በኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው አንደኛው ዙር ብሔራዊ የቦክስ ቻምፒዮና ነገ ይጠናቀቃል፡፡ ጠንካራ ፉክክር ሲያስተናግድ የቆየው ይህ የቡጢ ቻምፒዮና በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ኢትዮጵያን የሚወክሉ ቦክሰኞች እንደሚመረጡበት ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡
በአራት ዙሮች የሚካሄደው ብሔራዊ የቦክስ ቻምፒዮና የዘንድሮውን ዓመት የመጀመሪያ ዙር ውድድር በራስ ኃይሉ ትምህርትና ስልጠና ማዕከል በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ከየካቲት 12/2016 ዓ.ም አንስቶ በደማቅ ሁኔታ ሲከናወን የቆየው ውድድር ነገ እንደሚፈፀምም ታውቋል።
በውድድሩ ከተሳተፉ ዘጠኝ የቦክስ ክለቦች መካከል ስድስት የሚሆኑት በሁለቱም ጾታ ተፎካካሪዎች ያቀረቡ ሲሆን፤ የግል ተወዳዳሪዎችን ጨምሮ በድምሩ 106 ቦክሰኞች የቻምፒዮናው ተሳታፊ መሆናቸው ተጠቁሟል።አዲስ አበባ ፖሊስ፣ ኦሜድላ፣ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች፣ ኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ፣ ፋሲል ከተማ፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ወላይታ ጦና፣ ሀዲያ ሆሳዕና እና የጋሞ ክለቦች የውድድሩ ተሳታፊ ናቸው፡፡
በጠንካራ ፍልሚያዎች አጓጊ ፉክክር ታጅቦ እየተካሄደ በሚገኘው በዚህ ውድድር ላይ የተሻለ ብቃት ያሳዩ ተወዳዳሪዎች ለብሔራዊ ቡድን በመመረጥ በቅርቡ ለሚካሄዱ አህጉርና ሀገር አቀፍ ውድድሮች ላይ ይካፈላሉ፡፡ በዚህም መሰረት በፓሪስ ለሚካሄደው የ2024 ኦሊምፒክ የማጣሪያ ውድድር ከሳምንት በኋላ በጣሊያን የሚደረግ ሲሆን፤ ቀጥሎ በሚካሄደው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ላይም ኢትዮጵያን የሚወክሉ ይሆናል፡፡ ሌላኛው ውድድር ደግሞ በደቡብ አፍሪካ የሚደረግ የማንዴላ ካፕ እንዲሁም ሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ እንደሚሆኑ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ማሩ ገልጸዋል፡፡
ውድድሩ በተለያዩ ክብደቶች እየተካሄደ ሲሆን፤ በወንዶች መካከል በ48 ፣ በ51 ፣ በ54 ፣ በ57፣ በ60፣ በ63.5፣ በ69፣ በ75፣ በ80፣ በ92 እና ከ92 ኪሎ ግራም በላይ በርካታ ፉክክሮች ተደርገዋል፡፡ በሴቶች ደግሞ በ48፣ በ50 ፣ በ60 ፣ በ63 እና በ67 ኪሎ ግራም ቦክሰኞች ሲፎካከሩ ቆይተዋል፡፡
በውድድሩ በተለይም ወጣትና ተተኪ ቦክሰኞች ያላቸውን ተስፋ አሳይተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ይነሳ የነበረውን የልምድ ማነስ ችግር ለመቅረፍም መሰል ውድድሮች መካሄዳቸው ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው የተጠቆመ ሲሆን፤ በአህጉር እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች በሚኖራቸው ተሳትፎም ከዚህ ቀደም በስፖርቱ የታየውን ውጤታማነት ማሳደግ ይቻላል ተብሎ ታምኖበታል፡፡
ይህ ውድድር ኢትዮጵያ የአፍሪካን ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትነት መምራት ከጀመረች በኋላ የተካሄደ የመጀመሪያው ውድድር ሲሆን፤ በስፖርቱ ጥሩ መነቃቃት መፈጠሩን ለመታዘብ ተችሏል፡፡ የክለቦች ቁጥር መጨመርና በፉክክሩ ላይ ተሳታፊ የሆኑ ቦክሰኞች ተሳትፎ ለስፖርቱ እድገት ተስፋ የታየበት ሆኗል፡፡
ቻምፒዮናውን ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ልዩ የሚያደርገው የውድድሩ ተሳታፊ ቦክሰኞች ሙሉ የጤና ምርመራ ማድረግ በመቻሉ እንደሆነ የጽህፈት ቤት ኃላፊው ገልፀዋል፡፡ ቦክስ ከፍልሚያ ስፖርቶች መካከል አንዱ እንደመሆኑ በተለይ በንክኪ፣ በላብ፣ በደም… የሚተላለፉ የጉበት እና ኤች አይቪ ኤድስ በሽታዎችን እንዲሁም እርግዝናን በአስገዳጅ ሁኔታ የሚለይበት ምርመራ ለሁሉም ተወዳዳሪዎች ተደርጓል፡፡ ይህ ሁኔታ በሀገር ውስጥ በሚደረጉ ውድድሮች ጠንካራ ባይሆንም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚደረጉ ውድድሮች ግን ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ከዚህ ቻምፒዮና አንስቶ ትኩረት እንደሚሰጠው የተገለጸ ሲሆን፤ በምርመራው በሽታዎቹ እንዳለባቸው የተረጋገጠባቸው ቦክሰኞችም ፌዴሬሽኑ ባቋቋመው የህክምና ቡድን አማካኝነት የጤና እንዲሁም የስነልቦና ክትትል ይደረግላቸዋል፡፡
ከክለቦቻቸውና አሰልጣኞች ጋርም ከውጤት ባለፈ ጤናቸውን ቅድሚያ ሰጥተው አገግመው በሚመለሱበት ሁኔታ ላይ ንግግር መደረጉንም አቶ ስንታየሁ ተናግረዋል።
በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች በመዘዋወር በአራት ዙር የሚደረገው ብሔራዊ የቦክስ ቻምፒዮና ዘንድሮ መነሻውን አዲስ አበባ በማድረግ ከየካቲት 12/2016 ዓ.ም አንስቶ ሲካሄድ ቆይቶ ነገ ፍጻሜውን ያገኛል፡፡ ቀጣዮቹ ቻምፒዮናዎች ደግሞ በድሬዳዋ እና አርባ ምንጭ ከተሞች በማድረግ ማጠቃለያውን አዲስ አበባ ላይ ለማካሄድ መታሰቡንም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2016