
አሜሪካ ለጋዛ የመጀመሪያውን ሰብአዊ እርዳታ ከ30 ሺህ በላይ ምግቦችን በሦስት ወታደራዊ አውሮፕላኖች አማካይነት በፓራሹት ከአየር ላይ ማቅረቧን አስታወቀች።
ከዮርዳኖስ አየር ኃይል ጋር በጥምረት የተካሄደው ይህ ድጋፍ በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ለጋዛ ይሰጣል ተብሎ ከታወጀው የመጀመሪያው ነው።
ሐሙስ ዕለት ሕዝቡ ከመኪና ላይ እርዳታ ለመቀበል ሲሞክር ቢያንስ 112 ሰዎች ከተገደሉ በኋላ ፕሬዚዳንቱ እርዳታውን ለማጠናከር ቃል ገብተው ነበር።
የአየር ድጋፉ ወደ ጋዛ የተላከው አንድ ከፍተኛ የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣን በጋዛ ለስድስት ሳምንታት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ዕቅድ መኖሩን ከተናገሩ በኋላ ነው።
የባይደን አስተዳደር ባለሥልጣን ቅዳሜ ዕለት እንደተናገሩት፤ እስራኤል አዲሱን የተኩስ አቁም ስምምነት “ይብዛም ይነስም ተቀብላለች” ብለዋል።
“ሐማስ የተጋላጭ ታጋቾችን ማለትም የታመሙትን፣ የቆሰሉትን፣ አዛውንቶችን እና ሴቶችን ለመልቀቅ ከተስማማ ከዛሬ ጀምሮ በጋዛ ለስድስት ሳምንታት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈጻሚ ይሆናል”ሲሉ ስማቸው ያልተጠቀሰው ባለሥልጣን ተናግረዋል።
አንድ ባለሥልጣን እንደተናገሩት፤ በስምምነቱ ዙሪያ አንዳንድ ቴክኒካዊ ጉዳዮች አሁንም መፍትሄ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል። ለምሳሌ ምን ያህል የፍልስጤም እስረኞች በሐማስ በተያዙ ታጋቾች ምትክ እስራኤል ትለቃለች የሚለው አንዱ ነው።
ቅዳሜ ዕለት ሲ-130 የተባሉ የማጓጓዣ አውሮፕላኖች በጋዛ የባሕር ዳርቻ ላይ ከ30 ሺህ በላይ ምግቦችን ከአየር ወደ መሬት መጣላቸውን የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
“ይህ የአየር እርዳታ አቅርቦት በተሽከርካሪ የሚገባውን የእርዳታ ፍሰት ማስፋትን ጨምሮ ወደ ጋዛ ተጨማሪ እርዳታ ለማስገባት የሚደረጉ ቀጣይ ጥረቶች አካል ነው” ሲል አክሏል።
ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ግብፅ እና ዮርዳኖስን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት በተመሳሳይ መንገድ እርዳታ ወደ ጋዛ ያደረሱ ሲሆን፣ ይህ ግን ለአሜሪካ የመጀመሪያዋ ነው።
የአሜሪካ አስተዳደር ባለሥልጣናት የሐሙሱ “አሳዛኝ ክስተት፣ ለአስከፊው የሰብአዊ ሁኔታ ምላሽ ለመስጠት የሰብአዊ እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲደርስ ማስፋፋት እና ማስቀጠል ያለውን ጠቀሜታ” አጉልቶ አሳይቷል ብለዋል።
የእርዳታ ድርጅቶች ከአየር ላይ ወደ መሬት የእርዳታ አቅርቦትን መጣል በችግር ላይ ላሉት የጋዛ ነዋሪዎች ከሚያስፈልገው ድጋፍ አንጻር በቂ እና አስተማማኝ አይደሉም ብለዋል።
የጋዛ ከተማ ነዋሪው ሜድሃት ታሄር ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገረው፤ እንዲህ ዓይነቱ ዘዴ ለሚጠበቀው እርዳታ በቂ ምላሽ አይደለም።
“ይህ ለትምህርት ቤት በቂ ይሆናል? ይህ ለ10 ሺህ ሰዎች በቂ ነው? እርዳታን በድንበር በኩል መላክ በፓራሹት ከአየር ከማውረድ የተሻለ ነው” ብሏል።
ፕሬዚዳንት ባይደን አርብ ዕለት በሰጡት መግለጫ፤ ዩናይትድ ስቴትስ “የጋዛ ነዋሪዎች የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ እንዲያገኙ ብዙ የጭነት መኪናዎችን እና በርካታ መንገዶችን እንድታመቻች እስራኤልን አጥብቀን እንጠይቃለን” ብለዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ የእስራኤል የጦር ካቢኔ አባል የሆኑትን ቤኒ ጋንትዝን ሰኞ ዕለት ዋሽንግተን ውስጥ እንደሚገናኙ አንድ የዋይት ሐውስ ባለሥልጣንን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።
በሐሙሱ ክስተት በጋዛ ከተማ ደቡብ ምዕራብ ጫፍ ላይ የእርዳታ መኪኖችን የከበቡ 112 ሰዎች ሲገደሉ ከ760 በላይ ቆስለዋል።
በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተኩስ በመክፈቷ ፍልስጤማውያኑ ሕይወታቸው ማለፉን ጠቅሶ ሐማስ ቢከስም ቴል አቪብ ግን የማስጠንቀቂያ ጥይት ሲተኮስ በተፈጠረ መረጋገጥ አደጋው መድረሱን ገልጻለች።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች አስተባባሪ (ኦቻ) የጋዛ ንዑስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ጊዮርጊዮስ ፔትሮፖሎስ እርሳቸው እና ወደ አል-ሺፋ ሆስፒታል የተላከው ቡድን በጥይት የተጎዱ በርካታ ሰዎችን ማግኘታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሐማስ በበኩሉ ቅዳሜ ዕለት በደቡባዊ ጋዛ በራፋህ በሚገኝ የመጠለያ ጣቢያ ላይ በእስራኤል በተፈጸመ የቦምብ ጥቃት በትንሹ 11 ሰዎች መገደላቸውን ተናግሯል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም ጥቃቱን “አስደንጋጭ” ሲሉ ጠርተውታል። የእስራኤል ጦር በበኩሉ በአካባቢው በሚገኙ እስላማዊ ጂሃድ ታጣቂዎች ላይ “ዒላማውን የጠበቀ ጥቃት” ፈጽሜያለሁ ብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በጣም ትንሽ እርዳታ ባገኘችው እና 300 ሺህ የሚገመቱ ሰዎች በአነስተኛ ምግብ ወይም ውሃ በሚኖሩባት ሰሜናዊ ጋዛ ውስጥ ረሃብ ሊፈጠር እንደሚችል አስጠንቅቋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን የካቲት 26 ቀን 2016 ዓ.ም