ታላቅ ተስፋ ለሴቶች የሰነቀው የዓባይ ግድብ

ምዕራብ ጎጃም ደጋ ደሞት ወረዳ ተወልዳ እንዳደገች ትናገራለች ምንታምር ተመስገን። ምንታምር በነፋሻዋማ የገጠር ወረዳ ተወልዳ ያደገች ሲሆን እድሜዋ ለትምህርት እንደደረሰ ነበር ከመኖሪያ ቀዬዋ በእግር ከአንድ ሰዓት በላይ የሚያስጉዝ ትምህርት ቤት የገባችው።

ቤታቸው ውስጥ ሶስት ሴቶችና ሁለት ወንዶች ልጆች የነበሩ ሲሆን የመጀመሪያዋ እህታቸው በሕፃንነቷ ተድራ የቤት እመቤት በመሆኗ ምክንያት የትምህርት ቤትን ደጃፍ የማየት እድል አላገኘችም ነበር። የተቀሩት አራቱ ልጆች ግን ማልደው በመነሳት ትምህርት ቤት ከመሄዳቸው በፊት መጀመሪያ ውሃ ቀድተው ነበር ረጅሙን ጉዞ የሚጀምሩት።

ልጆቹ ሩቅ ተጓዥ በመሆናቸው ሰዓት ለመቆጠብ ሲሉ እህል ቢጤ አፋቸው ላይ ጣል የሚያደረጉትም እንኳን መንገድ ላይ እንደነበር ታስታውሳለች። ቀን ትምህርቱና መንገዱ አድክሞ ቤት ሲያደርሳቸው ቤት የተገኘቸውን ቀማምሰው ወንዶቹ ልጆች ደብተራቸውን ይዘው ለእረኝነት ሲወጡ ሴቶቹ ደግሞ ማጀት ገብተው እናታቸውን የማገዝ ኃላፊነት ተጥሎባቸው ነበር። ምንታምር እንደምትለው ከትምህርት ቤት በኋላ የቤት ሥራውንም ለመሥራት ቀን የተማሩትንም መለስ ብሎ ለማየት ኩራዝ ትልቁ አጋዣቸው ነበር።

እንደዚህም ሆኖ በትምህርታቸው ወጤታማ የነበሩት ልጆች ዛሬ የደረሱበት ለመድረስ በርካታ ውጣ ውረዶችን ማለፋቸውን ታስታውሳለች። አንድ ቀን ለዓመቱ ማጠቃለያ ፈተና በቂ ጥናት አለማድረጓ ስጋት የሆነባት ምንታምር ሌሊት ሙሉ ስታነብ ለማደር ኩራዙን ላንባ ሞልታ ለኩሳ ማንበብ ጀመረች። ሌሊቱ እየተጋመሰ ሲሄድ ድካም የበረታባት ልጅ ደብተሯን እንደገለጠች አጠገቧ የነበረው ኩራዝ ላይ እንቅልፍ ጥሏት ትወድቃለች። ኩራዙ ላይ በመውደቋ የተነሳ እሳቱ ጠፍቶ፤ ግማሽ ሌሊት የነደደው ላንባ መጠኑ ቀንሶ የከፋ ጉዳት ባያደርስም ይህ ሁሉ የመብራት ኃይል አለመኖሩ ውጤት እንደሆነ ታስታውሳለች።

በወቅቱ ለዓመታት ውጤታማ ለመሆን የነበረውን መፍጨርጨረ ስታስብ እንዲህ በተፈጥሮ ሀብት የታደለች ሀገር ውስጥ እየኖሩ መቸገራቸው እንደሚያስገርማት ታስረዳለች። ውሃ ዳር ተኝቶ ውሃ መጠማት፤ ሀብት ላይ ቆሞ ለምፅዋት እጅን መዘርጋት የሀገሪቱ ሕዝቦች እጣ ፈንታ መሆኑ የሚያሰቆጭ መሆኑን ታብራራለች።

ምንታምር ቁጭት አጠንክሯት ዛሬ ተምራ ከፍ ባለ ደመወዝ ከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ብትሆንም አሁንም ድረስ በተወለደችበት አካባቢ በቂ የኃይል አቅርቦት ባለመኖሩ የተነሳ ሴቶቹ ላይ ከፍተኛ ጫና መኖሩን ትናገራለች። ምንም እንኳን በእጅ የሚሰራ ድካምን የሚያቀል ወፍጮ ቢመጣም፤ በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ መብራቶች ቢኖሩም ሙሉ ለሙሉ የኃይል አቅርቦቱ ተሟልቶ ሴቶችን ሊያሳርፍ አለመቻሉን ታስረዳለች።

የታላቁ ሕዳሴ ግድቡ መጠናቀቅ በትንሹም ቢሆን የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ ጅማሮዎች አድገው የገጠሯን ሴት ሕይወት ይቀይሩታል ብላ እንደምታስብ ታስረዳለች። የኃይል አቅርቦት የሴቶችን ድካም ከመቀነሱም ባሻገር በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይም የማይናቅ አስተዋፅኦ ይኖራዋል ብላለች።

ሌላዋ ባለታሪካችን ወይዘሮ ይታይሽ አስማማው ይባላሉ። እሳቸውም ምዕራብ ጎጃም ይልማና ዴንሳ ወረዳ ውስጥ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ ናት። ወይዘሮ ይታይሽ የሚኖሩባትን እና መብራት አይታ የማታውቀውን የገጠር ጎጆ በብርሃን ለመሙላት፤ ገበያ ወርዶ ላንባ መግዛት የሴቷን ጉልበት ይጠይቃል። የቤቱን ሙቀት ለመጠበቅም ምድጃ የሚፈለገውን እንጨት ለማምጣትም ጫካ ገብታ እንጨት ለቅማ ተሸክማ መምጣት አለባት። ጠላ ለመጥመቅ ለሰባት ቀናት የተዘፈዘፈውን ደረቆት ለመቁላትም የሚሆኑ ወፋፍራም እንጨቶችን አዘጋጀታ ሌሊት ተነሰታ ያን ሁሉ ቆልታ ታደራለች። ማልዳ ለቤተሰቡ ያሰናዳችውን ቁርስና ቡና ከአፍ ካደረሰች በኋላ ደግሞ ከሴት ልጆቿ ጋር በመተባበር የተቆላውን ደረቆት ሙሉ ቀን በእጇ ስትፈጭ ትውላለች።

ጠዋት ልጆች ወደ ትምህርት እንደሄዱ ባሏን እህል አቅምሳ ወደ እርሻ ትሸኛለች፤ ከዛም የከብት በረቱን ማፅዳት እና ቤቱን የማሰናዳት ኃላፊነቷን ተወጥታ ደግሞ ባልዋን ከተል ብላ እርሻ ለማገዝ ትሄዳች። እርሻው ላይ ምሳ ሰዓት እስኪደርስ ደፋ ቀና ስትል ቆይታ ደግሞ ምሳ ለመሰናዳት ወደ ቤቷ እንደምትመለስ ትናገራለች። ከዛም ቤት ያፈራውን አስናድታ ተሸከማ፤ ጠላውን ምሳውን ውሃውን አዝላ ወደ እርሻ ትወርዳለች። ምሳ አብልታ ባልየው እጥላው አረፍ ሲል አረምና ጉልጋሎ ስትራዳ ቆይታ ወደ ቤት እንደምትመለስ ትናገራለች።

ቤት ገብታ ጋገራው፤ ወጥ ሥራሁ ስትል፤ ላይ ታች ስትሮጥ ማምሸቷ አነሷት ባሏ ሲገባ ነፍሰጡር ብትሆንም እንኳን አጎንብሳ እግር ታጥባለች። ይህን ሁሉ ኃላፊነት በሰዓቱ ለመጨረስ ደግሞ ከፀሐይዋ ጋር እሽቅድድም እንደሚገቡ ትናገራለች። ትግሉ ድካሙ ሁሉንም ለማቅለል መብራትን የሚያህል ረዳት ከየትም አይገኝም ትለናለች።

ወይዘሮ ይታይሽ እንደምትለው ለድግሱም ፤ ለማህበሩም፤ ለደቦውም ብቻ ባጠቃላይ ለሚያስፈልግ ድግስ በሙሉ እንጨት ከመልቀም አንስቶ ምግቡም መጠጡም ተሰናደቶ ሰው አፍ እስኪደርስ ድረስ የሴቷ ሙሉ አቅም ፈሶ ዓይኗ በጭስ ተጨናብሶ ወገቧ ጎብጦ ያለ እድሜዋ አርጅታ እንድታለፍ ትሆናለች። ከጉልበት ጠያቂው ሥራ በተጨማሪም አርግዞ መውለድ፤ ልጅ ማሳደግም አሁንም የሴቷን ሙሉ አቅም የሚፈልግ ተግባር ነው።

ይህ ሰቆቃ በኔ ይብቃ ያለች እናትም ልጆቿን ትምህርት ቤት ብትልክም ልጆቿ ትምህርት ቤት ከመሄዳቸው በፊት በሌሊት ተነስተው ውሃ ቀድተው ነው ጉዞን የሚጀምሩት። ልጆችም ትምህርት ቤት እንዳይረፍድባቸው እህል ቢጤ አፋቸው ላይ ጣል የሚያደረጉትም መንገድ ላይ ነው። ቀን ትምህርቱና መንገዱ አድክሟቸው ቤት ሲያደርሳቸው ቤት የተገኘቸውን ቀማምሰው ወንድ ልጆች ደብተራቸውን ይዘው ለእረኝነት ሲወጡ ሴቶቹ ልጆች ቤት ማጀት ውስጥ እናታቸውን ሲያግዙ ያመሻሉ።

ሥራው ሲያበቃ ምሽቱን የቤት ሥራ ለመሥራትም ሆነ የተማሩትን ለመመልከት ኩራዝ አብርተው የሚያመሹ ሲሆን ጭሱ አፈንጫቸውን ሞልቶ ለተለያዩ ችግሮች ያጋልጣቸዋል። ላንባ መግዣው ሳንቲም ሲያጥርም ሆነ በተለያየ ምክንያት ሲጠፋ ማጥናቱም ቀርቶ በጨለማ ይታደራል።

እንደ ወይዘሮዋ ገለፃ በዚህ ሁሉ ሰቆቃ ውስጥ ኑራቸውን ለሚገፉት ሴቶች መሠረት ደንጋዩ ከተጣለ 13ኛ ዓመቱን ያስቆጠረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ይዞ የሚመጣው ተስፋ ብሩህ ነው። የኃይል አቅርቦቱ በቀጭኑ መስመር የገጠር መንደሮችን በሙሉ ሲያዳርስ ጭስ ያጣፋው ዓይን ዳግም በተስፋ ብርሃን ይለመልማል።

ይህ ተስፋ የተጣለበት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ማክሰኞ 13ኛ ዓመቱን ደፍኗል። የግድቡ ግንባታ ከዛሬ 13 ዓመታት በፊት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ነበር የተጀመረው። በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊም ኢትዮጵያ በታላቁ የዓባይ ወንዝ ላይ ከአፍሪካ ቀዳሚ ከዓለም ደግሞ ተጠቃሽ የሆነ ግዙፍ ግድብ መገንባት መጀመሯን በማብሰር በይፋ የመሠረት ድንጋዩን አኑረዋል።

ከዚያም ወዲህ ግድቡ በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፏል። የነበሩበትን እንደ ጭለማ የከበዱ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች ተሻግሮ ከወር በፊት የመጀመሪያውን ኃይል ለማመንጨት ችሏል። ኢትዮጵያውያን ራሳቸው መሐንዲስም፤ የፋይናንስ ምንጭም ሆነው ይገነቡታል የተባለለት ግድቡ 5 ዓመታትን እንደሚፈጅ ነበር በወቅቱ የተገለጸው። ሆኖም በግንባታው በተለያዩ ምክንያቶች ተጓቶ እነሆ 13ኛ ዓመቱ ላይ ደርሷል።

ከ2010 ዓ.ም ወዲህም በግድቡ የግንባታ ፕሮጀክት ተስተውለዋል የተባሉ ህጸጾች ተነቅሰውና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች ተቋራጩን እስከ መቀየር እንዲሁም የተርባይኖቹን ቁጥር ከ16 ወደ 13 እስከ መቀነስ የደረሱ ርምጃዎች ተወስደው ግንባታው ቀጥሎ አሁን አጠቃላይ የግንባታ ወደመጠናቀቁ ቀርቧል።

ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የግድቡ ሥራ ተጠናቆ 95 በመቶ ላይ ደርሷል። ጉባ ላይ የከተመው ይህ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በአሁኑ ወቅት ከ42 ቢሊዮን ሜትር ኩዩብ በላይ ውሃም ይዟል።

ኢትዮጵያውያን ከመቀነታቸው ፈተው፤ ካላቸው ላይ አውጥተው የሰበስቡት ገንዘብም በአስራ ሶስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ 18 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር መድረሱንም ተሰምቷል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ በተገኘው መረጃ መሠረት የሲቪል ሥራው ግንባታው 98 ነጥብ 9 በመቶ የደረሰ ሲሆን የኤሌክትሪክ መካኒካል ሥራዎች አፈፃፀም 76 በመቶ፤ የውሃ ማስተላለፊያ የብረታ ብረት ሥራዎችም 87 ነጥብ 1 በመቶ መድረስን ተመልክተናል።

ከዚህም በተጨማሪ አጠቃላይ የግድቡ ግንባታ የደረሰበት አማካኝ ደረጃ 95 በመቶ ሲሆን ግድቡ የያዘው የውሃ መጠን 42 ቢሊዮን ሜትር ኩብ፤ ከዋና ግድቡ ኋላ የተኛው ውሃ መጠንም 160 ኪሎ ሜትር ነው። ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚይዘው የውሃ መጠን 74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ሲሆን ከግድቡ ኋላ የሚተኛው የውሃ መጠን 256 ኪሎ ሜትር መሆኑን ያመለክታል።

አሁን ላይ በሁለት ተርባይኖች እየተመረተ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል 540 ሜጋ ዋት ሲሆን ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚመረተው የኤሌክትሪክ ኃይልም 5 ሺ 150 ሜጋ ዋት ነው። በሰዓት የሚመነጨው ኤሌክትሪከ ኃይልም 15 ሺ670 መሆኑን ሰምተናል።

ታዲያ ይህ ሁሉ ኃይል ተመርቶ እኛ ደጅ ሰተት ብሎ ሲደርስ በእጅ መፍጨት ቀርቶ ወፍጮው በቅርብ ሲተከል፤ እንጨት መሸከም ቀርቶ ምጣዱም ወጡም በኤሌክትሪክ ምድጃ ሲጣድ ጭስ ያጠፋው ዓይን አይበራም ትላላችሁ? ጥቀርሻ አፋንጫቸውን ሞልተው ጥናት ሲሉ የሚታመሙት ተማሪዎችስ ሌሊቱን ሙሉ አጥነተው ከቁም ነገር ለመድረስ ማን ከልካይ ይኖራቸዋል።

ድካምን ቀናሽ ሀብት የሚያከማች፤ ለኢንዱስትሪው አቅም የሚሆነው ይህ ፕሮጀክት በፍጥነት አልቆ ወደ ሥራ ሲገባ በተለይም ሴቶች ቀናቸው ይበራል። የኃይል አቅርቦቱ ተሟልቶ ከእኛ ተርፎ ለጎረቤት ሲቀርብ አይችሉም ላሉቱ ችለን ከማሳየት በቀር ምን ደስ የሚል እውነት ይገኛል። አይችሉም መባልን ያስቀረ፤ አንድ የመሆን መንገድን ያመላከተ፤ ታላቅ ተስፋ በመሆኑም ብዙ እናቶችን ያኮራ ፕሮጀክት እንድንለው አድርጎናል።

ለዚህም ነው መሰል የዘንድሮው የ13ኛው ዓመት መሪ ቃል በህብረት ችለናል የሆነው። እውነትም በህብረት ችለናል፤ ከእንግዲሀ በኋላም ለሀገር አንድነትና ህብረት፤ በህብረት ችለን ወደፊት እንራመዳለን። የእናቶችም ጫና ተቀንሶ በጭስ የጮለጮለ ዓይናቸው በርቶ፤ እንባቸው ታብሶ ተስፋን የምናይበት ይሆናል ብዬ አበቃሁ። ቸር ይግጠመን።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You