ጥምቀት የሰላም ምልክት!

ጥር ስርወ ቃሉ የግዕዝ ሲሆን ነጠረ ማለት ነው። ሲፍታታ፤ጠረረ፣ ብልጭ አለ፣ ነጻ (ጠራ)፣ በራ ማለት ነው። የፀሐይን ግለት አመላካች ነው። የደስታ ተክለወልድ አዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላትም ጥር የወር ስም፣ ተጠራ፣ስም ጥር ፣ ጣራ ማለት በሚል ይፈታዋል። ጥር ወር የፍስሃ የደስታ ወር ነው። ዘመነ መርዓዊ ይባላል።

መርዓዊ፤ በግእዝና በትግርኛ ሙሽራ የሚል ፍቺ አለው። ገበሬዎች በብዛት በክረምቱ የዘሩትን አጭደው ወቅተው አበራይተው በጎተራ የሚያስገቡበት ጊዜ ነው። ገበሬው ከእርሻ ሥራው ፋታ አግኝቶ በደስታና በእፎይታ የሚዝናናበት ወቅት ነው።

በጥር ወር የሚከበረውም ጥምቀት በብዛት ለሦስት ቀናት የሚከበር የአደባባይ በዓል ነው። ጥምቀት የመጀመሪያው ከተራ፣ ሁለተኛው ጥምቀት ሦስተኛው የቃና ዘገሊላ በዓል ነው። የቃና ዘገሊላው በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ በሠርግ ቤት ተገኝቶ በወንጌል የመጀመሪያውን ተአምር የሠራበት ነው። ሠርገኞች የወይን ጠጅ ሲያልቅባቸው ውሃውን ወደ ወይን ጠጅ የቀየረበት በዓል ነው። አባቶች ሲያመሰጥሩት መርዓዊ ሰማያዊ በመርዓዊ ቤት ተገኘ። ሰማያዊው ሙሽራ በምድራዊ ሙሽራ ቤት ተገኘ ይሉታል። በመዝሙርም

ፀሐይ ሠረቀ

ክርስቶስ ተጠምቀ

አዳምን ለማዳን የመጣው ሙሽራ

በገሊላ መንደር ለሠርግ ተጠራ

ሠርግ ቤት እንዳለ በክብር ተቀምጦ

የወይን ጠጅ ሆነ ውሃው ተለውጦ …›› እያሉ ይዘምራሉ። ሁለቱ በዓላት ማለትም ጥምቀትና ቃና ዘገሊላ አባቶች የውሃ በዓልና የውሃ በዓል አንድ ላይ ይከበሩ በማለታቸው የሚከበሩ ናቸው። በዓሉ ሲከበር በየቦታው አማኙ ግልብጥ ብሎ ስለሚወጣ በከተሞች አካባቢዎች የሰው ብዛት ሲታይ ጠጠር መጣያ አይገኝም። ቤት የቀረም ሰው ያለ አይመስልም።

ወንዱ ሴቱ በባህላዊ ልብስ ደምቆ ያከብረዋል። በተለይ ሴቶች ያማረውን የጥምቀት ባህላዊ ልብስ ስለሚለብሱበት ‹‹ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ›› ተብሎለታል። ጥምቀት ሰላም የተመሠረተበት፤ ሕዝቡም በአደባባይ ወጥቶ በዓሉን ሲያከብር ሰላም መኖሩን የሚያሳይበት ቱሪስቶች በዓሉ ላይ ለመታደም የሚስብበት ነው።

በጥር ገበሬው ፋታ ስለሚያገኝ በየቦታው ጋብቻ ይበዛል። የሙሽራ ወር በሆነው ጥር በየዓመቱ በተመድ የሳይንስ የትምህርትና የባህል ድርጅት በዓለም የማይዳሰስ የኢትዮጵያ የባህል ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው ጥምቀት ይከበራል። ጥምቀት ጥር 11 ቀን የሚከበር ሲሆን ከየአድባራቱና ገዳማቱ ታቦታት በቀሳውስትና በምዕመናን ታጅበው በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ወንዝ ምንጭ ሄደው ያከብራሉ።

የዋዜማው በዓል የጥምቀት ከተራ ይባላል። ከተራ ከተረ፣ ገደበ የሚል ፍቺ አለው። ውሃን ለጥምቀት በዓል ብሎ መገደብ ማለት ነው። ታቦታትን አጅበው ጥምቀተ ባሕር ሸኝተው ገሚሶቹ ምዕመናን ሲመለሱ የተወሰኑ ደግሞ በጥምቀተ ባሕር ሜዳ በጸሎት በምስጋና ያድራሉ። ይህም ኢየሱስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ለሄደበት እና በዮሐንስ እጅ ለተጠመቀበት ማሳያ ነው።

ሲዘምሩም ‹‹ሖረ ኢየሱስ እምገሊላ ሀበ ዮሐንስ›› ኢየሱስ ከገሊላ ወደ ዮሐንስ ሔደ ማለት ነው። ወጣቶችም ሲዘምሩ በጥምቀትና በቃና ገሊላ ሠርግ የተፈጸሙትን በሚያስረዳ መልክ ነው።

‹‹…ባሕር ተጨነቀች ጠበባት መሬቱ

ዮርዳኖስም ሸሸ አልቆመም ከፊቱ

እንደተናገረው ዳዊት በትንቢቱ

የሰላሙ መሪ የሰላሙ ዳኛ

አምላክ ተወለደ ተጠመቀ ለኛ።

ልጁ በዮርዳኖስ ጽድቅን ሲመሠርት

መጣ በደመና ሰማያዊው አምላክ

እየተናገረ የልጁን ጌትነት ››

በዓሉ በሀገሪቱ ምዕመን በመላው ሀገሪቱ አካባቢዎች ሲከበር፤ በተለይ በዓለም ቅርስነት በተመዘገቡት በጎንደር ፋሲል ግቢ፣ በላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት በአክሱም ጽዮን ይከበራል። ሲዘምሩም

‹‹ነድ ለማየ ባሕር ከበቦ

ማየ ባሕር ሀበ የሐውር ጸበቦ›› ይላሉ። ፍቺው እሳት የውሃውን ባሕር ከበበው የባሕር ውሃውም የሚሄድበት ቦታ ጠበበው ማለት ነው።

ይህም ቱሪስቶች እንደ ጎንደር፣ ላሊበላ፣ ሐረር፣ አክሱም ለጥምቀት ሲሄዱ ‹‹በአንድ ወንጭፍ ሁለት ወፍ›› እንደሚባለው በአንድ ጊዜ የማይዳሰሰውን እና የሚዳሰሰውን የዓለም ቅርስ ሊያዩና ሊጎበኙ የሚችሉበትን ዕድል የሚፈጥር ለቱሪስቶቹም ሀሴት የሚያጭር በዓል ነው ማለት ይቻላል። የጥምቀት ከተራ ብቻ ሳይሆን የመስቀል ደመራን ስንጨምርባቸው በታሪካዊ ቅርሶቹ ሥፍራዎች በተለያየ ጊዜ ሁለት የማይዳሰሱ የዓለም በዓለት የሚከበርባቸው ሥፍራዎች ናቸው ማለት ይቻላል።

በሐረርም ይህንኑ የጥምቀት በዓል አማኙ ያከብረዋል። የጥምቀት ከተራን የመስቀል ደመራ አከባበርን ጨምረን በቅርቡ የሸዋል ኢድን አከባበርን የኢትዮጵያ የማይዳሰስ ቅርስ አድርጋ ላስዝመዘገበችው የዓለም ቅርስ ለሆነችው ሐረርም በተለያየ ጊዜ ሦስት የማይዳሰሱ የዓለም ቅርስ የሆኑ በዓላት የሚከበሩባት ያደረጋት ነው።

የጥምቀት በዓል ለዘመናት በትውፊት ሲከበር የነበረ የአደባባይ በዓል ነው። በዓሉን ሌሎች የእምነት ተከታዮች ጭምር ይታደሙበታል። በዓሉ ከመንፈሳዊነቱ አልፎ ሕዝብ ለሕዝብ የሚገናኝበት ሰላም የሚመሠረትበት፣ ፍቅር የሚጸናበት የትዳር አጋር የሚመረጥበት በዓል ነው ጥምቀት። ወራጅ ወንዝ ባለበት ሐይቅና ምንጭ ባለበት የሚከበረው ጥምቀት እንደአዲስ አበባ ባሉ ወንዝ አልባ ከተሞች የጥምቀት ገንዳ ተሠርቶ ይከበራል። ዘንድሮ የሚከበረውን የጥምቀት በዓል የጃንሜዳን ባህረ ጥምቀት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዝግጁ ለማድረግ የሚጠበቅበት እንደሠራ መረጃዎች ያሳያሉ።

በተለይ የጃንሜዳው ጥምቀተ ባህር ለቦታው በሚመጥን ደረጃ፣ መሠራት አለበት። ከበዓሉ መልስ ደግሞ ወጣቶች ታዳጊዎች የውሃ ዋና ስፖርት እንዲለማመዱበት፣ እንዲሠሩበት እንዲወዳደሩበት የሚደረግበትን መንገድ የውሃ ዋና ፌዴሬሽንም ተግቶ ሊሠራበት ይገባል ባይ ነኝ። በአበበ ቢቂላ ስታዲየም አካባቢ በሚከበረው የጥምቀት በዓልም በሥፍራው ጥምቀትን የሚያከብሩት አብያተ ክርስቲያናቱ ባለፈው ዓመት ጥምቀተ ባህሩን በጋራ ለማደስና በዘመናዊ መልኩ አሻሽለው ለመሥራት ሲንቀሳቀሱ ነበር።

የጎንደር ጥምቀት አከባበርን ለየት የሚያደርገው በጎንደር ነገሥታት ዘመን የተሠራ ዘመን ተሻጋሪ የውሃ ገንዳ ስላለው ጭምር ነው። ጥምቀት ሲከበርና ውሃውም በጳጳሳቱ ሲባረክ ወጣት ወንዶች ተወርውረው ውሃ ውስጥ ገብተው ሲዋኙ የሚታዩበት ነው።

በጥምቀት በዓል መዝሙር እንሰናበት!

‹‹ዮሐንስ አጠምቆ ለኢየሱስ

በፈለገ ዮርዳኖስ ›› ትርጉሙም፤ ዮሐንስ ኢየሱስን በዮርዳኖስ ወንዝ አጠመቀው። ማለት ነው። የዓመት ሰው ይበለን!

ኃይለማርያም ወንድሙ

 አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You