የተፋሰስ ልማት-ለምርታማነት

የተፋሰስ ሥራ ከማኅበረሰብ አቀፍ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች አንዱ ሲሆን፤ በግብርና ምርት ሥርዓቶች ላይ ለሚተገበሩ የሥነ ምሕዳር ሂደቶች ውጤታማነት የሚኖረው አስተዋፅዖ የጎላ ነው። በኢትዮጵያ ከ1970ዎቹ አንስቶ የተፋሰስ ልማት ወይም የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች በስፋት በዘመቻ መልኩ ሲሠሩ ቢቆዩም፤ በተጠቃሚው እና አስፈጻሚው አካል ያለው መናበብ የላላ በመሆኑ የተደከመበትን ያህል ውጤታማ እንዳልነበር በዘርፉ የተጻፉ መዛግብት ያስረዳሉ።

በመሆኑም ችግሩን ለመቅረፍም የግብርና ሚኒስቴር ከክልሎች የግብርና ቢሮዎች ጋር በመቀናጀት የማልማት ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል። የግብርና ሚኒስቴር መረጃዎቸው እንደሚጠቁሙትም ማኅበረሰቡን በባለቤትነት ባሳተፈ መልኩ በተለያዩ ክልሎች ንዑስ ተፋሰሶችን ተግባራዊ ተደርጎ ውጤታማ መሆን ተችሏል። ለምሳሌ፣ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ወዲህ ለተፋሰስ ልማት ሥራዎች በተሰጠው ትኩረት ግድቡ በደለል እንዳይሞላ የዓባይ ምንጭን ጨምሮ ገባር ወንዞች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ላይ የማልማት ሥራ ተሠርቷል። በዚህ መልኩ የተከናወነው ሥራም የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ አድርጓል።

ይሁን እንጂ አብዛኛው ኢትዮጵያ ክፍል ደጋማ በመሆኑ ዛሬም ድረስ ለአፈር መከላት የተጋለጠ ነው። ከዚህ አኳያ ቀጣይ የተፋሰስ ልማት ሥራው ውጤታማ እንዲሆን ኅብረተሰቡን በተለይም አርሶ አደሩን የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎችን ጥቅም እንዲረዳ በማድረግ ልማቱን በባለቤትነት እንዲያከናውን ማድረግ ያስፈልጋል። የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ሲሠሩና ሲጠናከሩ ደኖች ያገግማሉ፣ የተራቆቱና እና የተጎራረዱ የወል መሬቶች ከመጠገናቸውም ባሻገር ምጮች እንዲጎለብቱ ያደርጋል፤ የሚለውንም አርሶ አደሩ በተግባር እንዲገልጠው ማገዝ ይገባል።

ለምሳሌ፣ የተፋሰስ ልማት (የአካባቢ ጥበቃ ሥራ) መከናወኑ አርሶ አደሮቹ ከልቅ ግጦሽ የተጠበቁ የወል መሬዎች ላይ መኖ በማልማት፣ ከብቶቻቸውንም አስረው በመመገብ ብዙ ጥቅሞች እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። በእርከንና መሰል የተፋሰስ ሥራዎችም ምርታማነትን ማሳደግ፣ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት የገበያ ሰብሎችን በማምረት አመጋገባቸውን ማሻሻል እንዲችሉና ምርታማነትን እንዲያሳድጉ የሚያደርግ ነው። በመሆኑም ይሄን የሥራውን ቱሩፋቶች አርሷደሩ በላቀ መልኩ እንዲያጣጥማቸው እድል መፍጠር ያስፈልጋል።

በተጨማሪም የወል መሬቶችን ከእንስሳት ንክኪ ነፃ በማድረግ እና ወጣቶችን በማደራጀት በመስጠት በአትክልትና ሌሎች ፍራፍሬ ልማት እንዲሠማሩ በማድረግ ውጤታማ እንዲሆኑ መሥራት ይገባል። ይሀ ሲሆን ለተፋሰስ ልማት ሥራው በተጨማሪ አቅም ይሆናል። ምርታማነትን በማሳደግም አሁን ላይ እየናረ የመጣውን የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ ለማረጋጋት ይጠቅማል።

በዚህ ረገድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከናወኑ ያሉ የተፋሰስ ልማት ሥራው ያስገኛቸው ጠቀሜታዎች በግልጽ እየታዩ ሲሆን፤ በቀጣይነትም በጥናትና ምርምር የተደገፈ ሥራን ማከናወን ይጠይቃል። ምክንያቱም በተፋሰስ ልማት ሥራው የተከናወኑ በርካታ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ያስገኙት ውጤትና ጥቅም በአርሶ አደሩ ሕይወት ውስጥ የሚገለፁት፤ ተጠቃሚነቱንም የሚያረጋግጡት ከዚህ በሰፋ መልኩ ሲተገበር ነው።

በተፋሰስ ልማቱ በየዓመቱ በአርሶ አደሩ የሚሠሩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች የአካባቢ መራቆትን ከመከላከል፣ የአፈር ለምነትን ከመጠበቅና ምርታማነትን ከማሳደግ እንዲሁም የአፈር እርጥበት ከመቀነስ እና ውሃ መጠንን ከማሳደግ አንፃር ያላቸውን ጠቀሜታ በተለያየ መንገድ ከመስማትና ከማየት ባለፈ በተግባርም ጭምር እየተረጋገጠ ነው።

የተፋሰስ ልማቱ የሚያስገኛቸው ጠቀሜታዎች ከዚህ የሰፋና ከበርካታ ጉዳዮች ጋር ጭምር ሊያያዝ የሚችል እንደሆነ የዘርፉ ምሑራን የሚገልጹት ሐቅ ነው። ለአብነትም፣ የዓለም አቀፉን የአየር ንብረት መዛባት ተከትሎ ሀገራት እያጋጠማቸው ያለውን ያልተጠበቀ የአየር ንብረት መዛባት ሙሉ በሙሉ ማስቆም እንኳ ባይቻል ተፅዕኖውን መቀነስ ከብዙ ጠቀሜታዎቹ መካከል የሚጠቀስ ነው።

የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን በስፋት ተግባራዊ ማድረግ፣ በውሃ አካላት ላይ የሚደርስን በደለል የመሞላት እድል ይቀንሳል። ኢትዮጵያም በዚህ ረገድ የሠራችው ሥራ የተለያዩ ሐይቆችና ግድቦቿን በደለል ከመሞላት እየታደገላት እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ። ለምሳሌ፣ የጎንደር የአፈር ምርምር ቤተ ሙከራ መረጃ እንደሚጠቁመው፤ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ወደ ጣና ሐይቅ ይገባ የነበረውን የአፈር ደለልና የጎጂ ንጥረ ነገር መጠን ከ50 በመቶ በላይ ቀንሶታል። ይህ የተረጋገጠውም ዩኒቨርሲቲው በተከታታይ ዓመታት ባካሄደው የምርምር ሥራ ነው።

በዚህ ጥናት እንደታየውም፤ በጎርፍ ታጥቦ ወደ ሐይቁ ይገባ የነበረውን ‹‹ፎስፈረስ›› የተሰኘውን ጎጂ ንጥረ ነገር በግማሽ መቀነስ የተቻለ ችሏል። ይሄ ፎስፈረስ ደግሞ የሐይቁን ብዝኃ ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥልና የዓሣ ሃብቱን ጨምሮ ሌሎች በሐይቁ ውስጥ የሚገኙ ጠቃሚ ዕፅዋትን በመጉዳት ዝርያቸው እንዲመናመን የሚያደርግ ነው። በመሆኑም ባለፉት ዓመታት የተሠሩት የተፋሰስና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች የሐይቁን ብዝኃ ሕይወት ከመሰል አደጋዎች መታደግ ማስቻሉን መረጃው ያሳያል።

ይህ ለአብነት ይጠቀስ እንጂ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ የግብርና እና ግብርና ነክ ተቋማትና ድርጅቶች የተፋሰስ ልማት ሥራዎችን በማከናወን ላይ ናቸው። ልማቱ ግቡን እንዲያሳካ በጥናት ተደግፎ ሊከናወን፤ የቅንጅት ሥራንም የሚጠይቅ በመሆኑ የሚመለከታቸው ተቋማትና ድርጅቶች በስፋት ሊሠሩበት ያስፈልጋል።

የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራው የአካባቢ መራቆትን ከመከላከል፣ የአፈር ለምነትን ከመጠበቅና ምርታማነትን ከማሳደግ በተጨማሪ የብዝኃ ሕይወትን ሕልውና ጠብቆ በማቆየት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር ነው። በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች አሁን ላይ በስፋት ተግባራዊ በመሆን ላይ በሚገኘው የተፋሰስ ልማት፤ በተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ከእርሻ ማሳዎችና ከተዳፋት መሬቶች በጎርፍ አማካኝነት በከፍተኛ መጠን ይባክን የነበረውን አፈርና ውሃ ማስቀረት መቻሉን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የተፋሰስ ልማት የግብርና ምርትና ምርታማነት ከማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ጎን ለጎን፤ የተስተካከለ ከባቢያዊ ሥነ ምሕዳር ከመፍጠር አኳያ ሰፊ ጠቀሜታ አለው። በመሆኑም በአንድ በኩል በሀገራችን የተፋሰስ ልማቱ ውጤታማ እንዲሆን አርሶ አደሩን በማንቃት የተፋሰስ ልማቱ ያስገኛቸው ጥቅሞች ጎልተው እንዲታዩ ማድረግ ይገባል። በሌላ በኩል፣ የአፈር ለምነትንና እርጥበትን በማሳደግ የግብርና ምርታማነትንና የመሬቱን የዕፅዋት ሽፋንን ማሳደግ የቀጣይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ይገባል።

ግርማ ሞገስ

አዲስ ዘመን መጋቢት 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You