‹‹ልምድና ትምህርት ለመቅሰም ቅድሚያ መስጠት አለብን››  ወጣት ዲቦራ ኤርሚያስ

ዲቦራ ኤርሚያስ የ21 ዓመት ወጣት ስትሆን፤ እርሷን ጨምሮ ሁለት ሴት ልጆች ላላቸው ወላጆቿ የበኩር ልጅ ነች። ተወልዳ ያደገችው ብዙ ዕድል ይገኝባታል ብላ በምታምንባት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው። አዲስ አበባ ውስጥ የትምህርት፣ የሥራ፣ ራስን የማብቃት እና የማሳደግ፣ ከጥቃት የመጠበቅ፣ በተሻለ ሁኔታ የመኖር እና ሌሎች ብዙ ዕድሎች አሉ ብላ እንደምታምን ትናገራለች። እነዚህ ዕድሎች መኖራቸው ትንንሽ ከተሞችና በገጠሪቱ የኢትዮጵያ አካባቢ ላሉ ሴቶች ተስፋ መሆናቸውን ትገልፃለች።

ዲቦራ በዕድሉ በመጠቀሟ ገና በጠዋቱ ዕድሜዋ ብዙ ኃላፊነቶችን መውሰድ፤ በርካታ ተግባራትን በተመሳሳይ ጊዜ መፈፀም ችላለች። ዕድሎችን ፈጥና ትጠቀማለች። በቅርቡ አዲስ አበባ ከተማ ላይ የተዘጋጀውን ቀጣናዊ ትስስር ለዘላቂ ልማት መድረክ እንድትመራና እንድታስተባብር በስልክ ሲነገራት፤ መዘጋጃ ጊዜ የለኝም ብላ አልገፋችም። ፈጥና ፈቃዷን አሳየች። ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተለመደውን ባሕል በመስበር የተማሪ ተቀጣሪ ሆና የደሞዝ ተከፋይ መሆን የቻለች ጀግና ነች።

ነገር ግን ገንዘብ ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ ብዙ ነገሮችን ገና ከማለዳው ሊያበላሽ ስለሚችል፤ ልምድና ትምህርት ለመቅሰም ቅድሚያ መስጠት አዋጭ ነው ባይ ናት። ከዚህ አኳያ አብዛኛውን ጊዜዋን የምታሳልፈው ይሄንኑ በምታገኝበት የበጎ ፈቃድ ሥራ ላይ ነው። ሥራውን የምታከናውነውም ትልልቅ የኃላፊነት ቦታዎችን ወስዳ ነው። ለአብነት በእንደራሴ ወጣቶች ማኅበር ውስጥ የፕላንና ፕሮጀክት ዳይሬክተር ሆና እያገለገለች የምትገኘው ዲቦራ፤ እርሷን ያገኘንበትን ቀጣናዊ ትስስር ለዘላቂ ልማት የተሰኘውን ጨምሮ ትልልቅ ዓለም አቀፍ መድረኮችን በማስተባበርና በማስተዋወቅ ልምድ አካብታለች።

ለብዙ ወጣት ሴቶች አርዓያና ተስፋም ሆናለች። ዲቦራ በማናቸውም በአዲስ አበባ ከተማ በሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች መድረክ አትታጣም። ቢበዛ መድረኮቹን ስታስተባብርና ስትመራ ቢያንስ በመጋበዝ ስትሳተፍ ትታያለች። በእነዚህ መድረኮች የሚያስፈልገው የቋንቋ ተግባቦት ክህሎትም እሷ ጋር አለ። እታች ከአፀደ ሕፃናት ጀምሮ ኤቢሲዲ እያልን የመጣንበት ነው በምትለው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ከዓለም ሀገራት ከተውጣጡት የመድረኩ ታዳሚዎች ሁሉ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ያህል ስታወጋ ታፈዛለች። እየተማርኩት ነው በምትለው ፈረንሳይኛ ቋንቋም ጥሩ ተግባቦት አላት። ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባቦቷን ለማስፋትም የሀገር ውስጥ ቋንቋዎችን እየተማረች ትገኛለች።

ዲቦራ አሁን ላይ በኒው ጀነሬሽን ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዓመት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተማሪ ነች። ጎን ለጎንም በገሊላ ኢንተርናሽናል ሴሚናሪ ክርስቲያን የራስን ሀሳብና ዓላማ በመለየት ትኩረት በማድረግ የሚያጠነጥን ሶሻል ወርክ የሁለተኛ ዓመት ትምህርቷን እየተከታተለች ትገኛለች። በኢትዮጵያ አንድ ወጣት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሆኖ ተቀጥሮ የሚሠራበት ባሕል ባይጎለብትም እርሷ ከትምህርቷ በሚተርፋት ጊዜም ተቀጥራ ትሠራለች። ይሄ ተቀጥራ የምትሠራበት ቦታ ኤዲት ኤዱኬሽን ሰርቪስ ሲሰኝ ከስድስት እስከ 12 ዓመት ላሉ ታዳጊዎች ክህሎታቸውን የሚያሳድጉበት ሥልጠናዎችን በጨዋታ መልክ ትሰጣለች። በዚህ ቦታ ላይም ዲቦራ እንደተለመደው ትልቅ ኃላፊነትን በመውሰድ ረዳት አስተዳዳሪ ሆና እየሠራች ነው።

ገና በ21 ዓመት ለጋ ዕድሜዋ እነዚህን ሁሉ ትልልቅ ኃላፊነቶችን የሰነቁ ተግባራትን ማከናወን የቻለችው ለራሷ ወሰን የምትለውን ገደብ ባለማስቀመጧ እንደሆነ ትናገራለች። አቋም ያላት በመሆኑ በተቃራኒ ጾታ ግፊትም ሆነ በአቻ ተፅዕኖ ጉዞዋ ተሰናክሎ አልቆመም። በዚህ በኩል በወላጅና በትምህርት ቤት የተቃኘው አስተዳደጓ አስተዋፅዖ እንዳደረገላትም አጫውታናለች።

‹‹አስተዳደጋችን አቋም ለመያዝ እና ውጤታማ ለመሆን አስፈላጊና ወሳኝ ነው›› ብላናለች። ዲቦራን ያናገርናት በዓለም የሴቶች ቀን መባቻ እንደመሆኑ በዓሉ አዲስ አበባ ከሚገኙ ትላልቅ ሆቴሎች ወጥቶ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ቢያንስ በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ ከተሞች የሚከበርበት ሁኔታ ቢለመድ ለእንስቶች ሕይወት የተሻለ ለውጥ እንደሚያመጣም ትናገራለች።

ይሄን ያህል ስለ ወጣቷ ካስተዋወቅናችሁ ሰፋ ለማድረግ ስናነጋግራት ወደ አጫወተችን ወግ እንውሰዳችሁና አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተወለደችው ዲቦራ የተወለደችበት አካባቢ ሳሪስ ነው። አራት ዓመት ሲሆናት ወላጆቿ መኖሪያቸውን ወደ ጎሮ በማዛወራቸው እስከ አስራ አራት ዓመቷ ለተማረችበት አቤኔዘር የአፀደ ሕፃናት ትምህርት ቤት በአዕምሮዋ ያስቀረችው ትዝታ የላትም። የታዳጊነትና የወጣትነት ሕይወቷ ከአሁኑ መኖሪያዋ ጎሮ አካባቢ ጋር ይሰናሰላል። ጎሮ ፒስ ስኩል ቅድመ መደበኛ ትምህርቷን ተምራ ከአንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን ትምህርቷን ያጠናቀቀችው በአካባቢው በሚገኝ በቪዥን አካዳሚ ነው።

እዚህ ለሴቱም ለወንዱም ተማሪ መርዳትና ማገዝ የሚፈልጉ መምህራኖች አግኝታለች። ትምህርት ቤቱ ትምህርት በትክክል የሚሰጥበትና በሥነ ሥርዓት የሚታወቅ መሆኑም ረድቷታል። የሚናገሩበትን፤ ራሳቸውን የሚገልፁበትን ዕድሎች የሚሰጧቸው መሆኑም ለኋላ ሕይወቷ ጠቅሟታል። በትምህርት ቤቱ ሚኒ ሚዲያ ስታዘጋጅ ያደገች በመሆኗ ጋዜጠኛ ትሆናለችም እየተባለች ቆይታለች። እነዚህ ዕድሎች በተገቢው መንገድ ማውራትና ራሷን መግለጽ እንድትችል አግዟታል። ቤተሰቦቿ ከጣሉላት መሠረት ጋር ተዳምሮም የራሴ የምትለው አቋም እንድትገነባ በማድረጉ ረገድ አበርክቶው የጎላ ነበር።

ይሄ ለራስ ወሰን ማበጀት የምትለው አቋሟ ወደ ዩኒቨርስቲ ከገባች በኋላም ቢሆን በይሉኝታና ችግር ላይ እንዳትወድቅ አግዟታል። በተለይ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ሆና ጊቢ ውስጥ የምትቆየው ለትምህርት ብቻ ነበር። ከትምህርት በኋላ መድረኮችን ወደምትመራባቸው፤ ስዕል ወደምትስልባቸውና ሙዚቃ ወደ ምትጫወትባቸው ቦታዎች ትሄዳለች፤ አብዛኛውን ጊዜዋንም ከቤተሰቦቿ ጋር ታሳልፍ ስለነበር የደረሰባት ችግር አልነበረም። ግንኙነቷ ውሱን መሆኑና ለግንኙነቷ ገደብ ማስቀመጧ በዩኒቨርስቲ ቆይታዋ በተለይም በአዲስ ተማሪነት ወቅቷ ሊደርሱባት ከሚችሉ አላስፈላጊ ተግባራት የጠበቃት እንደሆነ በማስታወስ ሌሎች ታዳጊዎች በተለይም ለእያንዳንዱ ጉዳይ ይሄንኑ የእርሷ ዓይነት የግንኙነት ገደብ በማስቀመጥ ወይም አቋም በመያዝ ራሳቸውን እንዲጠብቁም ትመክራለች። በተለይ ችግር የለም ተብለው በይሉኝታም ሆነ በሌላ የሚገባባቸው ነገሮች ብዙ ጥፋቶች ይዘው እንደሚመጡና ሴቶች በተፈጥሮ ሊጎዱ ለሚችሉ ነገሮች ተጋላጭ በመሆናቸው እራሳችንን የምንሆንበትን ልክ ለራሳችን ማስቀመጥ ይገባል ትላለች።

ወደ መጀመሪያ ትምህርት ተማሪነቷ ወቅት እንመለስና ዲቦራ ስለ ወር አበባ ጉዳይ ያወቀችበትን ጊዜ ታስታውሳለች። ይሄንንም ስታብራራ ትምህርት ቤታቸው ለብቻ ሴቶችን ሰብስቦ ስለ ወር አበባና በእድገት ሂደት ውስጥ ስለሚታዩ የባሕሪ ለውጦች ያስተማረበት ሁኔታ ነበር ትላለች። በትምህርት ቤታቸው ይሄ ግንዛቤ እንዲኖር መደረጉ በጣም ትልቅ ነገር ነው የምትለው ዲቦራ፤ ያኔ የ11 ዓመት ታዳጊና የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ነበረች። ተማሪዋ ስለ ወር አበባና ከተቃራኒ ጾታ ጋር የሚኖር ግንኙነት ቤተሰብ ካልነገራት ወይም በምንም ሁኔታ የማታውቅ ሴት ከሆነች ልትደነግጥ ታምሜ ነው ብላ ልትጨነቅ ስለምትችል በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ትምህርት ቤቶች ትልቅ ሚና መጫወት እንዳለባቸው ትናገራለች።

በዚህ ላይ ትምህርት ቤት ከማስተማር ባለፈ አንዳንዴ በቤተሰብና በልጆች መካከል የሚኖር ክፍተት እንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ ለልጆች ላይነገር ስለሚችል ክፍተቱን ይሸፍናል ትላለች። ዲቦራ ታዳጊ ሴቶች አብዛኛውን ጊዜያቸውን በቀን ውስጥ ስምንት ሰዓት ያህሉን ትምህርት ቤት ውስጥ በሚያሳልፉበት ሁኔታ፤ አሁን ላይ ምን ያህል ትምህርት ቤቶች ለሴት ታዳጊ ተማሪዎቻቸው ይሄንን እያደረጉ እንዳሉም ትጠይቃለች። ትምህርት ቤቶች ላይ ታዳጊ ሴቶችን ለብቻ ሰብስቦ በጉዳዩ ላይ ማስተማርና ማሠልጠን ቢኖር ብዙ ክፍተቶችን ሊሞላ እንደሚችልም ትመክራለች። እርሷ በዚህ በኩል ትምህርት ቤቷ ላደረገላትም ታመሰግናለች።

የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለች ትምህርት በክብደቱ በብርቱ ፈትኗት እንደነበር ትናገራለች። ይሄኔ የደረጃ ተማሪ አልነበረችም። በውጤቷ የምታዘቀዝቅባቸውም የምትነሳባቸውም ጊዜያት ነበሩ። እነዚህ ጊዜያት ብዙ ትምህርት አስተምረዋት አልፈዋል። ከዚህ ተነስታም የደረጃ ተማሪ አይደለሁም ማለት ሕይወት ላይ ውጤታማ አልሆንም ማለት አይደለም ትላለች። ሕይወት ትምህርት የሚያስፈልገው ለብቻው የሚሠራበት ጉዳይ እንደሆነም ትናገራለች። በቆይታዬ የምጠላው ትምህርት አልነበረም። በጣም የሚከብደኝ ትምህርት ሂሳብ ቢሆንም እጠላዋለሁ አልልም። እጠላለሁ ካልኩ ራሴን አሳምኜ ልወድቅ ነውና፤ ሂሳብን እወደው ነበር ማለት አልችልም ትላለች። ያደኩት ግን ሁሉንም እወዳቸዋለሁ፤ አጠናቸዋለሁና ጥሩ ውጤት አመጣባቸዋለሁ እያልኩ ነው ትላለች።

ዲቦራ ባዮሎጂና ኬሚስትሪ ትምህርቶችን ብትወድም፤ 11ኛ ክፍል ላይ ምረጡ ሲባል የተፈጥሮ ሳይንስ ብትመርጥም ወደ ዩኒቨርሲቲ ስትገባ መጨረሻዋ የሶሻል ተማሪ ሆኗል። ምንም እንኳን የሚታወቀው ስትመረቅ ቢሆንም ለሦስት ተከታታይ ዓመታት እያስመዘገበች ባለችው የላቀ አፈፃፀም ከፍተኛ ነጥብ በማስመዝገቧ ተመራቂነቷ ለመረጋገጡ ጫፍ ላይ ደርሳለች።

ያኔ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆና የደረጃ ተማሪ ሆና ሳይሆን ስዕልና ሙዚቃ ውድድሮችን በማሸነፍ፤ የሚኒ ሚዲያና የተለያዩ ሌሎች መርሐ ግብሮችን በማዘጋጀትና በማቅረብ በተደጋጋሚ ትሸለም ነበር። ያ በልጅነቷ ታከናውን በነበረው ተግባር ዛሬ ዓለም አቀፍ መድረኮችን መምራትና ማስተባበር ላይ ደርሳለች። ከ200 በላይ የምስክር ወረቀቶችም ያሏት ሲሆን፤ ከትምህርቱ ጎን ለጎን ስዕል የመሳል፤ በተለያዩ የስዕል ውድድሮች ከመሳተፍ በተጨማሪ ሙዚቃ መጫወት ጀምራለች። በሚኒ ሚዲያም የተለያዩ መርሐ ግብሮችን ታዘጋጅ ነበር። ከጠዋት እስከ ማታ ከሚሰጠውና ፋታ ከሌለው አጨናናቂ ትምህርት ይልቅ፤ ስዕል መሳልና ሙዚቃ መጫወት ይስባት እንደነበረም ታስታውሳለች።

ዲቦራ ልክ ዩኒቨርስቲ ስትገባ ትምህርት አሰጣጡ ላይ የነበረው ጫና ቀለል ስላለላት ወደ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ችላለች። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ ባላት ልምድ ታግዛ የበለጠ ራሷን መግለጽ፤ በራስ መተማመኗን አጠናከረች። እንደውም ጎን ለጎን ሌሎች ትምህርቶችን መማር፤ ተቀጥራ የምትሠራበትን ጨምሮ በርካታ ሥራዎችን ለማከናወንም በቅታለች። የተዋጣላት ዓለም ዓቀፍ መድረክ አስተዋዋቂና አስተባባሪም ለመሆን የቻለችው ዲቦራ፤ በዚህ በኩል ከተማረችባቸው ትምህርት ቤቶች ባሻገር የአሁኑ ዘመን ቤተሰብ አይመስሉም የምትላቸው ወላጆቿ ትልቅ ሚና መጫወታቸውን ትገልፃለች።

‹‹የአሁን ዘመን ወላጅ በአብዛኛው ልጆቹ የቀለም ትምህርት ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ እንጂ ሌላ ነገር እንዲሠሩ አይፈልግም፤ የውስጥ ስሜታቸውን አያዳምጥም። የእኔ ወላጆች ግን ስዕል ልሳል ስላቸው ብዙ ነገር ተመቻችቶላቸው ባይሆንም የስዕል ደብተር፤ እርሳስ ከለር ያቀርቡልኛል። ሙዚቃ ልጫወት ስላቸውም እንዲሁ ጊታር፤ በገና፤ መሰንቆና ሌሎች መሣሪያዎችን ሳይቀር ይገዙልኛል። እንደ አባትና እናት በመካከላችን ክፍተት ሳይኖር ጉዳዮችን እያነሳሁ ከእነርሱ ጋር እንድወያይም ሰፊ ዕድል ሰጥተውኛል። እኔና ታናሽ እህቴ ከወላጆቻችን ጋር የምናደርገው ውይይት ውጭ ስንወጣ እንዳንሸማቀቅና በራስ መተማመን እንዲኖረን አድርጎናል። ከቤተሰብ ጋር ያሳለፍነው ጊዜ ብቻ ለዛሬ ማንነታችን ትልቅ አበርክቶ አለው›› ትላለች።

በኢትዮጵያ አንድ ወጣት የዩኒቨርስቲ ተማሪ ሆኖ ተቀጥሮ የሚሠራበት ልምድ ባይጎለብትም እርሷ ከትምህርት ጎን ተከፋይ ሆና ትሠራለች። ይሄ ተቀጥራ የምትሠራበት ቦታ ኤዲት ኤዱኬሽን ሰርቪስ ሲሰኝ ከስድስት እስከ 12 ዓመት ላሉ ታዳጊዎች ክህሎታቸውን የሚያሳድጉበት ሥልጠናዎችን በጨዋታ መልክ ትሰጣለች። ወጣቷ በዚህ ቦታ ላይ ረዳት አስተዳዳሪም ሆና እየሠራች ትገኛለች።

ዲቦራ ከ1 ሺ በላይ አባላትና 13 የአስተዳደር ኮሚቴ ባለው በእንደራሴ ወጣቶች ማኅበርም አባል ነች። ማኅበሩ ከተመሠረተ ሁለተኛ ዓመቱ ቢሆንም እርሷ የተቀላቀለችው በተያዘው ዓመት መስከረም ወር ውስጥ ነው። እንድትቀላቀል ያደረጋት አብሯት የሚማረውና በተደጋጋሚ እርሷ በምትሳተፍባቸውና በምታስተባብራቸው ዓለም አቀፍ መድረኮች ታገኘው የነበረው የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ብሩክ አስቻለው ነው። ዲቦራ ከብሩክ ጋር አብራ መማሯንም ታስታውሳለች። በመድረኮቹ መገናኘታቸው ሲጨመር አብረው ቢሠሩ ብዙ ወጣቶችን ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚችሉ ተወያዩና ወደ ማኅበሩ ተቀላቀለች። እዚህም ወጣቱን ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ፕሮፖዛል ከማዘጋጀት ጀምሮ በጋራ እንዲገመገም፤ ውይይት እንዲደረግበት፤ በውይይት እንዲዳብር ከማድረግ ጀምሮ በርካታ ተግባራትን ታከናውናለች።

ዲቦራ አሁን እዛም እዚህም በዝታለች። በማኅበሩ ውስጥ እንደተለመደው ትልቁንና ለእርሷ ብቃት የሚመጥነውን ኃላፊነት በመውሰድ የፕላንና ፕሮጀክት ዳይሬክተር ሆና እየሠራች ትገኛለች። የሚሠሩት እንደ ሀገር አቀፍ ባሉ ወጣቶች ላይ ሲሆን ወጣቶች የተለያዩ የሥልጠና፤ የሥራና ሌሎች ዕድሎችን እንዲያገኙና በማኅበሩ በኩል ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ማድረግን ያማከለ ስለመሆኑ አጫውታናለች። በተለይ ወጣቶቹ በበጎ ፈቃደኝነት ነፃ አገልግሎት ማድረግ ሲፈልጉ የት እንደሚያደርጉ ስለማያውቁ ነፃ የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉበትን ቦታ ያመላክቷቸዋል።

ዲቦራ እንደምትለው በአሁኑ ሰዓት ሥራ ለመቀጠርም ሆነ ከተቀጠሩ በኋላ በውጤታማነት ለማገልገል ያለው የትምህርት ሥርዓት ብቻ በቂ ባለመሆኑ፤ ብዙ ልምድ፤ ተጨማሪ ዕውቀት፤ በማስፈለጉ ነፃ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጥተው የምስክር ወረቀት የሚያገኙበትን ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ተስማምተውም ያመቻቻሉ። በተለይ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ወጣቶችን ወደ አዲስ አበባ በማምጣት ለሦስት ቀን ሥልጠና በመስጠት ከዩኒሴፍ፤ ከዩኒስኮ ጋር በመነጋገርና ወደ እዛው መልሶ በመላክ የሚበቁበትና ወደ ሥራ የሚሠማሩበትን ሥልጠና እንዲያገኙና ኅብረተሰቡን እንዲያገለግሉ ያደርጋሉ። አሁን ላይም የማኅበሩን አባላት ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ያሉትን ወጣቶችም ለማድረስ ከሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር እየተነጋገሩ ይገኛሉ።

እርሷን ጨምሮ ሁሉም ወጣቶች በተለይም አብዛኞቹ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ተቀጣሪ እንዳልሆኑና በበጎ ፈቃደኝነት በማኅበሩ ውስጥ እንደሚያገለግሉም ነግራናለች። ማኅበሩ ከሜሪ ጆይ ጋር ቅርብ ጊዜ በነበረው ሩጫ ላይ አብረው ሠርተዋል። እርሷ ዓለም አቀፍ መድረክ የምትመራበትን ጨምሮ እንዲህ ዓይነቶቹን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ወጣቶች ካወንስል ጋር በመቀናጀት መሥራታቸውን አሁንም ከእነዚሁ አካላትና ከሌሎች ዓለም አቀፍ አካላት ጋር እየሠሩ መገኘታቸውን አንስታለች። እርሷን ጨምሮ ብዙዎቹ ወጣቶች ግን በጎ ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ አገልግሎት የሚሰጡ እንጂ ገንዘብ ተከፋይ አይደሉም። ነገር ግን ለአገልግሎታችን ለምን አልተከፈለንም አይሉም። አንድ ሰው ሁል ጊዜ ግቡ ገንዘብ ማግኘት ከሆነ አደጋ አለው። ስለመሆኑም በተለይ ወላጆች እንደ ወላጅ ኅብረተሰቡም እንደ ኅብረተሰብ ከገንዘቡ ጋር ተያይዞ ለወጣቶች ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባውም ትመክራለች።

የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆና ብር ዝም ብለው ወላጆቿ እንደማይሰጧትና ብሩን የፈለገችበት ምክንያት ትጠየቅ የነበረበትን ሁኔታ ተገቢነቱን ታስታውሳለች። በሌላ በኩል በፊልምም ሆነ በሌላ አጋጣሚ በእርሷ ዕድሜ የሚገኙ የውጭ ተማሪዎችን የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ባገኙት ገንዘብ የትራንስፖርት ወጪያቸውን ሲሸፍኑ በማየቷ፤ ወላጆቿን ‹‹ለምን እኔና እህቴም እንዲህ እንድናደርግ ገቢ የሚያስገኝ ትንንሽ ሥራ እንድንሠራ አትፈቅዱልንም? ስትላቸው ወላጆቿን ትጠይቃለች።›› ገና የ16 ዓመት ልጅ እኮ ነሽ ትባል እንደነበር ትናገራለች። ሥራ የምትይዙት ዩኒቨርስቲ ገብታችሁ ተምራችሁ ዲግሪያችሁን ከያዛችሁ በኋላ ነው ይባሉ ነበር። ይህም አዕምሯዋ ውስጥ ተቀምጦ እንደነበር ትናገራለች። ይሄ ምን ያህል ኢትዮጵያዊ ወጣት ያለ ሥራ እንዲቀመጥ ተፅዕኖ እንዳደረገ ስለማሳየቱም ትጠቁማለች። ‹‹ሁልጊዜ ትንሽም ብትሆን በዕውቀትም በገንዘብም ራሳችንን የምናሳድግበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልገናል።›› ስትልም ሠርቶ ማግኘትን በበጎ ጎኑ ትጠቅሰዋለች።

ዲቦራ ተቀጣሪ ሆና ገንዘብ ከማግኘቷ በፊት ፎቶግራፍ፤ መሥራቷ፤ ቪዲዮግራፊ መሥራቷ፤ በተለይ በኮቪድ ጊዜ ብዙ ነገሮች መማሯ ትንሽ፤ ትንሽ ገንዘብ ያስገኙላት እንደነበር ነግራናለች። በእዚህም ለቤት የሆነ ነገር ትገዛና የትራንስፖርት ወጪዋን ራሷ ትሸፍን እንደነበረም አስታውሳለች። የተቀጣሪነት ዕድል የሚኖረው እንዲህ ዓይነቱ ትንሽ፤ ትንሽ ልምድ ሲኖር ነውም ትላለች። ይሄን እሴት በመጨመር ግራፊክ ዲዛይን የሚፈልጉ ሰዎች ጋር ሄጄ ግራፊክ ዲዛይን ተምሬያለሁ ማለት መቻሌ ተፈላጊነቴን ይጨምረዋል የሚልም ዕምነት አላት።

እሴት መጨመር ገንዘብ ላያስገኝ ቢችልም፤ እኔ አሁንም የያዝኩት እሴት መጨመርን ነው ብላናለች። ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ሠርታ ምንም ገንዘብ ሊሰጣት ያልቻለበት ሁኔታ ገጥሟትም ያውቃል። ሆኖም ለምን አልተሰጠኝም ብላ ከዛ መድረክ አልቀረችም። በማግስቱም ከዚያም በኋላ በመሄድ ልምድ ያካበተችበት ተሞክሮ አላት። ከገንዘብ ይልቅ ልምድ ይበልጥብኛል፤ ሰዎችም እተዋወቅበታለሁ የምትላቸው ሁኔታዎችም አሏት። ዋናው መማራችን ማደጋችን ራሳችን ላይ እሴት መጨመራችን ነው። ገንዘብ የሚመጣው፤ ከዚህ በኋላ ነው። ገንዘብ የሚገኝበትን ሂደትም ማመን አለብን። በአንዴ ለምን እንደዚህ አልተደረገልንም ካልን ብዙ ነገሮች እናበላሻለን። ገንዘብ በሂደት ቀስ እያልን የምናገኘው ስለሆነ አሁን ራሳችን ላይ መጨመር ያለብንን እሴት እንጨምር፤ እኔም አሁን ላይ እያደረኩ ያለሁት ይሄንኑ ነው ትላለች። በርካታ ዓለም አቀፍ መድረኮችን መምራት  የቻለችውም በዚህ ይዞታዋ ነው።

ዓለም አቀፍ መድረክ የማስተባበር ልምድ ዲቦራ እኛ ስታስተባብርና ስትመራ ያገኘናትን ቀጣናዊ ትስስር ለዘላቂ ልማት መድረክ ጨምሮ ብዙ ዓለም አቀፍ መድረኮችን አስተባብራለች። ወደ ሌሎቹ ሳንገባ ይሄን መድረክ ልትመራ ስለቻለችበት ሁኔታ ጠይቀናት እንደነገረችን፤ የእንደራሴ ወጣቶች ፕሬዚዳንት ብሩክ አስቻለው መድረኩን እንድትመራ የነገራት በዋዜማው ነበር። ፈጥና ፈቃደኝነቷን የሰጠች ሲሆን፤ ፈቃደኛ የሆነችው በዕድሉ ልጠቀም በሚል ብቻ አይደለም። ከዚህ በፊት በርካታ ተመሳሳይ መድረኮች አስተባብራለችና ነው። በተጨማሪ ሀገር ውስጥ ይሁኑ እንጂ በዓለም አቀፍ መድረኮች፤ ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብም አያሌ ሥልጠናዎችንም ሰጥታለች። ፈጣን ምላሽ የሰጠችው ልምድ በተለይም በራስ መተማመን በሌለበት እንዲህ ዓይነቱን ዓለም አቀፍ መድረክ መምራት የሀገር ገጽታ ጥሩ አንድምታ ላይኖረው ስለሚችል መጠንቀቁ ባይከፋም የትኛዋም ዓይነት ሴት ያገኘችውን ዕድል ማሳለፍ የለባትም ትላለች። ደረጃ በደረጃ ራስን እያበቁ መምጣት ዕድሎችን ላለማሳለፍ አንዱ ዘዴ እንደሆነም ትመክራለች።

መርሐ ግብሩ የተለያዩ የምሥራቅ አፍሪካ አመራሮች፤ ከቀጣናውና ከቀንዱም የተውጣጡ በርካታ ወጣቶች የተጋበዙበት ነበር። አብዛኞቹ እንግሊዘኛ አንዳንዶቹም ፈረንሳይኛ የሚናገሩ በመሆኑ፤ ብዙዎቹ ከውጭ ጉዳይ የመጣሁ ስለመሰላቸው እየጠሩ ስለሚፈልጉት ሁሉ መልስ እንድሰጣቸው ይጠይቁኝ ነበር ትላለች። በየደቂቃው እየጠሩ ብዙ ነገሮችን እንድታብራራላቸው የሚፈልጉም ነበሩ። ቋንቋ ሰውን ከሰው የሚያገናኝ እንደመሆኑ ሰውን በቋንቋው መልስ መስጠት የተሻለ ግንኙነት ይፈጥራል። ባሕልን እና ታሪክን ይዞ ይመጣል ትላለች።

‹‹እኔ ሁለቱንም ቋንቋ አውቅ ነበር። በተለይ እንግሊዝኛ ኤ፤ቢ፤ሲ፤ዲ እያልን ቆጥረን ለረጅም ጊዜ እየተማርን ያደግንበት፤ ረጅም ጊዜ የተማርነውና በሥራችንና በትምህርታችን ላይ የምንጠቀመው በመሆኑ መናገሩ የአፍ መፍቻዬ ያህል አልከበደኝም። ፈረንሳይኛም እየተማርኩት ያለ ቢሆንም አልታማበትም። በመሆኑም ከሁሉም ከቀጣናው ተውጣጥተው በመድረኩ ከተገኙ አመራሮች ጋር በጥሩ ሁኔታ መግባባት ችያለሁ።›› ትላለች።

እርሷ ማኅበሯን ወክላ ከኢትዮጵያ ወጣቶች ካውንስልና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር አብረው ሲሠሩ መቆየታቸውን ትናገራለች። ወጣቷ ‹‹አሁን ገና ትንሽ ነኝ፤ በዚህ ትንሽነቴ እነዚህን ትልልቅ ቦታዎችን ማየት ቀድሜ ብዙ ነገሮችን እንድዘጋጅ ቀድሜ ራሴን ብዙ እንዳሳድግ፤ ራሴ ላይ እንድሠራ ጥሩ ዕድል ሰጥቶኛልም።›› ብላናለች። የምናገለግልበት ይለያይ እንጂ ሁላችንም አገልጋዮች ነን የምትለው ዲቦራ ወደፊት የሕዝብ አገልጋይ እንድትሆን መሠረት የጣለላት ስለመሆኑም ታነሳለች። ቦታው ወደ ፊት የሕዝብ አገልጋይ መሆን ነው የምፈልገው ትላለች። ያኔ ቦታው ላይ መገልገል ያለበት ሰው እንዲገለገል የማድረግ ፍላጎቷ የሚሳካ ስለመሆኑም ትናገራለች።

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዴቦራ ዕይታ

ዓለም የሴቶች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበር ሲሆን የተነሳበት ዓላማም አለው። ከዓላማው ሴቶችን ከጥቃት መጠበቅና ለሴቶች ዕድል መስጠት በዋንኛነት ይጠቀሳሉ። በዓለማችን እኛ እንድንማር፤ ከወንድ እኩል የተሻለ ደሞዝ ተከፋይ እንድንሆንና በተሻለ ሁኔታ እንድንኖር፤ ዕድሎች እንድናገኝ ብዙ ሴቶች ዋጋ ከፍለዋል። ሆኖም በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እስካሁን አልቆመም። አሁን ወደ እዚህ ስመጣ ሴቶች እንደተደፈሩ የሚገልጽ ዜና እያነበብኩ ነበር። ይሄ በተለይ በገጠሩ አሁንም ፆታዊ ጥቃት እየደረሰባቸው ያሉ ሴቶች መኖራቸውን ያመለክታል። የሴቶች ቀን ማርች 8 ብቻ ሳይሆን ሁሌም እንደመሆኑ ሁልጊዜም በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል መጮህ አለብን። አዲስ አበባ ላይ ሕግም አለ፤ ከሌሎች አካባቢዎች በተሻለ ሴቶች ከጥቃት ይጠበቁበታል። ገጠር ላይ ግን ይሄ ሊኖርም ላይኖርም፤ ቢኖርም ላይከበር የሚችልበት ሁኔታ አለ። በመሆኑም የዓለም የሴቶች ቀንን ስናከብር ከተማ ላይ ባሉ ሆቴሎች ባንገደብ መልካም ነው። አንድ ቀን ብቻ ሳይሆን ሁሌም ዕለቱን እያሰብን፤እያስተማርን፤ ለኅብረተሰቡ ሥልጠና እየሰጠን ወጣ ብለን ብናከብረው ጥቃታቸውን መከላከል እንችላለን። በሕይወታቸውም ላይ ለውጥ እናመጣለን ብዬ አምናለሁ ብላለች። መልካም በዓል!

ሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን የካቲት 29 /2016 ዓ.ም

Recommended For You