
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ሐማስ ያቀረበውን የተኩስ አቁም ስምምነት ሃሳብ በወራት ውስጥ በጋዛ “ሙሉ ድል መቀዳጀት” ይቻላል በማለት ሳይቀበሉት ቀሩ።
ኔታንያሁ ይህን ያሉት አዲስ ለቀረበው የተኩስ አቁም ስምምነት ምላሽ ለመስጠት ሐማስ ጥያቄዎች ማቅረቡን ተከትሎ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቡድኑ ጋር የሚካሄድ ድርድር “የትም አይደርስም” ያሉ ሲሆን ሐማስ ያቀረበውን ጥያቄም “አስገራሚ” ብለውታል።
በሁለቱ ወገኖች መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ አሁንም ንግግሮች እንደቀጠሉ ነው። ሆኖም ኔታንያሁ ረቡዕ ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “ ከድል ውጪ ሌላ አማራጭ የለም” ሲሉ ተናግረዋል።
“ሐማስ በጋዛ ነፍስ እንዲዘራ የምንፈቅድ ከሆነ በቀጣይ ለሚፈፅመው ጭፍጨፋ ጥያቄው የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው የሚሆነው” ብለዋል። እስራኤል ሐማስ ላቀረበው ሃሳብ አዎንታዊ ምላሽ ትሰጣለች ተብሎ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም ሳትቀበለው ቀርታለች።
የእስራኤል ባለሥልጣናትም ሐማስ በራሱ ጊዜ ጦርነቱን ለማስቆም የሚያደርገውን ጥረት ተቀባይነት የሌለው አድርገው ተመልክተውታል። የሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሳሚ አቡ ዙሁሪ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት፤ የኔታንያሁን ንግግር “ “ፖለቲካዊ ድፍረት” ያሉ ሲሆን ፤ይህም በቀጣናው ያለው ግጭት እንዲቀጥል ያላቸውን ፍላጎት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
አንድ ግብጻዊ ባለሥልጣን በግብፅ እና በኳታር አደራዳሪነት በአዲስ ዙር የሚካሄዱት ድርድሮች በካይሮ እስከ ትናንትና ድረስ እንደሚቀጥሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ግብፅ ሁለቱ ተፋላሚ አካላት ስምምነት ላይ ለመድረስ ግትርነታቸውን እንዲተው ጥሪ ማቅረቧንም እኝሁ የቢቢሲ ምንጭ ገልጸዋል።
ኔታንያሁ “ ቅዠት” ያሉትን እቅድ ሳይቀበሉት መቅረታቸው የሐማስ ምላሽ ‘አዎንታዊ’ መሆኑን ከገለጸችው የኳታር አስተያየት ጋር ተቃርኗል። ሐማስ ለቀረበለት የተኩስ አቁም ስምምነት ቅድመ ሁኔታውን ያስቀመጠው ማክሰኞ ዕለት ነበር።
ሮይተርስ የዜና ወኪል የተመለከተው የሐማስ ረቂቅ ሰነድ እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች በምዕራፍ ከፍሎ አስቀምጧል። በምዕራፍ አንድ የ45 ቀናት የተኩስ አቁሙ ፋታ ሁሉም የእስራኤል ሴት ታጋቾች እና ከ19 ዓመት በታች የሆኑ ወንዶች፣ አረጋውያንና ሕሙማን በእስራኤል እስር ቤት ውስጥ ካሉ ፍልስጤማዊ ሴቶች እና ሕጻናት ጋር ልውውጥ እነደሚደረግ ሐማስ አሳውቋል።
የእስራኤል ኃይሎችም በጋዛ በርካቶች ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች ለቀው ይወጣሉ። ከዚህም በተጨማሪ በግጭቱ የወደሙ ሆስፒታሎችን እና የተፈናቃይ ካምፖችን መልሶ የመገንባት ሥራ ይጀመራል ላል የሐማስ ምዕራፍ አንድ ዕቅድ።
በምዕራፍ ሁለት ደግሞ የቀሩ የእስራኤል ወንድ ታጋቾች ከፍልስጤማውያን እስረኞች ጋር ልውውጥ ይደረጋል ። የእስራኤል ኃይሎችም ሙሉ በሙሉ ጋዛን ለቀው ይወጣሉ ብሏል። በምዕራፍ ሦስት እንዲሁ ሁለቱ ወገኖች አስክሬኖችን ይለዋወጣሉ፤ የሚል ውጥን አስቀምጧል፤ የቀረበው ረቂቅ ስምምነት ለጋዛ የሚቀርበው ምግብ እና ሌሎች ሰብዓዊ እርዳታዎች አቅርቦት እንዲጨምርም ይጠይቃል።
በ135 ቀናቱ የተኩስ አቁም ፋታም ጦርነቱን ለማስቆም የሚደረገው ድርድር እንደሚጠናቀቅም ሐማስ ገልጿል። ሐማስ ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ጥቅምት ወር ላይ በደቡባዊ እስራኤል በፈፀመው ጥቃት አንድ ሺህ 300 የሚሆኑ ሰዎች ተገድለዋል።
እስራኤል ለዚህ ጥቃት የአጸፋ ርምጃ መውሰድ ከጀመረች በኋላም በርካቶች የተገደሉ ሲሆን የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተግባራዊ ካልሆነም ሌሎች ጥቃቶች እንደሚቀጥሉ ይገመታል። ቀደም ብሎ እስራኤል፣ አሜሪካ፣ ካታር እና ግብፅ አቀረቡት የተባለው የተኩስ አቁም ስምምነት ይዘት ለሕዝብ ይፋ አልሆነም።
ነገር ግን የተኩስ አቁም ስምምነቱ ለስድስት ሳምንታት እንደሚቆይና ሐማስ የታገቱ እስራኤላዊያንን የሚለቅ ከሆነ ፍልስጤማዊያን እስረኞች በምትኩ እንደሚለቀቁ ተነግሯል። አሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፤ ሐማስ ስለሰጠው ምላሽ ከእስራኤል ባለሥልጣናት ጋር እንደመከሩ ገልጸዋል።
ብሊንከን የሐማስን ምላሽ አሜሪካ እንዴት እንደምትመለከተው ባይገልጡም ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን “ትንሽ ከበድ ያለ” ሲሉ መግለፃቸው የሚታወስ ነው። ባለፈው ኅዳር አንድ ሳምንት በቆየው የተኩስ አቁም ስምምነት ታግተው የነበሩ 105 እስራኤላዊያንና የሌሎች ሀገራት ዜጎች ሲለቀቁ በእስራኤል እሥር ቤቶች የነበሩ 240 ፍልስጤማዊያን ተለቀዋል። በእስራኤል እና ሐማስ መካከል የሚደረግ የተኩስ አቁም ስምምነት የመካከለኛው ምስራቅን ውጥረት ለማርገብ አንዱ መፍትሔ እንደሆነ አሜሪካ በተደጋጋሚ ገልጻለች።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን የካቲት 1 ቀን 2016 ዓ.ም