ጉባ መገኛ ወረዳው ነው፤ ክልሉ ደግሞ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ። ይህ ንብረትነቱ የኢትዮጵያውያን የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ የግንባታው መሠረተ ድንጋይ የተቀመጠው መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ሲሆን፣ ዛሬ 13 ዓመት ሞልቶታል። ዘንድሮ “በኅብረት ችለናል” በሚል መሪ ሐሳብ በተለያየ መርሐግብር የሚከበር መሆኑ ተጠቅሷል።
የህዳሴ ግድቡ ዛሬ ላይ ለመድረሱ ግን የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ በከፈለው ከፍተኛ መስዋዕትነት መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም። ወደፍጻሜው ለመቃረቡም በመንግሥት በኩል በተፈጠረው ቁርጠኝነት ነው። ግድቡ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ እስካሁኗ ሰዓት ማነቆው እጅግ ብዙ እንደነበር ይታወሳል። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን እንዳታጠናቅቅ በብዙ ተደክሟል።
በተለይም የኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የሦስትዮሽ ድርድር ሁሌም እንከን እንዲኖረው በግብፅ በኩል በብርቱ ሲሠራበት ሰንብቷል። ከመነሻው ጀምሮ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ምንም አይነት የልማት ሐሳብ እንዳይኖራት ለዘመናት ስትባዝን የኖረች ግብፅ፣ የህዳሴ ግድቡ የመሠረት ድንጋይ ሲቀመጥ በኢትዮጵያ ላይ የማስፈራሪያና የማስጠንቀቂያ ዶፍ ስታዘንብ መክረሟ የሚታወቅ ነው።
ከማስፈራራትና ከያዙኝ ልቀቁኝ በኋላ ዶሴዋን በመያዝ፤ ‘ሲሆን ሲሆን ግድቡ እንዳይገነባ በማደርገው ጥረት ከጎኔ ይቆማሉ፤ ካልሆነም ኢትዮጵያ ላይ ጫና ያሳድሩልኛል’ ወዳለቻችው አካላትም፤ ሀገራትም ዘንድ ተንከራታለች። ይሁንና ኢትዮጵያ በግብፅ ግልምጫም ሆነ ዛቻ እንዲሁም በሌሎቹ ሀገራት ጫና ከአቋሟ ዝንፍ ሳትል ግንባታዋን ሌት ተቀን ስታስኬደው ከርማለች።
ነገር ግን በዚህ ሁሉ ውስጥ ያጋጠማት ፈተና በርከት ያለ ከመሆኑም በላይ በየምክንያቱ ብዙ ነገሮችን እንድታጣ ተደርጋለች። በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ኢኮኖሚዋ እንዲዋዥቅ በብዙ ተጥሯል። ምክንያቱ ሌላ ይምሰል እንጂ በሀገር ቤትም ሆነ በውጭ አገር ባሉ ዜጎቿ ጫና ተፈጥሯል።
ግብፅ የህዳሴ ግድቡን ወደፀጥታው ምክር ቤት በማመላለስ ኢትዮጵያ በብዙ ጫና ውስጥ እንድታልፍ ከማድረጓም በተጨማሪ ሐሰተኛ በሆነ መረጃዋ፤ አንዳንድ አቅላቸውን በሳቱ አካላት ግድቡን ለማፈንዳት እስከማሰብ ተደርሷል። ስለ ዓባይ ግድብ ምንም የማያገባው የዓረብ ሊግም በጉዳዩ ላይ መግለጫ እስከማውጣት ደርሷል።
ይሁንና የቅኝ ግዛት ስምምነት ላይ ተጣብቃ አልላቀቅም ያለችው ግብፅ ጩኸትም ሆነ የግብፅን የተቃውሞ ስልት ተከትላ በምታሳየው የአቋም መዋዠቅ ወዲህ ወዲያ የምትለው የሱዳን ሁኔታም ኢትዮጵያን ከሥራዋ ለአፍታም ቢሆን አላስቆማትም። ይልቁኑ ከወራት በኋላ ኢትዮጵያውያኑ እንደ አካላቸው ክፋይ የሚያዩት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፍጻሜውን ሊያገኝ ተቃርቧል። አዲስ ዘመንም የግድቡን 13ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ለሚያዘጋጀው ልዩ ዕትም ግድቡ የሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ምን ይሆን ሲል ምሑራንን ጠይቋል።
ምሑራኑ እንደሚሉት፤ በመጀመሪያ ደረጃ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በርከት ያሉ ተግዳሮቶችን ተሻግሮ ለፍጻሜው መድረሱ ከምንም በላይ ትልቅ ስኬት ነው። ብዙዎች ይህ ግድብ እውን እንዳይሆን አቅማቸው የፈቀደላቸውን ሁሉ ማድረጋቸው አይካድም። በብዙ ጥረውና ደክመው የነበረ መሆኑም የሚረሳ አይደለም።
ካነጋገርናቸው ምሑራን መካከል አንዱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በንግድ ሥራ ኮሌጅ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ብርሃኑ ደኑ (ዶ/ር) ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አለው። የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ የሚያሻሽልና ቀጣይነት እንዲኖረው ከማድረግ አንጻር አስተዋፅዖው ከፍ ያለ ነው።
ከዚህ አንጻር በኢትዮጵያውያኑ ጥንካሬ የተገነባው እና ሊጠናቀቅ ጫፍ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ለዘመናት ወደኋላ ቀርቶ የነበረውን የኢኮኖሚ እድገት እና ግስጋሴ ወደፊት ለማስፈንጠር ሚናው የጎላ ነው ይላሉ። ሀገሪቷ ልታድግ የምትችልበትን፣ ምርታማነት የሚጨምርበትን፣ በከፍተኛ ደረጃ የሥራ ዕድል የሚከፈትበትንም ዕድል የሚፈጠር እንደሆነ ያስረዳሉ።
ብርሃኑ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፤ የኢኮኖሚ እድገት እና ጠቀሜታ ማለት አንደኛ የሕዝብን ኑሮ የሚያሻሽል ማለት ነው፡። የሕዝብ ኑሮ ማሻሻል የሚቻለው ደግሞ የሥራ እድልን በመፍጠር ነው። ሕዝብ የሥራ እድል ተፈጥሮለት የሚሠራ ከሆነ የገቢ ምንጭ ተገኘ ማለት ነው። ገቢን ከፍ ለማድረግ ዋንኛው መሠረት የሆነው ምርታማነትን መጨመር እና ማበራከት ነው።
ስለዚህ ሁሉ የኢኮኖሚ ሴክተሮች ወይም በሁሉም ክፍለ ኢኮኖሚዎች ማለትም በአገልግሎት መስጫ፣ በኢንዱስትሪ እና በግብርናው ዘርፍ ላይ ሁሉ የኤሌክትሪክ ኃይል በከፍተኛ ደረጃ አስፈላጊ መሆኑ እሙን ነው። ዘርፎቹም በተሳለጠ ሁኔታ ቀጣይነት እንዲኖራቸው የኤሌክትሪክ ኃይል ከፍ ያለ ፋይዳ ያለው ነው። ስለሆነም ወደፍጻሜው የተቃረበው የህዳሴ ግድቡ ለዚህ ሁነኛ መፍትሔ ነው።
እርሳቸው እንደገለጹት፤ ከዚህ ጎን ለጎን ቀጣይነት ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት መቻል ፋብሪካዎች የሚያመርቷቸውን የምርት አይነቶች በተገቢው መንገድ ማምረት እንዲችሉ ያደርጋል። በየኢንዱስትሪው እና በየፋብሪካው ያሉ ማሽኖች የምንጠቀምባቸው በኤሌክትሪክ ኃይል ነው። ስለዚህም እነዚህ ሁሉ ቀጣይነት ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል አገኙ ማለት በጣም ከፍተኛ የሆነ ምርታማነትን ማምጣት ያስችላቸዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሥራ አጥነት ጠፍቶ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እና ሥራ እየተስፋፋ ሲሄድ የሰው ኃይል የሚፈልግ በመሆኑ በርካታ ሰዎች የሥራ እድል ይፈጠርላቸዋል። ኢኮኖሚው እያደገ ሲሄድ በርካታ ዘርፎች የሰው ኃይል ፍላጎት ይኖራቸዋል።
ይህ ማለት ተምረው ሥራ አጥተው የተቀመጡ ዜጎችን ወደ ሥራው መስክ እንዲሳቡ የሚያደርግ ይሆናል የሚሉት ብርሃኑ (ዶ/ር)፣ በርካቶች በሥራ መስክ ተሠማሩ ማለት ገቢ አደገ ማለት ነው ይላሉ። የግለሰብ ገቢ ሲያድግ የራሱ የግለሰቡን ገቢ ከማሻሻል አልፎ በሀገር ደረጃ የመንግሥት ገቢ ከፍ ለማድረግ የራሱ አስተዋፅዖ እንዳለውም ያስረዳሉ። ምክንቱም ዜጎች ሥራ አግኝተው መሥራት ሲጀምሩ ታክስ ከፋይ ይሆናሉ። ይህ ደግሞ ለመንግሥት ገቢ የሚያበረክተው የራሱ የሆነ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል። ዜጋውም ሆነ ሀገርም ተጠቃሚ ሆኑ ማለት በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን እንቅስቃሴ የተያያዘ እንዲሆን ያደርገዋል ማለት ሲሉ ያመለክታሉ።
የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ኘሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በዓመት በአማካይ 15 ሺ 759 ጊጋ ዋት ሰዓት ኢነርጂ በማመንጨት ለሀገር አቀፍ የኤሌክትሪክ ትስስር ሥርዓት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ይኖረዋል፤ ኤሌክትሪክ ያልተዳረሰባቸው የገጠር መንደሮችና ከተሞች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግና አቅርቦቱን አሁን ካለበት 44 በመቶ ወደ 90 በመቶ ከፍ ለማድረግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የዚህ ኘሮጀክት ድርሻ ከፍተኛ ነው።
የህዳሴ ግድቡ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ሲታይ የባሕር ትራንስፖርትና የዓሣ ሀብት ልማት ትልቅ ድርሻ እንዳለው መረጃው የሚጠቅስ ሲሆን፣ 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ውሃ የመያዝ አቅም ያለው ሰው ሠራሽ ሐይቅ ስለሚፈጠር በአካባቢው በታንኳ እና በጀልባ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ እንዲሁም በዓለማችንም ተጠቃሽ የቱሪስት መዳረሻም እንደሚሆንም ያመለክታል። በተለይም በግድቡ ዙሪያ የተፈጠረው ሰው ሠራሽ ሐይቅ እየሰፋ ሲሄድና ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅም ከ78 በላይ ደሴቶች የሚፈጠሩ በመሆናቸው ይህም ዋንኛ የቱሪስት ማዕከል እንዲሆን የሚያስችለው መሆኑም ተጠቅሷል።
እንደ ጽሕፈት ቤቱ መረጃ ከሆነ፤ የውሃ አካሉን ተከትሎ ሪዞርቶች የሚገነቡ ይሆናል። የውሃ አካሉ ለዓሣ ልማት እና ለመሳሰሉት ኢኮኖሚያዊ አማራጮች ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ቀደም ሲል ተካሂዶ ይፋ በተደረገ ጥናት መሠረትም በዓመት ከ10 ሺ እስከ 50 ሺ ቶን ዓሣ ሊመረትበት እንደሚችል ተጠቁሟል። እስከ 80 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ የዓሣ ዝርያዎች በግድቡ መገኘታቸውን ተመልክቷል። ይህ የዓሣ ሀብት በከፍተኛ ደረጃ እየተራባ ሲሆን፣ ግድቡ በቀጣይም ለዓሣ ልማቱ በጣም ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል ተብሎ ታምኖበታል።
የኦሮሚያ ክልልዊ መንግሥት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የቀድሞ ዋና ዳይሬክተርና በአሁኑ ወቅት በቻይና የሦስተኛ ዲግሪያቸውን በመማር ያሉ አቶ አማን አሊ እንደሚሉት፤ ይህ ታላቅ ግድብ እንደቀላል የሚታይ ነገር አይደለም። በእርግጥ ሀገራችን ብዙ የሚነገርላት ታሪክ ያላትና የዚያ አኩሪ ታሪክ ባለቤትም ናት። ኢትዮጵያ በብዙ ጎዳናዎችም ድል ማስመዝገብ የቻለች ናት። ለምሳሌ ዓድዋን መጥቀስ ይቻላል። ኅብረት እና አንድነትን በመፍጠር የተለያየ ታሪክ መሥራት የቻለ ሕዝብ ነው። ይህም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከእነዚህ ታላላቅ ታሪክ ጋር መታየት የሚችል ነው።
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ግብፅ የህዳሴ ግድቡ እውን እንዳይሆን የምታደርገው ጥረት ሁሉ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ እንዳያድግ በማሰብ ነው። ምክንያቱም ግድቡ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍ ያለ ነው። በተለይም ከሥራ አንድ ሀገር የማይቆራረጥ የኤሌክትሪክ ኃይል አገኘ ማለት ተከታታይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብ ምቹ ሁኔታን ይፈጥርለታል።
የህዳሴ ግድቡ ተጠናቅቆ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንደሚያመጣለትም ሕዝቡ ስለሚያውቅ ከጉድለቱ ሁሉ ሲለግስ እንደነበር አቶ አማን አስታውሰው፤ ትናንት ከባዶ ነገራቸው ስጦታ ያበረከቱ ዛሬ በተለያየ መስክ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ጊዜ ቀርቧል ሲሉ ያስረዳሉ።
የህዳሴ ግድቡ የሁላችንም ንብረት በመሆኑም ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳውም በተጨማሪ አንድ በማድረጉ ላይ ትልቅ ትርጉም አለው የሚሉት አቶ አማን፣ እኛ ያለን ሀብት ነገ ተነገወዲያ እየበረከተና እየሰፋ ገቢ የሚያስገኝ ነው። ከዚህ በኋላም ልክ እንደታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁሉ በሌሎችም ሀብቶቻችን ላይ የተለያዩ ሥራዎች መሥራት የሚቻል በመሆኑ ኢኮኖሚው እያደገና የበለጸገ የሚሄድ ይሆናል ብለዋል።
ኢትዮጵያን ያለ ህዳሴ ግድብ ብናስባት በትክክል የምንደግመው ያለፈውን አይነት ኢኮኖሚያዊ ኋላ ቀርነትን ነው የሚሉት ብርሃኑ (ዶ/ር)፣ በኢኮኖሚ ኋላ ቀርነት ማለት ለልመና ራስን መዳረግ እንደማለት ነው ሲሉ ያስረዳሉ። ስለዚህም በቅርቡ የሚጠናቀቀው የህዳሴ ግድብ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው ይላሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ አንዱ እና ትልቁ ነገር ከኋላ ቀርነታችን ሊያላቅቀን ያልቻለው የኤሌክትሪክ ኃይል ማጣታችን ነው። ያለ ኤሌክትሪክ ኃይል የምንጠቀምባቸው የምርት መገልገያ መሣሪያዎችን ማንቀሳቀስ አንችልም። ፈጥነን በማምረት ተወዳዳሪነትን ማሳየት አንችልም። በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪነትን አሳይተን እና ገበያዎችን ሰብረን ገብተን የምናመርታቸውን እቃዎቻችንን በተሻለ ሁኔታ መሸጥ እና መገበያየት አንችልም። ስለዚህ የግድቡ መጠናቀቅ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው ነው።
ምሑራኑ እንደሚሉት፤ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በኋላ ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ተጠቃሚ ለመሆን የህዳሴ ግድቡን ሳናጠናቅቅ ‘እፎይ!’ ልንል አይገባም። ስለዚህ ፍጻሜው ስር ደርሰን ልናርፍ አይገባም። እስከ ዛሬ ድረስ የየበኩላችንን በማድረግ ወደፍጻሜው ተቃርበናል። ይህን ስናደርግ ደግሞ ሳንልፈሰፈስ፣ ሳንደክምና ለፕሮፖጋንዳ እጅ ሳንሰጥ ነው። ስለሆነም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ በዚህ በመጨረሻው ትንቅንቅ ላይ ተሳታፊ ከሆነ ከፍጻሜው የሚገኘውን ትሩፋት ተቋዳሽ ይሆናል ማለት ነው። በአሁኑ ወቅት ትሩፋቱን ልንቋደስ ከጫፍ እንደመድረሳችን ለፍጻሜው እንቀደመው ሁሉ ከሁላችንም ያላሰለሰ ድጋፍ ያሻል።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም