የማዕድን ሀብትን የሀገር ኢኮኖሚ አውታር የማድረጉ ጥረት

ኢትዮጵያ በርካታ የማዕድናት ሀብት ካላቸው የአፍሪካ ሀገራት አንዷ እንደሆነች ይታወቃል። በተለይም ወርቅና ፕላቲኒየም የመሳሰሉ የከበሩ ማዕድናት መገኛ እንደሆነች ይጠቀሳል። ከወርቅና የከበሩ ማዕድናት ተጨማሪ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ የኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ማዕድናት በስፋት ይገኛሉ፡፡ ፖታሽ፣ ኖራ፣ የድንጋይ ከሰል፣ ታንታላይት፣ ፊልድስፖር፣ ኳርትዝ፣ ዶሎማይት ያሉ የኢንዱስትሪ ማዕድናት በተለያዩ ክልሎች እንደሚገኙ በጥናት ተረጋግጧል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እንደ ብረትና የድንጋይ ከሰል የመሳሰሉ ለኢንዱስትሪ ልማት ዋነኛ ግብዓት የሆኑ ማዕድናት በስፋት እየተገኙባት እንደሆነ ይነገራል። እነዚህ ማዕድናት ታድያ በስፋት ከሚገኝባቸው አካባቢዎች መካከልም ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ዋነኛው ተጠቃሽ ነው። ሱማሌና አፋር እንዲሁም ሌሎችም ክልሎች ላይ መጠናቸው ይለያይ እንጂ በዓለም ገበያ እጅግ ተፈላጊ የሆኑ በርካታ የማዕድን ሀብቶች ይገኛሉ።

በአንዳንድ አካባቢዎች ሰፊ የማዕድን ሀብት ስለመኖሩ ለዘመናት በአካባቢው ማህበረሰብ ቢታወቅም በተጨባጭ በሳይንሳዊ መንገድ ጥናት በማድረግ መጠኑና አይነቱን ለይቶ ለሀገር ጥቅም ማዋል ላይ ሰፊ ክፍተት ይታያል፡፡ ይልቁንም ማህበረሰቡ በራሱ ባህላዊ የአመራረት ሂደት ማዕድን እያወጣ የተለያዩ ቁሳቁስ በማውጣት ለዘመናት የቆየ ታሪክ እንደሆነ ይታወቃል። መረጃዎች እንደሚያሳዩትም ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የሀገሪቱ ዜጎች በባህላዊ ማዕድን ምርት የተሰማሩ ሲሆን፤ አብዛኞቹ የሚያመርቱት ወርቅ ነው፤ በአንዳንድ አካባቢዎችም እንደ ኦፓል ያሉ የጌጣጌጥ ማዕድናት እንዲሁም የኢንዱስትሪ አለኝታ እንደሆነ የሚጠቀስለት የብረት ማዕድን በተወሰነ ደረጃ በማውጣት እያለሙ የሚጠቀሙ እንዳሉም በተለያዩ ጊዜያት የሚወጡት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ይሁንና ታዲያ የእነዚህ ማዕድናት መጠን በውል የማይታወቁ አይደሉም፡፡ ለዚህም ማዕድናቱ በአብዛኛው በባህላዊ መንገድ የሚወጡና የማውጣት ሂደቱም ሳይንሳዊ መንገድን ያልተከተለ መሆኑ ዋናው ምክንያት ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ታዲያ ጥቅም ላይ ከሚውለው ማዕድን ይልቅ ለብክነትና ለህገወጥ ንግድ የሚዳረገው እጅጉን የሚልቅ እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ያነሳሉ፡፡ የሀገሪቱ ዋነኛ የውጪ ንግድ የሆነው የወርቅ ምርት እንኳን ዛሬም ድረስ ከሚድሮክ ጎልድ በስተቀር ዘመኑን በሚዋጅ የአመራረት ሂደትን እየተከተለ አይደለም። ይህም ሀገሪቱ ከዘርፉ ልታገኝ የሚገባትን ገቢ ዝቅተኛ ያደረገ መሆኑ የዘርፉ ተዋናዮች የሁልጊዜም ቁጭት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከዘርፉ ተዋናዮች ባለፈም ሀገርና ሕዝብ ከዘርፉ መጠቀም የሚገባቸውን ጥቅም እያገኙ አይደለም፡፡

በሌላ በኩልም ኢትዮጵያ በከርሰ ምድሯ ተፈጥሮ የለገሳትን የኢንዱስትሪ ግብዓት ማዕድናት አውጥታ መጠቀም ባለመቻሏ፣ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማውጣት ከውጭ የተለያዩ ምርቶችን ታስገባለች፡፡ ለአብነት ያህል እንኳን ብንጠቅስ ሲሊካ የተባለ ለመስታወትና ጠርሙስ ማምረቻ የሚሆን ማዕድን በስምጥ ሸለቆ ውስጥ በብዛት ቢገኝም በስፋት ጥቅም ላይ ባለመዋሉ የመስታወት፣ ብርጭቆና ጠርሙስ ምርቶች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ እየገቡ ይገኛሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ብርጭቆና ጠርሙስ ለማውጣት በውጭ ምንዛሪ በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ይደረጋል፡፡

የቴክኖሎጂ አቅርቦት ዝቅተኛ መሆን፣ ለአምራቾች የሚደረገው የፋይናንስ፣ የቴክኒክና የአቅም ግንባታ ድጋፍ አነስተኛ መሆን ለዘርፉ ያለማደግ ምክንያት ተብለው ከሚጠቀሱ ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በተጨማሪም በዘርፉ ያለው የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ደካማ መሆኑ የዘርፉ ዋነኛ ማነቆዎች እንደሆኑ ይነገራል፡፡ ህገወጥ የማዕድን ምርቶች በተለይም የወርቅ ንግድ መስፋፋት፣ ምርቶች ላይ እሴት ጨምሮ አለመላክ፣ መንግሥት በዘርፉ የሚሰጠውን ድጋፍና ማበረታቻ ተግባራዊ አለማድረጉ ሌሎች ቁልፍ ችግሮች ናቸው።

ከዚህም ባሻገር በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢ ዎች የነዳጅ ሀብት ስለመኖሩ በመንግሥትም ሆነ በዘርፉ ተወናዮች ሲነገር ይደመጣል፡፡ ይሁንና የማዕድንና ነዳጅ ፍለጋ ሥራ ከፍተኛ መዋእለ ነዋይ የሚጠይቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በኢኮኖሚና በቴክኖሎጂ ወደኋላ የቀሩ ሀገራት በመንግሥት በጀት ለመሥራት የሚታሰብ ባለመሆኑ ሀብቱ ጥቅም ላይ አልዋለም፤ በዚህ ምክንያትም ሀገሪቱ ዛሬም ከውጭ ሀገራት ጥገኝነት መላቀቅ አልቻለችም። በእርግጥ በተለያዩ ጊዜያት የነዳጅ ፍለጋና ማውጣቱን ሥራ ለመስራት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መምጣታቸው ይታወቃል፤ ሆኖም በፀጥታና በተለያዩ ችግሮች የተጀመሩ ሥራዎች በብዛት ሲቋረጡ ይስተዋላል፡፡

በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች አጠቃላይ የማዕድን ልማት ሥራው በከፊልና ሙሉ ለሙሉ የሚቋረጥበት ሁኔታ አጋጥሟል። በተጨማሪም ግርግር ለሌባ ይመቻል እንዲሉ በሀገሪቱ የተከሰተውን አለመረጋጋት ተገን በማድረግ የሕዝብና የሀገር ሀብት የሆኑ ማዕድናት በህገወጥ መንገድ እየወጡና እየተሸጡ የህገወጥ ግለሰቦች ኪስ እያዳበሩ መሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ሰንበትበት ብሏል፡፡

መንግሥት ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በዘርፉ የሚስተዋሉትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍታት ያስችሉኛል ያላቸውን የተለያዩ የልማት ስትራቴጂዎች ነድፎ በመስራት ላይ ይገኛል። በተለይም ከአምስቱ የኢኮኖሚ ልማት ቁልፍ ተግባራት (ፒላሮች) አንዱ በማድረግ የማዕድን ልማት ዘርፉ ለሀገር እድገት ወሳኝ ሚና እንዲጫወት ርብርብ እያደረገ ስለመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ሪፖርት ሲያደርጉ ተደምጠዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ አሁን ባለው የሀገሪቱ ፖሊሲ ማዕቀፍ መሰረት ድረስ የሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ዘርፍ የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት እንዲሆን ታቅዷል፡፡

ምሁራን እንደሚገልፁት፤ ደግሞ ይህ የመንግሥት ትልም ሊሳካና የማዕድን ዘርፍ ልማት ውጤት ሊያመጣ የሚችለው በመለስተኛ የዕድገት አቅጣጫ የረዥም ጊዜ እቅድ ሲቀረፅ ነው፡፡ በማዕድን ዘርፍ ልማት ለመጠቀም፣ አሁን የሚታዩትን ችግሮች ለመቅረፍ፣ የማዕድን ፍለጋና የማዕድን ማውጣት የሥራ ፈቃድ የሚሰጥበት ግልፅ ፖሊሲ፤ ህጎችና ደንቦች ማስቀመጥ ይጠይቃል፡፡ በተጨማሪም የማዕድን ሚኒስቴር ተቋማዊ አቅም መገንባት፣ የተቆጣጣሪ ተቋማትን የአቅም ውስንነት ከግምት በማስገባት የማዕድን አልሚ ኩባንያዎችን በዘርፉ ንቁ ተሳታፎ ማድረግ ይገባል፡፡

ከዚህም ባሻገር ኢኮሎጂካዊ አዋጭ ስለሚባሉ አካባቢዎች በቂ መረጃ ማቅረብ፣ የማዕድን ገቢ ክፍፍል ሥርዓትን መቅረጽ ዘርፉን የሚያንቀሳቅሱ የመንግሥት ተቋማት ቀጣይ የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል፡፡ በረዥም ጊዜ ከፍተኛ የማዕድን ዘርፍ ከመፍጠር አኳያ፣ ፖሊሲ አውጪዎች ከዘርፉ የሚገኝን ጥቅም በበለጠ ማሳደግ የሚችሉበትን ዕቅድ ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁም በዘርፉ ልማት የተገኙ ውጤቶችን የእሴት ሰንሰለቶች ለመፍጠር ማበረታታት የግድ ይላል፡፡

በሌላ በኩል ለውጭ ገበያ በሚቀርቡ ዋና ዋና ማዕድናት የምርት አቅርቦትና ግብይት ላይ ያሉ መሰረታዊ ችግሮች፣ የመፍትሔ አቅጫዎች እና የባለድርሻ አካላት ሚና በመለየት ዘርፉ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ለማድረግ እየሰራ ስለመሆኑ መንግሥት በተደጋጋሚ ሲገልፅ ይደመጣል። የዘርፉ ተዋናዮች በበኩላቸው ግን መንግሥት እያደረገ ያለው ድጋፍ፣ ክትትልና ዘርፉ ካለው እምቅ አቅምና ከሚያስገኘው ገቢ አንጻር በመረዳት የሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ መሆኑን ያነሳሉ። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ያለው የህገ ወጥ የማዕድን ምርቶች ንግድ በህጋዊ መንገድ የሚሰሩ አካላት ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑንና መንግሥትም የተለየ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ያሳስባሉ። በዚህ ረገድ በተደጋጋሚ በማዕድኑ ዘርፍ ስላሉ ችግሮች ውይይት ቢደረግም የሚመለከታቸው አካላትም በጉዳዩ ላይ መፍትሄ በመስጠት እርምጃ ሲወስዱ ግን እንደማይታይ ያመለ ክታሉ።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በዘርፉ ተዋናዮች የሚነሱ ችግሮችን በሚመለከት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የኤክስፖርት አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማይክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ የዘርፉ ተዋናዮችን ባነጋገሩበት ወቅት እንደገለፁት፤ መንግሥት ከዚህ በፊት ትኩረት ያልተሰጠውን የማዕድኑን ዘርፍ ትኩረት እንዲያገኝ ወስኗል። ከህገ ወጥ ማዕድን ምርትና ሽያጭ በተለይም ከወርቅ ግብይት አንጻር የሚነሱ ተግዳሮቶች በጥልቀት የችግሩን ምንጭ መተንተን እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ረገድ አስፈላጊው ሥራ በመንግሥት በኩል እንደሚከወን የጠቀሱት አምባሳደር ግርማ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በኩል የማዕድን ዘርፉን ችግሮች መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የሚሰራ አምስት አባላት ያሉት ግብረ ኃይል መቋቋሙንም ጠቁመውም ነበር። በዘርፉ የሚነሱትን ችግሮች በዝርዝር ጥልቅ ውይይት እንደሚካሄድባቸውና ከፖሊሲና ከአሰራር አኳያ እንዲሁም መንግሥት ምን አይነት ድጋፍ ማድረግ አለበት? በሚለው ዙሪያ ዝርዝር የመፍትሄ ሃሳቦች እንደሚቀርቡም ማመልከታቸው ይታወሳል።

እንደተባለው የማዕድን ዘርፉ ለሀገር እድገት ሁነኛ አቅም ይሆን ዘንድ በተለይም የመንግሥት፤ ማህበረሰቡና አልሚዎች ቅንጅት አሰራር ማጠናከር ወሳኝ ሚና አለው፡፡ ከዚህም ባሻገር ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ ማድረግ፣ ምርቶች ላይ እሴት ጨምሮ መላክ፣ ህገ ወጥ ግብይትን ለመከላከልና እሴት መጨመር ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ላይ መንግሥት ሰፊ የቤት ሥራ እንዳለበት ይታመናል።

በዘርፉ ካለው እምቅ አቅም አኳያ በሥራ እድል ፈጠራም የላቀ ሚና እንዲጫወት ማድረጉ ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበት አጠያያቂ ጉዳይ አይደለም፡፡ እንዲሁም ባህላዊ ወርቅ አምራቾችን በማህበር፣ በአነስተኛና ጥቃቅን ማደራጀት፣ ዘመናዊ የአመራረት ዘይቤ እንዲጠቀሙ ሥልጠና መስጠትና የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ ሁኔታዎችን በማመቻቸት መንግሥት ወረዳና ቀበሌ ድረስ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ይገባዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ባህላዊ አምራቾች ያሉባቸውን ችግሮች በጥልቀት በማጥናት ችግሮቻቸውን መፍታት ይጠበቃል፡፡ በእርግጥም ኢትዮጵያ ላሰበችው የአስር ዓመት የኢኮኖሚ ልማት መርሀ ግብር እውን መሆን እነዚህ ድምርና የጋራ የቤት ሥራዎችን መከወን ለነገ የሚተው ተግባር አይደለም፡፡

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን የካቲት 15/2016

Recommended For You