በሀረሪ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ

ወይዘሮ እመቤት መንግሥቱ ትባላለች። የአራት ልጆች እናት ናት። የልጆችዋ አባት ከጎኗ ባለመኖሩ ያለ ረዳት ነው ብቻዋን የምታሳድገው። ሻይ ቡና፣ ፈጣን ምግብ አዘጋጅታ በማቅረብ በተሰማርችበት አነስተኛ የንግድ ሥራ በምታገኘው ገቢ ነው ራስዋን ጨምሮ አምስት ቤተሰቧን የምታስተዳድረው።

የምትኖረውና የምትሰራበት ቦታ የግለሰብ ቤት ኪራይ በመሆኑ ጫና ፈጥሮባታል። ግን ደግሞ ሌላ አማራጭ የላትም። ሁሉንም ተቋቁማ ልጆችዋን ማሳደግ አለባት። ወደ አነስተኛ ንግድ ሥራ ውስጥ የገባችው ከቤተሰብ በብድር ባገኘችው 10ሺብር መነሻ ሲሆን በሥራው ላይ ከአንድ ዓመት በላይ እንደሆናት ትናገራለች።

ወይዘሮ እመቤት እንደምትለው፤ በሥራዋ ትርፍ ከማግኘት ይልቅ ኪሰራው ስለበዛባት ብድሯንም መመለስ አልቻለችም። ንግዷን የማሳደግ ፍላጎት ቢኖራትም በገንዘብ አቅም ማነስ ምክንያት አልተሳካላትም። ይህ ደግሞ ኑሮዋ ከእጅ ወደአፍ እንዲሆን አድርጎታል።

ወይዘሮ እመቤት፤ ያጋጠማትን የገንዘብ አቅም የመፍጠር ችግር ለመፍታት ከመንግሥት ብድር የምታገኝበትን መንገድ ለማመቻቸት፣ እንዲሁም ከሌሎች ጋር በመሆን በማህበር ተደራጅታ ለመሥራት አማራጮችን ለማየት ጥረት አድርጋ እንደሆን ጠይቄያት አንዱንም እንዳልሞከረች ነው የገለጸችው። ምክንያቷ ደግሞ፤ በማህበር ተደራጅተው ብድር ወስደው ወደ ሥራ እንደገቡ የተበደሩትን ለመመለስ ሲጨናነቁ፣ አንዳንዶችም ገንዘቡ ሥራ ላይ ሳይውል ሲባክንባቸው፣ ከመካከላቸውም ገንዘቡን ይዞ የሚጠፋባቸው መኖሩን በወሬ ደረጃ በመስማቷ እርስዋም ይሄ እጣፈንታ ይገጥመኛል በሚል ቀድማ ስጋት ስላደረባት ነው። ሁሉም የማህበሩ አባላት በሥራ ላይ ያላቸው እንቅስቃሴ እኩል አለመሆንም ሌላው ምክንያቷ ነው። በዚህ ስጋት ነው ከዘመድ ገንዘብ ተበድራ ሥራ የጀመረችው።

አንዳንድ ደንበኞችዋ ብድር ብትጠይቅና በማህበርም ተደራጅታ ብትሰራ ተጠቃሚ ልትሆን እንደምትችል ምክር እንደሰጧትም ነግራኛለች። ይሁን እንጂ ገና አልወሰነችም። ገቢዋን ማሳደግ እንዳለባት ግን የኑሮው ሁኔታ እያስገደዳት እንደሆነ ነው የገለጸችው።

እንደ ወይዘሮ እመቤት ትኩስ ነገር ሻይ ቡና፣ የታሸገ ውሃ፣ ብስኩት(ፓስቴ)፣ ፉል፣ የመሳሰሉ ፈጣን ምግቦችን በጎዳና ላይ በማቅረብ አነስተኛ የሥራ መስክ ላይ የተሰማሩ ሴት እህቶች ናቸው በስፋት የተሰማሩት። የተሰማሩበት ሥራ የእለት ጉርስ ለመሸፈን እንደሚያሰችላቸው ግልጽ ነው።

ነገር ግን እነዚህ ሴቶች የእለት ኑሮን ከመደገፍ ባለፈ ውጤታማ እንዲሆኑ ምን ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው? በገንዘብ አያያዝና ቁጠባ ላይም ግንዛቤ እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድ የሴቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት፣ ብሎም የፖለቲካ ተሳትፎአቸውን ለማጎልበት የተቋቋመው የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ምን እየሰራ ነው? ስንል ለሀረሪ ክልል ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ፤ ለሆኑት ወይዘሮ መፍቱሀ አሊዩ ጥያቄን አቅርበናል ፤ ቢሮው ትልቅ ተልዕኮ ይዞ እየሰራ ያለው ግንዛቤ መፍጠር ላይ ነው። እየተከናወነ ባለው የግንዛቤ ፈጠራ ሥራም ሴቶች በማህበር ተደራጅተው ቢንቀሳቀሱ ያሉባቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በጋራ፤ መፍታት እንደሚያስችሏቸው ነው በማለት ይመልሳሉ።

በማህበር እንዲደራጁ ማበረታታት ብቻ ሳይሆን፣ ለንግድ ሥራ የሚያስፈልጋቸውን ክህሎትም እንዲያገኙ ነው የሚሰራው የሚሉት ኃላፊዋ ለአብነትም በንግድ አሠራር ውስጥ የገንዘብ አጠቃቀምና አያያዝ፣ በተለይም የቁጠባ ባህልን ማዳበር፣ አዋጭ በሆነ ንግድ ላይ ለመሰማራት ቀድሞ ማቀድ፣ በዚህ ረገድ በማህበራዊ አገልግሎቶች በተከናወኑት ሥራዎች እስካሁን ባለው ተሞክሮም ተጠቃሚ እየሆኑ ያሉት በማህበር ተደራጅተው ክህሎት አግኝተው በተለያየ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ሴቶች ናቸው።

ሌላው የግንዛቤ ማስጨበጫ የትኩረት አቅጣጫ ሴቶች  በራስ መተማመንን እንዲያዳብሩ ነው። ሴቷ በምትሰራው ሥራም ሆነ፣ በተለያየ ተሳትፎ ላይ በምታደርገው እንቅስቃሴ በራስ መተማመን እንድትፈጽም ማስቻል ነው።

ሴቶች ለአካላዊ፣ ለሥነልቦና እና ለጾታዊ ጥቃት ተጋላጭ እንዳይሆኑም ቢሮው ሰፊ የግንዛቤ ሥራ እየሠራ ይገኛል። በዚህ በኩል ግንዛቤ ከሚፈጠርባቸውና ተደራሽ ከሆኑት ትምህርት ቤቶች ይገኙባቸዋል። ሴት ተማሪዎች በሚደርስባቸው የተለያየ ጥቃት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይስተጓጎሉ አስቀድሞ ለመከላከል ያስችላል። በተጨማሪም በክልሉ በሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎችም በተመሳሳይ እየተሠራ ይገኛል። በወረዳዎች ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተውጣጡ አባላት የተካተቱበት የጥቃት ተከላካይ ኮሚቴ ተዋቅሮ ነው የግንዛቤ መፍጠሩ ሥራ ተጠናክሮ እየተሰራ ያለው። የኤፍኤም ጣቢያዎችን በመጠቀምም ግንዘቤን የማዳበሩ ሥራ በተጨማሪ እየተሰራ ነው። በተለያዩ አመራጮች ግንዛቤ የመፍጠሩ ሥራ መከናወኑ በከተማና በገጠር የሚኖረውም እኩል የሆነ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ ያስችላል።

እንደ ወይዘሮ መፍቱህ ማብራሪያ ግንዛቤ መፍጠሩ ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈለገው፤ ሴቶች በተለያየ መንገድ የሚያጋጥሟቸውን ማህበራዊ ችግሮች መፍታት የሚቻለው ሁሉም የኅብረሰተብ ክፍል ተሳትፎ ሲያደርግ ነው። ስለሴቶችም ሆነ የሕፃናትን ጉዳይ ሁሉም ኃላፊነት ወስዶ ሲንቀሳቀስ ነው። አንድ ቢሮ ብቻውን እንዲሰራ ማድረግ የትም አያደርስም።

ግንዛቤ የመፍጠሩ ሥራ በማኅበረሰብ ውስጥ ሰርጾ ሁሉም በያገባኛል ስሜት እንዲንቀሳቀስ፤ በቢሮው በኩል እየተከናወነ ያለው ሥራ ጥሩ ጅምር ሲሆን በተያዘው 2016 በጀት ዓመት ሰፊ የንቅናቄ ሥራ ነው የተሠራው። ለአብነትም የ16ቱ የፀረ ጾታ የጥቃት ቀንን በመጠቀም ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ ሴቶችን በማሳተፍ በስፋት ተንቀሳቅሰናል።

ሴቶች በኢኮኖሚ ተሽለው አለመገኘታቸውም ለተለያየ ችግር እንዲዳረጉ እንደሚያደርጋቸው የጠቀሱት ወይዘሮ መፍቱሀ፤ የኢኮኖሚ አቅም ፈጥረው በራስ ለመቆም እንዲችሉም በቢሮው በኩል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው የገለጹት። ‹‹በኢኮኖሚ ያደገች ሴት ለቤተሰቧም ትተርፋለች። አንዲት በኢኮኖሚ አቅም የፈጠረች ሴት ደግሞ ለአካባቢዋም ምሳሌ ሆና ታገለግላለች። እርሷን እያዩ ለማደግ የሚጥሩ ሴቶች ይፈጠራሉ። በዚህ መልኩ ነው ሥራ መሠራት ያለበት›› ብለዋል።

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በአካባቢያቸው ቀለብ(መሽሩፍ) አጥተው ለችግር የሚዳረጉ ሴቶች መኖራቸውንና አንዳንዶችም ለልጆቻቸው ምግብ ለማቅረብ፣ የትምህርት ቤት ቁሳቁስ ለማሟላት ሲቸገሩ ለቢሮአቸው ጥያቄ እንደሚያቀርቡ ወይዘሮ መፍቱሀ ይናገራሉ።

እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለመፍታትና በአጠቃላይ  ሴቶች የኢኮኖሚ አቅም ፈጥረው እራሳቸውን መርዳት እንዲችሉ፤ የሥራ እድል እና ብድር የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻችላቸው፣ ስለሚሰሩት ሥራ፣ ወጪ ገቢያቸውን እንዲያውቁ፣ እየሠሩ የተበደሩትን ገንዘብ እንዴት መመለስ እንደሚችሉ፣ አጭር ሥልጠና በመስጠት ሥራ እንዲፈጥሩ እንደሚደረግ ወይዘሮ መፍቱሀ አስረድተዋል።

እንደ ወይዘሮ መፍቱሀ ገለጻ፤ የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ቢሮው የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ብድር ማግኘት እንዲችሉ፣ ድጋፍም እንዲያገኙ ቢያደርግም ከዚህም በኋላ ብዙ መሥራት የሚጠበቅበት ነው ፤ ነገር ግን ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎችም ብዙዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።

በአጠቃላይ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ የሴቶችን ሁለተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሰላምና መረጋጋት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ የሚናገሩት ወይዘሮ መፍቱሀ፤ ሴቶችም ሰላምን ለማስፈን ድርሻቸውን እንዲወጡ በቢሮው በኩል እየተሰራ ነው።

‹‹አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም በሀገራችን እየተፈጠረ ቢሆንም ከጥቂት ዓመታት በፊት ግን የነበሩት አለመረጋጋቶች፣ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተካሄደው ጦርነት ከፍተኛ ቀውስን አስከትሏል። በዚህም በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዱት ሴቶችና ሕፃናት ናቸው። በመሆኑም ሰላም ለነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ወሳኝ ነው። ሴቶች ከአካባቢያቸው ጀምሮ በሀገር ላይ ሰላም እንዲስፍን በማድረግ ሚናቸው ከፍ ያለ በመሆኑ በዚህ ላይ ሰፊ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የማድረግ ሥራ ተሰርቷል›› ሲሉም አስረድተዋል።

ወይዘሮ መፍቱሀ እንዳሉት፤ ሰላም የማስፈኑ ሥራ የክልሉ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ከክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን ነው የሚሰራው በዚህ የሰላም ማስፍን ላይ ሚና እንዲኖራቸው የተደረገው የሰላም አምባሳደሮች ምርጫ ተካሂዷል። ተሳትፎአቸውም አካባቢያቸውን ከመጠበቅ ይጀምራል። የአካባቢያቸው ሰው ያለስጋት በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ፀረ ሰላም የሆኑ ኃይሎች በአካባቢው ላይ እንዳይኖር የጥበቃ ሥራ ይሰራሉ። በተጨማሪም በአካባቢያቸው ላይ ፀበኞች ካሉና በተለያየ ምክንያት ችግር ተፈጥሮም ከሆነ የተመረጡት የሰላም አምባሳደሮች በሽምግልና በማስታረቅ ሰላም እንዲፈጠር ያደርጋሉ።

በተለያየ ጉዳይ የሕግ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሴቶችንም የክልሉ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ በማገዝ ከጎናቸው ይቆማል ያሉት ወይዘሮ መፍቱሀ፤ ችግራቸው በውል ተለይቶ አቅጣጫ በመጠቆም መፍትሔ እንደሚሰጥ ነው የገለጹት። እርሳቸው እንዳሉት የፍትህ ጥያቄ ብዙ ሂደቶችን የሚጠይቅ በመሆኑ፤ በአጭር ጊዜ መልስ ለመስጠት ያስቸግራል። በዚህ በኩል ለጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት በሚፈጠር መዘግየት ቅሬታ ሊፈጠር ይችላል።

እንዲህ ያለውን ችግር ወይንም ክፍተት ለማስቀረት የተሻለ የሚሆነው ችግሮች ከምንጩ የሚቀሩበትን ሁኔታ መፍጠር እንደሆነና ቢሮውም ይህን እንደ አማራጭ እየሰራበት እንደሚገኝ ወይዘሮ መፍቱሀ ይናገራሉ። ቢሮው ከፍትህ ጋር ለተያያዙት ጉዳዮች የሕግ ክፍል እንዳለውና በክፍሉ እየሠሩ ያሉ ባለሙያዎችም ተገቢውን እገዛ እያደረጉ እንደሆነ ነው ያስረዱት።

እንደ ወይዘሮ መፍቱሀ ገለጻ፤ ከፍትህ ጋር በተያያዘ ከሚነሱት መካከል የቀለብ መቁረጥ ጉዳይ አንዱ ነው። ችግሩ ከፍች ጋር የሚያያዝ በመሆኑ፣ ቤተሰብ እንዳይበተን፣ ልጆችም በሁለቱም ወላጆቻቸው እንዲያድጉ፣ በሚፈጠረው ፍችም አንዱ ወገን ተጎጂ መሆኑ ስለማይቀር በተቻለ መጠንም በስምምነት እንዲያልቅ በሕግ ክፍሉ በኩል ተገቢው ምክር ይሰጣል።

ከቢሮው አቅም በላይ ሆኖ ሲገኝ ግን እንደ አስፈላጊነቱ ወደ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ይላካል። ጉዳያቸው ወደነዚህ ተቋማት ሲላክም የቢሮው እገዛ አይለያቸውም። የገንዘብ እና የተለያየ አቅም ማነስ ሊኖራቸው ስለሚችል ጉዳያቸውን ለመከታተል እንዲችሉ የተለያየ ድጋፍ ይደረግላቸዋል።

የተለያየ ችግር ሲያጋጥማቸው የት መሄድ እንዳለባቸው እንኳን የማያውቁ ሴቶች መኖራቸውን የጠቀሱት ወይዘሮ መፍቱሀ፤ በዚህ በኩል ቢሮው ብዙዎችን ማገዝ ችሏል ብለዋል። የቢሮው መኖር አስፈላጊ እንደሆነ እየሰጠ ካለው አገልግሎት መገንዘብ መቻሉንም አመልክተዋል። ሴቶቹ አገልግሎት ማግኘታቸው ብቻ ሳይሆን፤ በእነርሱ ላይ ጥቃት ወይንም ጉዳት ለማድረስ የሚነሳሳ እንኳን ቢኖር ጉዳያቸውን የሚከታተልላቸው ተቋም መኖሩን በመገንዘብ ከድርጊቱ ሊቆጠብ እንደሚችል ነው ያስረዱት።

ቢሮው ሴቶች ከሚያጋጥሟቸው የተለያዩ ችግሮች፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ክፍተቶች አንጻር ምን ያህሉን ማቅለል ችሏል? ወይንም ሥራውን በስኬት ያየዋል? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ወይዘሮ መፍቱሀ በሰጡት ምላሽ፤ ብዙ ሥራዎች እንደሚቀሩና የተሻለ ሥራን ለመሥራት አቅም በፈቀደ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው የሚናገሩት።

በ2016 በጀት ዓመት በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ በተከናወኑ ሥራዎች ለቢሮው ከሚበጀተው በጀት በተጨማሪ አጋሮችን በማፈላለግ በተሰራ ሥራ ለ1ሺ 5መቶ ሴቶች የአቅም ግንባታ ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል። 27 ሴቶች ደግሞ ለሥራ መነሻ የሚሆን ወደ 55ሺ ብር ብድር እንዲያገኙ ተደርጎ ወደ ሥራ ገብተዋል። በተጨማሪም ለሴቶችና ወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር ከሚሰሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመሆንም ሴቶች ምን ያህል የሥራ እድል እየተፈጠረላቸው እንደሆነ እየሠራን እንገኛለን።

ግርዛት፣ ያለእድሜ ጋብቻ ወዘተ በሴቶች ላይ ከሚፈጸም ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ጥቂቶቹ ናቸው። በዚህ ረገድ የተሠሩ ሥራዎችን በተመለከተም ወይዘሮ መፍቱሀ እንደገለጹት፤ በአካባቢው ላይ ከሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አንዱ ያለእድሜ ጋብቻ ነው። በዚህ ምክንያት ሴት ልጆች ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ይገደዳሉ። በተጨማሪም ለኢኮኖሚያዊ ጫና ይዳረጋሉ ልጆች ወልደውም ይቸገራሉ።

ሌላው ጠለፋ ነው። አሁን ላይ እየቀነሰ የመጣ ቢሆንም እንደ አንድ ተግዳሮት ይወሰዳል። ግርዛትም በገጠሩ ሙሉ ለሙሉ አልጠፋም። ሃይማኖትን መሠረት አድርጎ ተደራራቢ ጋብቻም ይፈጸማል። በአጠቃላይ ሴቶችን ተጎጂ የሚያደርጉትን ሁሉ ለመከላከል የሰዎችን ግንዛቤ በማሳደግ ነው። በዚህ ላይ እየሰራን ነው። ወይዘሮ መፍቱሀ ቢሮው በሚችለው ሁሉ እየሠራ ያለውን በዚህ መልኩ የገለጹ ቢሆንም ሴቶችን ተጠቃሚ የማድረጉ ሥራ ከዚህም በላይ ተጠናክሮ መከናውን ይኖርበታል።

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን የካቲት 29 /2016 ዓ.ም

Recommended For You