
ሜክሲኮ፣ የአሜሪካዋ ግዛት ባጸደቀችው ጠንካራ የስደተኛ ሕግ ምክንያት ከቴክሳስ ተይዘው የሚመለሱ ስደተኞችን አልቀበልም አለች።
የአገሪቱ መንግሥት “ሜክሲኮ ከቴክሳስ የሚመለሱ ማንኛውንም ስደተኞች በምንም ሁኔታ አትቀበልም” ብሏል። ሜክሲኮ ይህንን መግለጫ ያወጣችው የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕጉ ተግባራዊ እንዲሆን መፍቀዱን ተከትሎ ነው።
ይህ ሕግ የቴክሳስ ፖሊስ የአሜሪካ – ሜክሲኮን ድንበር በሕገ ወጥ መንገድ አቋርጧል ተብሎ የተጠረጠረን ስደተኛ እንዲያስር ይፈቅዳል።
የባይደን አስተዳደር ኤስቢ4 የተባለውን ሕግ “ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነ” ሲሉ ተቃውመውታል። ቀደም ብሎ ፍርድ ቤቶች የአገሪቷን የኢምግሬሽን ሕግ ማስፈፀም የሚችሉት ግዛቶች ሳይሆኑ የፌዴራል መንግሥቱ ብቻ ነው ብለው ነበር።
የአሜሪካን ድንበር በሕገ ወጥ መንገድ ማቋረጥ ወንጀል ቢሆንም እነዚህ ጥሰቶች የሲቪል ጉዳይ ተደርገው የሚታዩት በኢሚግሬሽን የፍርድ ቤት ሥርዓት ነው።
ኤስቢ4 ሕግ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ቴክሳስ የሚገቡ ስደተኞች እስከ 20 ዓመት የሚደርስ እስራት እንዲቀጡ ያዛል። የሜክሲኮ ባለሥልጣናት ቀደም ብሎ ሕጉን ‘ፀረ ስደተኛ’ ሲሉ ሕጉን የተቹት ሲሆን፤ ከአሜሪካ ጋር ያለውን ግንኙነት ሊያወሳስበው እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል። ይህ ስጋት በአሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤትም ተስተጋብቷል።
የሜክሲኮ የፍትሕ ሚኒስቴር ማክሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ እንዳለው፤ ሜክሲኮ ግዛቶች አሊያም የአካባቢ ባለሥልጣናት ስደተኞችን እንዲቆጣጠሩ፣ ዜጎችና የውጭ ዜጎችን ማሰር እና መመለስ የሚፈቅደውን ሕግ አትቀበለውም።
መግለጫው ጨምሮም ሕጉ በቴክሳስ የሚኖሩ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ሜክሲኮውያን ሰብዓዊ መብት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል ብሏል። የሜክሲኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ኤስቢ4 ስደተኛ ማኅበረሰቦች ለጥላቻ ንግግርና ለአድልዎ በማጋለጥ አስከፊ ሁኔታን ይፈጥራል ብሏል።
ሚኒስቴሩ ኤስቢ4 ሕግን ለማስቆም በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የሚደረገውን ሕጋዊ ጥረት እንደሚቀላቀልም አስታውቋል። ዋይት ሃውስ የፌዴራል የታችኛው ፍርድ ቤቱ ስለ ሕጉ ሕጋዊነት ላይ ጥያቄ ባነሳበት ሁኔታ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ማስተላለፉን ተችቷል።
የዋይት ሃውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ካሪን ጂን ፔሪ በሰጡት መግለጫ “ኤስቢ4 በቴክሳስ ያሉ ማኅበረሰቦችን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ብቻ ሳይሆን በሕግ አፈጻጸም ላይ ጫና ይፈጥራል። እንዲሁም በደቡባዊ ድንበር ላይ ትርምስ እና ግርታን ይፈጥራል” ብለዋል።
ሆኖም ሪፐብሊካኑ የቴክሳስ ገዥ ግሬግ አቦት፣ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አዎንታዊ ለውጥ በማለት አወድሰውታል። ምክትላቸው ዳን ፓትሪክም “ ሕገ ወጥ ስደተኞችን ማሰር እና ወደ ሜክሲኮ ጠርዞ መላክ አሊያም ወደ እስር ቤት መወርወር እንጀምራለን” ሲሉ ማክሰኞ ዕለት ለፎክስ ኒውስ ተናግረዋል።
ኤስቢ4 ሕግ የተፈረመው ታኅሣሥ ወር ላይ ሲሆን፤ ከመታገዱ በፊት ሚያዝያ 5 ላይ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ ነበር። አሁን ላይ ጉዳዩ ኒው ኦርሊያንስ ወደሚገኘው የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ይመለሳል። የቃል ክርክሩም ለረቡዕ ቀጠሮ ተይዞለታል። በክርክሩ ማንም ቢያሸንፍም ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መልሶ የመውሰድ አማራጭ አለ።
ሪፐብሊካኖች ብዙውን ጊዜ የዲሞክራቱን ባይደን አስተዳደር የአሜሪካ-ሜክሲኮን ድንበር በሚይዙበት አግባብ ይወቅሷቸዋል። ኅዳር ላይ ከሚካሄደው የዋይት ሐውስ ምርጫ በፊት ይህ የሕዝብ አስተያየት መኖሩም ለመራጮች ትልቅ ስጋት ነው።
የካቲት ወር ላይ በአሜሪካ ተቋም በተሰበሰበ የሕዝብ አስተያየት መሠረት አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት አሜሪካውያን ስደት፣ ኢኮኖሚ እና የዋጋ ንረት የአገሪቷ ትላልቅ ችግሮች እንደሆኑ ያምናሉ።
ባለፈው የታኅሣሥ ወር በሺዎች የሚቆጠሩ ከማዕከላዊ እና ደቡብ አሜሪካ አገራት የተውጣጡ ስደተኞች በእግራቸው ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ድንበር ማቅናታቸው የሚታወስ ነው።
ሕፃናትና አዋቂዎች ሳይቀሩ የተሰባሰቡበትና ስምንት ሺህ ገደማ የሚሆኑ በአብዛኛው ከቬንዝዌላ፣ ኩባ እና ሜክሲኮ የመጡ ስደተኞች ናቸው ወደ አሜሪካ ድንበር አቅንተው በርካታ ውዝግብ መፈጠሩ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2016 ዓ.ም