ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድር በአዲስ አበባ ይካሄዳል

21ኛው የባህል ስፖርቶች ውድድርና 17ኛው የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል ከሚያዝያ 12 እስከ 20- 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተናጋጅነት ይካሄዳል። ውድድሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ ቅድመ ዝግጅቶች መደረጋቸውን የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን፣ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እና የከተማዋ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታውቀዋል።

ውድድሩ የማህበረሰቡን በባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል ተሳታፊና ተጠቀሚ ለማድረግ አላማ አድርጎ “የባህል ስፖርቶቻችን ልማት ለገጽታ ግንባታችን” በሚል መሪ ሃሳብ ከነገ ጀምሮ ለተከታታይ 9 ቀናት ይካሄዳል። የባህል ስፖርቶች ለ21 ጊዜ እና የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል ደግሞ ለ17ኛ ጊዜ ቀጥሎ እንደሚካሄድ ከትናንት በስቲያ በተሰጠው ጋዘጣዊ መግለጫ ተገልጿል።

የውድድሩ መክፈቻ እና የመዝጊያ ቀን መርሀ ግብር በአንጋፋው የአዲስ አበባ ስቴዲየም የሚደረግ ይሆናል። ለጸጥታና ለውድድሩ አመቺነት ሲባል አብዛኞቹ ውድድሮች በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የሚካሄዱ ሲሆን፤ የፈረስ ጉግስና ፈረስ ሸርጥ ውድድሮች በጃንሜዳ ይደረጋሉ። ለዚህም ፈረሰኞች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ሜዳውን የማስተካከልና የመደልደል ሥራ እንደተሠራ ተጠቁሟል።

በዚህ ደማቅ ውድድር ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚሳተፉ ሲሆን፤ የትግራይ ክልል ባጋጠመው የበጀት እጥረት ላይሳተፍ እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን፤ ችግሩን ለመፍታት ግን ጥረቶች እንደሚደረጉ ተጠቁማል። በ11 የስፖርት ዓይነቶች (ፈረስ ጉጉስ፣ ፈረስ ሸርጥ፣ ትግል፣ የገና ጨዋታ፣ ገበጣ ባለ12 እና 18 ጉድጓዶች፣ ኮርቦ፣ ሻህ፣ ቡብ፣ ሁሩቤ እና ቀስት) 885 ወንዶችና 550 ሴቶች በድምሩ 1445 የባህል ስፖርተኞች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ ማደጉ ተነግሯል። እነዚህ ስፖርቶች ሕግና ደንብ ወጥቶላቸው እስከ ወረዳ ድረስ ሰፊ ውድድሮች እየተካሄደባቸው መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሕይወት መሐመድ፣ ውድድሩን በድምቀት ለማካሄድ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከአዲስ አባባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር በመቀናጀት ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ መቆየቱን ተናግረዋል። ይህም አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና በመሆኗ ከወትሮ በተለየ መልኩ የባህል ስፖርቶች ለዓለም የሚተዋወቁበትን አጋጣሚ እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።

ስፖርቱ ከሌሎች ስፖርቶች የሚለየው አርሶ አደሩን እና አርብቶ አደሩን ጨምሮ ማንኛውንም የኅብረተሰብ ክፍል ተሳታፊ የሚያደርግ በመሆኑ፣ ትልቅ የአብሮነት ትስስር የሚደረግበት መድረክም ጭምር ነው። የባህል ስፖርት የእኛነት መገለጫ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊያሳድገውና ሊያለማው ይገባል ተብሏል። መድረኩ የባህል ስፖርቶችን ለኦሊምፒክ ስፖርቶች ለማብቃት ጥረት የሚደረግበት እንደሚሆንም ተገልጿል። የባህል ስፖርቶች የጋራ መገለጫችን በመሆናቸው መንከባከብና በጋራ ማሳደግ እንደሚገባም ተገልጿል።

ውድድሩን በተሻለ መልኩ ለማካሄድ ሁለተኛ ደረጃ እና ኢንስትራክተር የሆኑ 20 ዳኞች ከየክልሉ የተመረጡ ሲሆን፤ ከውድድሩ በፊት የሙያ ማሻሻያ ስልጠና በመውሰድ ዝግጁ ይሆናሉ።

የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን፣ የውድድሩ ዋና አላማ ከስፖርታዊ ውድድርና ባህል ፌስቲቫልነት ባሻገር በሁሉም ክልልና ከተማ አስተዳደሮች መካከል አብሮነትን በመፍጠር የሀገርን መልካም ገጽታ የሚገነባ መሆኑን ተናግረዋል። ከተማዋ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና የአፍሪካ መዲና በመሆኗ፤ ይሄን የሚመጥን ውድድር ለማዘጋጀት ከተማዋ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነ አመላክተዋል።

ከተሰሩት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መካከል መሪ እቅድ በመዘጋጀት ከ36ቱ ፌዴሬሽኖችና አሶሴሽኖች እንዲሁም ከስፖርት ቤተሰቡ ጋር ውይይቶችን በማካሄድ በቂ ቅድመ ዝግጅት እንደተደረገ ተጠቁሟል።

ከሁሉም ክልልና ከተማ አስተዳደር ለሚመጡት የውድድሩ ተሳታፊዎች የማደሪያ እና የትራንስፖርት አገልግሎት በበቂ ሁኔታ ተዘጋጅቷል። በዚህም ሁሉም ተሳታፊ ልዑካኖች በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ የሚያርፉ ይሆናል።

የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ ለባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን ገልጸው፤ ስፖርት ሕዝብን የሚያቀራርብ፣ ለአንድነትና ለሀገር ግንባታ አስተዋጽኦ የሚያደርግ በመሆኑ በባህል ስፖርቶች ሀገራዊ የትውልድ ግንባታ ጉዞ ለማስቀጠል አላማ አድርጎ ይካሄዳል ብለዋል። በኢትዮጵያ የሚገኙትን የባህል ስፖርቶችን ማልማትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስተዋወቅ ትልቁ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቀዳሚ ሥራ መሆኑንም አክለዋል።

የባህል ስፖርቶች ውድድር በሀገር አቀፍ ደረጃ በ1990 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ስድስት የስፖርት አይነቶችን በመያዝ በአዲስ አበባ ተካሂዶ ነበር። ነገር ግን ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ 11 ስፖርቶችን አካቶ እስከ አሁን ሳይቋረጥ እየተካሄደ ይገኛል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You