የምን ጊዜም የቦክስ ስፖርት ንጉሡ መሐመድ አሊ የዓለም የቦክስ ቻምፒዮንና ታላቅ የቡጢ ተፋላሚ ብቻ አልነበረም። የሠብዓዊ መብት ተሟጋች፤ የጥቁር ሕዝቦች ሰንደቅ፤ በመላው ዓለም በስፖርትና በታላቅ ስብዕና ተምሳሌትም ጭምር ነው። ብዙዎች ቦክስ ስፖርት ሳይሆን የጥጋበኞች ድብድብ አድርገው ከመሳል አስተሳሰብ አውጥቶ የቦክስን ስፖርት ጥበባዊ ገፅታ በማላበስ ተወዳጅና አሁን ላይ በዓለማችን በአንድ ጊዜ በርካታ ሚሊዮን ዶላሮች የሚያሳቅፍ ግንባር ቀደምት ስፖርት እንዲሆን ተፅዕኖውን አሳርፏል። ሙዚቀኛም ሆኖ ለሂፕሆፕና ራፕ የሙዚቃ ስልቶች ጉልህ ሚና ተጫውቷል።
በቦክስ ስፖርት ታሪክ የምንጊዜም ምርጥ ቦክሰኛ የተባለውም በተለያዩ የቡጢ ፍልሚያዎች ዘመን የማይሽራቸው ገድሎችን በማስመዝገብ ነው። መሐመድ አሊ የቦክስ ጓንቱን ሰቅሎ ስፖርቱን በቃኝ ብሎ ከተሰናበተ ከሦስት ዓመታት በኋላ እኤአ በ1984 ከስፖርቱ ልምድ ጋር በተያያዘ ፓርኪንሰንስ በተባለ በሽታ ተይዞ ነበር፡፡ ለሰላሳ ሁለት ዓመታት ከዚህ ህመሙ ጋር ሲታገል ቆይቶ ከአምስት ዓመት በፊት በሰባ አራት ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡
መሐመድ አሊ ወደ ቦክስ ሕይወት የመጣበት አጋጣሚ አስገራሚ ነው። የአስራ ሁለት ዓመት ልጅ በነበረበት ወቅት ብስክሌቱ ተሰርቆበት በሊውስቪል ኬንታኪ ለሚገኝ ጆ ማርቲን ለተባለ ፖሊስ አመለከተ፡፡ «የሰረቀኝን ባገኘው ልክ አገባው ነበር» ብሎም ምሬቱን ይገልፃል፡፡ የቦክስ አሠልጣኝ የነበረው ፖሊስ ትንሹን መሐመድ ራሱን እንዴት ከጥቃት መከላከል መማር እንዳለበት መከረው። የተወሰኑ ሥልጠናዎችን ሲወስድ ቆይቶም ብስክሌቱ ከተሰረቀች ከስድስት ሳምንታት በኋላ በሰፈሩ በአንድ አማተር የቦክስ ግጥሚያ ላይ ተሳተፈና በነጥብ አሸናፊ መሆን ቻለ፡፡ ይህች አጋጣሚም በዓለም ለገነነበት ስፖርት የመሠረት ድንጋይ ነች።
መሐመድ የትውልድ ስሙ ካሴስ ክሌይ ቢሆንም በ19ኛው ክፍለ ዘመን ባሮችን ነፃ ለማውጣት በታገሉ ታላቅ ሰው መታሰቢያነት የወጣለት ስም ነበር፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ከባድ ሚዛን ቻምፒዮን ከሆነ በኋላ በማግስቱ ስሙን ለመቀየር ወሰነ፡፡ የነፃነት ታጋዩን ማልኮለም ኤክስ ከጎኑ አድርጎ በሰጠው መግለጫ «ዘ ኔሽን ኦፍ ኢስላም» የተባለውን ተቋም መቀላቀሉን በማሳወቅ የባርያ ስም ይለው የነበረውን ካሴስ ክሌይ በመቀየር በቀድሞ ስሙ ላለመጠራት ወሰነ። በወቅቱ «ኔሽን ኦፍ ኢስላምን» ይመራ የነበረው ኤልጅያህ መሃመድ እኤአ በ1964 ላይ መሐመድ አሊ የሚለውን ስም ካወጣለት በኋላ እሱን በማፅደቅ እስከ ሕይወት ዘመኑ መጨረሻ ተጠራበት።
ለሃያ አንድ ዓመታት በፕሮፌሽናል ቦክሰኛነት በርካታ የቡጢ ፍልሚያዎችን ከአሜሪካ እስከ አፍሪካ እንዲሁም ሌሎች ዓለማት ላይ የተፋለመው መሐመድ አሊ ለሦስት ጊዜ የዓለም ከባድ ሚዛን ቻምፒዮን ሆኗል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም የከባድ ሚዛን ሻምፒዮን ለመሆን የበቃውም የሃያ ሁለት ዓመት ወጣት እያለ ነው። ዓለም አቀፍ ደረጃ ባላቸው ፕሮፌሽናል የቦክስ ግጥሚያዎች ላይ ስልሳ አንድ ጊዜ ተሳትፎ ሃምሳ ስድስቱን ማሸነፍም ችሏል። ከእነዚህ ድሎቹም ሰላሳ ሰባት ያህሉን ተጋጣሚዎቹን በበቃኝ በመዘረር ነው። አስገራሚው ነገር በሰላሳ አንድ ተከታታይ የቦክስ ግጥሚያዎች ሳይሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሸነፈው የክፍለ ዘመኑ ምርጥ ፍልሚያ በተባለው ግጥሚያ በጆ ፍሬዘር ነበር። በፕሮፌሽናል የቦክሰኛነት ዘመኑም ሽንፈትን የቀመሰው አምስት ጊዜ ብቻ ነው።
የመጨረሻውን ፍልሚያም እኤአ በ1981 ከትሬቨር ቤሪቢክ ጋር በማድረግ ስፖርቱን በቃኝ ብሏል። አሜሪካ በቬትናም በ1970ዎቹ መጀመሪያ ያደረገችውን ጦርነት በመቃወሙ ለሦስት ዓመታት ከፕሮፌሽናል ቦክስ ውድድሮች ታግዶ የቆየው መሐመድ አሊ እገዳው በተጣለበት ወቅት ከአስር የማያንሱ የዓለም ከባድ ሚዛን ቻምፒዮናዎች ባያመልጡት አሁን ካሉት የበለጠ በርካታ ክብሮችን መጎናፀፍ ይችል ነበር። በዚህም ከሰማንያ ሚሊዮን ዶላር በላይ ሀብት ማፍራት ችሏል። ለዚህ ሀብቱም ምንጭ ስፖርቱን ከተሰናበተ ወዲህ ግንባር ቀደም ተዋናዮቹ ስሙንና ምስሉን የሚጠቀሙ ከአርባ በላይ ኩባንያዎች ናቸው። ታሪካዊው ኢትዮጵያዊ አትሌት አበበ ቢቂላ በ1960 የሮም ኦሊምፒክ በባዶ እግሩ ሮጦ ለጥቁር ሕዝቦች የመጀመሪያውን የማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ሲያስመዘግብ መሐመድ አሊም በቦክስ የወርቅ ሜዳሊያ አጥልቆ ነበር። ሁለቱ ታሪካዊ የጥቁር ሕዝቦች ከዋክብት ፊርማቸውን ተለዋውጠውም ነበር። ይሁንና መሐመድ አሊ ይህን የወርቅ ሜዳልያውን ለሀገሩ ከማበርከት ይልቅ በሊውስ ቪል ግዛት በሚገኘው የኦሃዮ ወንዝ ጨምሮታል። ሜዳልያውን ለአሜሪካና ለትውልድ ከተማው ሊውስ ቪል ቢቀዳጅም በርገር የመግዛት መብት ባለመኖሩ ተቃውሞውን ለመግለፅ ነበር ይህን ርምጃ የወሰደው።
በ1996 ሀገሩ አሜሪካ ባስተናገደችው የአትላንታ ኦሊምፒክ ችቦውን እንዲለኩስ ከመደረጉ ባሻገር ወንዝ የጨመረው የወርቅ ሜዳልያ ምትክ ሌላ ሜዳሊያ በአንገቱ ተጠልቆለታል። በ1980 በላስቬጋስ በተካሄደ የቡጢ ፍልሚያ በቴክኒካል የበቃኝ ውጤት ቢሸነፍም መሐመድ ትልቁን ክፍያ ስምንት ሚሊዮን ዶላር ያፈሰው በዚያ ውድድር ነው። «ራምብል ኢን ዘ ጃንግል» በተባለውና እስካሁንም ከስፖርት ቤተሰቡ አዕምሮ በማይጠፋው በአፍሪካ ምድር በተካሄደው ፍልሚያ መሐመድ አሊ ምን ጊዜም ይታወሳል።
እኤአ በ1974 መሐመድ አሊ በሰላሳ ሁለት ዓመቱ ሽንፈትን አይቶ ከማያውቀው ከሃያ አምስት ዓመቱ ጆርጅ ፎርማን ጋር በኮንጎ ኪንሻሳ የቡጢ ፍልሚያ ገጥሞ ነበር። በወቅቱ የኮንጎ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሞቡቱ ሴሴሴኮ ለሁለቱ ቦክሰኞች በኪንሻሳ ከተማ እንዲጫወቱ በነፍስ ወከፍ አምስት ሚሊዮን ዶላር ከፍሏቸው ነበር፡፡
መሐመድ አሊ በውድድሩ ስምንተኛ ዙር ላይ በዝረራ ቢሸነፍም ከወጣት ተፋላሚው ጋር ያደረገው እልህ አስጨራሽ የቡጢ ፍልሚያ እስካሁንም ከህሊና የሚጠፋ አይደለም። በ1970 የዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ መታሰቢያ ሽልማት የተቀበለው መሐመድ አሊ፤ የዓለም አቀፋዊ ወዳጅነት ተምሳሌት ሆኖም ያውቃል። የተባበሩት መንግሥታት የሰላም መልዕክተኛ ሆኖም ከ1998 እስከ 2008 በታዳጊ ሀገራት በመዘዋወር አገልግሏል። በሕይወቱ ዙሪያ በሚያተኩሩ ጥናታዊና የሙሉ ጊዜ ፊልሞች የሠራ ሲሆን በተለይ ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀውና ዘ ግሬተስት በተባለ ፊልም ላይ ተውኗል፡፡ የሕይወት ታሪኩ ላይ በማተኮር ከተሠሩ ፊልሞች የኦስካር ሽልማት በጥናታዊ ፊልም ዘርፍ ያገኘው «ዌን ዊ ዌር ኪንግስ»ና ዝነኛው የሆሊውድ ተዋናይ ዊል ስሚዝ በመሪ ተዋናይነት የተጫወተው «አሊ» የተባሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ታላቁን የደቡብ አፍሪካ ነፃነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ከእስር እንደተፈቱ በአካል ተገኝቶ ደስታውን ለመግለፅ መሐመድን የቀደመው የለም። በአካል ካገኛቸው ታላላቅ መሪዎች የእንግሊዟ ንግሥት ኤልሳቤጥ፤ የሮማው ሊቃነ ጳጳስ ፖፕ ጆን ፖል፤ የኩባው መሪ ፊደል ካስትሮ እንዲሁም የኢራቁ ሳዳም ሁሴን ይገኙበታል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 24 ቀን 2016 ዓ.ም