«በጎ ንግግርም ሆነ ሥራ የሚጀመረው ከቤት ነው» -ደራሲ አቶ ገብረኢየሱስ ኃይለማሪያም

የቀንዴን ያህል ተዋጋውልህ

የጭራዬን ያህል ተወራጨሁልህ

ጉራጌ ቋንቋህን ጠብቅ አይጥፋብህ

ያሉት የጉራጌኛ መጽሐፍን ለመጀመሪያ ጊዜ የፃፉት አቶ ገብረኢየሱስ ኃይለማሪያም ናቸው። እናት እና አባታቸው ጉዱ ወግበጋ (ታሪክ በየተራው) ብለው ስም ቢያወጡላቸውም፤ ሚሽን ትምህርት ቤት ሲገቡ ‹‹የክርስትና ስምህ ይሻልሃል›› ተብለዋልና አሁንም ድረስ ስማቸው በክርስትና ስም ገብረኢየሱስ እንዲሆን ፈቀዱ። የእርሳቸው ስም ብቻ ሳይሆን የአባታቸውንም ወግበጋ የሚለውን ስም ኃይለማሪያም በሚል በአባታቸው የክርስትና ስም ቀየሩ፡፡

በ1921 ዓ.ም ተወልደው 95ኛ ዓመታቸውን የያዙት አቶ ገብረኢየሱስ ዛሬም ቆፍጣና ናቸው። በደቡብ ክልል ሰባት ቤት ጉራጌ አካባቢ ጉመር ድርቦ መንደር ሲያድጉ፤ አባታቸው ሁለት ቤት የተለያየ ትዳር በመመሥረታቸው እናታቸውን እና አባታቸውን ሁለቱንም በቅርብ ለማግኘት እና ከሁለቱም ጋር አብሮ ለመኖር አልታደሉም፡፡

አባታቸው በስፋት በሚኖሩበት እንጀራ እናታቸው ቤት ለመኖር ተገደዱ፡፡ ነገር ግን እንጀራ እናታቸው እንደጠላቻቸው ስለተረዱ የእንጀራ እናታቸውን እና የአባታቸውን ልጅ ታናሽ እህታቸውን እየመቱ አስቸገሩ። ታናሻቸውን በመቱ ቁጥር የእንጀራ እናት ብትቀጣቸውም ከልጅቷ ጋር መጣላታቸውን አላቆሙም፡፡ አንድ ቀን የፈለጉት የሚሆንበት የተለየ የሕይወት አቅጣጫቸውን የሚቀይር አንድ አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡

የትምህርት ጅማሮ

ውሻ ነከሳቸውና እናታቸው ቤት ሔዱ። የውሻው ቁስል ቀላል አልሆነም፡፡ ለመዳን ስድስት ወር ፈጀባቸው፤ እየተሻላቸው ሲሔድ በእናታቸው ቤት አካባቢ የኔታ ተሰማ ቤት ፊደል መቁጠር ጀመሩ፡፡ ለአንድ ሳምንት ተማሩ፤ እንደዳኑ የሰሙት አባታቸው እናታቸው ቤት መጥተው በድጋሚ ወደ እንጀራ እናታቸው ቤት ወሰዷቸው፡፡ ትምህርታቸውን መቀጠል ፈልገዋልና ከእህታቸው ጋር መጣላታቸውን አጠናከሩ፡፡ ነገር ግን ከብት ይጠብቁ ስለነበር እንጀራ እናታቸው ልትለቃቸው አልፈቀደችም፡፡

አቶ ገብረኢየሱስ ትምህርት መማር በመፈለጋቸው እናታቸው ቤት በመኖር ለመማር አንድ ዘዴ አሰቡ፡፡ ለእንጀራ እናታቸው ‹‹ልጅሽ ከብቶች ትጠብቅ ለእዚህም እኔ ካሉኝ አራት በጎች ውስጥ ሁለቱን ልስጣት እናቴ ጋር ሔጄ ልማር» በማለት ሃሳብ አቀረቡ፡፡ የእንጀራ እናታቸው ተስማማች፡፡ ዘመዶቻቸው በሰጧቸው ሁለት በጎች እረኛ ገዙ፡፡

የጉመሩ የየኔታ ተሰማ ትምህርት ቤት ተስፋፍቶ መምህራን ተቀጥረው እዛው እስከ ሦስተኛ ክፍል ትምህርታቸውን ተከታተሉ። ቀጥለው እንድብር ሚሲዮን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አካባቢ ወዳለው ትምህርት ቤት ሲሔዱ፤ ስማቸውን እንዲቀየሩ ተጠየቁ፡፡ ጉመር የኔታ ተሰማ ትምህርት ቤት የሦስተኛ ክፍል ትምህርትን መላልሰው በመማራቸው፤ ስድስተኛ ክፍል ለመድረስ ሁለት ዓመት ብቻ ፈጀባቸው፡፡ የስድስተኛ ክፍል ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ አዲስ አበባ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገቡ። ትምህርት ቢወዱም የቋንቋ ጉዳይ ፈትኗቸው እንደነበር አልሸሸጉም፡፡

ከእንግሊዘኛ ቋንቋ ባልተናነሰ መልኩ አማርኛም እጅግ አስቸግሯቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ እንደምንም ጥርሳቸውን ነክሰው በብዙ ትግል ሁለቱንም ቋንቋ ማንበብም ሆነ መፃፍ በደንብ አወቁ፡፡ ስምንተኛ ክፍልን አልፈው ዘጠነኛ ክፍል ገቡ፡፡ በዛ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ዩኒቨርስቲ አልነበረም፡፡ ኮሌጅ ገቡ፡፡ እንግሊዘኛውም አማርኛውም ሁለቱንም ቋንቋ ከማወቅ እና አሸንፎ ከመውጣት አልፈው፤ መምህር ለመሆን በቁ፡፡ ከሥራቸው ጎን ለጎን ማታ ማታ በመማር በኢኮኖሚክስ ዲፕሎማ በሕግ ደግሞ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል።

የሥራ ሕይወት

አዲስ ዓለም ለሁለት ዓመት ካስተማሩ በኋላ አምቦ ሔዱ፡፡ አምቦም በመምህርነት ሲያገለግሉ ለብቻ ሕይወትን መግፋት አዳጋች ሆነ፡፡ ትዳር መሥርተው ኢትዮጵያ የተሰኘች አንዲት ልጅ ሲወልዱ፤ ሥራቸው ቀድሞ እንደነበረው ማስተማር ነበር። ሥራቸውንም ለመቀየር ከአምቦ ወደ አዲስ አበባ ለመግባት አስበው፤ አዲስ አበባ ከተማ ገብተው ባንክ ለመቀጠር ተወዳድረው በብቃት ፈተናውን አለፉ፡፡ ባንክ ማለፋቸው ተነግሯቸው በማግስቱ ሥራ ጀምሩ ተባሉ። ሌሊቱን ከአምቦ ወደ አዲስ አበባ እንዴት እንደሚገቡ እና የሚያገኙትን ደሞዝ እያሰቡ፤ እንዴት ዘመዶቻቸውን እንደሚረዱ ጓጉተው ሲያሰላስሉ ምንም እንቅልፍ ሳይተኙ ነጋ፡፡

ሥራ ለመጀመር ባንክ ሲሔዱ ግን አዲስ ጥያቄ ቀረበላቸው፤ ከትምህርት ሚኒስቴር መልቀቂያ ካላመጣህ አይሆንም ተባሉ፡፡ ሚስት እና ልጃቸውን ለማምጣት ሁኔታ አመቻችተዋል፤ ነገር ግን መልቀቂያውን ማግኘት አልቻሉም። ስለዚህ ሌላ ሥራ አዲስ አበባ ሲፈልጉ ፓስተር ኢንስቲቲዩት እንግሊዞች ቅጥር እንዳወጡ ሰሙ። በቋንቋው ጥሩ ተናጋሪ በመሆናቸው ለመቀጠር አልተቸገሩም፡፡

ፓስተር ለሦስት ወር በሁለት መቶ ብር ደሞዝ ተቀጠሩ፡፡ ከሦስት ወር በኋላ ግን ከፍተኛ ደሞዝ ታገኛለህ ተብለው ሥራ ጀመሩ፡፡ በ15 ብር ቤት ተከራይተው ለአንድ ወር ከቆዩ በኋላ፤ ‹‹ደሞዜ አልበቃኝም፤ መልቀቂያ ይሰጠኝ›› የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ፤ ጎበዝ ሠራተኛ መሆናቸውን የሚገልፅ መልቀቂያ ደብዳቤ አገኙ፡፡ መልቀቂያህን ካላመጣህ አትቀጠርም ወደተባሉበት ባንክ ሔደው ደብዳቤውን አስገቡ፡፡ ባንክ ሥራ ከጀመሩ በኋላ ደሞዛቸው በ15ቀን ቢሆንም በአጠቃላይ በወር 195 ብር ብቻ መሆኑን ሲያውቁ ተበሳጩ፡፡

በ15 ቀናቸው ለቅቀው ፖይንት ፎር ኤዱኬሽን የተሰኘ የውጪ ድርጅት አመለከቱ፤ አንዲት አሜሪካዊት በ285 ብር ቀጠረቻቸው። ለዘጠኝ ወር ከሠሩ በኋላ፤ በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) አዲስ አበባ ውስጥ ሲቋቋም ተወዳድረው ተቀጠሩ። እ.አ.አ በ1958 በ360 ብር በጸሐፊነት ከተቀጠሩ በኋላ ቀን እየሠሩ ማታ ማታ ይማሩ ነበር። በዛው ተቋም ለ33 ዓመታት ሲያገለገሉ የተለያዩ ሥራዎችን ይሠሩ ነበር፡፡ ከጸሐፊነት በተቀናጀ የከተማ ልማት ክፍል ኃላፊ ሆነው ተሹመው እስከ ማገልገል ደርሰዋል፡፡

የአቶ ገብረኢየሱስ መጽሐፍቶች

አቶ ገብረኢየሱስ 16 መጽሐፎችን ፅፈዋል። በተደጋጋሚ መጽሐፍ ሲያነቡ መጽሐፍ ስለመፃፍ ያስባሉ፤ ነገር ግን ጽፈው አያውቁም። በአጋጣሚ ኢሲኤ እየሠሩ ታመው ባልቻ ሆስፒታል ተኙ፡፡ ‹‹ከ15 ቀን በኋላ መጥተህ ቀዶ ጥገና ይደረግልሃል።» ሲባሉ፤ ቤቴ ሩቅ ሀገር በመሆኑ ለ15 ቀን እዚሁ ልተኛ አሉ፡፡ የአልጋ በቀን አምስት ብር እየከፈሉ ሆስፒታል ሲቆዩ፤ ‹‹ከንቱ ኑሮ›› የሚል የመጀመሪያውን ባለ 101 ገፅ መጽሐፍ ጨርሰው ወጡ፡፡

የመጽሐፉ መነሻ ጊዜያቸውን በቁማር በሚያጠፉ የጓደኞቻቸው ታሪክ ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው፡፡ መጽሐፋቸው ገበያ ላይ ሲውል በሰፊው ተፈላጊ ሆነ። ገበያውን አይተው ጉዱ እና ታሪኩ የሚል መጽሐፍ ለሕትመት አበቁ፡፡ ሦስተኛው መጽሐፋቸው የመዓዛ ጉዞ የተሰኘ ነው፡፡ ታሪኩ አዲስ አበባ ላይ አንድ ዘመዳቸው ሚስት ሊያገባ ሲል የምትዳረዋ ልጅ አያት በጣም ታላቅ ሰው በመሆናቸው ምንም እንኳ አዲስ አበባ ላይ ቤት ቢኖራቸውም ሲዳማ ቀብአለኝታ የተባለ አካባቢ ላይ ያላቸውን ንብረት ለማሳየት ድግሱን እዛ አደረጉት፡፡

ተጠሪው አንዴ በግሩ ሲደክመው በፈረስ በብዙ ችግር የሠርጉ ቦታ ደረሰ፡፡ የሠርጉ አካባቢ በጣም የሚያስደስት በመሆኑ እርሱን ድግስ መንገድ ላይ የነበረውን ውጣ ውረድ መነሻ በማድረግ የመጽሐፉንም ስም የመዓዛ ጉዞ አሉት፡፡ ቀጥለው የፃፉት መጽሐፍ ደግሞ ርዕስ ስጡልኝ የሚል ነው፡፡ የርዕሱ መነሻ መጽሐፉን ከፃፉ በኋላ ለቅድመ ምርመራ ሲያቀርቡ ርዕስ ቀይሩ ይባላሉ፡፡ ቀይረው ቢያቀርቡም በድጋሚ እንዲቀይሩ ሲነገራቸው፤ ርዕስ ስጡልኝ ብለው ሲሰጡ ርዕሱ ይኸው ይሁን አሏቸው፡፡ የመጽሐፉ ርዕስም አርዕስት ስጡልኝ የሚል ሆኖ ለኅትመት በቃ፡፡

5ኛው የጉራጌ መጽሐፍ ነው፡፡ በመንገድ ሥራ ድርጅት በኩል በ1954 ዓ.ም ጉመርን ወክለው ወደ አካባቢው ለማልማት ሔዱ። እዛው ሆነው ‹‹የኅብረት እንቅስቃሴ በማለት በልማቱ ላይ ማን ምን እንደሠራ በሚያመላክት መልኩ ጽፌያለሁ፡፡›› ይላሉ። በመጽሐፋቸው አልጋ ወራሽ ያደረጉትን ድጋፍ ስንት ብር ቃል እንደገቡ እና ስንት ብር እንደቀረባቸው ሳይቀር ፃፉ፡፡ በዚህ ምክንያት ንጉሡ በአስቸኳይ

 

ክፍያውን ፈጸሙ፡፡ ቀጥለው ጉራጌኛ የፃፉ ሲሆን፤ በመቀጠል የእንግሊዘኛ መጽሐፍ ጽፈዋል። አስከትለው ጉራጌኛ መጽሐፍ ጽፈዋል፡፡ በአጠቃላይ ሦስት መጽሐፎችን በጉራጌኛ ቢጽፉም አሁንም ቋንቋው እንዳይጠፋ ስጋት አለባቸው፡፡

እርሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ከእርሳቸው ቀጥለው ሦስት ሰዎች በጉራጌኛ መጽሐፍ ፅፈዋል፡፡ በእርግጥ ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ በአካባቢው የጉራጌኛ ትምህርት ሊጀመር መሆኑን መስማታቸውን ጠቅሰው ነገር ግን የአካባቢው ሰው ከራሱ ቋንቋ ይልቅ አማርኛ እና ኦሮሚኛን ቋንቋ በፍጥነት ተቀብሎ እየተግባባበት መሔዱ እና የጉራጌኛን ቋንቋ በስፋት ሲነጋገሩበት አለማየታቸው አስገርሟቸዋል፡፡

አቶ ገብረኢየሱስ የትኛውም ቋንቋ መለመዱ ጉዳት የለውም ጥቅም አለው ካሉ በኋላ፤ ነገር ግን የጉራጌ ችግር የሚሉትን ያብራራሉ፡፡ ጉራጌ ይባል እንጂ በጉራጌ ውስጥ አስር የተለያየ ቋንቋ አለ፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት አስሩም የተለያዩ ናቸው። ምክንያቱ ደግሞ አስሩም የየራሳቸው መንግሥት ስለነበራቸው መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

አንድ ለማድረግ የተሞከረውን ሲያስ ታውሱ፤ ከ220 ዓመት በፊት ከእነሞር ጎንቺዬ የሚባል ታዋቂ ሰው፤ ከሙሑር ደግሞ አጃሞ ኤነሞ የሚባል ሰው የጉራጌ ሕዝብ እንዳይለያይ አንድ እናድርገው ብለው ሰዎችን ቀስቅሰው በጉራጌ አካባቢ ብዙኃኑ በቅርብ ያለበት ቦታ ተመርጦ ቸሃ ላይ ሕዝቡን ጠርተው ስብሰባ አካሂደው ነበር፡፡ የጉራጌን ሕዝብ አንድ ለማድረግ አንድ ንጉሥ እና አንድ ቋንቋ ያስፈልጋል ብለው ተነጋገሩ፡፡

ከቸሃ ውስጥ አንድ ታዋቂ ሰው ይነግሣል ተብሎ ድግስ ተዘጋጀ፤ ነገር ግን ሁለቱ አዋቂ ሰዎች ተነጋግረው፤ ‹‹ይሔ ሰውዬ ይንገሥ ካልን ቸሃ ዘላለሙን ንጉሥ ሆኖ ሊቀር ነው። ስለዚህ ንጉሥ ሳይሆን አስተዳዳሪ እንሹም ተባባሉ።›› በተነጋገሩት መሠረት ንጉሥ ሳይሆን አስተዳዳሪ ሾሙ፡፡ ተሿሚው ለሦስት ዓመት ተኩል ጉራጌን በደንብ አስተዳደረ፡፡ ሃሳቡ ቋንቋውን እና ሕዝቡን አንድ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ቢሆንም አልተሳካም፡፡ ምክንያቱም እንዲያስተዳድር የተመረጠው ሰው ተገደለ፡፡ እንደገና ጉራጌ ተበተነ፡፡ ቀድሞ እንደነበረው ለየአካባቢው አስተዳዳሪ ተፈጠረ፡፡ ስለዚህ ጉራጌ አንድ መሆን አቃተው፤ አሁን ግን ሥነጽሑፎቹ ቢበዙ ቢያንስ ቋንቋውን ወደ አንድ ማምጣት ይቻል ነበር፡፡ ይላሉ፡፡

ሌላው በአቶ ገብረኢየሱስ የታሰበው የቤተ ጉራጌ ባሕል ማዕከል ነው፡፡ ኢሕአዴግ ሀገሪቱን በሚያስተዳድርበት ጊዜ ፖለቲካ ውስጥ ያሉ ጉራጌዎች ባሕል ማዕከል እንዲቋቋም ያግዛሉ ብለው ያሰቧቸውን ሰዎች አቶ ገብረኢየሱስ ቤት ውስጥ ግብዣ አዘጋጅተው ተንበርክከው የቤተ ጉራጌ ባሕል ማዕከል እንዲቋቋም ጥያቄ አቀረቡ። ጥያቄያቸውን ሁሉም በደስታ ተቀበለ፡፡ ግሎባል ሆቴል ትልቅ ስብሰባ ተደረገ፡፡ በሁለተኛው ቀጠሮ በዋናነት የባሕል ማዕከሉን ለማቋቋም ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩት እና በቀጣይም ሰፊ ሚና ይኖራቸዋል ብለው ያሰቧቸው ፊትአውራሪ ሀብተማሪያም በድንገት ሞቱ፡፡ ለስድስት ወር ከሠሩ በኋላ አቶ ገብረኢየሱስም ታመው ወደ ደቡብ አፍሪካ ለሕክምና ሔዱ፡፡

ሕክምናውን ከስድስት ወር በኋላ ጨርሰው ሲመለሱ እርሳቸውን ወክሎ ሲሠራ የነበረው ሰው ቦታውን አልለቅ አለ፡፡ እርሳቸውም ትንሳኤ ወይስ ስንብት የሚል መጽሐፍ ፃፉ። መነሻቸው የባሕል ማዕከሉ ጠንካራ ሆኖ ቢቋቋም ለጉራጌ አንድነት ትንሳኤ ነበር፡፡ አሁን አልተሳካም፤ ጭራሽ እርስ በእርስ ሽኩቻ ሆነ፡፡

ትዳር

አቶ ገብረኢየሱስ ጠበቅ ያሉ ሰው ናቸው፡፡ ባለቤታቸው ኦርቶዶክስ በመሆናቸው ተዋሕዶ ነኝ ማለትም እየሱስ ወደ ምድር ሲመጣም ሆነ ለሰው ልጆች ብሎ በመስቀል ላይ ሞትን ሲቀበል ተዋሕዶ ነው ሲሉ፤ አቶ ገብረኢየሱስ ደግሞ የካቶሊክ ሃይማኖት ተከታይ በመሆናቸው ክርስቶስ የሞተው በሥጋ ብቻ ነው፡፡ መለኮት አልሞተም፤ ተዋሕዷል ማለት አይቻልም የሚል ልዩነት ትዳራቸውን አፈረሰው፡፡ አቶ ገብረኢየሱስ የካቶሊክ ሃይማኖትን አጥብቀው ይወዱ ስለነበር፤ ከትዳር አጋራቸው ጋር የሃይማኖት ልዩነት መኖሩ ኢትዮጵያ የተሰኘች ልጅን ካፈሩ በኋላ ለመለያየት አስወሰናቸው። ኢትዮጵያ አሁን ላይ ሁለት ልጆች ወልዳ አሳድጋ አንደኛው ዶክተር ሆኗል፡፡ ድርጅት መሥርታም ለሀገሯ ብዙ እየሠራች ነው፡፡

ሁለተኛ ትዳር መሠረቱ፡፡ ከሁለተኛው ትዳራቸው አስር ልጆችን አፈሩ፡፡ ሁለቱ በሕይወት የሉም፡፡ አሁን አቶ ገብረኢየሱስ ሦስት ዶክተር የልጅ ልጆች አላቸው፡፡ ዘጠኙንም ልጆቻቸውን ሴንጆሴፍ ያስተማሩ ሲሆን፤ ልጆቻቸውን በቅርበት እንደሚከታተሉ እና ከልጆቻቸው በፍፁም እንደማይለዩ ይናገራሉ። ልጆችን መቆጣጠር የግድ መሆኑን በመጥቀስ፤ አንድም ልጅ የብሔራዊ ማጠቃለያ ፈተናን መውደቅ ቀርቶ ዝቅተኛ ውጤት ማምጣት አይፈቀድለትም ነበር፡፡ ስለዚህ በከፍተኛ ውጤት ማጠናቀቅ ግዴታቸው ነበርና ሁሉም ያንንም ማሳካት መቻላቸውን ይናገራሉ፡፡

ልጆቹም በአባታቸው የሚተላለፈውን ትዕዛዝ ለመቀበልም ሆነ ራሳቸውን ለማሳደግ ፈቃደኛ ናቸው፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ሥር ያሉት ታዋቂው ሼፍ ዮሓንስን ገብረኢየሱስን ጨምሮ ሦስት ልጆች ብቻ ናቸው፡፡ ሁሉም በተሰማሩበት መስክ ስኬታማ ሆነዋል፡፡ ልጆቻቸው ብቻ ሳይሆኑ የልጅ ልጆቻቸውን ስኬታማ እስከማድረግ የደረሱት አቶ ገብረኢየሱስ፤ አራተኛ ትውልድ ከማየት አልፈው የእነርሱም ሕይወት ስኬታማ እንዲሆን ሚናቸውን ለመወጣት ችለዋል፡፡

የአባት መልዕክት

ማንኛውም ሰው ከሌላ ሰው ዕርዳታ እና ድጋፍ መጠበቅ የለበትም በራሱ ሁሉንም ነገር ለመፈፀም ዝግጁ መሆን አለበት፡፡ ይህንን ሁሉም ሊያውቅ ይገባል በማለት የራሳቸውን ተሞክሮ ይጠቅሳሉ። ‹‹እኔ የቤተሰብ እርዳታ አልነበረኝም፡፡ ይህን ላድርግልህ የሚለኝ የለም፡፡ እኔም ከማንም ምንም እንዲደረግልኝ አልጠብቅም፡፡ በዘመኔ ያጣሁትን ለማግኘት ጥረት አደርጋለሁ፡፡›› በማለት፤ ከምንም ነገር በላይ ማንም ቢሆን በተለይ ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት መስጠት አለበት። ሰዎችም ገንዘብ ከመስጠት ይልቅ ለሰዎች ሥራ ቢያስተምሩ መልካም ነው፡፡ ሰው ማለት ገንዘብ የሚሰጥ ሳይሆን እየሠራ የሚያሠራ እና ሰዎችን ለሥራ የሚቀሰቅስ ሰው ነው፡፡ ገንዘብ ብቻውን እንደማያሳድግ ማወቅ ያስፈልጋል›› ይላሉ፡፡

‹‹አዲስ አበባ ላይ ኢሲኤ ከገባሁ በኋላ የአባቴን ፈረስ በየሦስት ዓመቱ እቀይርለት ነበር፡፡ በዛ ዘመን ሰዎች መደብ ላይ ሲተኙ፤ እኔ ግን ለአባቴ የሽቦ አልጋ ገዝቼ ከሰው በላይ አድርጌው ነበር፡፡ አሁን ቀላል ይመስላል፤ በጊዜው ግን ትልቅ ነገር ነው። ምክንያቱም የአካባቢው ሰዎች እኔ ገንዘብ ባልሰጣቸውም ለቤተሰቦቼ የማደርገውን እያዩ ለመማር ተነሳሱ፡፡ ወላጆችም ልጅን ማስተማር ትልቅ ነገር መሆኑን ተረድተው ማስተማር ጀመሩ። አዲስ አበባ ብገባም ከአካባቢው አልርቅም ነበር። በየጊዜው አባቴ ጋር እየሔድኩ ለክርስቲያንም ሆነ ለሙስሊም በሬ አሳርዳለሁ። ያ በአካባቢው ሕዝብ ውስጥ ትልቅ ምሳሌ እንድሆን አስገደደ። አሁን ጉራጌ አካባቢ 37 ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ሦስት ዩኒቨርስቲዎች አሉ። ይህ ሁሉ የመማሪያ ተቋም ሲገነባ ቀስቃሽ ነበርኩ።›› ይላሉ፡፡

አቶ ገብረኢየሱስ እንደሚናገሩት፤ በእርግጥ ሰዎች ለትልቅ ደረጃ የሚያደርሳቸው ዓላማቸው ነው፡፡ ስም ለማግኘት ሳይሆን ሥራ ሠርቶ ስኬታማ ለመሆን ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለአካባቢ ማኅበረሰብ መሥራት በጣም ጥሩ ነው፡፡ ከ1953 ጀምሮ እስከ 1966 ዓ.ም በቅርብ እየተመላለሱ በተወለዱበት በጉራጌ አካባቢ መንገድ እና ሌሎችም የልማት ሥራዎች እንዲከናወኑ ጥረት ማድረጋቸውንም ያስታውሳሉ፡፡

‹‹ሌላው በመንግሥት በኩልም መናገር ብቻ ዋጋ የለውም፡፡ ከመናገር ይልቅ መተግበር ይሻላል፡፡ በጣም ትልቅ ተስፋ ነበረን፡፡ ማጥፋት ሁሉንም ያጠፋል፤ ማልማት ሁሉንም ያለማል፡፡ ለሀገር ብሎ መሥራት ትልቅ ውጤት ያመጣል። እውቅናን ብቻ አስቦ መሥራት ግን ውጤቱ አያምርም፡፡ ከእልህ ይልቅ ሥራ ላይ ማተኮር ይሻላል፡፡ ምሳሌ መሆን ያለበት ሰው ምሳሌነቱ ሊታይ ይገባል፡፡ የሚከበረው ያከበረ ሰው ነው። ያላከበረ ሰው መከበር አይችልም፡፡ ጥፋትን ማመን ያስፈልጋል፡፡

የኢትዮጵያውያን ትልቅ ችግር ጥፋትን ለማመን ብዙ ሰው የሚቸገር መሆኑ ነው። ሰው ይቅርታን መልመድ አለበት፡፡ ሀገር የሁሉም ናት፡፡ ይህንን ሁሉም ማወቅ አለበት፡፡ ያለውን ማሻሻል እንጂ ሙሉ ለሙሉ መለወጥ ጥሩ አይደለም። ኢትዮጵያውያን ጥሩዎች ነን። መንግሥትን እንወዳለን፡፡ ስለሀገር መጥፎ ነገር መነገር የለበትም፡፡ በጎ ንግግርም ሆነ ሥራ የሚጀመረው ከቤት ነው፡፡ ሁሉም ሁሉንም ሊረዳ ይገባል፡፡›› ይላሉ፡፡

በመጨረሻም ‹‹በእርግጥ ቤተሰብን ማስተዳደርም ከባድ ነው፡፡ ሁሉንም ማስደሰት አይቻልም፡፡ አንድ የሚያስቸግር አይጠፋም። 100 ሚሊዮን ሕዝብን ማስተዳደር ብዙ ጣጣ አለው። ሁሉም ከቤቱ ጀምሮ ኃላፊነቱን ካልተወጣ ከባድ ነው፡፡ የመንግሥት ችግር የሁላችንም ችግር እንደሆነ ማሰብ አለብን። መንግሥትም ሕዝብን መውደድ አለበት፡፡ ዋናው ጉዳይ ሁላችንም እንተሳሰብ እንተዛዘን፤ ደግሞም ለሁላችንም ልብ ይሰጠን›› በማለት ሃሳባቸውን ጨርሰናል፡፡

ምሕረት ሞገስ

Recommended For You