በሁሉም አገልግሎቶች ላይ የአካል ጉዳተኞችን አካታችነት ማረጋገጥ ይገባል

እኤአ በ2011 የዓለም ባንክ እና የዓለም ጤና ድርጅት ባወጡት መረጃ መሰረት ከአለም ሕዝብ 15 በመቶ ያህሉ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ወደ 17 ነጥብ 6 በመቶው የሕብረተሰብ ክፍል የአካል ጉዳተኛ ነው። በዚህ በኢትዮጵያ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ከተለያየ ዓይነት የአካል ጉዳት ጋር እንደሚኖሩ ይታመናል።

ታዲያ በበቂ ሁኔታ አካል ጉዳተኞችን የሚመጥን የመሠረተ ልማት አውታር ግንባታ አለመኖር፤ እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለት በርካቶችን ለከፍተኛ እንግልት እና የጤና ችግር እንደዳረጋቸው ይነገራል።

በእርግጥም በየህንጻው ተመጣጣኝ የመጸዳጃ አገልግሎቶች አለመኖር፤ በመጓጓዣ አገልግሎቶች ዘርፍ ለአካል ጉዳተኞች ትኩረት አለመደረጉ ችግሮቹን የሚያባብሱ ጉዳዮች መሆኑንም የአካል ጉዳተኞች በተደጋጋሚ ጊዜያት በምሬት ሲናገሩ ይደመጣል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የልዩ ፍላጎትና አካቶ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶክተር አበበ የኋላወርቅ እንደሚያነሱት፤ የአካል ጉዳተኞች አካታችነት ላይ ሕጎች ተፈጻሚ እንዳይሆኑ የግንዛቤ ክፍተት ትልቁ እንቅፋት ነው፡፡

ማንም ሰው በራሱ ምሉዕ ባለመሆኑ አንዱ ለአንዱ የሚኖረው አበርክቶ የተለያየ ቢሆንም እጅግ ጠቃሚ ነው፤ የአካል ጉዳተኞች የጉዳት መጠናቸው ከፍና ዝቅ ባለ ቁጥር የሚሹት የድጋፍ መጠን ይለያያል የሚሉት ዶክተር አበበ፤ ለአብነትም በአይኑ ላይ ጉዳት የደረሰበት ሰው ጉዳቱ ከፊል የእይታ ችግር ከሆነ በመነጽር ሊስተካከል እንደሚችልና ነገር ግን ይህ የማይሆን ከሆነ የስነ ተግባቦት ሁኔታው የሚቀየር እንደሚሆን ያወሳሉ፡፡

እንደ ዶክተር አበበ ገለፃ፣ በኢትዮጵያ ያለው የአካል ጉዳተኞች ድጋፍ እራስ ቻይ ይሆናሉ በሚል መንፈስ ሳይሆን የበጎ አድራጎትን መሰረት ያደረገ መሆኑ ጠቃሚ አይደለም። እንዲሁም ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ አካል ጉዳተኞችን በመደገፍ ገነት ይገባል የሚል አመለካከት በመያዝ የእለት ጉርስ ማቀበል የተለመደ ሲሆን ፤ይህም በመብት ላይ ያልተመሰረተና ሥርዓት ያልተበጀለት ሲፈለግ የሚሰጥ ሲፈለግ የሚከለከል ነው።

መንግሥት ትምህርትን በነፃ የማቅረብ ግዴታ ያለበት ሲሆን፤ ማንኛውም ሰው ደግሞ የመማር መብት ቢኖረውም አካል ጉዳተኞች ተገቢውን ድጋፍ ባለማግኘታቸው ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ ያላቸው ተሳትፎ እየቀነሰ መምጣቱን መምህሩ ይጠቁማሉ።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት 95 በመቶ እድሜው ለአቅመ ሥራ የደረሰ አካል ጉዳተኛ ሥራ የለውም የሚሉት ዶክተር አበበ፤ በኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ድጋፍ ዝቅተኛ እንዲሆን ያደረገው አካል ጉዳተኞችን የሚመለከት የተቀናጀ ሀገራዊ ህግ አለመውጣቱ ነው። ስለዚህም ጊዜውንና የሰው ልጆችን እድገት የዋጀ ህግ ማውጣት አስፈላጊ መሆኑን ያነሳሉ።

ችግሩን ለማስተካከል ሁሉም በየደረጃው የሚመለከተው አካል በቅንነት መስራት አለበት። እንዲሁም የአካል ጉዳተኞችን ችግር የሚያቀሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ ማድረግ፣ በህብረተሰቡ ውስጥ ስለ አካል ጉዳተኞች ያለውን የተዛባ አመለካከት ማስወገድ፣ አካል ጉዳተኞችን በመንግሥት የስልጣን እርከን ውስጥ ማሳተፍና ሌሎችንም የመፍትሔ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ መምህሩ ያወሳሉ።

በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ የሚወጡ ህጎች ተግባራዊ አለመሆን መንግሥትን ጨምሮ በሁሉም ደረጃ የሚገኙ አካላት ኃላፊነት አለባቸው የሚሉት የአዲስ አበባ ከተማ አካል ጉዳተኞች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ገለታው ሙሉ ሲሆኑ፤ መንግሥት እንደ ሀገር የህግ፣ የፖሊሲና የአሰራር ሥርዓቶችን በማውጣት ተግባራዊ የማድረግ ሚናው የጎላ ነው ይላሉ፡፡

የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋም የአካል ጉዳተኞችን ችግር የኔ ነው ብሎ ማሰብ እንዳለበት የሚያነሱት አቶ ገለታው፤ አካል ጉዳተኞች ላይ የሚደርሱ ማህበራዊ ችግሮች በተለይም የአገልግሎት አካታችነት ላይ የፖሊሲና አፈጻጸም ችግሮች የሚስተዋሉ በመሆናቸው በጋራ በመስራት ችግሮቹን መቅረፍ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡

በአካል ጉዳተኞች ላይ በስራ እንቅስቃሴ የተለያዩ ችግሮች እየገጠማቸው ሲሆን ለአብነትም መስማት የተሳናቸው ዜጎች በየተቋማት አገልግሎት ፈልገው ሲሄዱ የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ አለመኖር ተግዳሮት እየሆነ እንደሆነ አቶ ገለታው አንስተዋል፡፡ በዚህም ማህበሩ በአዲስ አበባ ነዋሪ በሆኑ አካል ጉዳተኞች የሚደርስባቸውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በመለየት ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት የመፍትሄ ሀሳቦች ላይ ለመድረስ ጥረት እያደረገ ነውም ይላሉ።

እንደ አቶ ገለታው ገለፃ፣ ማህበሩ ከአብዛኛው የመንግሥት ተቋማት ጋር ቅርብ የሆነ ግንኙነት በመፍጠር በጋራ እየሰራ ሲሆን፤ እንዲሁም ከአንዳንድ ተቋማት ጋር በሚኖሩ የስብሰባ፣ የወርክ ሾፕና የስልጠና መድረኮችን በመጠቀም ስለ አካል ጉዳተኞች አካቶ እየሰራ ነው፤ የፖሊሲና የአሰራር ክፍተቶች ሲፈጠሩ ወደሚመለከተው ተቋሚ በመሄድ ችግሮቹን ለመፍታት ይጥራል፡፡ መስማት የተሳናቸው ዜጎች በተለያዩ መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት እንደልብ አገልግሎቶችን ማግኘት እየቻሉ እንዳልሆነ የሚያነሱት ደግሞ አቶ አበበ ታምራት ናቸው።

አቶ አበበና ባለቤታቸው መስማት የተሳናቸው ሲሆኑ ባለቤታቸው ለምርመራና ለወሊድ ወደ ህክምና ተቋሚ ሲሄዱ አስተርጓሚ ባለመኖሩ ከህክምና ባለሙያዎች ጋር መግባባት እንዳልቻሉ አስታውሰው፤ በህክምና ተቋማት መገልገል ያለባቸው ጉዳት አልባዎች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ሊገለገል እንደሚገባ ያነሳሉ፡፡ “ለአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ስኬት ትርጉም ያለው ትብብር” በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ ለ31ኛ ጊዜ፤ በአለም አቀፍ ደረጃ ለ32ኛ ጊዜ የአካል ጉዳተኞች ቀን በመከበር ላይ ይገኛል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ጥር 9/2016

Recommended For You