ሶስቱ ጓደኛሞች ምንም እንኳ ከአስር ዓመታት ያላነሱ ጊዜያትን አብረው ቢያሳልፉም፤ የኑሮ ደረጃቸው በእጅጉ የተለያየ ነው። አንደኛው ምክንያት ቤት ነው። ገብረየስ በደህና ጊዜ የጋራ መኖሪያ ቤት ደርሶታል። ተሰማ ደግሞ በቅርቡ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት ዕድለኛ ሆኖ ከኪራይ ቤት ወጥቶ በቤቱ ለመኖር በቅቷል። ዘውዴ ግን አሁንም በኪራይ ቤት እየተንገላታ ነው። ዘውዴን የቤት ኪራይ ዋጋ ቁልቁል እንደካሮት ሲቀብረው አዲስ ቤት ያገኘው ተሰማ ደግሞ ተመችቶት ዓለሙን መቅጨት ጀምሯል።
ሶስቱም ከተገናኙ ሰነባብተዋል። መቆየታቸውን ምክንያት በማድረግ ከሌላ ጊዜው ለየት ያለ ቦታ መሔድ ፈልገዋል። ቀድመው በመነጋገራቸው ጋባዡ ተሰማ መንግስቴ የሚያውቀው መጠጥ ቤት በከፍተኛ ወጪ ሊጋብዛቸው መፈለጉን አስታወቀ። ዘውዴ መታፈሪያ እና ገብረየስ ገብረማሪያም ለመጋበዝ በመጓጓታቸው ይሁን ወይም ከተገናኙ በመቆየታቸው ገና ሳይመሽ አስር ሰዓት ቀድመው ማምሻ ግሮሰሪ እየተጨዋወቱ ተሰማን ሲጠብቁት ዘውዴ የተለመደ ምሬቱን መናገር ጀመረ።
‹‹ከአከራዮቼ ጋር በዚህ ወር ቤቱን እንደምለቅላቸው ተስማምቼ ነበር። በየሶስት ወሩ 50 በመቶ እየጨመሩብኝ ሲያማርሩኝ ለሶስት ወር አልጨምርም፤ ከዛም እለቅላችኋለሁ ብያቸው ነበር። የተከራየሁትን ቤት ለመልቀቅ ሳስብ ደግሞ የሚገኘው ቤት ከነበርኩበት የወረደ ዋጋው ደግሞ ቀድሞ ከምከፍለው በእጥፍ የሚጨምር ነው። በተጨማሪ ደላሎቹ ቀድሞ የስድስት ወር ክፈል ብለው ያስገድዳሉ። ለእነርሱ የሚከፈለው የ10 በመቶ ክፍያ በስድስት ወር ሲባዛ የአንድ ወር የቤት ኪራይ የሚያህል ነው። በእኔ ደሞዝ እንኳን ልጆች ይዞ ለብቻም ለመኖር አዳጋች ሆኗል። ብቻዬን ብኖር ጎዳና ላይም እተኛ ነበር። አሁን አሁንማ ልጆቼን አስቤ እንጂ አንዳንዴ መሞት ያምረኛል›› በማለት ሰሞኑን ሲያስጨንቀው የነበረውን ለገብረየስ ተነፈሰ።
ገብረየስ በበኩሉ ‹‹ ዛሬ እኮ በዘመኑ አለኝ የሚል ሰው የሚጠጣውን መጠጥ ለመጠጣት እና በሰፊው ለመዝናናት በተቀናጣው መጠጥ ቤት ለመገናኘት የምንችልበት ቀን ነው። ቢያንስ ዛሬ አትማረር።›› አለው። ይህንን እየተነጋገሩ፤ የገብረየስ ስልክ ጠራ። ደዋዩ ተሰማ ነበር። ቦሌ አካባቢ የሚገኘውን የመጠጥ ቤት ስም ጠርቶ ‹‹ከተገናኛችሁ ሲመሻሽ ጠያይቃችሁ ኑ።›› አለ። ገብረየስ በተሰማ ሃሳብ አልተስማማም፤ ‹‹ ግብዣው ከልብህ ከሆነ መጥተህ ውሰደን፤ የጠራኸው መዝናኛ ቤትን አናውቀውም። ያለአንተ ቦሌ ደርሰን መዝናናት አይሆንልንም።›› አለው።
ተሰማ ‹‹ ሳቀና እሺ እንደውም ቅርብ ነኝ፤ መጥቼ እወስዳችኋላሁ።›› አለ። ገብረየስ ፈገግ ብሎ፤ ‹‹ይቀልዳል እንዴ? በምናችን እንዴት ብለን ልንደርስ ነው?›› ሲል፤ ዘውዴ በራሱ ሃሳብ ተጠምዷልና ገብረየስ የሚለውን አልሰማም። ዘውዴ ፍዝዝ ብሎ ፊት ለፊቱ ያለውን ድራፍት ሲጎነጭ፤ ገብረየስ አዘነለት። ‹‹ እኔ የምልህ የዛሬው ግብዣ ይቅር እና የአንድ ወር የቤት ኪራይ ይክፈልልህ።›› ሲለው፤ ዘውዴ በጣም ተበሳጨ። ‹‹ ይህን ያህል ዓመት ተምሬ፤ ከሁለት አስርት ዓመታት ለሚበልጡ ዘመናት ሕዝብን እና መንግስትን አገልግዬ ቢያንስ ያለጭንቀት በልቼ ከነልጆቼ የማርፍበት ማጣቴ ያሳዝናል። አልፌ ተርፌ ልመና ውስጥ ከምገባ ሞቴን እመርጣለሁ።›› አለው።
ገብረየስ፤ ‹‹ ዛሬ ደጋግመህ ስለሞት የምትናገረው ምን ሆነህ ነው? ሞትማ ለማንም አይቀርም። ነገር ግን ራሱ ሲመጣ እንጂ በግድ ልሙት ብሎ ከፈጣሪ ጋር መከራከር ውጤት አያመጣም። ሁሉም ያልፋል። ምናልባት አንተም የቤት ባለቤት የምትሆንበት ቀን ይመጣል። በዛ ላይ አዲሱ የመኖሪያ ቤት አዋጅ ወጥቷል። እርሱን በደንብ አንብብ እና ከአከራዮችህ ጋር ተደራደር።›› ሲለው ተሰማ ደረሰ።
‹‹ደግሞ የምን ድርድር ነው›› ሲል ጥያቄ አቀረበ። ‹‹የዘውዴ የቤት ችግር ከስሩ የሚፈነቀለው መቼ እንደሆነ ይናፍቃል።›› ሲል ገብረየስ ምላሽ ሰጠ። ‹‹ እኛ ደህና፤ የቤት ችግር ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ አይደለም። የትም አገር መካከለኛው እና ከፍተኛው እንጂ የዝቅተኛ ደረጃ ነዋሪው የቤት ችግር የሕይወት ዘመኑ የታሪክ አካል ነው። በእርግጥ የእኛ አገሩ ችግር ከባድ ቢሆንም በሂደት መሻሻሉ አይቀርም። እንደሰሞኑ ለተከራይም ለአከራይም የሚያመቹ አዋጆች ከወጡ በቀጣይም ችግሩ የሚቃለልበት ሁኔታ ትኩረት ከተሰጠው አትጠራጠር ችግርህ መቃለሉ አይቀርም።›› አለው።
ዘውዴ በበኩሉ፤ ‹‹በእርግጥ ለእናንተ ለማስረዳት ከባድ ነው። ምክንያቱም የችግሩ ስፋት እና ጥልቀት አይገባችሁም። አሁን ላይ አዲስ አበባ ውስጥ የቤት ባለቤት አለመሆን ድህነት ብቻ ሳይሆን ለውርደት የሚዳርግ ከባድ ችግር ነው። እጅግ ሞራል የሚነካ ራስን የሚፈታተን ታግሎ አሸናፊ ለመሆን የማይቻልበት ትልቅ ፈተና ነው።›› ሲል ተሰማ ፈገግ አለ።
ተሰማ፤ ‹‹ በዘመንህ በጣም ብዙ ፈተናዎች አሉብህ። ፈተናዎቹን ለማለፍ የምትችለው አንተ ነህ። የሌሎች አካሎች ማለትም መንግስትን የመሳሰሉ አካላት ሲደግፉህ ዕድሉን መጠቀም አለብህ። አሁን አንተ የምትኖረው ተከራይተህ ነው። የቤት ኪራይ ዋጋ ያለአግባብ እንዳይጨመርብህ መንግስት አዋጅ አውጇል። መንግስት ካልፈቀደ መጨመርም ሆነ ማባረር አይችሉም። ከዚህ በኋላ የሚጨመርብህ መንግስት ባስቀመጠው መሠረት ብቻ ነው። ልቀቅ የምትባለውም በአዋጁ መሠረት ቤቱ ላይ ዋጋውን የሚቀንስ ጉዳት ስታስከትል፣ ቤቱን ከተከራየህበት ማለትም ከመኖሪያነት ውጪ ለሌላ ዓላማ ካዋልክ ወይም ቤቱ ከተሸጠ እና የቤት ኪራይ በአግባቡ የምትከፍል ካልሆነ ነው።
አንተ ቤቱን በአግባቡ ያዝ፤ የሚጠበቅብህን የቤት ኪራይ ገንዘብ በአግባቡ ክፈል፤ ከዛ ውጪ ውጣ ብትባል ለማህበረሰባዊ ፍርድ ቤት፣ ለፖሊስ ጣቢያ ወይም ሌላ መሃል ላይ ሆኖ ችግሩን ሊፈታ ለሚችል አካል አሳውቅ። በተረፈ ማንም ቢሆን ሊያስወጣህ አይችልም። ስለዚህ ጭንቀት አያስፈልግም።›› አለው።
ዘውዴ ፈገግ ብሎ፤ ‹‹ ወይ መሬት ያለ ሰው!›› አለው። ተሰማ በበኩሉ ‹‹ መሬት ላይ እንደማልኖር አየር ላይ ተንጠልጥዬ ወደቅኩ አልወደቅኩ እያልኩ እንደምሳቀቅ ታውቃለህ። ነገር ግን ብወድቅም አልሳቀቅም። ነገር የሚከብደው ባከበድከው ልክ ነው። ቀለል ስታደርገው ራሱ ይቀላል። በአዋጁ ደስ ልትሰኝ ይገባል።›› አለው።
ገብረየስ በበኩሉ፤ ‹‹ በእርግጥ አዋጁ ደስ ይላል። ነገር ግን አንተ በምትኖርበት የጋራ መኖሪያ ቤት ወለል ላይ ብዙ ቤት ተዘግቶ ሰው እንደማይኖርበት ነግረኸኝ ነበር። ወይም ለምን እዛ አይከራይም?›› አለው። ‹‹ በእኛ አካባቢ ባሉ መኖሪያ ቤቶች ትልልቅ ፎቆች ውስጥ በትንሹ ከ40 ያላነሱ ቤቶች ሳይከራዩ በራቸው ዝግ ነው። የኤሌክትሪክ አገልግሎትም ሆነ ውሃ ገብቷል። የሚገርመው አንዳንዶቹ ቤቶች በደንብ ፀድተው የተሰሩ ናቸው። ነገር ግን የቤቶቹ ባለቤቶች ይሁኑ ደላሎቹ የሚጠሩት ዋጋ በጣም የተጋነነ ነው። በዚህ ምክንያት ከእያንዳንዱ ሕንፃ በአማካኝ 40 ቤት በአጠቃላይ ከ13 ሕንጻ ምን ያህል ቤት ሳይከራይ ቁጭ ብሏል ብሎ ለማስላት ቀላል ነው። በእርግጥ ለአከራዮቹ ተራ ነገር ሊሆን ይችላል። በዛች አካባቢ ያለውን የቤት ፍላጎት ለማስታገስ የሚጫወተው ሚና ቀላል አይሆንም። አዋጁ የጋራ መኖሪያ ቤት ያለነዋሪ መቀመጥ የለበትም ብሎ ቢያስገድድ መልካም ነበር።›› ሲል ያለውን ሃሳብ ገለፀ።
ገብረየስ በበኩሉ፤ ‹‹ ለነገሩ ያ ብቻ አይደለም። አሁንም በስፋት ግንባታቸው ተጀምሮ ያልተጠናቀቁ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አሉ። ሌሎች ደግሞ ዕጣ ከወጣባቸው አምስት ዓመታትን ቢያሳልፉም እስከ አሁን ኤሌክትሪክ እና ውሃ ያልገባባቸው ለነዋሪዎች ምቹ ያልሆኑ ሕንፃዎች አሉ። እነዚህን መሠረተ ልማቶች የማሟላት ግዴታ ያለባቸውን ተቋማት ምክር ቤትም ሆነ ሌላ ተቆጣጣሪ አካል አስጨንቆ እንዲሰሩ እና የከተማዋ የመኖሪያ ቤት ችግር እንዲቃለል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ለነዋሪ የተላለፉ ግን ደግሞ የተዘጉ የማይከራዩ ቤቶች እንዲከራዩ ያለበለዚያ ወደ መንግስት እንደሚመለሱ እና ዕድሉን ላላገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚተላለፉ ቢገለፅ ሁሉም ያከራይ ነበር። የሚከራይ ቤት ሲበዛ ደግሞ ዋጋውም ይረጋጋል።›› አለ።
ዘውዴ በበኩሉ፤ ‹‹ችግሩ አንድም ተገቢውን ሕግ አለማውጣት ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ የወጣውን ሕግ አለማስተግበር ነው። ችግሩ የሰፋ በመሆኑ ተከራዮች አከራዮች የሚሉትን በሙሉ ለመፈፀም ዝግጁ ናቸው። አከራዮች ደግሞ ሕግን ለመተግበር ፈቃደኞች አይደሉም። የከተማ አስተዳደሩ አከራዮች ዋጋ እንዳትጨምሩ ቢልም፤ አከራዮችም ዋጋ ሲጨምሩ ተከራዮችም ጨምሩ የተባሉትን ሲከፍሉ ኖረዋል። ችግሩ የሚቃለለው በአዋጅ ሳይሆን እጥረቱን በሚያቃልል መልኩ ቤቶችን በብዛት መስራት ሲቻል ነው። የቤት ኪራይ ችግር ከሥሩ ይፈነቀላል የሚል እምነት የለኝም።
በየትኛውም ዓለም የመኖሪያ ቤት እጥረት አለ። ነገር ግን የኢትዮጵያን በተለይ የአዲስ አበባን ያህል የቤት ችግር ያነቀው እና ያስጨነቀው ከተማ አለ ለማለት እቸገራለሁ። በእርግጥ ሰሞኑን ወደ አቃቂ ቃሊቲ ከገላን አቅራቢያ 60 ሺህ ቤት ሊገነባ መሆኑን ይፋ ተደርጓል። የመሠረት ድንጋይም ተቀምጧል። ነገር ግን አንተ እንዳልከው ሳይጠናቀቁ ተንጠልጥለው ያሉትን በፍጥነት ማጠናቀቅ፤ መሠረተ ልማት ያልተሟላላቸውን በአስቸኳይ እንዲሟላላቸው ማድረግ፤ ተመኑን በተመለከተም በፍጥነት ይፋ ማድረግ ይገባል። የወጣው አዋጅም እንዲተገበር እስከ ታች መግፋት ያስፈልጋል። ይህ ከሆነ ቢያንስ የግል ቤት ባይኖረንም በኪራይ ቤት ተረጋግተን መኖር እንችላለን።›› ሲል መሠራት አለባቸው ብሎ የሚያምንባቸውን ጉዳዮች ገለፀ።
ተሰማ በበኩሉ፤ ‹‹ በእርግጥ ይህ አዋጅ በጣም ለመተግበር የሚመች አዋጅ ነው። አከራዩንም ሆነ ተከራዩን የሚጠቅም ነው። ተፈፃሚ ካልሆነ ያለውን ተጠያቂነትም አስቀምጧል። በተረፈ መንግስትም ተገቢውን ግብር እንዲሰበስብ ያግዛል። ስለዚህ የአሁኑ አዋጅ ማንንም የሚያስደስት እንጂ የሚያስከፋ አይደለም። በተለይ እንደአንተ አይነት በየጊዜው ጨምር እና ውጣ እየተባለ የሚንገላታ ተከራይ መደሰት አለበት። አሁን ሰዓቱ እየደረሰ ነው ወደ መዝናናታችን ብንሔድ ይሻላል።›› ብሎ ወደ አሽከርካሪው ደወለ።
ቦሌ ያ ብዙዎች ያደነቁት ቤት ደረሱ። መቀመጫው እንደማምሻ ግሮሰሪ ደረቅ ወንበር ሳይሆን የተቀናጣ ሶፋ ነው። ገና በጊዜ በመግባታቸው ብዙ ሰዎች እና ሰፊ መስተንግዶ አላገኙም። እየቆየ ቤቱ መሙላት ሲጀምር ግን መስተንግዶ ተቀላጠፈ። የሙዚቃ ባንድ ቆሞ ዘፋኞች በየተራ እየወጡ መዝፈን ጀመሩ። አስተናጋጆች ሳይጠሩ፤ ‹‹ ምን እናምጣ? ምን ይጨመር?›› እያሉ ተክተለተሉ። አሻሻጭ ሴቶች ተኮለኮሉ።
ለጠጪዎች ‹‹ ይህ መጠጥ እኮ ምርጥ ነው። ይህኛው ከዚህኛው ይሻላል። ያንን አምጡላቸው ይህንን ቀይሩላቸው።›› እያሉ በየጠረጴዛው የሚዞሩት አጫፋሪዎች፤ ምንም እንኳ ተኳኩለው መልካቸው ቢያምርም፤ ዘውዴ ግን ስጋ ያየ ጥንብ አንበሳ አድርጎ ሳላቸው። ዘፋኞቹ ደጋግመው ተቀራራቢ ዘፈን ይዘፍናሉ። መጠጡም ሆነ ዘፈኑ አጠቃላይ የቤቱ ሁኔታ ዘውዴ እና ገብረየስን አስገርሟቸዋል። ተሰማ ደግሞ ደስ ብሎት መጨፈር ጀመረ። ዘውዴ ከመደሰት ይልቅ አይ ዘመን እያለ የተቀዳለትን መጠጣቱን ቀጠለ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2016 ዓ.ም