“አፊኒ” – የሲዳማ ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት

ሀገራችን የአያሌ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሙዚየም በመባል ትታወቃለች። እነዚህ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተለያዩ ባሕሎች ያሏቸው ሲሆን፣ እነዚህ ባሕላዊ እሴቶች በርካታ ፋይዳ አላቸው። ከእነዚህም መካከልም ግጭት ለመፍቻ የሚያገለግሉ ባሕላዊ እሴቶች ይጠቀሳሉ። በሀገሪቱ በርካታ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መኖራቸው፣ በርካታ ግጭቶችን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችሉ እሴቶች እና ባሕላዊ ሥርዓቶች የሚገኙባት እንድትሆን አስችለዋታል።

የእዚህ ግጭት መፍቻ ሥርዓት ባለቤት ከሆኑት መካከልም የሲዳማ ብሔረሰብ አንዱ ነው። ብሔረሰቡ ከጥንት ጀምሮ ሲመራባቸውና ሲተዳደርባቸው የኖረባቸው ለዘመናት ጠብቆ ያቆያቸው ባሕላዊ ተቋማት፣ ዕሴቶች፣ ልማዳዊ አሠራሮችና የእምነት ሥርዓቶች አሉት። ከእነዚህ መካከልም የአስተዳደርና የዳኝነት፣ የግጭት አፈታት፣ ባሕላዊ ሕግና ሥርዓት፣ የሉዋ ተቋም፣ እንዲሁም በኅዘንና በደስታ ጊዜ የሚጠቀምባቸው ባሕላዊ ጨዋታዎች (የአባቶች ቄጠላን ጨምሮ)፣ የሙዚቃ መሣሪያዎች፣ ባሕላዊ አለባበስና ጌጣጌጦች፣ የዘመን አቆጣጠር ቀመር፣ የቀንና የወራት አቆጣጠርና የዘመን መለወጫ ዕለተ ቀን “ፍቼ” እንደ ምሳሌ ይጠቀሳሉ።

መደማመጥ ይበልጥ ግጭቶችን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁልፍ ሥርዓት እንደሆነ የተመላከተበት እና ለዘመናት ጥቅም ላይ ከዋሉ ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሀገር በቀል እሴቶቻችን መካከል በዚህ ጽሑፍ የሲዳማ ብሔረሰብ ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓትን ለማየት ወደናል። በዚህ ባሕላዊ እሴት ላይ በቅርቡ መጽሐፍ የጻፉትን የዶክተር አራርሶ ገረመው ጽሑፍም ለእዚህ ሥራ ተጠቅመናል።

አራርሶ ገረመው (ዶ/ር) በትምህርት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ፣ በነገረ መለኮት ከኢቫንጀሊካል ቲዎሎጂ ኮሌጅ፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በኮኦፕሬቲቭ ዴቨሎፕመንት ከሀዋሳ ዩኒቨርስቲ እንዲሁም የፒኤች ዲግሪያቸውን ከቪዥን ኢንተርናሽናል ከዩ.ኤስ.ኤ ካሊፎርኒያ አግኝተዋል። በአሁኑ ወቅትም በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ሆነው እያገለገሉ ሲሆን፣ ትውልድ በሁለንተናዊ ዕድገት እንዲበለፅግ የሚተጉ እና ከአፊኒ ዲቨሎፕመንት ኢንሺየቲቭ ፎረም መሥራቾች አንዱም ናቸው።

አራርሶ (ዶ/ር) “አፊኒ” በተሰኘው መጽሐፋቸው እንዳብራሩት ፤“አፊኒ” ወይም በጥሬ ትርጉሙ “ሰማችሁ ወይ?” እየተባለ በሲዳማ ብሔረሰብ ሸንጎ ላይ የሚሠራበት ባሕላዊ ሥርዓት፣ የሸንጎው ታዳሚዎች የሚጠያየቁበት፣ ጥበባዊ ሂደት ያለው አስደማሚ የብሔረሰቡ ባሕላዊ የሠላም እሴት ነው። ይህም የትናንትን የሚያጎላ፣ ለዛሬ ጥንቃቄን የሚያስገነዝብ፣ ለነገ ትኩረት የሚሰጥ የሰጥቶ መቀበልን መርሕ ያዳበረ ዴሞክራሲያዊ የሆነ አካሄድ ያለው ባሕል ነው ሲሉ ያብራራሉ።

በግጭት አፈታት ሂደቱ ላይ የሸንጎው ተሰብሳቢ “ሰማችሁ ወይ?” እየተባባለ የሚጠያየቀው ለጉዳዩ ትኩረት ለመስጠት፣ ልብ ከቀልብ ሆኖ ለመደማመጥ ክርክሩ (ውይይቱ) መስመር እንዳይለቅ እና ከስሜታዊነት ለመጠበቅ እና እውነታውን ለመፈለግ የሚደረግ የግጭት አፈታት ሥርዓት ነው። በርካታ ጉዳዮች ወደ ግጭት ከሚያመሩባቸው ነገሮች አንዱ አለመደማመጥ እና አንዱ የአንዱን ሀሳብ አለማዳመጥ የሚሉት አራርሶ (ዶ/ር)፣ “የአፊኒ” ሥርዓት አስፈላጊነትም ተገቢውን ጊዜ ወስዶ ነገሩን በአግባቡ ለማብላላትና ለማሰላሰል ይረዳል ሲሉ በመጽሐፉ ላይ አስፍረዋል።

እንደ አራርሶ (ዶ/ር) ማብራሪያ፤ የአፊኒ ሥርዓት ተቋም ነው፤ ጊዜንና ቦታን የያዘ እሴት ነው። አፊኒ በሲዳማ ብሔረሰብ ዘንድ የሚታወቅና የሚከበር ነው፤ ሁሉም ለሥርዓቱ እንዲገዛ የሚያደርግ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ወጉን ጠብቆ አሁንም ድረስ የዘለቀ እሴት ነው። ከ500 ዓመታት በፊት ይኖር የነበረ አንድ የሲዳማ ሰው ምናልባትም ፈጣሪ ፈቅዶ ተመልሶ ቢመጣ ከቴክኖሎጂ ዕድገት አንፃር ሁሉም ነገር ቢቀያየርበት አፊኒን ግን ከነውበቱ እና ግርማ ሞገሱ በሲዳማ ያገኘዋል።

አፊኒ ተቋም ነው ሲባልም በመደበኛ አይነት አሠራር ቢሮ ኖሮት የተቀጠረ ሰው ያለው ተቋም ሳይሆን፣ ኢ-መደበኛ በሆነ መልኩ የሚከወን፣ ነገር ግን አሠራሩ ለሁሉም ግልፅ የሆነ ተቋም በመሆኑ ነው። አፊኒ ቦታ ነው ሲባልም ሥርዓቱ የሚከናወንበት ቦታና ጊዜው ይሄንኑ ስያሜ ስለያዘ ነው፤ አፊኒ ሥርዓትም፣ ተቋምም እንዲሁም ቦታን አመልካች ነው። አፊኒ የስክነት ውበት፣ የአስተውሎት ጥግ ነገሮችን የመተንተን እና ችግርን በስምምነት እና በጋራ የመፍታት እምቅ አቅም እንዳለው በመጽሐፉ ተጠቁሟል።

የሲዳማ ባሕል ልዩ መገለጫዎች ማለትም ፍቼ- ጫምባላላ (የአዲስ ዓመት በዓል አከባበር)፣ የሉዋ ሥርዓትና በሌሎች በርካታ ባህላዊ እሴቶችና ማኅበራዊ ልምዶች እጅግ የበለጸገ ነው። አፊኒም በሲዳማ ሕዝብ ትልቅ ትርጉምና ቦታ አለው። የአፊኒ ሥርዓት በግጭት አፈታትና ሠላም ግንባታ ሂደት በሲዳማ የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ የሚገኝ፣ ታሪካዊና በሰፊው ጥቅም ላይ የዋለ ባሕላዊ ሥርዓት ነው።

የአፊኒ ተቀዳሚ ሚና አስመልክቶ በመጽሐፉ እንደተመለከተው፣ በሲዳማ ባሕል በዋናነት አብሮ መኖር፣ ለጋራ መግባባትና እሴት፣ ለይቅርታና ዕርቅ ምቹ ሁኔታ መፍጠሪያ መድረክ ነው። በተጨማሪም ሰላማዊ፣ ግልጽና ዴሞክራሲያዊ ውይይት በማድረግ ተሳትፎንና ፍትሐዊነትን በከፍተኛ ደረጃ ያጎለብታል። የአፊኒ የመጨረሻ ግብ በሁሉም ጉዳዮች ስምምነት ላይ መድረስ ነው።

የአፊኒ ሥርዓት ልክ እንደ ሲዳማ ብሔረሰብ ታሪክ፣ ብሔራዊ ማንነት፣ ቋንቋና የተለያዩ የባሕል አካላት የረዥም ጊዜ ሁነት መሆኑም በመጽሐፉ ተመልክቷል። ጤናማ ግንኙነትን ለማካሄድና በማኅበረሰቡ መካከል ማንኛውም ውሳኔ ላይ ለመድረስ ልዩ መሣሪያ ሆኖ ጥቅም ላይ ይውላል። በዚህ ሁኔታ ውይይቱ ወይም ንግግሩ የሚፈለገው ግብ ላይ እስኪደርስ በባሕል መሪዎች ወይም ማኅበራዊ ደረጃቸው ከፍተኛ ቦታና ክብር በሚሰጣቸው አዛውንቶች ይከወናል። ያለ አፊኒ ሥርዓት ምንም ዓይነት ውሳኔ ሊሰጥ አይችልም።

አራርሶ (ዶ/ር) በመጽሐፋቸው እንዳሉት፤ አፊኒ በሲዳማ ውስጥ እንደ ወሳኝ ያልተጻፈ የሕግ ቻርተር ይቈጠራል። ማንኛውም ግጭት ወይም ችግር በአፊኒ ሥርዓት ሊታይ ይችላል። በማኅበረሰቡ ውስጥ በማንኛውም ደረጃ የሚከሠቱ ከቀላል ጉዳይ ጀምሮ እጅግ ውስብስብ እስከሆኑ ጉዳዮች ድረስ ያሉትን ሁሉንም ጉዳዮች ማስተዳደርም ይችላል።

የአፊኒ ሥርዓት የሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮችን ጨምሮ የሴቶችን መብቃት ያበረታታል። ይህም በዋናነት የሴቶችን መሠረታዊ መብቶች ለማስከበርና ለመጠበቅ፤ የወንድ የበላይነትን ለማስወገድ ይጠቅማል። ለምሳሌ “ያካ” በሲዳማ ውስጥ በፆታ ላይ የተመሠረተ ትንኮሳና የሴቶች መብት ጥሰትን ለመቃወምና ለማስጠበቅ በማኅበረሰቡ ዘንድ በሕገ ልቦናነት የታወቀ ጠንካራ ሕግ ነው። የሲዳማ ሴቶች በዚህ ረገድ አፊኒን አስፈላጊ ከሆነ በወንዶች ላይ ከባድና አስተማሪ ቅጣት በመጣል ጉዳዩን ለመቆጣጠር ቁልፍ ሚና የሚጫወትበትን “ያካ” በተደራጀ አግባብ ሠላማዊ ሰልፍ በማድረግ መብታቸውን የሚያስጠብቁበት ስልት አርገው ይጠቀሙበታል።

ሁሉም የአፊኒ ሂደቶች የሚመሩትና የሚተገበሩት በባሕላዊ ደንቦችና ሕጎች “ሴራ” መሠረት ነው። ሴራ ጥፋተኛ ሆነው በተገኙና ከአፊኒ ትእዛዝ ውጪ በሆኑ ግለሰቦች ላይ የሚበየን ከማንኛውም ማኅበራዊ መስተጋብርና ጥቅማ ጥቅሞች የሚያገል፣ ከሌሎች ጋራ የሚኖራቸውን ግንኙነት የሚገድብ የባሕል ማዕቀብ መሆኑን መጽሐፉ ያመለክታል። የሴራ ሥርዓቱና ማዕቀቡ እጅግ በጣም ከፍተኛና በማኅበረሰቡ አባላት በሙሉ በጥብቅ የሚተገበር እና የተለያዩ ሀገራት በሌሎች ሀገራት ላይ እንደሚጭኑት ዓይነት ማዕቀብ ያህል ከባድ ቅጣት መሆኑንም ያስረዳሉ። አፊኒ ሁሉንም አስፈላጊ መረጃዎችን በማካፈል፣ እውነታውን (ሐላሌ) በመፈለግና በመመርመር በግጭት አፈታትና በአጠቃላይ ለሠላም ግንባታ ወሳኝ ሂደት መሆኑንም ያስገነዘባሉ።

በአፊኒ ሥርዓት አጥፊ ይቀጣል፤ ተበዳይም ይካሳል። ይህን ሥርዓት የሚጥስና ላለማክበር የሚያንገራግር ግለሰብም ሆነ ቡድን የሚደርስበት ማኅበራዊ ቅጣት ከፍ ያለ ነው። ሴራ በመባል የሚታወቀው ቅጣት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና መንፈሳዊ ቅጣት ብቻ ሳይሆን የሚያስከትለው ሥነልቡናዊ ቀውስም በቀላሉ የሚሽር አይደለም።

“አፊኒ” በሸንጎ ውይይት ወቅት በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ላይ ተሰብሳቢው በነፃነት ሀሳቡን እንዲገልጽ የሚፈቅድ ባሕላዊ ሥርዓት ነው። በመሆኑም በሲዳማ ምድር የሚኖሩ ማናቸውም ብሔረሰቦች በዚህ ሥርዓት መነሻ ትልቅ ዋስትና ይሰማቸዋል። በማኅበረሰቡ መካከል በሚኖሩበትም ጊዜ ከፍተኛ መተማመንና ደህንነትም ይሰማቸዋል። የአፊኒ ዕሴት ተነጋግሮ መደማመጥን የተላበሰ፣ ትዕግሥትንና መረጋጋትን የሚያጎናጽፍ፣ መደማመጥን የሚያጎለብት፣ ከመቃቃር ይልቅ ስክነትን የሚመርጥ ትልቅ ሥርዓት ነው። ይህ ዕሴት የመላ ኢትዮጵያውያንና የአፍሪካውያን የዕርቀ ሰላም ማውረጃ መሣሪያ ቢሆን ምን ያህል ሀገራችንም ሆነ አህጉራችንም ተጠቃሚ በሆነች ሲሉም በቁጭት ይገልፃሉ።

በሲዳማ ባሕል ሰዎች ሲናገሩ “አፊኒ” ሳይባል ጣልቃ አይገባም። በሌላ መልኩ አንድ የተበደለ ሰው ማናቸውንም ዓይነት ርምጃ ከመውሰዱ አስቀድሞ አጠገቡ ላሉት ወይም ለታላላቆቹ “አፊኒ” በማለት ማስታወቅ ባሕላዊ ግዴታው ነው። ይህን ሳያደርግ በግብታዊነት ርምጃ የወሰደ እንደሆነ ባሕላዊ ሴራ (ቅጣት) ይጣልበታል።

“አፊኒ” እውነትን ከማፈላለግና ከፍትሕ አሰጣጥ ጋራ በእጅጉ ይተሳሰራል። እውነትን በማጣራትና በማረጋገጥ ወደሚቀጥለው ተግባር ለመሄድ “አፊኒ” በጉዳዩ ላይ ዕውቀት ያለው ማንኛውም ሰው መረጃ እንዲሰጥ ሰፊ ዕድል ይቸረዋል። በባሕላዊ የአስተዳደርና የዳኝነት ሥርዓት የበለጸገውና የከበረው የሲዳማ ሕዝብ ከዚህ በላይ ከተዘረዘሩትም በላቀ ቁጥር በርካታ ባሕላዊ ዕሴቶችን አክብሮና ጠብቆ በመኖሩ ሊመሰገን ይገባዋል።

በብሔረሰቡ ውስጥ ግጭትና ሁከት እንዳይከሠትም ሆነ ከተከሠተ በኋላ ነገሮችን ለማረጋጋትና ወደ ቀድሞው ሠላማዊ ሁኔታ ለመመለስ የሚደረገው ባሕላዊ ሥርዓት “ሲጮ” በመባል ይታወቃል። ውሳኔ ያገኙ ችግሮች፣ ግጭቶችና ሁከቶች በዕርቅ እንዲያልቁና ዳግመኛ እንዳያገረሹ ቃል ኪዳን የሚገባበት ሥርዓት ደግሞ “ጎንዶሮ” በመባል ይታወቃል።

“ቀጌፊጫ”ም ሌላኛው ባሕላዊ ሥርዓት ነው። ይህም አንድ ሰው ሆነ ብሎ የሌላውን ነፍስ ያጠፋ እንደሆነ በባሕሉ መሠረት የሚወሰንበትን የደም ካሣ ከከፈለ በኋላ በሟችና በገዳይ ቤተሰቦች መካከል የጠላትነት ስሜት እንዳይኖር ለዘለቄታው እልባት የሚበጅበት ሥርዓት መሆኑ በመጽሐፉ ተብራርቷል። ይህም የሚከወነው ሥርዓቱን ማስተዳደርና መምራት በሚችሉ ክፍሎች ነው። ምንም እንኳ የከረረ ጥልና ክርክር ቢኖርም እንኳ በመደማመጥ መርሕ እልባት ሳያገኝ አይታለፍም፤ ለዚህም በየእርከኑ የሚገኙ የሥርዓቱ አስፈጻሚዎች “ሐላሌ”ን ወይም እውነታውን በመፈለግና በመመርመር እንደ መርሕ ይዘው የሚተገብሩት ይሆናል።

ይህ ባሕላዊ የፍትሕ ሥርዓት የሲዳማ ብሔር በታሪክ ለረዥም ዘመናት ማዕከላዊ መንግሥት ሳይመሠረት የሉዋ ሥርዓት በየጎሣዎቹ ራስ ገዝ የአስተዳደር መዋቅሮችን ዘርግቶ ሲሠራበት ቆይቷል። ሲዳማ ገጸ-ብዙ ባሕሎች፣ ልማዶች፣ ሀገር በቀል ዕውቀቶች እና የአኗኗር ሥርዓቶች ያሉት ብሔር ነው።

አራርሶ (ዶ/ር) የመመረቂያ ጽሑፋቸውን ያደረጉትም በአፊኖ እሴት ነው፤ በአፊኖ ጥበብ፣ በጎንዶሮና በሲጮ ዕሴት ተኮትኩተው ያደጉ የሲዳማ ልጆች በየትኛውም የዓለም ክፍል ውይይት ሲያደርጉ በአፋቸው ቀድሞ የሚመጣው ቃል አፊኒ! አንደሆነ ተናገረዋል። ይህ ሥርዓት ሳይበረዝና በዘመን አመጣሽ ሁኔታ ፈር እንዳይለቅ ትውልዱ በትልቅ አትኩሮት ከአባቶች መማርና ባሕሉንም ከነሙሉ ክብሩ ማስቀጥል አለበት ሲሉም በመጽሐፋቸው አስገንዝበዋል። የሲዳማ ብሔር ሞቴዎች፣ ጋሮዎች ወይም ጌሎዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የተከበሩ የሲዳማ እናቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ በአጠቃላይ ሕዝቡ ለዚህ ዕሴት መበልጸግ የበኩላቸውን እንዲወጡ ሥልጠናዎችን በመስጠት የበለጠ ሥራ መሥራት አስፈላጊ ነው ሲሉም ያሳሰባሉ።

የሲዳማ የሀገር ሽማግሌ “ለወዳጅ ለመወሰን ተሂዶ ለባላንጣ ይፈረዳል” ሲሉ እንደሚናገሩ አራርሶ (ዶ/ር) ጠቅሰው፣ ይህም የእውነትን (ሐላሌ)ን የበላይነት እንደሚያመለክት አስታውቀዋል። ግልጸኛነት፣ ሐቀኝነት፣ ቀጠሮ አሰጣጡ፣ ከነገሩ ጋራ የሚስማማ ተረት እና ምሳሌያዊ አነጋገር አዋዝቶ በማቅረብ ውስብስቡን እንቆቅልሽ የሆነን ችግር እሳት እንደነካው ሰም ይቀልጣል ሲሉም የዕሴቶቹን ችግሮች የመፍታት አቅም ያስረዳሉ። በመጽሐፉ ላይ እንደተመለከተው፤ በአፊኒ እሴት አስታራቂዎቹ የሐላሌ ምትክ ናቸው፤ ሞቴዎች ወይም የጎሣ መሪዎች አብዛኛውን ጊዜ ማኅበራዊ ጉዳዮችንና ትልልቅ ክሥተቶችን የማስተዳደርና ትክክለኛ መስመር የማስያዝ ሚና በመጫወት ያገለግላሉ። በጎሣ ውስጥ ማኅበራዊ ግጭቶችና አለመግባባቶች ሲከሠቱ ጉልሕ ተሳትፎና ሚናቸውን በማሳረፍ ማኅበረሰቡን የማገልገል ሥራ ይሠራሉ።

የአፊኒ ሥርዓት ማንኛውንም ቅራኔ ግጭቱ ወደ ከፋ ደረጃ ሳይደርስ ለሀገር ሽማግሌዎች በፍጥነት በማድረስና በደል የደረሰበት አካል ሸንጎ በመቅረብ የደረሰበትን ያሳውቃል። በደሉን፣ ኀዘኑን፣ ቅሬታውን በማሳወቅ እነሆ ፍትሕ ስጡኝ የሚል ስሞታውን ያቀርባል። በሸንጎውም የሚሳተፉት የሀገር ሽማግሌዎች፣ ጭሜዬዎች፣ አያንቶዎች፣ የጎሣ መሪዎች፣ ጋዳናዎችና ሌሎችም ለተከሠተው ችግር ብሎም ገና ሊፈጸም ላለው ችግር እጅግ በሳል በሆነ የፍርድ አሰጣጥ የሚዳኙበት እሴት መሆኑንም አራርሶ (ዶ/ር) ያስረዳሉ።

እነዚህን የመሳሰሉ ሀገር በቀል እሴቶችን ልንጠብቃቸው እና ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከየትኛውም ጊዜ በላይ አሁን ልንጠቀማቸው ይገባል። እነዚህን እሴቶች ለትውልድ ለማስተላለፍ እንዲሁም በመደበኛው የፍትሕ ሂደት የሚታየውን ጫና ለማቃለል ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን ተገንዝቦ መሥራትም ያስፈልጋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን  የካቲት 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You