የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ያጋለጠው ሰሞነኛው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብልሽት

ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ዓርብ መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ምሽት ላይ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የገንዘብ ዝውውር ሥርዓት ላይ ችግር ተፈጠረ። የተፈጠረው ችግርም ከባንኩ የዲጂታል ሥርዓት ጋር የተያያዘ መሆኑን የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል። በዚሁ ችግር ምክንያትም የባንኩ መደበኛ አገልግሎቶች ለተወሰኑ ሰዓታት መቋረጣቸው ይታወቃል።

በወቅቱም ከ490 ሺህ በላይ ጤነኛ እና ሕጋዊ ያልሆነ ግብይት መከናወኑን ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰው በዚህ ሂደትም የተዘዋወረ ገንዘብ ወጪ እንዳይሆን መታገዱን አንስተዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ የተከናወኑ ግብይቶችን የመመርመር ሥራው መቀጠሉንና በተለይም ከፍተኛ ግብይት ያከናወኑትን ለፀጥታ አካላት ማሳወቅ መቻሉንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በገንዘብ መክፈያ እና ማዘዋወሪያ ሥርዓቱ ላይ ያጋጠመው ችግር በተለይ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዘንድ በስፋት ተሰራጭቷል። ከሌሊቱ 6 እስከ 8 ሰዓት ድረስ ተማሪዎች በብዛት ሲደዋወሉ እንደነበረ እና አንዳንዶቹም ‹‹ቢዝነስ እንሠራ በሚል›› ለሩቅ ዘመዶቻቸው ጭምር እየደወሉ ሲያሳውቁ ነበር። ከዛም አልፎ ሁሉም በዘረፋው እንዲሳተፍ በማኅበራዊ ሚዲያ ጭምር መልዕክት ሲተላለፍ ነበር።

በተጨማሪም በምሽት በትምህርት ተቋማቱ ውስጥ እና በአቅራቢያው ባሉ የገንዘብ መክፈያ ማሽኖች (ኤቲኤም) አካባቢ ረዣዥም ሰልፎችን ሠርተው ጥሬ ገንዘብ ወጪ ሲያደርጉ እንደነበረ ተማሪዎች ለቢቢሲ አማርኛ ዝግጅት ክፍል ተናግረዋል። እስካሁን ያልመለሱ ተማሪዎችም ገንዘቡን እንዲመልሱ ጠይቀዋል። ይህንንም ተከትሎ በባንክ ሂሳባቸው በቂ ገንዘብ ሳይኖራቸው በርከት ያለ የገንዘብ ዝውውር ፈጽመዋል የተባሉት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሆናቸው ተሰምቷል። ፕሬዚዳንቱ አቶ አቤ እንደተናገሩት ተማሪዎቹ የእራሳቸው ባልሆነው የገንዘብ ዝውውር ውስጥ የገቡት ባንኩ የሳይበር ጥቃት አጋጥሞት እንደሆነ እና ሊደረስብን አይችልም በሚል የተሳሳተ ግምት ነው ብለዋል።

ይህን ጉዳይ አስመልክቶም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቢ ሳኖ በዚህ ድርጊት ላይ የተሳተፉት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሆናቸውን ገልጸዋል። ንግድ ባንክም የብዙዎቹን ተማሪዎች ስም ይፋ አድርጓል። ለመሆኑ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በዚህ አይነቱ ሕገ ወጥ ድርጊት እንዴት ሊሳተፉ ቻሉ? የሀገርና የሕዝብ ንብረት ሲዘረፍ ዋና ተዋናይ ሆነው የተገኙበት ገፊ ምክንያትስ ምንድን ነው? የሚሉና መሰል ጥያቄዎች በብዙዎች ዘንድ ሲመላለስ ሰንብቷል።

የተማሪዎቹን ሕገወጥ ድርጊት የትምህርት ሥርዓቱን ውድቀት ፍንትው አድርጎ ያሳየ ነው የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የዘለቀው የትምህርት ፖሊሲ ለሀገሪቱ የትምህርት ጥራት መውደቅ በዋነኛ ተጠያቂ ሆኖ ሲተች ቆይቷል። በተማሪዎች ብቃት እንዲሁም በአንዳንድ ቦታም በመምህራን የማስተማር አቅም ላይ ሳይቀር ያስከተለው አሉታዊ ተጽዕኖ ዛሬ በየደረጃው እየታየ መሆኑን በመረጃ የሚሞግቱ አሉ።

በሌላ በኩል የብሔራዊ ፈተና ስርቆቶች የአደባባይ ጉዳይ ከሆኑ የሰነበተ እንደመሆኑ ድርጊቱ ከማኅበረሰብ ሞራል ይዞታ ጋር ያያይዛሉ። በዚህ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ የሚወጣው ተማሪ ምን ያህል ብቃት ያለው እና ኃላፊነት የሚሰማው በሥነምግባርም የታነጸ ነው የሚለውን አጠያያቂ አድርጎታል።

ጎበዝ ተማሪዎች እንዳሉ ሆነው አብዛኛው ተማሪ ግን በፈተና ስርቆት ጭምር የሚጠረጠር ነው። ስለዚህም ፈተና በመስረቅና በመኮረጅ የሚታማው ተማሪ ብር ሲያገኝ ወደ ዘረፋ መግባቱ የሚያስገርም አይደለም የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ‹መማር ያስከብራል፤ አገርን ያኮራል› በሚል ለትምህርት ከፍተኛ ቦታ ለሚሰጠው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተማሪዎቹ ድርጊት አንገት የሚያስደፋ ነው።

አሁን ያሉት ተማሪዎች ያለፉት ሃያ ዓመታት የተበላሸ ሥርዓተ ትምህርት ውጤት ናቸው። ከእነዚህ መሐል ጥቂት የሚባሉ (በሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና እንደታየውም ከ3 በመቶ ያልበለጡ) ችግሩን ተሻግረው ለሀገርና ለወገን የሚጠቅሙ ዜጎች የሚሆኑ ታይተዋል። ብዙኃኑ ግን አሁንም በቂ ክትልልና ድጋፍ የሚሻ ነው። አልፎ ተርፎም እንደሰሞኑ አይነት ሕገ ወጥ ድርጊት ሲታይ ወቀሳ ጭምር ከማኅበረሰቡ ሊሰማ ይገባል። የራሳቸው ያልሆነን ገንዘብ ከባንክ የሰረቁና ለመስረቅም የሚሞከሩ ተማሪዎች ሊወቀሱ ይገባል።

ይህ ሳይሆን ሲቀር ግን ዜጎች ለሀገር ሸክም ይሆናሉ። የተሠራን የሚያጠፋና የሚያወድም ትውልድም ይፈጠራል። ከወቀሳው ጎን ለጎን ግን ለዚህ ታዲያ ቁልፍ መሠረቱ የትምህርት ሥርዓቱ መሆኑን መተማመን ይገባል። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የፈጸሙት የገንዘብ ስርቆትም የየትምህርት ሥርዓቱ ምን ዓይነት ተማሪዎችን እያፈራ እንዳለ አመላካች ነው።

ዩኒቨርስቲዎች የዕውቀት ማዕከሎች፤ የክርክርና የውይይት መድረኮች ናቸው። ኢሞራላዊ ድርጊቶች የሚወገዙበት ለሀገርና ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩባቸው ማማዎች ናቸው። አልፎ ተርፎም የሀገር ወደ ኋላ መቅረትና የሕዝብ ብሶትና ግፍ ይበቃል በሚል ሕይወታቸውን ጭምር የገበሩ ምሑራን የፈለቁባቸው አውድማዎች ናቸው። በተገኘው አጋጣሚም እውቀትን ከብዕርና ወረቀት ጋር በማገናኘት ኢ-ሞራላዊ ድርጊቶችን ሲያወግዙና ሲተቹ የቆዩ በርካታ ምሑራንን ያፈሩ የዕውቀት በሮች ናቸው።

የተማሩ ሰዎች በየትኛውም ጊዜና ቦታ የሰዎች ነፃነት ሲገፈፍና ፍትሕ ሲዛባ በይፋ በመናገርና በመፃፍ ተቃውሟቸውን ይገልፃሉ፤ ይሟገታሉ። ነፃነትና እኩልነት ሲረጋገጥም ድጋፍና ደስታቸውን በይፋ ይገልፃሉ። እነዚህ የነፃነትን ጣዕም የሚያውቁ በሁሉም ጊዜና ቦታ ለሰው ልጆች ነፃነትና እኩልነት ይሟገታሉ፤ ድንቁርናና ጭቆናን ፊት-ለፊት ይጋፈጣሉ፤ ለመላው የሰው ልጆች ነፃነትም መሟገት ይጀምራሉ።

በአጠቃላይ “ምሑራን” ወይም የተማረ ሰው ማለት ሃሳብና አስተያየታቸውን በአደባባይ በመግለፅ የሕዝብን ጥያቄ የሚያንፀባርቁ እንዲሁም ኋላ-ቀር አመለካከትና ግትር አቋምን በይፋ የሚሞግቱ አካላት ናቸው። በተጨማሪ የትምህርት ዋና ተግባር መሆን ያለበት አንድን ሰው እንዴት በትኩረት እና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ማሰብ እንዲችል ማድረግ እንደሆነ አጠቃላይ የትምህርት ሥርዓት ሂደት ያስረዳናል። አንድን ድርጊት ከመፈጸም በፊት ይህ ጉዳይ ጥሩ ነው ወይስ መጥፎ ፤ ሀገርን ይጎዳል ወይስ ይጠቅማል ብሎ በምክንያታዊነት ማሰብ የአንድ ምሑር የእውቀት መጀመሪያ ይመስለኛል።

ከራስ በፊት ለሀገርና ለወገን መቆርቀር፤ ለእውነት መቆም፤ በጅምላ ከማሰብ በፊት በግል ቆም ብሎ ማሰላሰልና ሞራላዊና ኢ-ሞራላዊ ድርጊቶችን መገንዘብ በትምህርቱ ዓለም ያለ ሁሉ የሚገነዘበውና የሚተገብረው ነው። ዛሬ ግን ይህ ሁኔታ እየኮሰመነ መጥቶ ይባስ ብሎም የሀገርና የሕዝብ ሃብትን በሌሊት መዘረፉን ሰምተናል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ‹‹ተማሪዎቹ የእራሳቸው ባልሆነው የገንዘብ ዝውውር ውስጥ የገቡት ባንኩ የሳይበር ጥቃት አጋጥሞት እንደሆነ እና ሊደረስብን አይችልም በሚል የተሳሳተ ግምት ነው›› በሚል የገለጹት ተማሪዎቹ ለሕሊናቸው ያላቸውን ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ነው።

‹‹ሰው አየኝ አላየኝ፤ ተደረሰብኝ አልተደረሰብኝ›› ብሎ ኢሞራላዊ ድርጊት ማድረግ ከአንድ የዩኒቨርስቲ ተማሪ የሚጠበቅ አይደለም። ሆኖም ይህንን ድርጊት ሲያወግዙ የነበሩና በምንም አይነት መልኩ በዘረፋው ውስጥ ያልተሳተፉ በርካታ ተማሪዎች መኖራቸውንም ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባ ግን ልብ ሊባል ይገባል። የሆነ ሆኖ ግን በዚህ ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ግን የብዙኃኑን ተማሪ ስም ማሰነሳቱ አልቀረም።

በአጠቃላይ ግን ባለፉት አሥርት ዓመታት የትምህርት ሥርዓቱና ፖለሲው፣ ከመምህራን አሠለጣጠንና ስምሪት፣ ከነበረው የምዘና ሥርዓት፣ ከመዋዕለ ሕጻናት ጀምሮ ተማሪዎቹ ያለፉበት የትምህርት ሥርዓትና ሂደቱ በችግሮች የተሞላ መሆኑ በሥነምግባርም ሆነ በብቃት ተወዳዳሪ የሆኑ ምሑራንን ማፍራት እንዳይቻል አድርጓል። ሰሞኑን ከንግድ ባንክ ጋር የተያያዙ ችግሮችም ይሁኑ የፈተና ስርቆት የመሳሰሉ ኢ-ሞራላዊ ድርጊቶች የዛሬ ስብራት ሳይሆኑ ለዘመናት የቆዩና የከረሙ ችግሮች ናቸውና ዘለቄታዊ መፍትሔ የሚያሻው ነው።

የተማሪዎቹ ጥፋት እንዳለ ሆኖ ከዚህም አልፎ የትምህርት ሥርዓቱ ያስከተለው ጦስ መሆኑን አምኖ ከመቀበል ባሻገር የማኅበረሰቡን የሞራል እሴቶች መሸርሸርንም ያሳየ ክስተት ነው። አለመዋሸት፤ አለመስረቅ፤ ታላቅን ማክበር፤ ለታናሽ መታዘዝ፤ ሕዝብን መውደድ፤ ሀገርን ማፈቅር፤ የሰውን ገንዘብ አለመንካት፤ ወንድማማችነትና አንድነት የመሳሰሉት እሴቶች በሂደት እየተሸረሸሩ መምጣትና በምትካቸውም በአቋራጭ መበልጸግ፤ የራስ ያልሆነን መመኘት፤ መለያየት፤ መጠላትና መቆራቆዝ እና የመሳሰሉት ስፍራውን መቆጣጠራቸው እንደ ሀገር አዘቅት ውስጥ እየከተተን መሆኑን የሚያመላክቱ በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል።

ከሁለት ዓመታት በፊት ዩኒቨርስቲዎች የትምህርትና የምርምር ተቋማት ከመሆን ይልቅ የተማሪዎች እሬሳ በገፍ የሚወጣባቸው የሁከትና የብጥብጥ ማዕከላት ሆነው እንደነበር የሚታወስ ነው። በወቅቱም ለብዙዎቻችን ጥያቄ ሆኖ የነበረው የዕውቀትና የምርምር ማዕከላት እንደሆኑና የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች ማፍሪያ የሆኑት ተቋማት እንዴት በዚህ መልኩ ሰዎች ወደሚገዳደሉባቸው የጦር አውድማነት ሊቀየሩ ቻሉ የሚለው ነበር።

ብዕር መጨበጥ የሚገባው እጅ ስለትና የጦር መሣሪያ አንግቦ የወጣቶችን ነፍስ ሲነጥቅ መመልከት በእጅጉ ስሜት የሚነካ ነበር። ይህ እንግዲህ ሊሆን የቻለው ተማሪዎቹ ከየመጡበት አካካቢ በወረሱት የጥላቻ አስተሳሰብ የተነሳ እንደሚሆን መገመት አይከብድም። እንደማኅበረሰብ የገባንበት የጥላቻና የመለያየት ድባብ ተማሪዎቻችንንም መርዞ እርስ በእርሳቸው የሚገዳደሉ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። የሚገዳደሉ አካላትን መገሰጽና ወደ ትክክለኛው መስመር መምራት የሚገባቸው የትምህርቱ ተዋናዮች እራሳቸው የለየላቸው ነውጠኞች ሆነው ሲገኙ በወቅቱ ብዙዎቻችንን አስደንግጧል።

እንግዲህ ሰሞኑን በንግድ ባንክ ላይ የተፈጸመውም ኢ-ሞራላዊ ድርጊት ከዚሁ የሥነምግባር መውረድ እና እሴት መላላት ጋር የተያያዘ ነው። እንደማኅበረሰብ እሴቶች ሲላሉ የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎችም ከዚሁ የላላ ዕሴት ሊያመልጡ የሚችሉበት አጋጣሚ አይኖርም።

እንደ ሀገር እነዚህን የተዳከሙ እሴቶቻችንን ለመመለስ ጥረት ካላደረግን በሁሉም ዘርፍ የሚጠብቀን ውድቀት ነው። ሙስና፤ ብልሹ አሠራር፤ ተገልጋይ ማጉላላት፤ ማመናጨቅ፤ አርፍዶ መግባትና በሥራ ሰዓት ከቢሮ ውጭ መገኘትና የመሳሰሉት የእሴቶች መሸርሸር የፈጠረው ክፍተት ነው። በእነዚህ ጉድለቶች ውስጥ ያለፉ ተማሪዎችም የዕዳው ተሸካሚ መሆናቸው እሙን ቢሆንም ያሉበት ደረጃ ግን ይህንን ለማድረግ የሚፈቅድላቸው አይደለም።

የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ እንደሚባለው ነገ ተመርቀው የሥራ ዕድል የሚያገኙበትን ተቋም አብረው ሲያወድሙ ለተመለከተ ስለነገዋ ኢትዮጵያ መጨነቁ አይቀርም። ስለኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፋንታ ማሰቡ የግድ ነው።

ስለሆነም የተዳከሙትን ማኅበራዊ ዕሴቶቻችንን ማጠናከር የትምህርት ሥርዓቱን ማዘመንና ወጣቱ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት አሁን እያጋጠሙ ካሉን ችግሮች ለማምለጥ ያስችለናል። በተለይም ደግሞ ትምህርት የሁሉም ነገር ቁልፍ እንደመሆኑ መጠን ጥራት ያለው ትምህርት ማዳረስ በክህሎትም ሆነ በሥነ ምግባር ብቁ የሆነ ዜጋን ለማፍራት ያስችላል።

አሊ ሴሮ

አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2016 ዓ.ም

Recommended For You