ኢትዮጵያውያን የማይደፈር የሚመስለውን ደፍረው፣ የማይቻል የሚመስለውን ችለው በአንድነት የጀመሩትን፣ በአንድነት በማጠናቀቅ ምዕራፍ ላይ ይገኛሉ። ለእዚህ ደግሞ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። በከፈሉት ዋጋም ልክ ዛሬ የግድቡን ግንባታ 95 በመቶ አድርሰዋል። ፡
መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን በዓባይ ወንዝ ላይ የዓባይ ግድብን ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ካኖሩ እነሆ 13 ዓመታት ተቆጠሩ። የመላው ኢትዮጵያውያንን ርብርብ የጠየቀው የዚህ ግድብ ግንባታ በእነዚህ ዓመታት የመላ ኢትዮጵያውያን ርብርብ ተደርጎበታል፤ በሌላ በኩልም በውጭ ኃይሎችና በሀገር ውስጥ ጠላቶች በብዙ ተፈትኗል።
‹‹ትዕግስት ፍሬዋ ጣፋጭ ነው›› እንዲሉ ታዲያ የመላው ኢትዮጵያውያን ተስፋ የሆነው የዓባይ ግድብ በብዙ ጥረትና ትጋት ዛሬ ላይ ደርሶ የኢትዮጵያውያን የመቻል አቅም ማሳያ ሆኗል። ፕሮጀክቱ በገጠሙት ውጣ ውረዶች ምክንያት ይጠናቀቃል ከተባለበት ጊዜ እጅግ ቢዘገይም፣ ከታቀደለት ገንዘብ በላይ ከፍተኛ ወጪ ቢጠይቅም፣ ኢትዮጵያውያኑ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ አንድነታቸውን አጠናክረው በመቀጠል ከማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ አድርሰውታል። በመሆኑም ግድቡ የኢትዮጵያውያን የመቻል ሚዛን የተጠበቀበት እንዲሁም የማድረግ አቅም ማሳያ ምልክት ሆኗል።
ይህ በሀገር ልጅ ጥሪት ብቻ እየተገነባ ያለ ግዙፍ ፕሮጀክት ኢትዮጵያውያን ‹‹እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን›› በሚል መርሕ ከሕይወት መስዋዕትነት ጀምሮ ገንዘባቸውን፣ ጊዜያቸውን፣ ዕውቀታቸውንና ጉልበታቸውን ሳይሰስቱ አበርክተውታል። በተለይም ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ መንግሥት ለፕሮጀክቱ ትልቅ ትኩረት በመስጠቱ ግንባታው ሳይስተጓጎል መቀጠል ችሏል። በመሆኑም ግድቡ ዛሬ 13ኛ ዓመቱ ሲከበር አጠቃላይ የግድቡ ግንባታ አፈጻጸምም በአማካይ ከ95 በመቶ በላይ ደርሷል። ይህንን የመቻል ማሳያ በግሉ ዘርፍ ኩባንያዎችን በማንቀሳቀስ የሚታወቁት ኢትዮጵያውያን ታዋቂ ሰዎች መላ ኢትዮጵያውያን በእጅጉ አስተሳስሮ ለፍጻሜ የተቃረበ ብለውታል።
የቀድሞው የሜድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሥራ አስፈጻሚ አረጋ ይርዳው (ዶ/ር) የዓባይ ግድብ በሀገሪቱ አሉ ከሚባሉ ማናቸውም ፕሮጀክቶች እጅግ ግዙፉና ታሪካዊ ፕሮጀክት መሆኑን ይገልጻሉ። ግድቡ የእያንዳንዱ ዜጋ ዐሻራ ያረፈበት፣ የሀገሪቷ ኢኮኖሚ እድገት አጋር፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጉጉት የሚጠብቀው፣ መላ ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው መጓዝ እንዲችሉ አንድነትን በመፍጠር ትልቅ ምሳሌ የሆነ ፕሮጀክት ነው ሲሉ ያብራራሉ።
‹‹አንዳንድ ፕሮጀክቶች ወደ ትግበራ ሲገቡ ይሄ ቢቀድም ያኛው ቢዘገይ ይባላል። ›› ያሉት አረጋ(ዶ/ር)፣ ዓባይ ግድብ ላይ ግን እንዲህ አይነት አስተያየቶች የሉም›› ሲሉ ገልጸዋል። ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያውያንን አንድ ያደረገና ሁሉም ሰው በአንድ አይነት ስሜት በጉጉት የሚጠብቀው ፕሮጀክት በመሆኑ ነው ብለዋል።
ወደፊትም ሁለት፣ ሦስት፣ አራት… መሰል ፕሮጀክቶች እየመጡ ተግባራዊ እንደሚሆኑ ተስፋ አለኝ ሲሉም አመልክተው፣ ፕሮጀክቱ ዛሬ በ13 ዓመት የግንባታ ጉዞው 95 በመቶ መድረስ መቻሉም እጅግ እንዳስደሰታቸውና እንዳስደመማቸው ገልጸዋል።
የፕሮጀክቱ ግንባታ 95 በመቶ በመድረሱ ሁለት ጉዳዮችን እንደሚመለከቱ የጠቀሱት አረጋ (ዶ/ር)፣ አንደኛው እንደ መሐንዲስ የምመለከተው ግድቡ ቦታ ላይ የተሠራው የሲቪል ሥራው (ግንባታው) ብቻ ከሆነ እሱ ምንጭ (ሶርስ) እንደሆነ ተናግረዋል፤ በግድቡ ቦታ የተሠራው የሲቪል ሥራ ትልቅ መሆኑን አስታውቀዋል። በዚህ ሥራ የተገኘውን ምንጭ ወደሚፈለገው አካባቢ ማከፋፈል ሌላው ሁለተኛው ሥራ እንደሆነ ጠቁመዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ሁለተኛው ሥራ የተገኘውን የኤሌክትሪክ ኃይል (ሀብት) ካለበት ቦታ ወደ ሚፈለገው አካባቢ ማሰራጨት ያስፈልጋል። ይህን ሀብት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ተደራሽ መሆን እንዲችል መስመር የመዘርጋቱ ሥራም ሌላኛው ፕሮጀክት ነው።
ስለዚህ ፕሮጀክቱ 95 በመቶ ደረሰ ሲባል የሲቪል ሥራው የደረሰበት ደረጃ እና የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራዎቹን ጨምሮ ከሆነ እሰየው ነው የሚሉት አረጋ (ዶ/ር)፤ የግድቡ ጀነሬተሮች ተከላ ተጠናቅቆ ከዚህ በኋላ የስርጭት ሥራ ብቻ የሚቀር ከሆነም በግልጽ ማስቀመጥ ተገቢ እንደሆነ አስታውቀዋል።
በእሳቸው እምነት የግድቡ ሥራ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቀቀ የሚባለው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ደጅ ሲደርስ መሆኑንም ጠቅሰው፣ ሁለተኛው ፌዝ ብዙ ሥራ ይኖረዋል የሚል ዕምነት እንዳላቸው አስገንዝበዋል። ያም ቢሆን አይቻልም የተባለው ተችሎ ሥራው ሳይስተጓጎል ዛሬ ላይ መድረሱ መላው ኢትዮጵያውያንን የሚያስደስትና የሚያስደንቅ ነው ብለዋል።
ብዙ ሰዎች ግድቡ ብዙ ዓመት እንደወሰደና ከተቀመጠለት ወጪ በላይ እንደጠየቀ ሲናገሩ ይደመጣል ያሉት አረጋ (ዶ/ር)፤ ግድቡ የቱንም ያህል ጊዜና ገንዘብ ቢወስድ ብዙ ነገር የሠራ፣ የለወጠና ብዙ ያተረፍንበት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ቴክኖሎጂን በማምጣት ኢትዮጵያውያን በዚህ ሙያ ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ ጉልህ አበርክቶ አድርጓል። አፍሪካ ብዙ ግድቦች የሚያስፈልጋት እንደመሆኗ ይህን ዕውቀት በሀገሪቱ መፍጠር መቻሉ ትልቅ ዕድል ነው። በመሆኑም ከኤሌክትሪክ ኃይል በተጨማሪ ኢትዮጵያውያን ክህሎታቸውንና ሙያቸውን ጭምር ኤክስፖርት ማድረግ የሚችሉበት አጋጣሚ ተፈጥሯል። ስለዚህ ግዱቡ የወሰደው ጊዜና ገንዘብ ካበረከተው አስተዋፅዖ አንጻር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ግድቡ ለኢትዮጵያውያን ትምህርትና ሥራ ከመሆን ባለፈ ትልቅ ሀገራዊ ዕድገት አምጥቷል ብለዋል።
መላው ኢትዮጵያውያን የተረባረቡበት የዚህ ግድብ ግንባታ ሲጀመር አንስቶ ሁሉም የኢትዮጵያ መንግሥታት ድርሻ እንደነበራቸው የጠቀሱት አረጋ (ዶ/ር)፤ ሀገሪቷን የሚመራ መንግሥት ሁሉ መንግሥት ነው። መንግሥትነት እንደማንኛውም ሥራ በቅብብሎሽ የሚሄድ እንደመሆኑ የግድቡን ሥራ ለጠነሰሱትም፤ ለጀመሩትም፤ መሐል ላይ ላደረሱትም ሆነ ላጠናቀቁት መንግሥታት እኩል ዋጋ መስጠት ያስፈልጋል፤ ሊመሰገኑም ይገባል ብለዋል። ወደፊትም ተቀብለው የሚሠሩ በመኖራቸውም ለሁሉም እንደየተሳትፏቸው ዋጋ መስጠት እንደሚገባ ገልጸዋል።
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ ከመንግሥት ባለፈም በርካታ ሰዎችም ተሳትፎ አላቸው፤ ሼር በመግዛትና በሌሎች ድጋፎች የተረባረቡ ሁሉ መመስገን ይኖርባቸዋል። ምንም ሼር ያልገዙና ያላዋጡ ወደፊት የሚመጡ ትውልዶችም በተጠቃሚነት የሚያግዙ እንደመሆናቸው ሊመሰገኑ ይገባል።
እንደዚህ አይነት ግድብ ወደፊት ጥገና የሚያስፈልገውና ቀጥለው መሠራት ያለባቸው የተለያዩ ሥራዎች እንደሚኖሩትም አስታውቀው፣ ሥራው መጪው ትውልድ ተረክቦ በቅብብሎሽ የሚያስቀጥለው መሆኑንም ተናግረዋል። ስለዚህ ፕሮጀክቱን ወደፊት የሚያስፋፉትና የሚጠቀሙትም ጭምር ይመሰገናሉ። ምክንያቱም ማመንጨት ብቻ ሳይሆን መጠቀምም ያስፈልጋል፤ ደንበኛ ንጉሥ ነው እንደሚባለው የሚጠቀሙትንም ማመስገን ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን የውጭ ወራሪ ጠላትን ለመመከት በአንድነት ቆመው ባደረጉት ተጋድሎ የጦርነት ስጋትን ማስወገድ እንደቻሉ ሁሉ፤ አሁን ደግሞ ኢትዮጵያውያን በዓባይ ወንዝ ላይ በገነቡት ግድብ ድህነት የተባለውን ጠላት ተባብሮ ማጥፋት እንደሚቻል አሳይተዋል ሲሉ አረጋ (ዶ/ር) ገልጸዋል። ዓድዋና የዓባይ ግድብ በመንፈሳቸው ተመሳሳይነት እንዳላቸው ጠቅሰው፣ አንድነትን በማጠናከር ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነን ድህነት የተባለውን ጠላት ማጥፋትና ሀገሪቷ እንድትበለጽግ መሥራት ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ የቤት ሥራ ነው ብለዋል።
አረጋ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት፤ ወደፊት ሀገራት የሚለኩት በወታደር ኃይላቸው ሳይሆን፤ በኢኮኖሚያቸው ነው፤ አንድ ሀገር ትልቅና ኃያል ሆኖ የሚታየው በኢኮኖሚ ነው። ኢኮኖሚን ከማዳበር አንጻር ደግሞ የዓባይ ግድብ የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ትልቅ አቅም ይሆናል። ለዚህም ዓረብ አገራት በነዳጅ አማካኝነት በዶላር እንደሚንበሸበሹ ሁሉ ኢትዮጵያም ከነዳጅ የበለጠ ንጹሕ የሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይል በምትሸጥበት ጊዜ በኢኮኖሚ የበለፀገች ትልቅ አገር መፍጠር ትችላለች።
የሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለቤት አቶ ሳሙኤል ታፈሰ በበኩላቸው የዓባይ ግድብ ብዙ የተለፋበትና ፈተና የታየበት የመላው ኢትዮጵያውያን ኩራት መሆኑን ይገልጻሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ የኢትዮጵያን ዕድገት የማይፈልጉ ሀገራት ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገነባውን ግድብ ለማስተጓጎል ብዙ ድንጋይ ፈንቅለዋል። ኢትዮጵያውያን ተስፋ ሳይቆርጡ በርብርብ ግድቡን ዛሬ ላይ አድርሰውታል። አጠቃላይ የግድቡ ግንባታም አሁን ላይ 95 በመቶ መድረሱ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ እጅግ እንዳስደሰታቸው አቶ ሳሙኤል ተናግረዋል።
የግድቡ ግንባታ ዛሬ ላይ 95 በመቶ መድረስ መቻሉ አለቀ እንደማለት ነው በማለት ያስረዱት አቶ ሳሙኤል፤ የቀሩት ሥራዎች ቀሪውን የውሃ ሙሌትና የተርባይን ተከላ ማጠናቀቅ መሆናቸውን ይላሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ ይህ እንደ ሀገር የሚያኮራና ትልቅ ለውጥ ነው። ዛሬ ነዳጅ የሚፈልገው መኪና በአዳዲስ ቴክኖሎጂ በኤሌክትሪክ የመተካት ዕድሉ ሰፊ ነው። የኤሌክትሪክ ኃይል ግን የማይቋረጥ ፍላጎት ያለውና በምንም ቴክኖሎጂ የማይተካ ለፋብሪካም ሆነ ለማንኛውም አገልግሎት አስፈላጊ በመሆኑ እጅግ ተመራጭ ነው። ከዚህ በኋላም ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት የሚችልበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። ይህም እጅግ የሚስደስትና የሚያኮራ ነው ብለዋል።
የዓባይ ግድብ ግንባታ ዛሬ ላይ መድረሱን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በጉጉት ሲጠብቀው መቆየቱን አቶ ሳሙኤል ጠቅሰው፤ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ካለው ላይ ቀንሶ ተሳትፎ ያደረገበትና በሙያው፣ በጉልበቱና በገንዘቡ ብዙ ያወጣበት እንደሆነ ተናግረዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የግድቡ ትልቅና ከባዱ ሥራ የሲቪል ሥራው ሲሆን የሜካኒካል ሥራ ደግሞ የመጨረሻውና ቀላል ሥራ እንደመሆኑ ተርባይኑ ማምጣትና መግጠም በመሆኑ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ እጅግ የሚያስደስትና ለመላው ኢትዮጵያውያን ትልቅ የምሥራች ነው።
ግድቡ ከሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር ኢትዮጵያዊ አንድነትን በማጠናከር ትልቅ ምሳሌ ነው የሚሉት አቶ ሳሙኤል፤ በሀገሪቱ አሁን ላይ የእርስ በእርስ ግጭቶችና መከፋፈሎች ቢኖሩም በዓባይ ግድብ ጉዳይ ግን መላው ኢትዮጵያዊ አቋሙ አንድና አንድ ነው በማለት ያስረዳሉ።
‹‹ብዙዎቻችን በተለያዩ ጉዳዮች ላንስማማ እንችል ይሆናል፤ ነገር ግን በዓባይ ግድብ ጉዳይ ከከተማ እስከ ገጠር ያለው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለ ልዩነት አንድ አቋም ነው ያለው። ሁሉም ኢትዮጵያዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ያስፈልገዋል። ሁሉም መልማትና መበልጸግ ይፈልጋል›› በማለት ግድቡ የሁሉምና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚስተሳስር እንደሆነ አስረድተዋል።
የኤሌክትሪክ ኃይል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን እንደሚሰጥ ጠቅሰው፣ እንደ ሀገር የሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ጉልህ ነው ይላሉ። አንድ ፋብሪካ ቢከፈት የኤሌክትሪክ ኃይል ከሌለ ምንም ጥቅም እንደማይኖረው አስታውቀው፣ በየትም አገር ውድ የሆነው የኤሌክትሪክ ኃይል በሀገር ውስጥ መኖሩ በሀገሪቱ በርካታ ፋብሪካዎች እንዲከፈቱና ሰፊ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ዕድል ይሰጣል ብለዋል። ከዚህ ባለፈም የኃይል ምንጩን ለጎረቤት ሀገራት በመሸጥ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪም እንዲሁ ለኢኮኖሚ ዕድገቱ ይዞ የሚመጣው በረከት የኢትዮጵያን መጻኢ ተስፋ ብሩህ ያደርጋል ሲሉ አቶ ሳሙኤል አስታውቀዋል።
ከውጭ ድጋፍ ሳይገኝ በኢትዮጵያውያን አንጡራ ሃብት ብቻ የተገነባውን የዓባይ ግድብን ግንባታ ለመጀመር ጀምሮም ለማጠናቀቅ በየዘመኑ የነበሩ የኢትዮጵያ መንግሥታት ጥረት ማድረጋቸውን እሳቸውም ጠቅሰው፤ ለእዚህ ሚናቸው ሊመሰገኑ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተለይም ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሀገሪቷ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ሆና ግንባታው ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል መደረጉ መንግሥትን እጅግ የሚያስመሰግን እንደሆነ የገለጹት አቶ ሳሙኤል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብም በህዳሴ ግድብ ጉዳይ ያለውን አቋም አንድ በማድረግ በጉልበቱ፣ በገንዘቡ፣ በሙያውና በተለያዩ ድጋፎች ተረባርቦ ዛሬ ላይ ያደረሰ በመሆኑ ትልቅ ምስጋና የሚገባው ነው በማለት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የእንኳን ደስአላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም