‹‹ ኢትዮጵያ በእኔ የኑሮ ደረጃ ልክ አትታይም ቢርበኝም ቢጠማኝም ሀገሬ ናት››የመቶ አለቃ አይዳ አላሮ የአየር ወለድ ማሰልጠኛ የዲስፓቸር ባለሙያ

ወኔ ፣ ድፍረትና ለሐገር መቆምን ከአባት ከአያቶቿ እንደወረሰችው ትናገራለች። በአየር ወለድ ውስጥ ለ 37 ጊዜያት ከአውሮፕላን ላይ ዘላለች። በልጅነቷ ከተቀላቀለችው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ያገኘችው የሀገር ፍቅር ስሜትን የሚያላብስ ቁርጠኝነት በሙያው በጽናት ለ18 አመታት እንድትቆይበት አድርጓታል ። ጊዜዋን እና ህይወቷን የሰጠችለት ሙያዋ በአየር ወለድ ውስጥ በሁለቱም ጾታዎች ከአውሮፕላን ላይ ለ37 ጊዜያት የዘለለች ብቸኛዋ ሴት ሆና እንድትመዘገብ አድርጓታል ። የዛሬዋ የአዲስ ዘመን የሴቶች ቀን (ማርች 8 ) ልዩ እትም እንግዳችን የመቶ አለቃ አይዳ አላሮ ።

የመቶ አለቃ አይዳ ተወልዳ ያደገችው በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ አካባቢ ደንበል ህንጻ ጀርባ ልዩ ስሙ ‹‹ፍላሚንጎ›› በሚባለው ሰፈር ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷንም በነጻነት ብርሃን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምራለች። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በቦሌ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቃለችⵆ የዲፕሎማ ትምህርቷን ለመከታተል ደግሞ በቀድሞው ምስራቅ አጠቃላይ በአሁኑ ምስራቅ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ነበር ያቀናችው።

ወደ ውትድርናው ዓለም ስትገባ በእድሜ ልጅ እንደነበረች የምትናገረው መቶ አለቃ አይዳ በወቅቱ ስለ ውትድርና በቂ ግንዛቤ እንዳልነበራት ታስታውሳለች። ይሁን እንጂ ተወልዳ ባደገችበት “መሿለኪያ አካባቢ አራተኛ “ የሚባል የወታደሮች ካምፕ ነበርና በልጅነት እድሜዋ በወታደር ልብስ የሚንቀሳቀሱትን ስትመለከት ልዩ ስሜት ይፈጥርባት እንደነበር ትዝ ይላታል።

ደጋግማ እንደምትለው ወደ ሙያው ስትቀላቀል እምብዛም እውቀቱ አልነበራትም ።ይሁን እንጂ በርካቶች ወደ ውትድርና ከገቡ በኋላ የሀገር ፍቅሩ እና ቁርጠኝነቱ እንሚያይልባቸው ሁሉ እኔም “ሳልወጣ ቀርቻለሁ” ትላለች። ይህ እውነታም ለ18 አመታት በሙያው ውስጥ እንድትዘለቅ ማድረጉን ትናገራለች።

መቶ አለቃ አይዳ የውትድርና ስልጠናን እንደዚህ ትገልጸዋለች። “አንዲት እናት ልጅ እንደወለደች በመጀመሪያው ቀኗ ለልጇ ጥሩ ጥቅልል ጉርሻ አታጎርሰውም። ጡት ታጠባዋለች። ያንን ሂደት ሲያልፍ ደግሞ የላመ ነገር ይበላል ፤ ከዛም ልጁ አቅሙ ሲጠነክር እራሱ ወደ አጥንት መጋጡ ይሄዳል። ልክ እንደዚሁ እኛም በአንድ ጊዜ ወደ አጥንት መጋጡ ስራ ወይም ወደ ከባዱ ስልጠና አልሄድንም” ትላለችⵆ

በመጀመሪያ መሰረታዊ የእግረኛ ስልጠና ለስድስት ወራት በብር ሸለቆ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት፣ ሁርሶ እና ጦላይ ማሰልጠኛ ወስደዋል። የውትድርና ሙያ ሰዎች የራሳቸውን ባህል ፤ ወግ እና ስርአትን ይዘው የሚገናኙበት ከመሆኑ አንጻር ‹‹ትንሿ ኢትዮጵያ››ያለችው እዛ ውስጥ ነው። ሁሉም የራሱን ይሰጣል የሰውንም ይቀበላል። ውትድርና ውስጥ ሰው ያለውን ሲሰጥ ‹‹ያንተ ያንሳል›› እያለ አይደለም ሲቀበልም ‹‹የኔ ስለሚያንስ ነው›› አይልም። ውትድርና ሰዎች በደንብ የሚዋሃዱበት እና ኢትዮጵያን የሚያውቁበት ቦታ ነው።

አዲስ ወደ ውትድርና ሙያ የሚቀላቀል ሰው ያለው የባህል እና የቋንቋ መለያየት በጥቂቱ ሊፈትነው ይችላል። አንዳንድ ቃላት በአንዳንዱ ማህበረሰብ መደበኛ ሲሆን ያው ተመሳሳይ ቃል በሌላው ማህበረሰብ ዘንድ አጸያፊ ሊሆን ይችላል። በዚህም ሳይታሰብ አብሮን ከሚሰለጥነው ባለሙያ ጋር ሊያጋጭን ይችላል።

መሰረታዊ የውትድርና ስልጠና ተጠናቆ ወደ ኮማንዶ ስልጠና ሲገባ ፈታኝ የሆኑ ነገሮች ይኖሩታል። የአካላዊ እና ስነልቦናዊ ብስለትንም የሚጠይቅ ነው። መሰረታዊ የውትድርና እውቀቱን በመጀመሪያ ያገኘ ሰው ወደ ኮማንዶ ሲመጣ ከአካላዊ ጥንካሬ ጎን ለጎን የሚሰጠውን እያንዳንዱን ነገር ለመቀበል እና ለማድረግ ዝግጁ መሆን ይጠበቅበታል። ኢትዮጵያ ላይ እንደተወለደች ሴት ከአባቶቻችን የምንወርሰው ወኔ እና ድፍረት አለ ። ይህ ደግሞ ያጀግነናል። እኔም ያለኝ ድፍረት ከአባት ከአያቶቼ የወሰድኩት ነው ።

መቶ አለቃዋ እንደምትናገረው በአየር ወለድ ውስጥ ለ37 ጊዜያት ከጦር አውሮፕላን ላይ ዘላለች። እንዲህ በሆነ ግዜ በመጀመሪያው አምስት ዝላይ የ አንድ ክንፍ መለያ /ዊንግ / ይሰጣል። አንድ አየር ሀይል 30 ዝላይ ሲያስመዘግብ ደግሞ ዊንግ ላይ ኮከብ ይጨመርበታል። አየር ወለድ ላይ ሰዎች የዝላይ ቁጥር በጨመሩ ሰአት ፍርሃታቸውም ይጨምራል። ምክንያቱም ሰዎች ሲሰበሩ፤ ፓራሹት ሳይከፈት ሲቀር የማየት እድል ስለሚያጋጥም ፍርሃትን ያጭራልና።

ምንም የማያውቅ ሰው ‹‹ ወጥቼ ምን ይገጥመኝ ይሆን? ይላል እንጂ ወድቄ እሰበራለሁ ፓራሹቱም ላይከፈት ይችላል›› አይልም። ምክንያቱም አጋጣሚውን ስለማያውቀው። የአየር ወለድ ህግ ‹‹የዝላይ ቁጥር በጨመርክ ቁጥር ስጋቱ ይጨምራል ›› ይላል። አሁን ላይ “የአየር ወለድን የበፊት ክብር ለመመለስ ያማረ ትምህርት ቤት ተገንብቷል። እኔም ለሀገሬ የሰናፍጭ ቅንጣት የምታክል አስተዋጾ ማድረግ ከቻልኩና ስሟን ማስጠራት ከቻልኩ አደርገዋለሁ።” ትላለች።

“በዝላይ ህይወቴ ያን ያህል የከፋ አደጋ ደርሶብኝ አያውቅም ፤ በ33ተኛ ዝላይ ላይ ብቻ ትንሽ ወለምታ ተከስቶብኝ ነበር ፤ ይሁን እንጂ ከዛ በኋላም ሌሎች ዝላዮችን አድርጊያለሁ”ትላለች። የመጀመሪያውን የዝላይ ታሪኳን ስታስታውስም “ለመጀመሪያ ጊዜ በ1998 ዓም በአንቶኖቭ አውሮፕላን በፓራሹት ዲ 6 ዝላይ ስናደርግ አንድ ሰልጣኝ ተሰውቶ ነበር። አውሮፕላን ላይ ከተወጣ በኋላ ‹‹ወራጅ›› አለ ማለት አይቻልም፤ ሆዴን ቆረጠኝ አይቻልም። ምንም አይነት ሰበብ አይፈቀድም። ምናልባት በወቅቱ የነበረው ጓድ ስጋት ይኖርበት ይሆን እርግጠኛ አይደለሁም። ሰልጣኙ መሰዋቱን ያዩት የዝላይ አሰልጣኞች ወዲያው ፊታቸው ሲቀያየር አየሁ። ያን ጊዜ በጣም አስታውሰዋለሁ።”

የአየር ወለድ ከጠላት መሃል፤ ፊት፣ ወይም ኋላ የሚዘል እና ለወገኑ የሚደርስ ጦር ነው። አንድ ጦርነት ላይ አየር ወለድ ሲመጣ ድል ይጨምራል፤ አየር ወለድ ሲመጣ ታሪክን የሚቀይር እና ሀገርን የሚያስቀጥል ነው። አየር ወለድ ዝም ብሎ ለታይታ የሚዘል ብቻ አይደለም። እንደነ ብርጋዴል ጀነራል ተስፋዬ ሀብተማርያም ያሉ ሰዎችን የሚያፈራ ታላቅ ተቋም ነው። አየር ወለድ ‹‹ማርሽ ቀያሪ›› የሚባለውም ለዚሁ ነው።

አንድ የአየር ወለድ ከአውሮፕላን ከዘለለ በኋላ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን ይጓዛል። ትከሻው እስኪያብጥ ድረስ የሚሸከመው ሸክም አለ። ወገቡ እስኪጎብጥም ድረስ የሚይዘው ትጥቅ አለ። መሬት ላይ ከወረደ በኋላም ያለበትን የግጭት ህመም ተቋቁሞ፤ ፓራሹቱን ደብቆም ይሁን አቃጥሎ መድረስ ያለበት ቦታ ላይ መድረስ አለበት።

አየር ወለድ ከአውሮፕላን ላይ ሲጣል የሚጣለው የጠላት ወረዳ ላይ ነው። በዛ ውስጥ አለመብላት፤ መጠማት እና ብዙ ችግሮችን ተጋፍጦ የተላከበትን ሀገርን ከጠላት የመጠበቅ ተልዕኮ ማሳካት አለበት ። ይህም ዛሬ የምናያትን አንድ የሆነችዋን ኢትዮጵያ ቀና ለማድረግ የሚተጋ ባለሙያ ነው››

መቶ አለቃ አይዳ ትዳር አልመሰረተችም። ስለ ትዳር ያላትንም ሃሳብ እንዲህ ትገልጻለች። “ማግባት እና መውለድ ጥሩ ነገር ቢሆንም ሴቶች ወደ ትዳር ሲገቡ ብዙ ጊዜ እጅ ይሰጣሉ። ሰው የሚኖርበት አላማ ካለው ያንን መኖሩ ጥሩ ነው። ይህን ስንል ግን አግብተው ወልደው ሀገራቸውን ማስጠራት የቻሉ እንስቶች የሉም ማለት ግን አይደለም። ምሳሌ ብናነሳ እንደ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ እና ደራርቱ ቱሉ ያሉ ድንቅ የሆኑ አትሌቶቻችን ካገቡ እና ከወለዱ በኋላም ለሀገራቸው ወርቅ ማምጣት ችለዋል። ነገር ግን ወደ ህይወታችን የሚመጣው አካል ወደ አላማችን ከመግፋት ይልቅ የሚያስቀረን ሊሆን አይገባም። ሆኖም ማግባት እና መውለድ አያስፈልግም ግን አልልም ፈጣሪ ሲፈቅድ የሚሆን ነገር ነው።”

በኢትዮጵያ ውስጥ በቀድሞ ሰራዊት ለበርካታ ጊዜ ከአየር ላይ የዘለሉ ቢኖሩም አሁን ባለው እውነታ ግን አይዳ ለ37ተኛ ጊዜ በመዝለል በሁለቱም ጾታዎች በአንደኝነት ደረጃ ላይ ትገኛለች። የመቶ አለቃዋ ለሴቶች ያላትን ምክርም እንደዚህ ትለግሳለች ። “ አንድ ሰው ምድር ላይ ሲፈጠር ያለ ምክንያት አልተፈጠረም፤ የሚችለውን ጠጠር ለሀገሩ እንዲወረውር ነው ፤ ብዙ ጊዜ ባለንበት ሁኔታ ነገሮችን መለካት የለብንም። እኛ ያለንበት ሁኔታ ሊሆን ይችላል እንዳንሄድ የሚያደርገን። ለምሳሌ አግብተን ሊሆን ይችላል፤ ወልደንም ሊሆን ያችላል፤ ኤኮኖሚያዊ የሆኑ ችግሮች ሊኖሩብን ይችላሉ ፤ የስራ ሁኔታ ላይመቸን ይችላል፤ የማይመች ሁኔታ ውስጥም ልንሆን እንችላለን ነገር ግን ሰው ከስኬት ላይ የሚደርሰው በሚመች ሁኔታ ውስጥ ብቻ አልፎ በመሄድ አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።

ለምሳሌ ማዕበል ሲነሳ አንዳንድ ነገሮች መያዝ ያለባቸውን ስፍራ እንዲይዙ ያደርጋል። ምናልባትም በህይወታችን ውስጥ የሚፈጠሩ ከፍታና ዝቅታዎች የኛን ነገር የሚያስተካክሉ ሊሆኑ ይችላሉ። ሰዎች ፊታቸውን ጸጉራቸውን ጠብቀው ቢሮ ውስጥ መስራትን ሊወዱ ይችላሉ። አንዳንድ ነገሮች ምናልባትም የተፈቀዱት ለ10ሺ ሴቶች ሊሆን ይችላል።

አንዳንዶች ደግሞ በጦርነት ሜዳ ላይ ጀብድ እንዲሰሩ ፤ሌሎች ደግሞ ሲሚንቶ አቡክተው ግንባታ እንዲያሳምሩ ሊሆን ይችላል የተፈጠሩት ። ሁሉም ሰው የየራሱ መዳረሻ አለው። በሀገራችን እና በቤታችን ያልተስተካለ ነገር ካለ ያንን ለማስተካከል መስራት አለብን። የትኞቹንም ችግሮቻችን በሶስተኛ ወገን ብቻ የሚስተካከሉ ናቸው ብሎ መጠበቅም አያስፈልግም ።

ሴቶች በአድዋ ላይ የነበራቸው ተሳትፎ የሚዘነጋ ካለመሆኑም በላይ ድሉ እንዲመጣም የእቴጌ ጣይቱ ሚና የላቀ ነበር። እኔ ራሴን ከወንድ ጋር አላወዳድርም። ሴት ለወንድ ጥሩ አጋዥ መሆን ትችላለች ወንድም እንዲሁ ለሴት ጥሩ አጋዥ መሆን ይችላል በሚለው አምናለሁ። አይዳ ስለኢትዮጵያ ያላት ስሜት ለየት ይላል። ውድ ሀገሯን የምትገልጻትም እንዲህ በማለት ነው።

‹‹ኢትዮጵያ በኔ የኑሮ ደረጃ ልክ አትታይም። ቢርበኝም ሀገሬ ናት ቢጠማኝም በውጣ ውረዷ ውስጥም ሀገሬ ናት። ምክንያቱም መሄጃ የለኝም፤ እሷም ያለኔ ማንም የላትም ።እኔም ያለሷ ማንም የለኝም። ብዙ ሰው ሀገሩን እንደሚወድ ይናገራል። ነገር ግን ድርጊት ከቃል ይበልጣልና የንግግራችንን ያህል ተግባርም ሊታከልበት ይገባል ።ኢትዮጵያ የቃልኪዳን ሃገር ናት። ኢትዮጵያ አምላክ አላት። ነገር ግን ለእኛ ለህዝቦቿ ተሰጥታናለች። ህዝቦቿ ናቸው የሚሰሯት። አንዳንዴ ምንም ባለማለት ሃገርን ማገዝ ይቻላል ፤ የምንናገረው ነገር ጥፋት ከሆነ ሌላውን የሚሰብር ከሆነ ፤ መከባበርን የማያመጣ ካሆነ ዝም ማለት ያስፈልጋል።

በሀገር ላይ በፍቅር፣ በመተሳሳብ አንድ ሆኖ ስለመዝለቅና አሁን ያለውን ገጽታ አይዳ ከሌሎች አገራት ወቅታዊ እውነታ በማነጻጸር እንዲህ ትገልጸዋለች። ‹‹ሁላችንም ከሚያጣሉን ታሪኮቻችን ይልቅ የሚያስማሙን ይበልጣሉና በፊት እንደልጅነታችን ተጣልተናል ብለን ተመልሰን እንደምንገናኝ ሁሉ አሁንም እንደዛ ማድረግ ይገባናል። ሶርያ ምንም አትሆንም ሶርያ ፈጣሪ አላት ኢራቅ ምንም አትሆንም ኢራቅ ፈጣሪ አላት ይባል ነበር ። ነገር ግን በአውሮፓውያን ደባ ዛሬ ላይ ህጻናት የት እንደሚሄዱ ግራ ገብቷቸዋል። ስለዚህ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያ ላይ ለሚሆነው ነገር ሃላፊነት አለበት። ሁሉም ለሰላም መስፈን ቆም ብሎ ማሰብ አለበት ብዬ አስባለሁ። ሰላም ከውስጥ ነው የሚፈልቀው ይህ ሰላም ነው ወደሌላ ሰው እና ማህበረሰብ የሚጋባው ። ሁላችንም የምንኮራባትን ሀገር ለማግኘት ዛሬን በመተሳሰብና በፍቅር ልንኖር ይገባል›› ።

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን የካቲት 29 /2016 ዓ.ም

 

Recommended For You