ከፅንፍ ረጋጮቹ ተርታ መሰለፍ እንደማይፈልጉ ደጋግመው የሚገልፁት ተሰማ መንግሥቴ፣ ገብረየስ ገብረ ማሪያም እና ዘውዴ መታፈሪያ ጠርሙስ እያጋጩ ይከራከራሉ:: ፅንፈኛ መባልን ሁሉም እንደማይፈልጉ ቢገልፁም፤ በተቃራኒው በንግግራቸው ውስጥ ፅንፍ ሲረግጡ ማስተዋል አያዳግትም:: በተለይ በዕልህ ሲናገሩ ፅንፈኛ መሆናቸው ያስታውቃል:: የዘውዴ ደግሞ የተለየ ነው:: ደጋግሞ ፅንፈኝነትን እንደሚቃወም ቢናገርም፤ በተግባር ግን ፅንፈኛ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶችን ማንም በሚያውቀው መልኩ ያመለክታል::
በተደጋጋሚ የሰዎችን አመጣጥ እና አጠቃላይ የኢትዮጵያን ታሪክ ሲናገር፤ የራሱ ወገን ሀገር እንዳፀና ደጋግሞ ይገልፃል:: ስለዚህ የኢትዮጵያ መስራች እና የሀገሪቱ ዋልታ የእርሱ ሰዎች ብቻ መሆናቸውን ያስረዳል:: ‹‹ትክክል አይደለህም›› ብሎ የሚናገረው ካለ፤ ሃሳባቸውን ለማጣጣል እና ሰዎቹ በሚሰነዝሩት ሃሳብ ለማሸማቀቅ የማያደርገው ጥረት የለም::
የሃሳብ ልዩነትን ከመቀበል እና ከማክበር ይልቅ መራር ወቀሳዎችን ከመሰንዘር ወደ ኋላ አይልም:: የግለሰቦችን ሃሳብ የመስጠት ፍላጎት ከመዝጋት አልፎ ሲለው ለማስፈራራት ይሞክራል:: አለማዳመጥ ብቻ ሳይሆን ያፈጠጠውን እውነት ለማየት አይፈቅድም:: ገብረየስ ለዘውዴ በተደጋጋሚ ይህ አካሔድ እንደማያዋጣው ቢነግረውም ለማዳመጥ ፈቃደኛ አይደለም::
ገብረየስ፤ ‹‹እኔ ለዓመታት ከለፋሁለት እና ብዙ ዋጋ ከከፈልኩበት ከድርጅቴ የወጣሁበት ዋነኛ ምክንያት አቋም ስላልነበረኝ አይደለም:: በድርጅቱ ውስጥ ያሉ ሰዎች ፅንፈኛ እና የራሳቸውን ጥቅም ብቻ አሳዳጅ እንዲሁም እነርሱ ከሚሉት ውጪ ሌሎችን የማያዳምጡ ሆነው በማግኘቴ ነው:: ተዉ ስል የሚሰማኝ በማጣቴ ብቻ ነው:: በተቃራኒው እውነትን በመያዜ ለመገለል:: በመጨረሻ ያልኩት አልቀረም፤ እነርሱ ገንዘብን በማምለክ እና ሕዝብን በመርሳታቸው ዋጋ ከፈሉ::
ቁስ የሰው ልጆች መገልገያ እንጂ የሚመለክ የህልውና ጉዳይ ተደርጎ መወሰድ የለበትም:: ከቁስ በላይ ሰው ይቀድማል:: ብዬ ብነግራቸውም ሊሰሙኝ አልቻሉም:: በመጨረሻ አፍ እንጂ ጆሮ የሌላቸው መሆኑን ደጋግሞ ሲናገር የነበረው ሕዝብ አንቅሮ ተፋቸው::›› ብሎ ሊቀጥል ሲል ተሰማ አቋረጠው::
ተሰማ፤ ‹‹ ቁስ አያስፈልግም ብሎ መጨፈን አያዋጣም:: ምክንያቱም የሰው ልጅ በቁስ መጠቀሙ ሕይወቱን በተሻለ መልኩ እንዲኖር የሚያስችለው መሣሪያ ነው::›› አለው:: ገብረየስ ‹‹ቁስ አያስፈልግም አላልኩም:: ነገር ግን ከቁስ ሰው ይበልጣል:: ሁለቱም ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ናቸው:: አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ መሔድ አያዋጣም:: በተለይ ከሰው በላይ ቁስ ሲመለክ ውጤቱ አደገኛ ይሆናል::›› አለ::
ተሰማ ገብረየስ የተናገረውን በቅጡ የሰማ አይመስልም፤ ‹‹ሰው ሲሠራ ለቁስ ትኩረት አትስጡ ብሎ ማጣጣል ተገቢ አይደለም:: ቢያንስ ካለመሥራት መሥራት ይሻላል:: እናንተ ግን በተቃራኒው ሰው ሲሠራ በርቱ እያላችሁ ከማነሳሳት ይልቅ የሚታያችሁ ክፍተቱ ብቻ ነው::›› አለ::
ገብረየስ ከት ብሎ ሳቀ፤ ‹‹ አንተም ከእርሱ የተለየህ አይደለህም:: እያንዳንዱ አካሔድ ሊተች እና ሊወቀስ አይገባም ማለት ትክክል አይደለም:: ተተችቶ ቢታረም ነውር የለውም:: በየጊዜው የሚያጋጥሙ ትችቶች ተስፋ ሊያስቆርጡ አይገባም:: በሌላ በኩል ከቁስ ጋር ልዩ ፍቅር ውስጥ መገባትም የለበትም:: ምክንያቱም ቁስ ያረጃል፤ የፈጣሪ ልዩ ፍጥረት የሰው ልጅ ግን ቢያረጅም ትቶት እና ተክቶት የሚያልፈው ብዙ ነገር አለ:: ለቁስ ሲሉ ሰው መጉዳት አይገባም:: የሰው ልጅ ጉዳት ጠባሳው የሚሻገር ነው:: ከቁስ በላይ ስለሰው ሕይወት መስራት ቀዳሚ ጉዳይ መሆን አለበት:: ›› ሲል ተናገረ::
ተሰማ ፤‹‹ እኔ ማንም ምንም መናገር የለበትም አላልኩም:: ትችት ሲኖር በልኩ መሆን አለበት የሚል እምነት አለኝ:: በሚሠራው ሥራ መደሰት እና ማድነቅ ቢያቅተንም ስንተችም በጥንቃቄ ሊሆን ይገባል ባይ ነኝ:: ዘውዴ ግን እንደምታየው በተደጋጋሚ የእርሱን አቋም የማይደግፉ ሰዎችን በፅኑ ይቃወማል:: የሚናገሩትን ለመስማት ፈፅሞ ዕድል አይጣቸውም:: በተደጋጋሚ ሃሳቡ ከኢኮኖሚ ጋር የተሳሰረ ቢመስልም እያነሳ የሚጥላቸው አጀንዳዎች መደምደሚያዎቹ ፅንፍ የወጡ ናቸው:: ለምሳሌ ኑሮ ተወዷል፤ ሲል መነሻ ምክንያት የሚያደርገው የሆነ ቡድንን ብቻ ነው:: ሁሉንም ጥፋት ሰብስቦ ለአንድ ቡድን ሲሰጥ፤ ‹ትክክል ነህ› ከሚለው ሰው ውጪ ሌሎችን ማዳመጥ አይፈልግም::
አንድ ሰው ከእርሱ ጋር ያለውን የሃሳብ ልዩነት ለማሳወቅ አለሳልሶ ‹በእርግጥ አንተ ተጠያቂ ያደረግከው ቡድን ክፍተቶች አሉበት፤ ነገር ግን ኑሮ እየተወደደ ያለው በኢትዮጵያ ወይም በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ሀገር እና በሁሉም ከተማዎች ነው:: ይህ የሆነው ዓለም አቀፍ ችግሮች ተደራርበው በመምጣታቸው ነው::› ብሎ ሊያስረዳው ቢሞክር ለመስማት ፈቃደኛ አይደለም::
በሰዎች ግላዊ ግንኙነት ላይ ሳይቀር ለሚሰጠው አስተያየት ዘውዴ የእርሱን አቋም የሚወስድ ከሌለ ፍፁም ይነቅፋል:: ሕግ ከተነሳ ሰዎች በሕግ ፊት እኩል ናቸው ቢባልም በተግባር እኩል አይደሉም ብሎ ሲናገር ተቃዋሚ እና የሆነ አሳማኝ ምክንያት አቅራቢ እንኳ ቢመጣ ለመቀበል ፍላጎት የለውም::›› በማለት ተሰማ ዘውዴ ፅንፈኛ እንደሆነ እና የሰዎችን ሃሳብም ሆነ አቋም ለመስማት እንደማይፈልግ አልፎ ተርፎ ወደ ጥላቻ እንደሚያዘነብል ሲናገር ዘውዴ በመከፋት እና በትዝብት ተሰማን አየው::
ገብረየስ በበኩሉ፤ ‹‹ ሁለታችሁም የተለያያችሁ ናቸው:: ተሰማ ሀገራችን ልታድግ እና ልትበለፅግ ነው ብለህ በትልቅ የተስፋ ባህር ውስጥ በደስታ ስትዋኝ፤ ከዚህ በኋላ ችግር አይኖርም የሚል ፅኑ እምነት እንዳለህ በማስተጋባት ሁሉም ያንን መቀበል እንዳለበት ታስተጋባለህ:: ዘውዴ ደግሞ በተቃራኒው በአንድ ለሊት ሀገር ልትፈርስ ነው ብለህ ታስባለህ:: አንተ እንዳሰብከው እና እንደተናገርከው ቢሆን ኖሮ ገና ድሮ ሀገር ፈርሳ ነበር:: ነገር ግን ሀገር ትፈርሳለች ብለው ከሚያስቡት በላይ ሀገራችን ትልቅ ተስፋ አላት:: ሀገራችን በፍፁም አትፈርስም የሚሉት ስለበዙ ሀገራችን አሁንም አለች:: ይህ የእኔ እምነት ነው::
በእኔ በኩል በተደጋጋሚ እኔ እጎዳለሁ፤ ቤተሰቦቼ ያልቃሉ፤ ሀገር ትፈርሳለች ከማለት ይልቅ እንዳልጎዳ እና ቤተሰቦቼ እንዳያልቁ ሀገሬ እንዳትፈርስ ምን ላድርግ ብሎ ማሰብ እና ያንንም ግዴታ መወጣት እንዲሁም የሚጠበቅብህን መሥራት ይሻላል:: ፍፁም ጽፅልመት ምንም መፍትሔ አያመጣም፤ መጨረሻው በተመሳሳይ መልኩ ያው ጽልመት ነው:: የሚሻለው ከጽልመት ወደ ብርሃን መምጣት ነው:: ራስን ማየት መገምገም እና ማረም፤ ፍፁም መስመር ከለቀቀ ፅንፈኝነት ወደ መካከለኛው መንገድ መምጣት ያስፈልጋል::›› አለ::
ተሰማ በበኩሉ እርሱ ሳይሆን ፅንፈኛው ዘውዴ እንደሆነ ለማስረዳት፤ ‹‹ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያለች ሀገር እንደሆነች እየታወቀ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ይሆናል ብሎ መጠበቅ የዓለምን ተጨባጭ ሁኔታ ካለመረዳት የመነጨ ይመስለኛል:: ዘውዴ ይህንን አይገነዘብም ትንሽ ትችት ሲነሳ ያዙኝ ልቀቁኝ ይላል:: ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ እንደሆነ ሁሉም ሰው እንዲያስብ ይፈልጋል:: ይህ ደግሞ እንኳን ኢትዮጵያን በመሰለ ሀገር ቀርቶ አደጉ በሚባሉት ሀገራት እንኳን የሚታሰብ አይደለም::
ሁልጊዜም ከጥሩ ሥራዎች ጎን ለጎን የሚተቹ፤ የሚታረሙና የሚወቀሱ ሥራዎች ሊኖሩ ይገባል:: ሀገርም የምታድገው ጎሽ፤ ጎሽ በሚሉ ሃሳቦች ሳይሆን የሰላ ትችት በሚያቀርቡ ዜጎች ጭምር ነው:: ስለዚህም አድናቆት ብቻ ሳይሆንም ትችትንም አጥብቆ መሻት አለብን:: ›› አለ::
ዘውዴ ሁለቱም በየተራ ሲወርዱበት ምላሽ አልሰጠም:: የተናገረው፤ ‹‹እንደፈለጋችሁ ማለት ትችላላችሁ:: እኔ ያልኩት መሸፋፈን ይቅር ነው:: ነገሮችን በመሸፋፈን ቁጥር ለመፍትሄውም እየራቅን እንመጣለን:: ደግሞ ብዙዎቹ የምንሸፋፍናቸው ነገሮች ሳይውል ሳያድር መታወቃቸው አይቀርም:: ቢታወቁ እንኳን ችግር የሚያመጡ አይደሉም::
የመሸፋፈን አባዜ ስለተጠናወተን የማይሸፈነውን ሁሉ ለመሸፋፈን እንሞክራለን:: ይህ ሲሆን ደግሞ ነገሩ ከአቅሙ በላይ ግዝፈት አግኝቶ የሰው ቀልብ ይስባል:: እውነታው ሲገለጥ ግን የሸፈንነው ጉዳይ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም:: ስለዚህም ሁላችንም የመፍትሄው አካል እንድንሆን ነገሮችን በግልጽ አውጥተን እንወያይባቸው:: ይህን ተገንዝቦ እኮ መንግሥት በግልጽ እንወያይ፤ እንመካከር እያለ ነው:: የምክክር ኮሚሽን አቋቁሞ የደባበቅናቸውን ሃሳቦች በሙሉ በግልጽ እንነጋገርባቸውና መፍትሄ እናስቀምጥላቸው እያለ ነው:: በግልጽ ስንወያይ፤ ስንመካከረው ነው መፍትሄ ላይ የምንደርሰው የሚል ጽኑ እምነት አለኝ::
የኢትዮጵያ ችግር ለዘመናት ሳይፈታ እዚህ የደረሰው መነጋገር ባለመቻላችን ነው:: ዝምታን መርጠን ፤መወያየትን ፈርተን ፤ ተደባብቀን በመኖራችን አሁንም ችግራችንን ታቀፈን ይዘናል:: ስለዚህም ማለባበስ ይቅር ነው ያልኩት ›› ብሎ ሃሳቡን ቋጨ::
ገብረየስ በበኩሉ፤ ‹‹እኔ አትተች አላልኩም:: መተቻቸት ሃሳብን በሃሳብ መቃወም አስፈላጊ ነው:: ያለበለዚያ ሰዎች ከስህተታቸው ሳይታረሙ እዛው በተቸከሉበት ይቆማሉ:: ቆሞ መቅረት ደግሞ ፍሬ አያስገኝም:: የማያዳምጥ እርሱም ቆይቶ አዳማጭ ማጣቱ የማይቀር ነው:: የሚያዳምጥ ይማራል፤ እርሱም ተደማጭ ይሆናል:: አሁን በዋናነት የሚያስፈልገው ተደጋጋሚ ትችት እና ወቀሳ አይደለም:: ይህ ሲባል አትተቹ ለማለትም አይደለም:: ገንቢ ትችት ቦታ ሊሰጠው ይገባል:: በዋናነት ግን ማንም ቢሆን ራሱን ለመተቸት ማዘጋጀት አለበት:: የሚሠራ ቢተች ችግር የለውም:: ራሱን ያሻሽላል:: የማይሰራም ሥራው መተቸት ብቻ ሊሆን አይገባም:: ደግሞ በወቀሳና በምክክር መካከል ያለውን ልዩነት መርሳት አይገባም::
ሁሉም ሥራውን መሥራት እና ግዴታውን መወጣት አለበት:: መታረምም የትልቅነት መገለጫ ነው:: ሰው አብሮ ሲኖር መጋጨቱ አይቀርም:: ወይም በመኖርም ሆነ በመምራት ሂደት አንድ ሰው ከስህተት የፀዳ አይሆንም:: ማንም ሆነ ማን ሊያጠፋ ይችላል:: እንኳን የሚመራ እና የሚሠራ አብሮ እየበላ የሚኖር አንድ ቤተሰብም እርስ በራሱ የማያስማሙት ነገሮች ሊጋጥሙት ይችላሉ:: ለዚህ መፍትሔው አንዱ ሌላውን ማዳመጥ እና ራሱን በዛ ሰው ቦታ ላይ ተክቶ ማየት ያስፈልጋል:: ዋናው ጉዳይ ማንም መጎዳት የለበትም:: ሁሉም አንድ ወገንን ለመጥቀም እና አንዱን ወገን የበላይ ለማድረግ ሳይሆን ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግ ይሥራ፤ ይህ እንዲሆን የእውነት ምክክር ያስፈልጋል:: ይሄንን ከልቤ እቀበላለሁ::
ምክክር የሁሉም ነገር መፍትሄ እንደሆነ ማመን ይገባናል:: አንዳንዶቹ እኮ እንመካከር ሲባል እንታኮስ የሚሉ ናቸው:: በጠረጴዛ ዙርያ እንወያይ ሲባሉ በጥይት እንፈታተሽ የሚሉ በርክተዋል:: የሀገር ፍቅርና ከብር ተዘንግቷቸው ብሄር አምላኪ ሆነው ብሄሬ ተነካ በሚል ሽፋን ጦር የሚመዙ መብዛታቸው ሁላችንም እየኖርንበት ያለው ሀቅ ነው::
እናም ጽንፈኛ ሆነን ስንገኝ በተዘዋዋሪ እነዚህን ሰዎች ሃሳብ መደገፋችን መሆኑን ማስተዋል አለብን:: ከየትኛው አካባቢ ይምጣ የጽንፈኛ አስተሳሰብ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም:: የአንዱ ቅዱስ የሌላው ርኩስ የሚሆንበት አጋጣሚ አይኖርም:: ካወገዝንም ፤ ከደገፍን አንድ መሠረት ላይ ቆመን ሊሆን ይገባል:: ይህ መሠረታችን ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ነው:: ኢትዮጵያ የሚጎዳ በሙሉ ከየትም ይምጣ ሊወገዝ ይገባል:: ኢትዮጵያን የሚጠቅም ከሆነ ደግሞ ማንም ይናገር ፤ ማንም ይሥራው ሁላችንም በደስታ ልንቀበለው ይገባል:: ጽንፍ ላይ ቆመን የምንደግፈውም ሆነ የምንቃወመው ነገር ውጤቱ እኩል ነው:: ከጽንፈኛ አስተሳሰብ የሚወጣ መልካም ቃላትም ሆነ ድርጊት የለም:: ሁሉም ጎጂ ነው:: በማለት ገብረየስ ሁለቱንም ፈገግ ብሎ አያቸው:: ተሰማ ገራገር በመሰለ ፊቱ ፈገግ አለ:: ዘውዴ ግን ግንባሩን እንደቋጠረ ‹‹ ወይ መሬት ያለ ሰው?›› ብሎ ከመቀመጫው ተነሳ::
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም