ፕሬዚዳንት ባይደን 1.2 ቢሊዮን ዶላር የተማሪዎችን ዕዳ ሰረዙ

በጋዜጣው ሪፖርተርየባይደን አስተዳደር 153 ሺህ ተበዳሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ 1.2 ቢሊዮን ዶላር የትምህርት ዕዳ መሰረዙን አስታወቀ።

የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከዚህ ቀደም ከ40 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ አሜሪካውያን የትምህርት ዕዳቸውን ለመሰረዝ ፕሬዚዳንት ባይደን አቅርበው የነበሩትን ዕቅድ ማገዱ ይታወሳል። ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ባይደን ሥልጣናቸውን ተላልፈው በቢሊዮን የሚቆጠር የትምህርት ዕዳ ለመሰረዝ መወሰናቸው ትክክል አይደለም ሲል ቀልብሶታል።

የአሁኑ ዕዳ ስረዛ የሚመለከተው በክፍያ ዕቅድ ውስጥ የተካተቱ እና የተወሰኑ መስፈርቶችን ለሚያሟሉ ብቻ ተግባራዊ ይሆናል። የዕዳ ስረዛው የሚመለከታቸው በባይደን አስተዳደር በተዘረጋው የፍቃደኝነት የክፍያ ዕቅድ ውስጥ የተመዘገቡና ቢያንስ ለ10 ዓመታት ክፍያ ሲፈጽሙ የቆዩ እና መጀመሪያውኑ 12 ሺህ ዶላር ወይም ከዚያ በታች የተበደሩትን የሚመለከት ይሆናል።

የዕዳ ስረዛው የሚመለከታቸው አሜሪካውያን ከተነገራቸው በኋላም ወዲያውኑ ተፈጻሚ እንደሚሆንም ተገልጿል። «በተለይም አነስተኛ ዕዳ ያለባቸውን የማኅበረሰብ ኮሌጆች የቀድሞ ተማሪዎች እና ሌሎች ተበዳሪዎችን የሚጠቅም ይሆናል። አብዛኛውንም ከትምህርት ዕዳ በፍጥነት ነፃ አውጥቶ ወደ ትክክለኛው መስመር ያስገባቸዋል» ሲልም ዋይት ሃውስ በመግለጫው አትቷል።

በትምህርት ዲፓርትመንት መረጃ መሠረት በባይደን አስተዳደር በተቋቋመው የክፍያ ዕቅድ ውስጥ የተመዘገቡ አሜሪካውያን ቁጥር ሰባት ነጥብ አምስት ሚሊዮን መሆኑን ነው። በዚህ ዕቅድ ውስጥ የተመዘገቡት ሁሉም ሰዎች ከ20-25 ዓመታት ውስጥ ክፍያ ከከፈሉ በኋላ በዕዳ ስረዛ ውስጥ ለመካተት ብቁ ይሆናሉ።

ሆኖም ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አነስተኛ ዕዳ ላለባቸው ግለሰቦች ጊዜውን በማሳጠር ለአስር ዓመታት ያህል ብድራቸውን የከፈሉ ሰዎች በዕዳ ስረዛው ፕሮግራም መካተት እንዲችሉ አድርገዋል። የሀገሪቱ የትምህርት ዲፓርትመንት በዕዳ ስረዛው ለመካተት ብቁ የሆኑትን ነገር ግን በዚህ የክፍያ ዕቅድ ውስጥ ያልተመዘገቡ ሰዎችን ማነጋገር እንደሚጀምርም ተገልጿል።

ባይደን እስካሁን ድረስ ፕሬዚዳንታዊ ሥልጣንን በመጠቀም 3.9 ሚሊዮን ለሚጠጉ ሰዎች 138 ቢሊዮን ዶላር የትምህርት ዕዳቸውን መሰረዛቸውንም ዋይት ሃውስ ገልጿል። የአሜሪካ የትምህርት ሥርዓትን በሚያጠናው የትምህርት መረጃ ኢኒሺዬቲቭ መሠረት የአሜሪካ የትምህርት ዕዳ አንድ ነጥብ 77 ትሪሊዮን እንዲሁም አንድ ሰው በአማካኝ ከ37 ሺህ ዶላር በላይ ብድር አለበት።

ጆ ባይደን በምርጫ ቅስቀሳ ሰሞን ዕዳ መሰረዛቸው ለምርጫው እንዲያመቻቸው ነው የሚሉ አልጠፉም። እሳቸው ግን በቅርቡ የ26 ሰከንድ ርዝማኔ ባለው የቪዲዮ መልዕክት አርፍደው የቲክቶክ ተጠቃሚ መሆናቸውን ይፋ አድርገው ቅስቀሳቸውን አጣጡፈውታል።

የፕሬዚዳንቱ የቲክቶክ ተጠቃሚነት ወሬ የተሰማው አጫጭር የቪዲዮ ምስሎች መጋሪያው የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአብዛኛው በሪፐብሊካን ፓርቲው ወገኖች እና በባይደን አስተዳደር ጭምር በዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ከፍተኛ ትችት ሲሰነዘርበት ከቆየ በኋላ ነው።

በቻይናው ኩባንያ ባይት-ዳንስ ንብረት የሆነው ቲክቶክ በበርካታ የዩናይትድ ስቴትስ ፖለቲከኞች ‘የቤጂንግ የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ነው’ የሚል ክስ ሲቀርብበት የቆየ ነው። ይሁን እንጂ ኩባንያው ውንጀላውን አጥብቆ ያስተባብላል።

በባይደን የምርጫ ዘመቻ ስም የወጣው የእሁዱ ቪዲዮ ከዴሞክራት ፓርቲው ወገን የሆኑት የ81 አመቱ ፕሬዚዳንት ባይደን፡ ከፖለቲካ ነክ ጉዳዮች እስከ የዩናይትድ ስቴትስ እግር ኳስ የፍጻሜ ዋንጫ ውድድር በተለያዩ ርዕሶች ዙሪያ ያላቸውን ሃሳብ በጨዋታ ለዛ ሲያነሱ ያሳያል።

ሱፐር ቦል በመባል ከሚታወቀው የውድድሩ የፍጻሜ ጨዋታ እና የተለየ ትኩረት ዘንድሮ ለዚያ በተሰየመው ድምጻዊ አሸር በተመራው ከሚስበው የጨዋታው አጋማሽ ትርኢት የቱን እንደሚመርጡ ተጠይቀው፣ ‘ጨዋታውን መመልከት’ ብለዋል።

ኮከብ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኟ ቴይለር ስዊፍት ዝነኛነቷን ተጠቅማ ባይደንን ለመጥቀም የጠነሰሰችው ‘ምስጢራዊ ውጥን አለ’ የሚለውን የቀኝ አጥባቂዎች የሴራ ወሬ አስመልክቶም ለተጠየቁት “ብነግርህ ችግር ውስጥ እገባለሁ”ሲሉ በጨዋታ መልሰዋል።

በተያያዘ በ2024ቱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጽንስ የማቋረጥ መብት ለመራጮች ቁልፍ ጉዳይ እንደሚሆን ዋይት ሃውስ ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን የካቲት 15/2016

Recommended For You