ነገሮቻችን በሙሉ በትናንት ላይ የሚያተኩሩ ናቸው። ትናንትን ማሞገስ ወይም መውቀስ፤ ትላንትን የእኛነታችን መገለጫ አድርጎ መውሰድና ዛሬን ሙሉ ለሙሉ መዘንጋት የእኛ የኢትዮጵያውያን መገለጫ ሆኗል ብል ማጋነን አይሆንም፡፡
ትናንትን ማሰብ፤ ማስታወስና መመርመር ጥሩ ነው። ነገር ግን የትላንት ትኩረታችን ዛሬንና ትላንትን መጉዳት የለበትም። ትላንት ዛሬንና ነገን የሚጎዳ ከሆነ ትላንትን መተው ይሻላል። በትላንት ላይ የምንታጠርና ዛሬንና ነገን የምንጎዳ ከሆነ ትላንትን ከነጣጣው ለትላንት መተው ይሻላል፡፡
የትናንት ፍቅር ከግለሰብ እስከ ማኅበረሰብና አልፎ ተርፎም እስከ ሀገር ድረስ የዘለቀ ደዌ ይመስለኛል። ክብርት ፕሬዚደንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በ2016 የሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ላይ ያስተላለፉትም መልዕክት እኛ ኢትዮጵያውያን ዛሬን ትተን በትናንት ላይ ሙጥኝ ማለታችንን የሚያሳይ ነው፡፡
ፕሬዚደንቷ እንደተናገሩትም የሀገራችንን የዘመናት ታሪክ ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከት፤ የተለያዩ ገጽታዎችን እናስተውላለን። በአንድነት ብዙ ችግሮችን ተሻግረን ህልውናችንን አስጠብቀናል። ተከባብረንና ተሳስበን በአብሮነት ዘመናትን ተሻግረናል። በኅብረት ቆመን ተባብረን ሀገራችንን ለመውረር እና ሕዝባችንን ለማንበርከክ የተንቀሳቀሱ ጠላቶችን አሳፍረናል። የታላላቅ ሥልጣኔዎች መገለጫ የሆኑ ትእምርትን አንፀናል። ለዓለም ሕዝብ ጥበብ፣ ፍልስፍናን፣ ሕግን፣ የእህል ዘሮችን፣ ተቋማትን፣ አበርክተናል። የአልገዛም ባይነት ምሳሌዎች በመሆን ጥቁር ሕዝቦች ከጫፍ እስከ ጫፍ ለነፃነታቸው እንዲንቀሳቀሱ የአርበኝነት መንፈስ ፈጥረናል።
በሌላ በኩል ደግሞ ሁላችንንም ሊያግባባ የሚችል ሀገራዊ ትእምርት መፍጠር አቅቶናል፤ ሁላችንም ሊያሰባስብ የሚችል ትርክት መገንባት ተስኖናል፤ በአብዛኞቻችን ዘንድ ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት ማጽናት አቅቶናል፤ እርስ በእርስ ተከፋፍለን፤ ልዩነቶችንም ማቻቻል አቅቶን፤ ወደ እርስ በእርስ ግጭትና ጦርነት በመግባት እንደ ሀገር የማይተካ ዋጋ ከፍለናል አሁንም እየከፈልን እንገኛለን። ሀገራዊ ጸጋዎቻችንን ባለመጠቀም በድህነት ማቅቀናል።
በዚህ የተነሣ ባለ ሁለት መልኮች ሆነናል። አንዱ ያለንን ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊ እና መልክአ ምድራዊ ዕድል የሚያሳየው መልካችን ነው። ሌላው ይሄን ከመጠቀም ይልቅ ራሳችንን በሚያቀጭጭ መንገድ የተጋጨንበት፣ የተከፋፈልንበትና ራሳችንን በራሳችን ያወደምንበት መልክ ነው። በመሆኑም ጥንካሬያችንና መልካም ገጽታችንን የሚያበላሹ፤ የታደልነውን ጸጋ በአግባቡ እንዳንጠቀም የሚያባክኑ፤ ትውልድ የሚያመክኑ፤ የተቃረኑ ገጽታዎቻችንን ማረም አለብን። ስብራቶቻችንን በመጠገን፤ ልዩነቶቻችንን በማጥበብ ሀገራችንን በማይናወጥ መሠረት ላይ ለማቆም በትጋት መሥራት ይጠበቅብናል።
ይህንን ለማድረግም አሁን ቆም ብለን የመጣንበትን መንገድ መገምገም ይገባናል። ያተረፍነውንና ያጎደልነውን ማስላት አለብን። ያተረፍንበትን አብልጠን በመያዝ፣ ያላዋጣንን ደግሞ በሌላ መንገድ በመተካት፣ በተለወጠ ሃሳብና በተለወጠ ልቦና ልንነሣ ይገባል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ በዚህ ትውልድ አዲስ የለውጥ ፋና ተለኩሷል። አዲስ የሁለንተናዊ ብልጽግና ምዕራፍ ተከፍቷል። ይህ የለውጥ ምዕራፍ የተወሰኑ ግለሰቦች፣ የጥቂት ቡድኖች ወይም የሆነ አካባቢ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን ምዕራፍ ነው። ስለዚህም የጎደለውን እየሞላን፤ ያነሰውን እየጨመርን፣ ያልተስማማንበትን እያቆየን፣ በተስማማንበት እየሠራን፤ በልዩነቶች ላይ ቆመን ሳንጋጭ፤ በተግባባንበት አብረን እየተጓዝን፤ ባልተግባባንበት ወሳኝ ሀገራዊ ጉዳይ ሲኖር ምልዐተ ሕዝቡ በነፃነት ተወያይቶ እንዲወስንበትና የሕዝብን ድምጽ እያከበርን በመሄድ ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገር ልናስረክብ ይገባል።
ያደጉ የምንላቸው ሀገራት ዛሬ ላይ የደረሱት ልዩነቶች ስለሌሏቸው አይደለም። ልዩነቶቻቸውን በማቻቻል፤ ልዩነቶቻቸውን ከግጭት በመለስ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ስለቻሉ ነው። ልዩነትም አንድነትም ተፈጥሯዊ ነው። የሰው ልጅ የመልክ፣ የእምነት፣ የባህል፣ የቋንቋ፣ የመኖሪያ አካባቢ፣ የአስተሳሰብ ልዩነት አለው። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ የሚያደርጉት የሰውነት ጉዳዮችም አሉ። ወሳኙ ነገር ልዩነትን እንደ ጌጥ አንድነትን እንደ ማስተሳሰሪያ ኃይልና አቅም መጠቀሙ ነው።
ትናንት ለነገ ዕንቅፋት መሆን የለበትም። ትምህርት እንጂ። የትናንት ታሪክ የአብሮነት መገንቢያ እንጂ የልዩነት መነሻ እንዳይሆን መሥራት አለብን። እየተደማመጥን፤ እየተመካከርን፤ ለሃሳብና ለውይይት በራችንን ክፍት እያደረግን እንጓዝ። ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን እናጠንክር፤ ለሀገራችን መፃኢ ዘመን በጋራ እንትጋ። ከትናንት ይልቅ ጉልበታችንንና ጊዜያችንን በነገ ላይ እናውል። ይህ ነው የዚህ ትውልድ ትልቁ ኃላፊነት ሲሉ ሃሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡
እውነት ነው እኛ ኢትዮጵያውያን ልዩነት በእኛ የተጀመረ ይመስል ከግዙፍ አንድታችን ይልቅ ጥቃቅን ልዩነቶቻችን ላይ እናተኩራለን። ልዩነታችንንም ደርዝ ለመስጠት ዛሬን ትተን ትናንት ላይ እንሻገራለን። በምንቀይረው ዛሬና ነገ ላይ ማተኮር ትተን በማንቀይረው ትናንት ላይ ጊዜ እንፈጃለን፡፡
የኢትዮጵያን ትናንት ስንመለከተው ደግሞ የፖለቲካ ቁርሾ የበዛበት፤ በረባ ባልረባው ሰዎች የሚጠፋፉበት፤ ከንግግርና ውይይት ይልቅ ነፍጥ ማንሳት የሚመረጥበት፤ ‹‹እኛ›› እና ‹‹እነሱ›› በሚል ኅላቀርና በታኝ ትርክት ሀገር ስትማቅቅ የኖረችበት ነው። ይህ መጥፎ አካሄድ ደግሞ ዛሬን ጭምር ተጭኖት ይገኛል። የዛሬ ግጭትና አለመግባባት ብሎም ጥርጣሬና አለመተማመን ትናንት የተፈጠረ ነው። በአጠቃላይ የሀገራችን ፖለቲካ ጥንስሱ የተጀመረው ትላንትና ነው ማለት ይቻላል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ጥያቄ በይፋ ለውይይት ከቀረበ ሃምሳ ዓመታት ቢሞላውም ዛሬም የብሄር ጥያቄ ፋሽን ሆኖ ሁሉም ‹‹ብሄሬ ተነካ ››በሚል ፈሊጥ ነፍጥ ሲያነሳ ይታያል። የብሄር ጥያቄ መነሳት ከጀመረ ጀምሮ ሁነኛ መፍትሄ ሳያሠጥ በመቆየቱ አንዳንድ ጊዜም ከሀገሪቱ አቅም በላይ የሆኑ ጥያቄዎችን በብሄር ሽፋን በመጠየቅ ብጥብጥና ሁከት የሚጠምቁ ፖለቲከኛ ነን ባዮች በሚያስነሱት ወጀብ በኢትዮጵያ ምድር መከራ ወርዷል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ አልቀዋል።
ኢትዮጵያን ሁሉንም በእኩልነት የምታስተናግድ አገር ለማድረግ በጋራ መሥራት እየተቻለ፣ መለስተኛ ቅራኔዎችን ከመጠን በላይ በመለጠጥ በጠላትነት መተያየት ቀጥሏል። በኢትዮጵያ ምድር ኅብረ ብሔራዊ ሥርዓት መገንባት እየተቻለ፣ ዛሬም ብሄርንና ኢትዮጵያዊነትን ጽንፍ ለጽንፍ በመጎተት አሰልቺ ንትርክ ውስጥ እንገኛለን። መቋጫው የት እንደሆነም ግባ ያጋባል፡፡
ኢትዮጵያ ከፊቷ የተጋረጡ በርካታ ችግሮች ያሉባት አገር ናት። የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ ለመነጋገርና ለመደማመጥ ጊዜ መስጠት አለባቸው። በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ድርቅና የምግብ ችግር አለ። የኑሮ ውድነቱ ፈተና ነው። የሥራ አጥነቱ መጠን በፍጥነት እያሻቀበ ነው። ከትውልድ ወደ ትውልድ ሳይከፈል ቆየና እየተንከባለለ የመጣ የውጭ የዕዳ ጫና አለ። ጥራት ያለው የትምህርትና የጤና አገልግሎት ተደራሽነት በጣም ዝቅተኛ ነው። በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በተፈጥሮ ሀብቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው። በገጠርም ሆነ በከተማ የሚኖሩ በርካታ ሚሊዮኖች ከድህነት ወለል በታች ይኖራሉ፡፡
እኛ ግን እነዚህን ተጨባጭ ችግሮች ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ በትላንት ታሪክ ውስት ተዘፍቀን በችግር አዙሪት ውስጥ መኖርን የመረጥን እንመስላለን። መስራት እንኳን ቢያቅተን የሚሰሩ ሰዎችን የምናበረታታ ስንቱዎቻችን ነን?
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዋስትና ያለው ሰላምና ልማት ያስፈልገዋል። ለዚህም ሲባል ሁሉን አካታች የሆነ ሰላማዊ ንግግርና ድርድር ለማድረግ ሀገር አቀፍ ምክክር ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ያለው። ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት ቆዩ ችግሮቻችንን በማስወገድ የወደፊቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት ዕድል ይሰጠናል። በተለይም ትናንት ላይ ተቸንክረው ፖለቲካን በሴራ እና በተንኮል እየጠነሰሱ መኖር ለሚሹ ወገኞች አካሄዱ ላይዋጥላቸው ይችላል። ሆኖም ሀገር ወዳድ ለሆንን ዜጎች ግን ከምክክርና ውይይት ውጪ አማራጭ የለንም፡፡
ሸፍጠኝነት፣ ሴረኝነት፣ ቂመኝነት፣ ጉልበተኝነትና ወገንተኝነት ተወግደው የሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ የጋራ መግባባት መፈጠር ይኖርብናል። ብሔርን፣ እምነትን፣ የፖለቲካ አቋምን፣ ጥቅምንና ሌሎች ተገቢ ያልሆኑ ሰበቦችን በመታከክ ሕዝብና አገርን ሰላም መንሳት መቆም አለበት።
ኢትዮጵያ በረዥም ዘመናት የታሪክ ጉዞዋ ጥሩም ሆነ መጥፎ ታሪኮችን አሳልፋለች። የነጻነትና የአይበገሬነት ተምሳሌት የመሆኗን ያህል የጦርነት፤ የርሃብ፤ እርዛት፤ የመፈናቀልና የጥላቻ ትርክትን የያዙ ታሪኮችም ባለቤት ነች፡፡
አብዛኛውን የኢትዮጵያን የውስጥ ታሪክ መለስ ብሎ ላየው የውስጥ አለመግባባት፤ ግጭትና ጦርነት የበዛበት ነው። በጋራ ታሪኮቻችን ላይ መግባባት ካለመቻላችንም በላይ የግጭትና የጦርነት መንስኤ እስከ መሆን ደርሷል።
ይህ ደግሞ ሀገሪቱን በማያባራ ግጭትና ጦርነት ውስጥ ከቷል፤ ለበርካታ ሰዋዊና ቁሳዊ ኪሳራም ዳርጓል። ለሀገሪቱ ዕድገትም ፈተና ሆኗል። በአንድ ሀገር ላይ ቆመን የጋራ ትርክት መገንባት አቅቶናል። ባለፈው ታሪካችንም መግባባት ካለማቻላችንም በላይ መጪውንም ለመተንበይ አዳጋች ሆኖብናል፡፡
ባልኖርንበት ትናንት በምናደርገው መጋጋጥም የብዙህ ንጹሃን ዜጎች ሕይወት እየተቀጠፈ ነው። በየጫካና በየዱሩም ነፍጥ በሚያነሱ ቡድኖች ምክንያትም አርሶ አደሩ ተረጋግቶ የእርሻ ስራውን እንዳያከናውን፤ ገበሬው ነግዶ እንዳያተርፍ፤ ተማሪው በዕውቀት ገበታ ላይ እንዳይገኝ፤ ሰዎች ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ተንቀሳቅሰው እንዳይሰሩ ተደርገዋል። አልፎ ተርፎም ነፍጥ ባነሱ ቡድኖች አማካኝነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ ተሰደዋል፤ አካል ጉዳተኛ ሆነዋል፤ ሕይወታቸውንም አጥተዋል፡፡
ይህ የታሪካችን ጠባሳ ግን አንድ ቦታ መቆም አለበት። የግጭት፤ የጦርነት፤ ያለመግባባት ታሪካችን ተዘግቶ በጋራ ታሪኮቻችን ላይ የምንግባባ፤ ለጋራ ሀገራችን የምንተጋ፤ ለልጆቻችንም የበለጸገች ኢትጵያን ለማውረስ የጋራ ዕሳቤ የጨበጥን አዲስ ትውልድ መሆን ይገባናል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከሚታወቅባቸው አኩሪ ባህሪያቶቹ መካከል የሚጠቀሱት፣ ሕግ አክባሪነቱና ሰላም ወዳድነቱ ናቸው። ከሕግ አክባሪነቱና ከሰላም ወዳድነቱ ጋር ደግሞ ለዘመናት በጋራ የገነባቸው ትውልድ ተሻጋሪ ማኅበራዊ እሴቶቹ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጣቸው ናቸው። እርስ በርስ በሚያደርጋቸው የዕለት ተዕለት መስተጋብሮቹ ተዋዶና ተከባብሮ መኖር ብቻ ሳይሆን፣ የብሔርና የሃይማኖት ልዩነቶች ሳይገድቡት በጋብቻ ጭምር የተሳሰረ ነው፡፡
ትናንት ያለፈ ታሪክ ነው። ትናንት አስደሳችም፤ አሳዛኝም ሊሆን ይችላል። በየትኛውም ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ አስደሳች ትናንት የለም። አሳዛኝም እንዲሁ። ትናንት የአስደሳች እና የአሳዛኝ ገጠመኞች ድምር ነው። ገጠመኞች ደግሞ በጊዜ ሂደት ታሪክ ይሆናሉ። የእኛም የኢትዮጵያውያን ታሪክ ከዚህ ነባራዊ ሀቅ የተለየ አይሆንም። ደጉንም መጥፎውንም እንደ ሀገር አሳልፈናል። ክፉን ብቻ እየመረጡ ለፖለቲካ መጠቀሚያ ማድረግ የዘመናችን ብሂል ከሆነ ሰነባብቷል፡፡
ለዘመናት አብሮ የኖረውን ሕዝብ ጥቃቅን ልዩነቶችን እየፈለጉና አልፎ ተርፎም ከአሁን አብሮነቱ ይልቅ ቀድሞ የተፈጠሩ እንከኖችን በማጉላት እርስ በእራሱ እንዲተላለቅ የሚሹ አካላት በየስርቻው አሉ። ‹‹ብሄርህ ተነካ፤ ኃይማኖትህ ተደፈረ›› በሚል ሰበብ የራሳቸውን የስልጣን ጥም ለማርካት የሚውተረተሩ የትየለሌ ናቸው።
ኢትዮጵያ ከገባችበት የቀውስ አዙሪት ውስጥ እንድትወጣና ለሕዝብ ማሰብ ከተቻለ፣ ጦር ከመስበቅ ባሻገር ያለውን ሰላማዊ መንገድ መያዝ ዘመኑን የሚዋጅ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰለቸው ግጭት፣ ዕልቂትና ውድመት ነው። ለሕዝብና ለአገር እናስባለን የምትሉ ሰላም አውርዱ። ሕዝብና አገርን ሰላም ከመንሳት መቆጠብ ይገባል!
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን መጋቢት 5 ቀን 2016 ዓ.ም