጸው በሀገር ደረጃ ነው። በነገራችን ላይ አዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ከተሞች አርአያ (ሮል ሞዴል) ናት። አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚሰራው ጥሩም ሆነ ክፍተት ያለበት ነገር እንዳለ በሌሎችም የኢትዮጵያ ከተማ ውስጥ በፍጥነት ይተገበራሉ። በግሌም ቢሆን የማስበው ሌሎች ከተሞችም የአዲስ አበባ ከተማን ተሞክሮ ብቻ ቢጠቀሙ ጥሩ ነው። አዲስ አበባ ከተማ ከራስዋ ነባራዊ ሁኔታ እየሞከረች እንጂ ሁሉም ትክክል አይደለም።

በትግበራ አፈፃፀም ላይ አሳጣን ብዬ የማስበው፤ ውስን የሆነውን የሀገር ሀብት በፕላን፣ በእቅድ በተመራ መልኩ ለተገቢው ፕሮጀክትና ልማት ማዋል ስንችል አንዳንዴ ነገሮችን ደጋግመን በመሥራት ወጪ እንዲያስወጡ እናደርጋለን። ማልማት፣ መልሶ ደግሞ ማፍረስ ይፈጠራል። ይሄ ደግሞ አንድ እይታ ብቻ ሳይሆን፤ በተቃራኒው ምን ይፈጥራል የሚለው መታየት አለበት። ከተሞች በተደጋጋሚ በዚህ ሂደት ውስጥ የሚሄዱ ከሆነ የኑሮ ተመራጭነታቸውን ከማሳጣት በተጨማሪ ኢንቨስትመንትን የመሳብ ሁኔታ

ጥያቄ ውስጥ ሊገባ ይችላል።

ኢንቨስተሮች በአንድ ከተማ ውስጥ ሀብታቸውን ለማፍሰስ ሲወስኑ በአንድና ሁለት ዓመት ጥቅም እናገኛለን ብለው ሳይሆን ቢያንስ የ30 ዓመት እቅድ አውጥተው ወደ ሥራ የሚገቡ በመሆናቸው በተቻለ መጠን የከተማ ፕላን የረጅም ጊዜ መሆን አለበት። ያለማነውን በአጭር ጊዜ ውስጥ መልሰን የምናፈርሰው መሆን የለበትም። የረጅም ጊዜ እቅድ መኖሩ ለነዋሪውም ሆነ ሀብቱን ኢንቨስት ለማድረግ ለሚመጣውም ሰው አስተማማኝ ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በኪነ ሕንፃም ሆነ በመንገድ መሠረተ ልማት ከሌሎች የዓለም ሀገራት የምትለይበትና የራስዋ የሆነ መገለጫ አላት?

አርክቴክት ብሥራት፡- የእኛን የአኗኗር ሁኔታ የሚገልጽ ኪነሕንፃ ልናስብ እንችላለን፤ ያ ማለት ግን ይሄ ኢትዮጵያዊ ሕንፃ ነው ብለን እንደመገለጫ ማስቀመጥ፤ አንድ ቅርጽ ወይም ምስል፣ ገጽታ፣ ቁስ አለ ለማለት ይከብደኛል። አዲስ አበባ ከተማ ፍጹም ከሌሎች ከተሞች የተለየች ናት። እንደነ ላልይበላ ከድንጋይ ተፈልፍሎ የሚሰራ ነገር የለም። በከተማዋ ውስጥ ባለው ቁስ፣ አየር ንብረትና የሕዝብ አሰፋፈር ልክ ልናስበው የምንችለው የዲዛይን፣ የአከታተም፣ እሳቤ መፈጠር አለበት፤ እንጂ እንደ ኢትዮጵያ የኪነ ሕንፃ ወይም የአርክቴክቸር መልክ አለን ለማለት አልደፍርም።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የሕንፃ ግንባታ በአስገንቢዎች ፍላጎት ላይ የተመሠረተ እንደሆነና የባለሙያዎች ምክረ ሃሳብ ወደ ጎን የሚባልበት ሁኔታ ስለመኖሩ ይነገራል። እርስዎ ምን ይላሉ?

አርክቴክት ብሥራት፡- በፊትም ቢሆን ስታንዳርድ አለ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገር ደረጃ በጣም ጥሩ የሚባል የተሻለ የሕንፃ ግንባታ ኮዶች ፀድቀው ተተግበረዋል። ካለፉት አስር አመታት ወዲህ የተተገበሩት ኮዶች ሕንፃዎቻችንን ለአንድ መቶ ዓመት መጠቀም የሚያስችል ነው። አስፈፃሚው አካል ማድረግ ያለበት የሕንፃ ኮዶቹ በአግባቡ መተግበራቸውን፣ መከታተል፣ መቆጣጠርና ማስፈጸም ነው።

አዲስ ዘመን፡- የሕንፃ ግንባታዎች ከታሪክ ጋር የተያያዙ መሆን ይኖርባቸዋል?

አርክቴክት ብሥራት፡- አዎ! ለምሳሌ ኢሮፕ፣ አሜሪካን፣ ኤዥያ፣ በጣም የሚለዩበትና ትኩረት የሚሰጡት ነገር ቢኖር መንገዶቻቸውን፣ ሕንፃዎቻቸውን፣ የከተማውን የተለያዩ ስፍራዎች ያላቸውን ታሪካዊ ፋይዳ ወደ ኢኮኖሚ ጥቅም ይቀይሩታል። በኢትዮጵያም ቢሆን ለምሳሌ ሐረርን ብንወስድ መንገዶችዋ ለተሽከርካሪ ምቹ ያልሆኑ ለእግረኛ ብቻ የሚሆኑ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለተሽከርካሪ ብቻ የሚሆኑ አሏት። ሐረር ውበቷ ይሄ ነው። የመንገዶችዋ፣ የሕንፃዎች አቀማመጥ፣ የእግረኛ መንገድ ስብጥር ይለያያል። አዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን የመንገድና የህንፃ ግንባታ ሐረር ላይ ለመተግባር ጥረት ቢደረግ ሐረር የምትታወቅበትን ታሪክና ሀብት ታጣለች። ስለዚህ የመንገዶች፣ የሕንፃዎችና የታሪክ ትስስር የሚሰጠን ጥቅምና የሚነግረን ታሪክ አለው።

አዲስ ዘመን፡- በአንዳንዶች ከሚቀርቡ ትችቶች፣ በባለሀብት የሚገነቡ ሕንፃዎች ግለሰቡ ውጭ ሄዶ ያየውን ግብዓትና ዲዛይን የመጠቀም ሁኔታ ነው። የእርስዎ ምልከታና አስተያየት ምንድነው?

አርክቴክት ብሥራት፡- ሁሉም ሳይሆኑ፤ የተወሰኑ ሰዎች ያደርጋሉ። እኔ ሃሳቡን እንደችግር አላየውም። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች እንዲህ ያለውን ርምጃ ለመውሰድ የሚገደዱት በከተማ ውስጥ በሚሰሩ ሕንፃዎች ደስተኛ ስለማይሆኑ ነው። እንደ ወረደ የመጣውን ገልብጦ መተግበር ትክክል አይደለም። ወንጀልም ነው። ከሀገር ውጭ ብቻ አይደለም በሀገር ውስጥም ቢሆን የሌላውን አስመስሎ መሥራት ሙያዊ ሥነ ምግባር አይደለም። የባለቤትነት መብት አለ።

ነገር ግን የሌላውን ሀገር የሕንፃ ውበትና መገለጫዎች ወስዶ በማጥናት ለሀገራችን ተስማሚ በሆነ መልኩ በእኛ አስተሳሰብ አሻሽሎ መሥራት ችግር የለውም። እርሱን ማድረግ ከቻልን በጣም ጥሩ ነው። ማድረግ ባለመቻላችን የሌሎቹን ወስደን በሀገራችን ውስጥ ለመተግበር እንሞክራለን። ይሄ ግን አግባብ አይደለም። በሀገራችን ውስጥም ቢሆን እንኳን አንዱ አካባቢ የሚሰራው ሕንፃ በሌላው አካባቢ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ሁሉም አካባቢዎች የየራሳቸው የሆነ የአየር ንበረት፣ የአኗኗር ሁኔታ፣ ባህል፣ የግንባታ ቁስ ተደራሽነት አላቸው።

አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ለሕንፃ ግንባታዎች የሚውሉ ግብዓቶች ከጭቃ፣ ከብሎኬት፣ ወደ ቀላል ተገጣጣሚ ግብዓቶች እየተሸጋገረ መጥቷል። እንዲህ ያለው መቀያየርና የደረጃ ጉዳይ እንዴት ይታያል?

አርክቴክት ብሥራት፡- በጭቃ ግብዓት መጠቀም በኢትዮጵያ ደረጃ ካየን፤ ያለውን የሕዝብ ቁጥር የሚመጥን ከፍተኛ ልማትን በጭቃ ለመሥራት የማያስችሉ ሁኔታዎችን በተመለከተ ከአንዳንዶች እለያለሁ። ተጠቃሚው ጋር ፍላጎቱ አለ ብሎም ማየት ያስፈልጋል። የገጠር ነዋሪው ሳር ቤቱን በቆርቆሮ ለመቀየር ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ይስተዋላል። እያንዳንዱ ሰው ለሚኖርበት ቤት የመወሰን መብት እንዳለው መዘንጋት የለበትም። የባለሙያውም ሆነ የአስፈጻሚው ድርሻ እንዴት በተሻለ ሁኔታ እንስራለት የሚል መሆን አለበት። የአካባቢ ብክለትን የሚቀንስ ምን ግብዓት እንጠቀም የሚል ሊሆን ይገባል።

አዲስ አበባ ከተማ ውስጥም ቢሆን እጅግ መስተዋት የበዛባቸው፤ የውጭውንና የውስጡን ሙቀት በከፍተኛ ሁኔታ የሚጨምሩ፤ ሰዎች በውስጡ እንዳይቀመጡ የሚያደርጉ ምቾት የሚነሱ እያደርግን ያለንበት ሂደት አግባብ አይደለም። ውስጣቸው ለተጠቃሚው የተሻለ ምቾት የሚፍጥሩ ውጫያቸው ደግሞ ውበት ያላቸው ለከተማው ጥሩ ገጽታ የሚያላብሱ መሆን አለባቸው።

ግብዓት አጠቃቀም ላይ ሀገር ውስጥ ያለውን ቁስ መጠቀም ይመረጣል። ኢትዮጵያ ውስጥ መሬት ውስጥ ብዙ ሀብት አለ። በግንባታው ዘርፍ ውስጥ ብዙ የሰው ኃይል በማሰማራት በእኛው አቅም መጠቀም እንችላለን። ከውጭ በግዥ ከምናስገባው ግብዓት ይልቅ ሀገር በቀል የሆኑ የግንባታ ቁሶችን ወይም ሀብት አሟጦ ለመጠቀም የሚያበረታታ ደጋፊ ሕግና መመሪያ ያስፈልጋል። ምክረ ሃሳብ ብቻውን በቂ አይደለም የሚል እምነት አለኝ። ምክንያቱም አንድ ነገር እስኪለመድ የራሱ የሆነ ክፍተት እንዳለው መርሳት የለብንም።

አዲስ ዘመን፡- በሕንፃ ግንባታ ጥቅም ላይ ከሚውሉት ግብዓቶች አንዱ ቀለም ነው። አሁን ላይ መንግሥት የከተሞች የሕንፃ ቀለም ግራጫ እንዲሆን መርጧል። የቀለም ምርጫው ምን መሆን አለበት ይላሉ?

አርክቴኬት ብሥራት፡- የሕንፃ ቀለም ወይም ኮድ አስገዳጅ መሆኑ በብዙ ሀገሮች የተለመደ አሠራር ነው። እያንዳንዱ የራሱን ፍላጎት የሚያንፀባርቅበት ሳይሆን እንደ ከተማ ምን ዓይነት ገጽታ ይኑር የሚለውን ለማየት የምንሰራበት ነው። ሆኖም ግን የቀለም ኮድ መመሪያ ሲወጣ መካተት ያለበት ነገር አለ። ለምሳሌ አንድ ከተማ በአንድ አይነት ቀለም የሚለው እየቀረ የመጣ እሳቤ ነው።

ደቡብ አፍሪካንም እንደ ምሳሌ ብንወስድ፤ ሄለንቦሽ በምትባል ከተማ ውስጥ ሁሉም ሕንፃ ነጭ እንዲቀባ ግዴታ ሆኖ ነበር። ውበት ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ድባቴን የሚያመጣ ነገር ይፈጥራል። አንድ የሆነ ቀለም ልናስብ አንችልም ግን ደግሞ ተቀራራቢ የሆኑ፣ በጣም የማይጣረሱ፣ ወይንም ምቾትን የማይነሱ፣ ሊሆኑ ይገባል።

በተለይ ደግሞ ከተፈጥሮ የምናገኛቸውን ቀለሞች ማካተት አለብን። ለምሳሌ ከመሬት ውስጥ ተፈልፍሎ የሚወጡ እንደ ሸክላ፣ ግራናይት፣ ማርብል፣ ባዛልት፣ የመሳሰሉት የየራሳቸው ቀለም ስላላቸው እነዚህን የተፈጥሮ ቁሶች ከሕንፃ ጋር አጣጥሞ መሥራት ሊፈቀድ ይገባል። እንደነ ኔዘርላንድ፣ እንግሊዝ፣ ቤልጄየም ያሉ ሀገሮች ሕንፃዎቻቸውን የሰሩት የተፈጥሮ ሀብቶቻቸውን በመጠቀም ነው ።

እንዲህ ዓይነት ቀለም ተፈቅዷል ሲባል፤ ከእርሱ ጋር የሚቀራረብ የተፈጥሮ ግብዓቶችን መጠቀም ያስፈልጋል። እነዚህ ግብዓቶች ሲታዩ የማይጨንቁ፣ ውበትም ያላቸው ከተፈጥሮ ጋርም የሚስማሙ፣ ጥሩ የሆነ ገጽታ የሚፈጥሩ ናቸው። ግብዓቶቹ በፋብሪካ ውስጥ ሳያልፉ ቅርጽ ብቻ ሰጥተናቸው ልንጠቀምባቸው የምንችላቸው ናቸው። በኢትዮጵያ ያለ ድካም ልንጠቀማቸው የምንችላቸው የምድር ውስጥ ሀብቶች አሉን።

የቀለም እይታ ከብዙ እይታና ምርጫ የሚመነጭ ነው። ሆኖም ግን ቀለም እይታን ብቻ ለመሳብ ተብሎ የተለያዩ ጥቅሞችንም እንዳያሳጣን መጠንቀቅ ይገባል። አሁን ላይ ስለተመረጠው ግራጫ ቀለም ለማንሳት፤ ግራጫ በነጭና በጥቁር መካከል ያለ ቀለም ነው። በጣም ደማቅ ቀለሞች ለሕንፃ መሆን የለባቸውም በሚለው እስማማለሁ። ደማቅ ቀለሞች ከተገቢው በላይ የማግነን ባህሪ አላቸው። በኔ እምነት እነዚህ ቀለሞች ሕንፃው ላይ መግባት የለባቸውም ብለን መደምደም ደግሞ የለብንም።

በወጣው የቀለም ኮድ ላይም እንደሁኔታው አስገዳጅ ሆኖ የወጣውን የቀለም ሕግ የማይተገበርበት ሁኔታ ተቀምጧል። በከተማው ላይ ገጽታ ሊሰጡ የሚችሉ ለየት ያሉ ሕንፃዎች ላይ በባለሙያ ከቀረበ ሊፈቀድ የሚችልበት ሁኔታ ቢኖር ጥሩ ነው። ለምሳሌ ዓድዋ ዜሮ ዜሮ ሙዚየም የተቀባው ቀለም ከቀለም ኮዱ ጋር አይሄድም። ሙዚየሙ የተቀባውን ቀለም በከተማው የግንባታ ቀለም ኮድ መሠረት እንገምግመው ብንል አሁን ያለውን ውበት ልናገኝ አንችልም። ምክንያቱም ከዓድዋ ተራራዎችና አቀማመጥ ታሪክ የተቀዳ በመሆኑ ነው። ልክ እንደዚህ ፕሮጀክት አስገዳጅ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። በዚህ ምርጫ አርክቴክቱ ትልቅ ኃላፊነት ስላለበት ለእርሱም ቢሰጠው ጥሩ ነው።

አዲስ ዘመን፡- በአንድ ከተማ ውስጥ ሊገነባ የሚገባው የሕንፃ ወለል ከፍታ ምን መምሰል አለበት? አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ስላሉት ሕንፃዎች የእርስዎ ግምገማ ምንድነው?

አርክቴክት ብሥራት፡- እንደየሀገሮች ተጨባጭ ሁኔታ ሊለያይ ይችላል። የሕንፃዎች ከፍታ እንደተከረከመ ጸጉር እኩል የሆነባቸው ሀገሮች አሉ። የአከታተም ሁኔታ በአንድ መመሪያ ሁሉም የዓለም ከተሞች የሚተገብሩበት ሳይሆን፣ ከራሱ ባህል፣ የኢኮኖሚ አቅም፣ የህብረተሰብ ፍላጎት፣ የመሬት አቀማመጥ፣ የአየር ንብረት አንፃር የሚታይ መሆን አለበት ።

አዲስ አበባ ከተማ ትክክለኛ አቅሟን የተረዳች አይመስለኝም። ለምሳሌ የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ሲጀመር አራት ፎቅ በመሥራት የመኖሪያ ቤት ችግርን ለማቃለል ነበር። አምስት ዓመት ሳይሞላ ወለሉ ወደ 8፣12፣18 ከፍ እንዲል ተደረገ። አሁንም ከዚያ በላይ እያሰብን ነው። ከተማ አርቃ የምታስበው አምስት ወይም አስር ዓመት ብቻ ከሆነ አቅሟን እንዳላወቅን የሚያሳይ ነው። እየሰራን እያፈረስን የምንሄድ ከሆነ ጠንካራ የሆነ የከተማ እድገት እንዳይኖር ያደርጋል። ስለዚህ ግንባታችን አዲስ አበባ በዓለም አቀፍ ተወዳድራ ልታመጣ የምትችለውን ኢኮኖሚ ግምት ውስጥ ያስገባ መሆን ይኖርበታል።

አዲስ ዘመን፡- በሀገር ውስጥ የሙያ ክህሎትን ለማሳደግ በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ በስፋት እየተሰራ እንደሆነ ይታወቃል፤ ይሄንን እንዴት ይዩታል?

አርክቴክት ብሥራት፡-የቴክኖሎጂ ሽግግሩ ለእኛ መልካም አጋጣሚ ነው። የቴክኖሎጂ ሽግግሩ ክፍተታችንን ለመሙላት ያስችለናል። ሰፋ አድርገን በማየት በቀጣይ እራሳችንን የምንችለበትን ሁኔታ መፍጠር አለብን። ሥራው ወደ እኛ እንዲመጣ ማድረግ አለብን።

አዲስ ዘመን፡- መንግሥት እያከናወነ ያለው የኮሪዶር ልማትና ተያያዥ ሥራዎች ላይ ያለዎትን ሙያዊ አስተያየት ቢገልጹልን?

አርክቴክት ብሥራት፡- መንገዶች በተሻለ መልኩ ታሳቢ ተደርገው መሰራታቸውን ጥሩ ነው። በዚህ ሂደት ጥንቃቄ መወሰድ አለበት የምለው ልማቱ እግረኛውን፣ የተሽከርካሪውንም ሁሉንም ያማከለ መሆኑን እያረጋገጡ መሄድ ያስፈልጋል። አንዱ ለሌላው እንቅፋት መሆን የለበትም።

እንዲህ ባለው ልማት አምስተርዳም በጥሩ ምሳሌ ትነሳለች። ነዋሪዎችዋ ብስክሌት በመጠቀም ቀዳሚ ናቸው። ሆኖም ግን የልማት ሥራው አንዱ የሌላውን በሚጋፋ መልኩ ሳይሆን፤ ጥሩ የሆነች ከተማ መፍጠር የተቻለው ሳይክሉ፣ ሞተሩ፣ መኪናው፣ ባሱ፣ ባቡሩ፣ ጀልባው፣ እግረኛው ሁሉም ዓይነት የትራንስፖርት አማራጮች ተናብበው እንዲንቀሳቀሱ በሚያስችል ሁኔታ የተሰራች ከተማ በመሆኗ ነው።

አዲስ ዘመን፡- በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ባለው የኮሪዶር ልማት የባለሙያው ተሳትፎ እንዴት ይገለጻል?

አርክቴክ ብሥራት፡- ተሳትፎ የለም ለማለት አልደፍርም። በቂ ነው ብዬ ግን አላምንም። ከዚህ በላይ ግብዓቶችን መሰብሰብ ቢቻል የበለጠ የተሻለ ነገር መሥራት ይቻላል ብዬ አምናለሁ።

አዲስ ዘመን፡- በዚህ የከተማ የመሠረተ ልማትና የሕንፃ ግንባታ እንደ አንድ ባለሙያ ከተማዎቻችን ምን ደረጃ ላይ ደርሰው ማየት ይመኛሉ?

አርክቴክት ብሥራት፡- ፕላን ሲወጣ አርቆ መታሰብ አለበት። ለምሳሌ አዲስ አበባ ከተማ በ2050 ዓ.ም ምን መምሰል አለባት የሚለው በፕላኑ ውስጥ መኖር አለበት። ብዙ ሀገሮች እቅዳቸው የረጅም ጊዜ ነው። እድገታችን ምን መሆን አለበት? የከተማው ነዋሪስ የት ይደርሳል? በእያንዳንዱ ቤት ውስጥ ምን ለውጥና ጥቅም ይኖራል? በሚል በሙያ የተደገፈ፣ ከተለያየ አቅጣጫ የታየ ጥናት ያስፈልጋል። ከእዚህ ጥናት ውስጥ እየተመነዘረ የሚተገበር፣ መድረሻው የማያሻማ ግልጽ እና ነፃ የሆነ ነገር ቢኖር ምኞቴ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።

አርክቴክት ብሥራት፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን  ግንቦት 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You