ጎብኚዎቹን አምባሳደሩ ያደረገው ግድብ

የአባይ ግድብ ግንባታ የዛሬ 13 ዓመት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም በይፋ ከተበሰረበት አንስቶ ኢትዮጵያውያን ግድቡ እውን እንዲሆን ከፍተኛ ርብርብ አድርገዋል። መንግስታቸው ባደረገላቸው ጥሪ መሰረት ድጋፋቸውን አደባባይ በመውጣት ባረጋገጡትና ግንባታውን ለመደገፍ ቃል በገቡት መሰረት ለግድቡ ግንባታ የሚያስፈልገውን የፋይናንስ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ። ኢትዮጵያውያኑ ለግንባታው ተጠናክሮ መቀጠል ትልቅ አቅም በመሆን በርካታ ተግባሮችን ሲያከናወኑ ቆይተዋል።

ከእነዚህ ተግባሮች መካከል በግንባታው ስፍራ በአካል በመገኘት በስፍራው እየተካሄደ የሚገኘውን ርብርብ ተመልክተዋል፤ በዚህም መሰረት ጋዜጠኛው እየተከናወነ ያለውን ተግባር በመዘገብ፣ ባለሀብቱ ለተጨማሪ ድጋፍ ራሱን በማዘጋጀት፣ ዲፕሎማቱ በዲፕሎማሲው መስክ በመፋለም፣ የመከላከያ፣ የፖሊስና ሌሎች የጸጥታ አካላት ግንባታው ያለምንም የጸጥታ ችግር ተጠናክሮ እንዲቀጥል በድጋሚ ቃል በመግባት ለግድቡ ግንባታ ተጨማሪ አቅም መሆን ችለዋል።

መምህር መለሰ በቀለ ግድቡን የመጎብኘት እድል አግኝተው በ2009 ዓ.ም ጎብኝተዋል። መምህሩ ግድቡን ለመጎብኘት እድሉን ሲያገኙ ከመጠን ያለፈ ደስታ ተሰምቷቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።

ኢትዮጵያ ግድቡን በራሷ አቅም በኢትዮጵያውያን የተባበር ክንድ ለመገንባት ይቻላል ብላ ስትነሳ ሕዝቡ ለግንባታው ድጋፉን በሰላማዊ ሰልፍ ማረጋገጡን ጠቅሰው፣ የገባውን ቃል በቻለው አቅም ሁሉ ሲደግፍ መቆየቱን መምህር መለሰ ይገልጸሉ። ይህ ሁሉ የኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበትን ግድብ ግንባታ ሂደት ለመጎብኘት እድሉን አግኝተው ቦታ ላይ በተገኙበት ወቅት በተመለከቱትና በተሰጣቸው ማብራሪያ በእጅጉ ተደንቀዋል፤ ተገርመዋል።

እሳቸው ግድቡን የጎበኙበት ወቅት ግንባታው ገና በጅምር ላይ እንደነበር አስታውሰው፣ በዚያ ደረጃም እየተሰራ የነበረው ስራ ግን ለኢትዮጵያውያን የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀ ነበር ይላሉ። የግድቡን ግንባታ ብቻ ሳይሆን ግድቡ የሚገኝበትን ቦታና የአካባቢው ውበት ምን ያህል አስደማሚ ስለመሆኑ በቃላት መግለጽ እንደሚከብድ ይገልጻሉ። ስፍራው ከፍተኛ ሙቀት ያለበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያውያን ይህን ሙቀት ተቋቁመው ለአገራቸው እየከፈሉ ያሉት መሰዋዕትነት ትልቅ ዋጋ ያለው መሆኑንም መምህሩ ያስታወሳሉ።

መምህር መለሰ ግድቡን በጎበኙበት ወቅት ግድቡ ገና ጅምር ላይ የነበረ ቢሆንም፣ ለሀገሪቱና ለመጪው ትውልድ ትልቅ ተስፋ ይዞ እየመጣ መሆኑን በሚገባ ተገንዝበዋል። ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን አይችሉም ሲሉን እንደምንችል ያሳየንበት፣ የማንነታችን አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበት ነው›› በማለት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ግድቡን ከጎበኙ በሁዋላም ግድቡ ስለደረሰባቸው የተለያዩ ምእራፎች አፈጻጸምና ለውጥ በሚዲያ መረጃውን ሲከታተሉ መቆየታቸውን ተናግረው፣ በተለይ ከለውጡ በኋላ የተደረጉ ማስተካከያዎች ተከትሎ በርካታ ትላልቅ ተግባሮች መከናወናቸውን እንደሚያውቁ ያመላክታሉ።

የግድቡ የውሃ ሙሌት በተለያዩ ዙሮች መካሄዱ፣ ግንባታው ሃያ አራት ሰዓት እየተካሄደ አሁን ትልቅ ደረጃ ላይ መድረሱ፣ ግንባታው በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ዝግጁ እንደሚሆን ማሳያ እንደሆኑ ይገልጻሉ።

‹‹ የግድቡ ግንባታ አፈጻጸም 95 በመቶ ያህሉ ተጠናቅቆ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ መድረሱን በሚዲያ ስከታተል መጀመሪያ ግንባታውን ስጎበኝ ከተሰማኝ ደስታ የበለጠ ተሰምቶኛል። ያኔ የተመለከትኩት እዚህ ደርሶ ማየት መቻሌ ተስፋዬ ይበልጥ እንዲለመልም፤ ስለመጪው ዘመን ብሩህ ጊዜ እንዳይ አስችሎኛል›› ሲሉ አብራርተዋል።

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ እያንዳንዱ ዜጋ ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበረው በትምህርት ቤቶች ተማሪዎች፣ መምህራንና ሁሉም የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ በሚችለው አቅም ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው፣ መምህራን በተለያዩ ዙሮች ከአራት ጊዜያት በላይ ቦንድ በመግዛት የራሳቸው አስተዋጽኦ ማድጋቸውን አመልክተዋል፤ በእሳቸው በኩል ግንባታው እስኪጠናቀቅ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ይናገራሉ።

‹‹ግድቡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ ሆነ በማህበራዊ ጉዳዮቻችን ላይ ትልቅ ለውጦችን ያመጣል ብዬ አስባለሁ›› ያሉት መምህር መለሰ፤ ግንባታው ሲጠናቀቅ ‹‹ የአገራችን እድገት ማስፈንጠሪያ ሊሆን የሚችል፣ ከእኛ አልፎ ለጎረቤት አገር የሚተርፍ ትልቅ ፕሮጀክት ነው።›› ሲሉም አስታውቀዋል። አገራችን ዓለም አቀፍ ጫናዎችን ጭምር ተቋቁማ የገነባችው ግድብ በመሆኑ ግንባታው ተጠናቅቆ ለማየት በጉጉት እየጠበቅን ነው›› ብለዋል።

‹‹ ኢትዮጵያውያን በተባባረ ክንድ የገነቡት፣ የእያንዳንዱ ዜጋ አሻራ ያረፈበት ግድብ እንደመሆኑ ከዚህ ቀደም እንደተደረገው ሁሉ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ እስከሚጠናቀቅ የበኩላችን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበናል›› ያሉት መምህሩ ግድቡን እንደ አይናችን ብሌን እየጠበቅን ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባናል ሲሉም አስገንዘበዋል።

ጋዜጠኛ ጸጋዬ ጥላሁን ግድቡን ከጎበኙት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች አንዱ ነው። ጋዜጠኛው በ2011 ዓ.ም ግድቡን በጎበኘበት ወቅት የግንባታው አፈጻጸም 67 በመቶ አካባቢ ደርሶ እንደነበር ያስታውሳል።

በወቅቱ ግድቡ የሚገነባበት ጉባ ደርሶ የግንባታውን ሂደት እንደተመለከተ፤ ‹‹ይህ ፕሮጀክት እውን ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችው ነው? እኛ እየሰራነው ነው? ይህን ያህል አቅምስ አለን? ›› የሚል ጥያቄ አዘል ግርምት ተጭሮበታል። በተለይ የኮርቻ ግድብ እና ሌሎችም ትላልቅ ቦታዎችን መጎብኘቱ የግድቡን ትልቅነት ይበልጥ ገዝፎ እንዲመለከት እንዳደረገው ተናግሯል።

ጋዜጠኛው ሌላው ግርምት የፈጠረበት የግድቡ ሠራተኞች ተነሳሽነት መሆኑን ጠቅሶ፣ አድናቆቱን ችሯቸዋል። ‹‹እዚያ በረሃ ውስጥ ሆነው ሙቀትና ሀሩሩን ተቋቁመው የግድቡን ሥራ የሚሰሩ ሠራተኞች ስመለከት ምን ያህል የሀገር ፍቅር እንዳላቸው ተረድቻለሁ ይላል። ለሀገር እድገትና ብልጽግና ብለው የሚከፍሉትን መስዋዕትነት እንዲመለከትም አስችሎታል።

ፕሮጀክቱን ሲመለከት ‹‹ኢትዮጵያ ይህን ያህል ፕሮጀክት የመገንባት አቅም አላት ወይ የሚል ጥያቄ እንዲያነሳ ያደረገው ቢሆንም፣ በየጊዜው እየተሰራ ያለው ሥራ መቻሏን አሳይቷል›› ሲል ጋዜጠኛ ጸጋዬ ተናግሯል። አሁን የግድቡ ግንባታ 95 በመቶ መድረሱን ሲሰማ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማው ጠቅሶ፣ ‹‹በሕይወቴ እንደዚህ አይነት ሰፊ ቦታ ያያዘ ትልቅ ፕሮጀክት፣ ሃያ አራት ሰዓት ሥራ የሚሰራበት ፕሮጀክት አይቼ አላውቅም›› ሲል የተሰማውን ገልጧል። ‹‹እውነቱን ለመናገር እንደዚያን ጊዜ ተደስቼ አላውቅም ፤ ልዩ ስሜት ነው የተሰማኝ።›› ሲልም አብራርቶ፣ ሁኔታው በድጋሚ ግድቡን ለመጎብኘት ከፍተኛ ጉጉት እንዲያድርበት እንዳደረገውም አስታውቋል።

‹‹ግድቡ ትልቅ ፕሮጀክት ነው፤ ኢትዮጵያውያን እድለኞችን ነን፤ ወንዙና ግድቡ የሚሰራበት ስፍራ ፈጣሪ በተፈጥሮ ምን ያህል ሀብት እንደሰጠን ማየት የሚቻልበት ነው። መስማማትና መግባባት ቢኖር ምንያህል ማደግ እንደሚቻልና ሀብት እንዳለን ያየሁበት ነው። የግድቡ ግንባታ ለኛ ኢትዮጵያውያን ልዩ ፕሮጀክታችን መሆኑን አይቼበታለሁ›› ሲልም አብራርቷል። ላለፉት አምስት ዓመታት በተከታታይ ቦንድ መግዛቱን ያነሳው ጋዜጠኛው አሁን የግድቡ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ እንደመሆኑ እሱ በሚችለው አቅም የበኩሉን ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል አረጋግጧል።

ጋዜጠኛው እንዳስታወቀው፤ የሚዲያ ባለሙያዎች በሚችሉት አቅም ስለግድቡ ግንባታ ሕዝቡን በማሳወቅ፣ በማስተማር እና ግንዛቤ በማስጨበጥ እያንዳንዱ ዜጋ ግንባታው እስከሚጠናቀቅ ድረስ የራሱን አስተዋጽኦ ማድረጉን አጠናክሮ እንዲቀጥል መስራት ይጠበቅባቸዋል። ለዚህ ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ ላይ እየተሰሩ ላሉ ሌሎችም ፕሮጀክቶች እንደ ሚዲያ ባለሙያ መስራት አለባቸው። ሕዝቡም በሚችለው አቅም ፕሮጀክቱን ከጅምር አንስቶ በአንድነትና በትብብር እንደሰራ ሁሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፍ በማድረግ እና ሌሎች ፕሮጀክቶች እንዲሰሩ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የሚዲያ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም፤ የግድቡ ግንባታ ከ95 በመቶ ላይ መድረሱ ምን ያህል ትልቅ ዋጋ እንዳለው የምናውቀው መነሻውን ስንመለከት ነው ይላሉ። በኢትዮጵያ ታሪክ ከጥንት ጀምሮ አባይን ለመገደብ ሃሳብ ያልነበረው መሪ የለም። ሲሉም ጠቅሰው፣ ግደቡን ለመገንባት ያልተቻለበት ዋንኛ ምክንያት በውጭ ሴራና በውስጥ ሸኩቻ የተነሳ ነው። ያም ሆኖ ግን ኢትዮጵያ ይህን ሁሉ ተቋቁማ ግድቡን በመገንባት የግድቡን ግንባታ 95 በመቶ ማድረስ ተችሏል ብለዋል።

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በርካታ ዜጎች ግድቡን ስፍራው ላይ ተገኝተው መጎብኘታቸውን የጠቀሱት አቶ ኃይሉ፤ ከየመስሪያ ቤቱ፣ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ወዘተ. የተወጣጡ እያሌ ሰዎች ግድቡን መጎብኘታቸውንም ይገልጻሉ። እስካሁንም ከ300ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን፣ ከ400 በላይ ሚዲያዎች እና የተለያዩ ዲፕሎማቶች እና የአገራት ልዑካን (የሳውዲ፣ ኳታር እና የመሳሳሉት) ቡድኖች ግድቡን ጎብኝተውታል። የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽርን ጨምሮ የሱዳንና የግብጽ ጋዜጠኞች ግድቡን መጎብኘታቸውን አስታውቀዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአገሪቷ የጸጥታ ሁኔታ እንደ ፊቱ በየብስ ትራንስፖርት ግዱብን ሄዶ ለመጎብኘት አስቸጋሪ ሆኖ መቆየቱን ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት ግድቡ እየተጎበኘ ያለው በአውሮፕላን በመሄድ መሆኑን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ግድቡን እየጎበኙ የሚጎበኙት በውጭ አገር ሆነው ስለግድቡ ሲወራ ይሰሙ የነበሩ የዲያስፖራዎች መሆናቸውን ገልጸዋል። እሳቸው እንደሚሉት፤ ዲያስፖራዎች እስካሁን ለግድቡ ድጋፍ ለማድረግ ድንበርና ርቀት ሳይገድባቸው ካሉበት ሆነው በቻሉት አቅም ሲደግፉ ኖረዋል። ለግድቡ ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል። ከዚህ ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስለግድቡ በመከራከር፣ በዓለም አደባባይ ድምጻቸውን በማሰማት እና በተለያዩ ጊዜያት ሰላማዊ ሰልፎች በማድረግ ከአገራቸው ጎን በመቆም ለግድቡ ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ በመላ ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች በቡድን በመደራጀት በዘመናዊው የሚዲያ አማራጭ በኦንላይን በመጠቀም፣ የተለያዩ ጆርናሎችን በመጻፍ፣ በተለይ በአረብ ሚዲያ እየተጠቀሙ በግድቡ ላይ ያላቸውን አዎንታዊ አቋም በመግለጽ ትልቅ ሥራ እየሰሩ ናቸው። ከዚህ አልፎ የአረቡን ዓለም ለማንቃት ኢትዮጵያውያኑ ብቻ ሳይሆኑ የሌሎች አገራት (የሱዳን፣ የአልጀሪያ—) ጋዜጠኞች ጭምር ሲሳተፉ ቆይተዋል። እነዚህ ዲያስፖራዎች ትልቅ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራ እየሰሩ ናቸው።

እንደዚህ አይነት ሥራ የሚሰሩ ዲያስፖራዎች ወደ አገራቸው ሲመጡ ደግሞ ግድቡን ለመጎብኘት እንዲችሉ የጉብኝት ፕሮግራም ይመቻችላቸዋል ያሉት አቶ ሀይሉ፤ በ2016 ዓመት ብቻ ዲያስፖራዎች በሦስት ዙር ግድቡን መጎብኘታቸውን አስታውቀዋል። ማስተባባሪያ ጽሕፈት ቤቱ ለጎብኘቱ የሚሆን በጀት እንደሌለው ተናግረው፣ ዲያስፖራዎች በቡድን ሆነው በራሳቸው በጀት ቻርተር አውሮፕላን ተከራይተው ግድቡ ድረስ በመሄድ ጎብኝተው እንደሚመለሱ አስታውቀዋል።

ዲያስፖራዎች ለጉብኝት መልስ ያላቸው ስሜት ለየት ያለ እንደሆነም ጠቅሰው፣ ግድቡን ሲመለከቱ በጣም የተለየ ስሜት እንደሚፈጥርባቸው ይናገራሉ። ዲያስፖራዎቹ ተጨማሪ ቦንዶች በመግዛት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ጠቅሰው፣ ግድቡን እየገነቡ ላሉ ዜጎች ጭምር ድጋፍ እንደሚያደርጉም ነው የተናገሩት። ወደመጡበት ሀገር ሲመለሱም የሀገሪቱን /የግድቡ/ አምባሳደር በመሆን ዲያስፖራው ቦንድ እንዲገዛ በመቀስቀስ እንደሚሳተፉ ያስረዳሉ።

ማስተባባሪያ ጽሕፈት ቤቱ፤ ሕዝቡ ግድቡን እንዲጎብኝ ለማስቻል ሁለት ነገሮች ታሳቢ ያደረገ ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ያስታወቁት አቶ ኃይሉ፤ የመጀመሪያው ሕዝቡ ግድቡ ድረስ ሄዶ መገብኘት እንዲችል ማድረግ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ግድቡን በምስል ማሳየት የሚችል የሕዳሴ ግድብ ፓርክ መሥራት ነው። ፓርኩን በአዲስ አበባ ከተማ ዓለም ባንክ አካባቢ ለመገንባት የሚያስችል ዲዛይን ተሰርቶ ለአዲስ አበባ ከተማ ጽዳትና ውበት ጽሕፈት ቤት መስጠቱን ጠቁመው፤ የአዲስ አበባ ከተማ ጽዳትና ውበት ጽሕፈት ቤት ሥራውን ተግባራዊ ሳያደርግ ይዞ መቆየቱን ይገልጻሉ።

እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ ማስተባባሪያ ጽሕፈት ቤቱ እስካሁን ካሉት ፓርኮች የተለየ ትልቅና ዘመናዊ የሆነ የውሃ ፓርክ ለመስራት ያለመ ሥራ በሙሉ ጨርሶ ለአዲስ አበባ ጽዳትና ውበት ጽሕፈት ቤት የሰጠው ትልቅ የውሃ ፓርክ እንዲሰራ በማሰብ ነው። የፓርኩ ዲዛይን የሚገርም በመሆኑ የግድቡን ሞዴል በሚገባ ሊያሳይ እንዲችል ተደርጎ የተሰራ ነው። ይህ እንዲሆን የተደረገበት ዋንኛ ምክንያት በተለይ ግድቡ ድረስ መሄድ ለማይችሉ ሰዎች የግድቡን ሞዴል በማየት ግድቡ አጠቃላይ ገጽታ ይህንን ይመስላል የሚል እይታ እንዲኖራቸው ለማድረግ በማሰብ ነው። ለግድቡ ደህንነት ጥንቃቄ ሲባልና ግንባታውም በማጠናቀቂያ ምእራፍ ያለ በመሆኑ ሰዎች በየብስ ትራንስፖርት ግድቡ ድረስ ሄደው እንዲጎበኙ ለማድረግ አሁን የሚቻልበት ሁኔታ አለመኖሩን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

‹‹ወደፊት የአባይ ግድብ ለአገሪቱ ገቢ የሚያስገኝ የቱሪዝም መስህብ እንደሚሆን እናምናለን›› አቶ ኃይሉ፤ ግንባታው ሲጠናቀቅ ከ78 በላይ ደሴቶችና ሪዞርቶች እንደሚኖሩትና አሳ የሚመረትበት መሆኑን ጠቅሰው ግድቡ ሲጠናቀቅ ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንደሚኖሩትም ጠቁመዋል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You