ስታርትአፖች – ለሀገራዊ ምጣኔ ሀብት ዕድገት

ወደ ገበያ ሊወጣ የሚችል የተለያየ የፈጠራ ሃሳብና ችግር ፈቺ የሥራ እቅድ ይዘው ነገር ግን አሳሪ በሆኑ ሕጎች፣ ትኩረት ባለማግኘታቸውና በተለያዩ ምክንያቶች የፈጠራ ሃሳባቸው መክኖ የሚቀርባቸው ሥራ ፈጣሪዎች ብዙ ናቸው::

የመፍጠር ክህሎት (ታለንት) ያላቸው ነገር ግን ክህሎታቸውን ወይንም ሃሳባቸውን ወደ ተግባር ለመለወጥ እክል ያጋጠማቸው በርካታ ወጣቶች አሉ:: በዋነኝነትም ለሥራ መነሻ የሚሆን የገንዘብ አቅም አለመኖር፣ የሥራ ቦታ አለማግኘት፣ የሚደግፋቸው ሕግ አለመኖርና የመንግሥት ትኩረት ማነስ በዋናኝነት ከሚገጥሟቸው ችግሮች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው::

እነዚህን ተግዳሮቶች ተቋቁመው ውጤታማ ከሆኑ ከጥቂት የፈጠራ ሃሳብ አፍላቂዎችና ችግር ፈቺ የሥራ እቅዳቸውን ከተገበሩት በስተቀር ብዙ የፈጠራ ሃሳቦችና እቅዶች ባክነው የሚቀሩ ናቸው::

ለገበያ ሊውሉ የሚችሉ የፈጠራ ሃሳቦችና ችግር ፈቺ የሥራ እቅድ ያላቸው ስታርትአፕ ኢንተርፕሪነሮች (ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች)፤ በአጭር ጊዜ ፈጠራ የታከለበት፣ በአጭር ጊዜ ደግሞ በርካታ ሀብት ለማመንጨት የሚችሉ ጀማሪ ቢዝነሶች ተብለው ይገለጻሉ:: በዚህ መልኩ የሚገለጹት ኢንተርፕራይዞች አብዛኞቹ በወጣትነት እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ እንደሆኑ ይገመታል::

ሃሳባቸውና የሥራ እቅዳቸው ወደተግባር ቢሸጋገር አፍላ በሆነው እድሜያቸው ለሀገር ብዙ የሚጠቅም ነገር ሊያበረክቱ እንደሚችሉ ይታሰባል:: ለዚህም ይመስላል መንግሥት ስታርትአፕ ኢንተርፕሪነሮችን በሚችለው ሁሉ በመደገፍ የሚበረታቱበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እንቅስቃሴውን ያጠናከረው:: አሳሪ የሆኑ የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ ርምጃ በመውሰድና የተለያዩ ድጋፎችንም በማድረግ መንግሥት ዝግጁነቱን በተግባር አሳይቷል::

መንግሥት ስታርትአፕ ኢንተርፕሪነሮችን ለማገዝ ያለው ዝግጁነትና ቁርጠኝነት፣ እንዲሁም ሥራ ፈጣሪዎች መበረታታቸው በሀገር የኢኮኖሚ እድገት ላይ ሊኖረው የሚችለው ፋይዳ እንዴት ይገለጻል? ስንል ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ባለሙያዎችና ኃላፊዎች አነጋግረናል::

በጉዳዩ ላይ፤ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው የሆኑት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ እንደሚናገሩት ፤ ስታርት አፕ የሀገር ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር ነው::

በሌላው ሀገር ኡበር በሚል የሚታወቁና በኢትዮጵያ ደግሞ ራይድ የሚባሉ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በቢሊየን ዶላር የሚቆጠር ሀብት ማፍራት የቻሉ ስታርትአፖች ናቸው::

እንደ ምጣኔ ሀብት ባለሙያው ማብራሪያ፤ ሀገራችን ውስጥም ወጣቶች የፈጠራ ችሎታቸውን በመጠቀም ትልቅ ኩባንያ መፍጠር ይችላሉ:: ለምሳሌ ናይጄሪያ፣ ኬኒያ፣ ሴኔጋል፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ስታርትአፕ የሚባሉ ከውጭ ሀገር በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ካፒታል መሳብ ችለዋል:: በአፍሪካ ውስጥ በቢሎን ዶላር የሚቆጠር ሀብት ያሰባሰቡ ስታርትአፖች አሉ::

ያደጉ የዓለም ሀገራት እንደነ ሰሜን አሜሪካ፣ ደቡብ አሜሪካ፣ እስያ ያሉ ሀገራት በአሁኑ ጊዜ የተጨናነቀ በመሆኑ በርከት ያለ ኢንቨስትመንት እየመጣ ያለው ለአፍሪካ ስታርትአፖች ነው:: ይሄ ለአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ጥቅም አለው::

ስታርትአፕስ ብዙ ጊዜ የሚገናኙት ከካፒታል ገበያ ጋር ነው:: ሃሳባቸውንና የሚያቅዱትን ነገር በካፒታል ገበያው ላይ ትንሽ ካንቀሳቀሱ በኋላ በካፒታል ገበያው ላይ አክሲዮን በመሸጥ ከፍተኛ ገንዘብ ያገኛሉ:: ሰሜን አሜሪካንና ቻይና ያሉ ብዙ ስታርትአፕስ በካፒታል ገበያው ላይ ነው እራሳቸውን በማሳደግ ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው::

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ የኢትዮጵያ መንግሥትም ይህን ሁሉ ከግምት ውስጥ አስገብቶና የሀገርን ተጠቃሚነት አስቀድሞ ለዚህ ጉዳይ ትኩረት መስጠቱ ያስመሰግነዋል ብለዋል::

እርሳቸው እንደሚሉት፤ ስታርትአፕስ ካፒታል የላቸውም፤ ባንኮችም ብድር ለመስጠት መያዣ (ኮላተራል) ይጠይቃሉ:: ወይንም ደግሞ በቅድሚያ 30 በመቶ ወይንም 40 በመቶ እንዲያሲዙ የሚጠየቁቡት አሰራር ነው ያለው:: በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አንድ ስታርትአፕ ቢሮ መክፈት፣ አድራሻ ማሳወቅ አለበት:: የሥራ ፈቃድ የመሳሰሉት ማነቆዎች አሉ:: ስታርትአፖች ግን በዚህ ሁሉ አስጨናቂ ሁኔታ አልፈው መሄድ የሚያስችል አቅም የላቸውም:: ስለዚህም መንግሥት እነዚህም ማነቆዎች እየፈታ መምጣቱ ስታርትአፖች በቀላሉ ፍሬ እንዲያፈሩ በር የሚከፍት ነው ሲሉ ተናግረዋል::

በሌላም በኩል በኢትዮጵያ የውጭ ባንኮች መግባት ለስታርትአፖች ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ባለሙያው ይናገራሉ:: ‹‹የውጭ ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገቡ ከዚህ ቀደም በመንግሥት ተገልጿል::

እነዚህ ባንኮች የፈጠራ ችሎታ ያላቸውን ወጣቶች ያበረታታሉ ተብሎ ይጠበቃል:: ባንኮቹ በመያዣነት የሚጠይቁት ፕሮጀክታቸውን ነው:: ወጣቶቹ አዲስ ኩባንያ በሚጀምሩበት ጊዜ የወሰዱትን ብድር ምን ላይ አዋሉት የሚሉ መስፈርቶችን አስቀምጠው ነው እየተቆጣጠሯቸው ገንዘብ የሚሰጧቸው:: ስታርትአፕስ በዚህ መንገድ ከታገዙ ለሀገር ጥቅም የሚሰጡ ናቸው›› ሲሉም አስረድተዋል::

በንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ መደበኛ ያልሆኑ፣ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች ተብለው በደንብ አስከባሪዎች የሚሳደዱት የፈጠራ ሥራ ስላላቸው እንደሆነና እነዚህ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች አድገው ነገ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ሊሆኑ እንደሚችሉም ገልጸዋል::

መንግሥት በስታርትአፖች ላይ ስጋት ሊያድርበት አይገባም የሚሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ ስታርትአፕስ ከሥራ አጥነት ወደ ሠራተኛነት፣ ብሎም ወደ ሠራተኛ ቀጣሪነት የሚሸጋገሩ እንደሆኑ፣ የመንግሥትን ሥራ የመፍጠር ጫና በከፍተኛ ሁኔታ የሚያቃልሉ መሆናቸውን አመልክተዋል:: መንግሥት የሚያሠራ ፖሊሲ ማውጣትና ሌሎችንም ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው የሚጠበቅበት ሲሉ ገልጸዋል:: የጉምሩክ አሠራሮችን በቀበሌና በወረዳ ያሉ የአሠራር ማነቆዎች እንዲፈቱና የተቀላጠፈ አገልግሎት መኖር እንዳለባቸውም ይጠቅሳሉ::

የውጭ ባንኮች በሀገር ውስጥ ሥራ ጀምረው ለስታርትአፖች የሚሆን መዋዕለ ነዋይ እስኪያመቻቹ ድረስ መንግሥት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይጠበቅበታል የሚሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ ‹‹ጊዜውን በትክክል ባልገልጸውም ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ይመስለኛል መንግሥት ወደ 10 ቢሊየን ብር በመመደብ ወጣቶች በተለያየ የሥራ መስክ ላይ እንዲሰማሩ ሁኔታዎችን አመቻችቶ ነበር:: እንዲህ ያሉ ነገሮች ያስፈልጋሉ:: ይህን በልማት ባንክ ወይንም በንግድ ባንክ በኩል ማመቻቸት ይቻላል:: የኢንቨስትመንት ባንኮች ከመጡ በኋላ ግን ስታርትአፖች እራሳቸው ሃሳባቸውን እያቀረቡ በቀላሉ ብድር የሚያገኙበት ሁኔታ ይፈጠራል›› በማለት የመንግሥት ዋነኛ ተግባር የተቀላጠፈ አሠራር ሥርዓት መዘርጋት መሆኑን አስምረውበታል::

እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ገለጻ፤ ሃሳብ ሁሉ ስታርትአፕ መሆን ይችላል:: ለምሳሌ ወጣቶች ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የተለያዩ ነገሮችን መሥራት የሚያስችላቸው ዕድሎች አሉ:: እንደ ሕንድ ናይጄሪያ ሴኔጋል ያሉ ሀገሮች በተንቀሳቃሽ ስልካቸው በግብርና ሥራ ላይ ለተሰማሩ የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ እያገዟቸው ነው:: ማዳበሪያን ጨምሮ የተለያዩ የግብርና ግብዓቶችን መግዛት ያስችላቸዋል:: እንዲህ ያለው ሃሳብ ትንንሽ ሊመስል ይችላል:: ነገር ግን ጥቅሙ ሰፊ ነው:: ቴክኖሎጂውን ተጠቅመው ለአርሶ አደሩ ሁኔታዎችን የሚያመቻቹ ጥቅሙ ለሀገርም ጭምር መሆኑን ይናገራሉ::

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ የውጭ ሀገራትን ተሞክሮ አስመልክተው እንደተናገሩትም ‹‹ዛሬ ስመጥር የሆኑት እነ አፕል፣ ማይክሮሶፍት በቤተሰባቸው የመኪና ጋራዥ ውስጥ በአነስተኛ ሥራ ተጀምረው ነው በዓለም ውስጥ በሀብት መጠናቸው በከፍተኛ ደረጃ ሊጠሩ የበቁት::

በኢትዮጵያም አስፈላጊውን ነገር ማመቻቸት ከተቻለ እንዲህ ያለውን እድል ማምጣት የማይቻልበት ሁኔታ አይኖርም:: መንግሥት ሕግ ከማስከበር፣ መሠረተ ልማትን ከማሟላት አልፎ የግሉ ዘርፍ ሊሠራቸው በሚችላቸው ነገር ውስጥ መግባት አይጠበቅበትም:: እንደ ሀገር ከሚሰበሰብ ታክስ ገቢን ለማሳደግ የግሉን ዘርፍ ማበረታታት ያስፈልጋል::›› ሲሉ ሃሳባቸውን ደምድመዋል::

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው፤ የመንግሥት እገዛ ከንግግር ባለፈ በተለያየ መንገድ የሚገለጽ መሆኑን ይናገራሉ::

የመንግሥት ቁርጠኝነት በተግባር የተረጋገጠ መሆኑንን በመጥቀስ፤ የተጀመረውን ሥራ ለማሳለጥ የሚችሉ ተቋማትን በማደራጀት፣ በአሠራር፣ በፖሊሲ፣ በሕግ በፋይናንስ ድጋፍ መሥሪያና መሸጫ ቦታዎችን ምቹ በማድረግና በሌሎችም ድጋፎችን እያደረገ ባለው ሥራ ይገለፃል ብለዋል::

አዳዲስ ፖሊሲዎችን በማውጣት የወሰደው ርምጃ ሌላው መገለጫ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሯ ለአብነት ጥቃቅን፣ አነስተኛ፣ መካከለኛ የሚባሉ ኢንዱስትሪዎችና ከፍተኛ የማደግ አቅም ያላቸውን ኢንዱስትሪዎች ጨምሮ ሁሉንም ሊደግፍ የሚችል ፖሊሲ መውጣቱንም ተናግረዋል:: ፖሊሲው ስታርትር አፖችን ሊደግፉ የሚችሉ ወደ ዘጠኝ ገደማ የሚሆኑ ምሶሶዎችን የያዘ መሆኑንም አንስተዋል:: ፖሊሲውን ተከትሎም አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ይወጣሉ ብለዋል::

እገዛው ሥራን አስቸጋሪ በሆነ መንገድ መፍጠር ሳይሆን፤ በተሻለና በተሳለጠ መንገድ መፍጠር የሚቻልበትን እድል የሚሰጥ እንደሆነ የጠቀሱት ወይዘሮ ሙፈሪያት፤ የስታርትአፕ ፖሊሲውም እንዲሁ ከሕግና ከፖሊሲ አኳያ፣ እንዲሁም ሌሎች ከአሠራር ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል::

ፖሊሲው ወደ ዘጠኝ ገደማ የሚሆኑ ትላልቅ የፖሊሲ ሃሳቦችን የፋይናንስ ጉዳዮችን ጨምሮ የክህሎት ልማት ሥራዎችን ያካተተ የአእምሮ ንብረት ባለቤትነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ጨምሮ ስታርትአፖች ለሚሰሯቸው ሥራዎች የሚያገኟቸውን ሀብቶች መልሰው ለሥራቸው ጥቅም ላይ እንዲያውሉ ማድረግን የሚጨምር እና የመሥሪያ የመሸጫ የሚባሉ ቦታዎችን ችግር የሚፈታ መሆኑን አብራርተዋል:: በዚህም መንግሥት ትልቅ ውሳኔ ማሳለፉን አስረድተዋል::

ወይዘሮ ሙፈሪያት፤ እንደሚሉትም ‹‹በሥራ ዕድል ፈጠራው አንዱ ትልቁ ነገር ወይንም ጉልበት ሃሳብ ነው:: የሥራ ሃሳብ ፈጠራን ያበረታታል:: ፈጠራ አለ ማለት ደግሞ ያልተቋረጠ እድገት አለ ማለት ነው:: ያልተቋረጠ እድገት አለ ማለት ደግሞ ተወዳዳሪ የሆነ ኢኮኖሚ ይፈጠራል:: የኢኮኖሚው ተወዳዳሪነት ደግሞ በዜጎች ሕይወት ውስጥ ትርጉም ያለው ያደርገዋል:: ጥራት ያለው ተጠቃሚነትን ማረጋገጥና የሥራ እድል እንዲያገኙ ያልተቋረጠ ገቢ እንዲያገኙ ማድረግን ሁሉ ያካትታል:: ሂደቱ ያልተቋረጠ አዳዲስ ፈጠራ ላይ የተመሠረተ የሥራ ሃሳብም ይፈጠራል›› ሲሉ አብራርተዋል::

እንደ ወይዘሮ ሙፈሪያት ማብራሪያ፤ አሁን ላይ የሥራ ዕድል መፍጠሪያ መንገድ የተለየ ሃሳብ እንዲይዝ ተደርጓል:: አሁን ያለው አቅጣጫ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሥራ ዕድል መፍጠር ሳይሆን፣ ሀብት ሊያመነጭ የሚችል የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር ነው:: ኢትዮጵያ ወደ ሀብት ሊቀየር የሚችል እምቅ የሆነ ሀብት ወይንም ፀጋዎች አሏት:: ከሕዝቧ 70 በመቶ የሚሆነው በወጣትነት እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ የሚሠራ የሰው ኃይሏም ከፍተኛ ነው:: እነዚህን ዕድሎችና አቅሞች ለሀገር ሀብት በሚፈጥር ሁኔታ መጠቀም ይገባል:: ሀብት መፍጠር ሲባል ደግሞ የማይቋረጥ፣ ታይቶ የማይጠፋ፣ ዘላቂነት ያለው የሀብት ፈጠራ ሥርዓት እንዲኖረው ተደርጎ ነው የተቀረጸው::

የሥራ ዕድል ፈጠራ (ኢንተርፕሪነርሺፕ) ባህል በተለመደው አካሄድ ሳይሆን፣ ባልተለመደ መንገድ ችግር መስለው የሚታዩ ጉዳዮችን ኃላፊነት ወስዶ በድፍረት ወደ ዕድል መቀየር ማለት ነው:: ይሄን አስተሳሰብ ይዞ ወደ ሥራ መግባት ሳይሞከር ገና በርቀት የሚፈሩና ችግር ይሆናሉ ተብለው አስቀድሞ በስጋት የሚታዩ ነገር ግን በውስጣቸው ወደ ሀብት ሊቀየሩ የሚችሉ ነገሮችና እድልም እንዳላቸው እንድንመለከት የሚያደርግ አዲስ የማያ መነጽር ነው የሚሆነው::

እንደ ወይዘሮ ሙፈሪያት ገለጻ፤ ወጣ ያለ ነገር ለመሥራት የሚሞክሩ ሰዎች አሉ:: እንዲህ ያለውን ማበረታታትና ብዙ ሰዎችም እንዲከተሉትና ባህልም ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ ያስፈልጋል:: በአካባቢ ላይ ያሉ ፀጋዎችን ለማስተዋል እንዲቻልም የሚያግዝ በመሆኑ ይህንን በመኮትኮት፣ በማሳደግ፣ እንደ ሀገርም ያሉንን እምቅ ሀብቶችንና አቅሞችን አውጥቶ ጥቅም ላይ ማዋል ይጠበቃል:: ከእለት ጉርስ ያልተላቀቀ የሥራ ዕድል ሳይሆን፤ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ የሚያሻሽል፣ በሀገር የኢኮኖሚ እድገት ላይም ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ዘላቂነት ያለው የሥራ እድል መፍጠር ሲቻል በሂደት ሀብት ያመነጫል::

በአጠቃላይ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጡት ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎች፤ ስታርትአፕ ኢንተርፕራይዞችን በተለያየ መንገድ መደገፍ ሀገራዊ ፋይዳው በተለይም ምጣኔያዊ እድገት ላይ የጎላ ሚና ሊኖረው እንደሚችል በማጉላት ነው ሃሳባቸውን ያጠቃለሉት::

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You