ግሎባላይዜሽን /ሉላዊነት/ አድማሱን አስፍቷል፤ ዓለም የአንድ መንደር ያህል እየሆነች ትገኛለች። አንዱ የዓለም ክፍል የሚፈልጋቸው ነገሮች ርቀት ሳይገድባቸው በፍጥነት የሚደርሱበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ለእዚህ መቀራረብ ደግሞ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ትልቁን ስፍራ ይይዛል።
ሰዎች ይህንን ቴክኖሎጂ ተጠቅመው መረጃዎችን በቀላሉ መለዋወጥ፣ ስራቸውን ማቀላጠፍ፣ ንግዳቸውን ማጧጧፍና ሌሎችንም ተግባራትን እየፈጸሙ ይገኛሉ። ዛሬ በረቀቁ የዲጂታል ቴክኖሎጂ መንገዶች በመጠቀም ንግድን ማቀላጠፍ፣ መማርና ማስተማር፣ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የፋይናንስ ስርዓቶችን መቆጣጠር፣ ሕዝብን መምራት፣ ማገልገል፣ ክፍያዎችን መፈጸም፣ ወዘተ. ቀላል ሆኗል።
ለሀገራችን ይህ ክስተት የቅርብ ጊዜ ቢሆንም፣ በዚህ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አማካይነት ብዙ ነገሮች እየተፈጸሙ ይገኛሉ። በሀገሪቱ ከጥቂት ዓመታት በፊት የዘርፉን የፈጠራ ስራዎች ለማበረታትና የስራ እድል ለመፍጠር ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ወደ ስራ ተገብቷል። በተለይ ዲጂታል ኢኮኖሚ በመገንባት ረገድ ብዙ እየተሰራ ይገኛሉ።
ሀገሪቱ ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት ሰጥታለች። ሀገሪቱ በአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትኩረት ከሰጠቻቸው አምስት የምጣኔ ሀብቱ ዘርፎች አንዱ ይሄው የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ነው። ይህን ተከትሎም በዘርፉ በርካታ ተግባሮች እየተከናወኑ ናቸው።
ዲጂታል ኢኮኖሚ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ፣ የንግድ አገልግሎትን በዘመናዊ መልኩ ለማቀላጠፍ፣ የአገልግሎት ጥራትን ለመጨመር፣ ዘላቂ እድገት ለማስመዝገብ ብሎም ዜጎች በሁሉም መስኮች ክህሎት እንዲያዳብሩ ለማድረግ ፋይዳ የጎላ እንደሆነ ታምኖበታል።
ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ በ2025 የዲጂታል ኢኮኖሚን እውን ለማድረግ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ነድፋ እየሰራች ትገኛለች። ስትራቴጂውም የተለያዩ የትኩረት አቅጣጫዎችን የያዘ ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥ የዲጂታል ኢኮኖሚውን ለማቀላጠፍ የሚረዱ መሰረተ ልማቶችን መገንባት፣ የዲጂታል ፕላትፎርሞችን መመስረትና የዲጂታል ስነ ምህዳር ልማትን ማስፋፋት የሚሉት ይገኙበታል።
በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገቱን የሚመጥን የዲጂታል ኢኮኖሚ ስርዓት መገንባትና በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ኢኮኖሚ እንዲኖር አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት እየተሰራ ቢሆንም፣ በማህበረሰቡ በኩል ያለው የዲጂታል ቴክኖሎጂ እውቀትና የግንዛቤ ደረጃ ዝቅተኛ መሆን አሁንም በዚህ ዘርፍ ለማደግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ እንደ አንድ ተግዳሮት ሆኖ ይጠቀሳል።
አቶ ዳንኤል በቀለ የአሸዋ ቴክኖሎሎጂ መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ነው፤ በሙያውም ሶፍትዌር ኢንጂነር ነው። እሱ እንደሚለው፤ ድርጅቱ አሸዋ ቴክኖሎጂ በቅርቡ ‹‹ናሀቢ›› የተሰኘ የድረገፅ መገንቢያ መሳሪያ ይፋ አድርጓል። የድረ ገፅ መገንቢያ መሳሪያ ድር ተኮር/web based/ መተግበሪያ ሲሆን፣ ማንኛውም የመንግሥትም የሆነ የግል ተቋም ድረ ገፅ መስራት ቢፈልግ ጥልቅ እውቀት እንዲኖረው ሳይጠበቅበት በፍጥነትና በአስተማማኝ ሁኔታ ለመስራት ያስችለዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ባለው ሂደት በዚህ ደረጃ የተዘጋጀ የድረ ገፅ መገንቢያ መሳሪያ የለም። ይሁንና ይህ ቴክኖሎጂ በሌላው አለም የሚታወቅና የተለመደ ነው። ለአብነትም ዎርድ ፕረስ፣ ዊክስ፣ ሾፕ ፋይል እና የመሳሰሉትን የድረ ገፅ መገንቢያዎች መጥቀስ ይቻላል።
አሸዋ ቴክኖሎጂ ይዞት የመጣው ስርዓት በዚህ ዘርፍ ላይ ያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት የያዟቸውን ቴክኖሎጂ ነው። ከዚህ አንፃር ቴክኖሎጂው ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ገበያም ጭምር ይተርፋል። ድረ ገፅ መገንቢያው የተሰራው በአፍሪካና በመላው ዓለም ካሉ ተመሳሳይ የድረ ገፅ መገንቢያ ቴክኖሎጂዎች ጋር ተወዳዳሪ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሲሆን፤ ከሁሉም በላይ ለኢትዮጵያ ገበያ እጅግ ጠቃሚ መሳሪያ ነው።
አቶ ዳንኤል እንደሚሉት፤ የዲጂታላይዜሽን ዘመን እንደመሆኑ ድርጅትና ቢዝነስ ያላቸው ሰዎች፣ ባለሙያዎች የመንግሥትና የግል ተቋማት በዚህ የድረ ገፅ መገንቢያ አማካኝነት በቀላሉ የራሳቸውን ድረ ገፅ ገንብተው ቢዝነሳቸውን፣ ንግዳቸውንና ሌሎችንም የሚፈልጓቸውን ነገሮች ማቀላጠፍ ይችላሉ። ለምሳሌ አንድ ባለሙያ እውቀቱን መሸጥ ቢፈልግ በዓለም አቀፍ ዙሪያ ካሉ ባለሙያዎች ጋር ተወዳድሮ በኦንላይን ራሱን ለገበያ እንዲያቀርብና ከበርካታ ደንበኞች ጋር የመገናኘትን እድል ድረ ገፅ መገንቢያው ይፈጥርለታል፤ ብራንዱን/መለያውን/ ይገነባለታል፤ ተአማኒነቱን ይጨምርለታል።
ደምበኞች ስለ አንድ ድርጅት አድራሻና መረጃዎች ቢፈልጉ በቀላሉ ማግኘት ያስችላቸዋል። በራስ ድረገፅ አማካኝነት በኦን ላይን ምርቶችን ለመሸጥም ያግዛል። የድረ ገፅ መገንቢያው ከዓለም ጋር ለመራመድ እድል የሚሰጥም ጭምር ነው ።
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ34 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ናቸው ተብሎ ይታሰባል። ከዚህ አንፃር እያንዳንዱ የመንግሥትም ሆነ የግል ድርጅት ብሎም ግለሰቦችና የቢዝነስ ሰዎች ምርቶቻቸውን በዲጂታል ወይስ በተለመደው መንገድ እያስተዋወቁ ስለመሆናቸው ራሳቸውን መጠየቅ ይኖርባቸዋል። ከዚህ አንፃር የድረ ገፅ መገንቢያ በሀገር ውስጥ ብቻ የታጠረ ባለመሆኑና ለአለምም ጭምር ክፍት በመሆኑ እነዚህ አካላት ምርቶቻቸውን በዲጂታል መንገድ የሚያስተዋውቁ ከሆነ ብራንዳቸውን/መለያቸውን/ ከፍለማድረግ እድል ይሰጣል።
አቶ ዳንኤል እንደሚያብራሩት፤ ዓለም በቴክኖሎጂ ፈጥኗል። ኢትዮጵያ ደግሞ ዓለም የደረሰበት የቴክኖሎጂ ደረጃ ላይ ለመድረስ አሁንም ገና ብዙ መስራት ይጠበቅባታል። ከቴክኖሎጂው ጋር ያለመግባባትና ቴክኖሎጂው በደረሰበት ደረጃ ልክ አውቆ ወደፊት የመጓዝ ችግሮች ይታያሉ። እንደዛም ሆኖ ፈጥነው የመጡ የውጪ ሀገር ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም ‹‹ፔን ፓል›› እና ‹‹ማስተር ካርድ›› የተሰኙት ደርጅቶች የውጪ ምንዛሪን ይጠይቃሉ። በዚህም ምክንያት በርካታ ወጣቶች፣ የፈጠራ ስራ ባለሙያዎችና ድርጅቶች የድረ ገፅ ባለቤት እንዳይሆኑ ችግር ፈጥሮባቸዋል። በእዚህ አይነት ሁኔታ እነዚህን አካላት የቴክኖሎጂ ተደራሽ ማድረግም ቀላል አይደለም።
አሸዋ ቴክኖሎጂ እንደ አንድ የቴክኖሎጂ ድርጅት እየሰራ ያለው ቴክኖሎጂውን ለሕብረተሰቡ በሚፈለገው ልክ ተደራሽ ማድረግ ላይ ነው። ከዚሁ ጎን ለጎን በዲጂታል እውቀትና አጠቃቀም ዙሪያ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎችን ይሰራል፤ ውይይቶችንም ያደርጋል። በተመሳሳይ ከሌሎች አጋር ድርጅቶችና በዘርፉ ካሉ ባለሙያዎች ጋር በትብብር እየሰራ ዘርፉን ለማሳደግ ጥረት እያደረገ ይገኛል።
እንደ ሌሎች ዘርፎች ሁሉ ዲጂታል ቴክኖሎጂው በርካታ ስራዎች ሊሰሩበት የሚችል ሰፊ ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰው፣ ማሕበረሰቡ ቴክኖሎጂው ገብቶት እንዲጠቀምበት ብቻ ሳይሆን በይበልጥ ሕይወቱንም የሚቀይርበት እድል የሚሰጠው መሆኑን ማሳየት ያስፈልጋል ይላሉ፤ ለእዚህ ደግሞ ቴክኖሎጂውን አስመልክቶ ሕብረተሰቡን ማስተማርና ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
‹‹በርካታ ሰዎች ድረ ገፅ አለን ቢሉም የድረ ገፅን ጥቅም በሚገባ ስለማያውቁ ድረ ገፅ እንዳላቸው እንኳን አይሰማቸውም›› ሲል ገልጾ፣ አብዛኛዎቹ ግለሰቦች የሚያውቁት ድረ ገፃቸውን እስከሚያሰሩበት ድረስ ያለውን ደረጃ እንጂ፣ ድረ ገፁ ከዛ በኋላ ይዞት ሊመጣ የሚችለውን በረከት፣ ሊያመጣ የሚችለውን ውጤትና ምን ያህል ሕይወት ቀያሪ እንደሆነ በቅጡ አይረዱም ይላል። ስለዚህ ይህንንም ጭምር ለሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ማስገንዘብ፣ የማሰልጠንና የማስተዋወቅ ስራዎች በድርጅቱ በኩል እየተሰሩ ይገኛሉ።
በአሁኑ ጊዜ መንግሥት የመንግሥት ተቋማትን ‹‹አውቶሜት›› የማድረግ፣ በቴክኖሎጂ የማዘመን፣ በቴክኖሎጂ እንዲመሩና አገልግሎቶችን ቀልጣፋና ምቹ የማድረግ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ይህም አበረታችና ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው። ነገር ግን ከዚህ ተግባር በተጨማሪ ድርጅቱ ለማሕበረሰቡ የዲጂታል መፍትሄ አቅራቢ መሆን ይፈልጋል። አንድ ተቋም ወይም ግለሰብ ምንም አይነት መተግበሪያና ድረ ገፅ ቢፈልግ ድረ ገፅ የማበልፀግ ስራ ይሰራል፤ ቴክኖሎጂውን ተደራሽ ለማድረግም ይተጋል። ማሕበረሰቡ ወደዲጂታል ቴክኖሎጂ መሄድ ፈልጎ ችግሮች ሳይገድቡት መስራት የሚችልበትን መድረክ ድርጅቱ ፈጥሯል። ይህ አይነቱ አገልግሎት በአሸዋ ቴክኖሎጂም ይሁን በሌሎች መሰል የቴክኖሎጂ ድርጅቶች በበዛ ቁጥር ደግሞ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ይቻላል።
በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰርና የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶክተር ለምለም ካሳዬ፤ በዚህ ትምህርት ዘርፍ ያሉ ተማሪዎች የቴክኖሎጂ ፕሮጀክቶችን እንደሚሰሩ ጠቅሰው፣ ለዲጂታላይዜሽንም እጅግ የቀረቡ መሆናቸውን ይናገራሉ። የሚያከናውኗቸው ፕሮጀክቶች መደርደሪያ ላይ ከመቀመጥ ውጪ ስራ ላይ ውለው ውጤት እያመጡ አይደሉም ሲሉ ዶክተር ለምለም ይናገራሉ።
አሸዋ ቴክኖሎጂ ስራ ላይ ያዋለው ‹‹ነሃቢ›› የተሰኘው ድረ ገፅ መገንቢያ በዲጂታል ቴክኖሎጂው ዘርፍ ትልቅ እምርታ የታየበት ነው ብለዋል። ለሀገርም ሆነ ለወጣቱ የስራ እድል ፈጠራ አስተዋፅኦው የጎላ መሆኑን ጠቁመው፣ በተለይ በዚህ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ለሚንቀሳቀሱ ወጣቶች ትልቅ መነቃቃትን እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።
ዶክተር ለምለም እንደተናገሩት፤ ሕብረተሰቡ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ሃብቶች እጁ ላይ አሉ። ስልክ፣ ታብሌት፣ ላፕቶፕ፣ ዴስክቶፕና ሌሎችም የቴክኖሎጂ ውጤቶች በሕዝብ እጅ ውስጥ ገብተዋል። የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ (የአይ ሲ ቲ) ቴክኖሎጂም የዛኑ ያህል በፍጥነት አድጓል። ሆኖም ግን አሁን ባለው ሁኔታ አብዛኛው ሰው የቴክኖሎጂ ሀብቱን በሚገባ እየተጠቀመበት አይደለም።
ከዚህ አኳያ በቅድሚያ ትልቅ ስራ መሰራት ያለበት በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዙሪያ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጥ ነው ሲሉም ያስገነዝባሉ። በሕብረተሰቡ በዲጂታላይዜሽን ላይ ያለው አመለካከት እንዲጨምር ተጨማሪ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግም ተናግረው፣ በዛው ልክ ደግሞ የቴሌኮም መሰረተ ልማት አሁን ሀገሪቱ በደረሰችበት ኢኮኖሚያዊ እድገት ልክ አብሮ ማደግ ይጠበቅበታል ብለዋል። የኢንተርኔት ዋጋ ክፍያ ፍትሃዊ ካልሆነም መስተካከል እንደሚኖርበት ነው ያስገነዘቡት።
እንደ ኃላፊዋ ማብራሪያ፤ በኢትዮጵያ በተለይ በዲጂታል መንገድ ንግድ ማካሄድ አሁን አሁን በመጠኑ ተጀመረ እንጂ ከዚህ በፊት አልተለመደም። ቻይናን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት ግን አብዛኛውን ግብይታቸውን የሚፈፅሙት በዲጂታል ቴክኖሎጂ አማካኝነት ነው። በኢትዮጵያ ዲጂታል ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም በሕብረተሰቡ በኩል ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆን ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም ካለው የእውቀት ክፍተት ጋር ተዳምሮ በዲጂታል ቴክኖሎጂው ብዙ ርቀት አልተሄደም።
ዶክተር ለምለም የፒ ኤች ዲ ዲግሪያቸውን የሰሩት በዋይርለስ ኮሙዩኒኬሽን መሆኑንም ጠቅሰው፣ በዋይርለስ ኮሙዩኒኬሽን ሕብረተሰቡ ምን ያህል ተጠቅሞበታል የሚለው መጠናት እንዳለበት ይጠቁማሉ። እነዚህን ገመድ አልባ የመግባቢያ መሳሪያዎች በምን ያህል ደረጃ ሕብረተሰቡ እየተጠቀመባቸው እንዳለ ብቻ ሳይሆን እነዚህ መሳሪያዎች የመጠቀም እውቀቱ ምን ያህል እንደሆነ ተጨማሪ ጥናት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ። ‹‹እንዴት መጠቀም እንደሚቻልም ተመሳሳይ ጥናት ማድረግ እንደሚገባና ይህን ማድረግ የሚቻል ከሆነ ወደ ዲጂታል ዓለም የምናደርገውን ግስጋሴ ማፋጠን እንችላለን›› ይላሉ።
የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ክፍተትና የግንዛቤ እጥረት ብቻ ሳይሆን ድህነትም ተጨማሪ ምክንያት መሆኑንም ዶክተር ለምለም ተናግረው፤ ዲጂታል ቴክኖሎጂውን የሚጠቀመው በአብዛኛው በከተማዎች አካባቢ የሚኖረው የሕብረተሰብ ክፍል መሆኑን ገልጸዋል። ቴክኖሎጂውን በተቀረው የኢትዮጵያ ክፍሎችም ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ያመለክታሉ። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ከድህነት መላቀቅ እንደሚገባት ይጠቁማሉ።
ዶክተር ለምለም እንደሚሉት፤ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የመንግሥትን ትኩረት አግኝቶ እየሰራ የሚገኝ ትልቅ ተቋም ነው። በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይ ሲቲ)፣ በዳታ፣ በሳይበር ሴኪዩሪቲ፣ በሶፍትዌር ቴክኖሎጂ የልህቀት ማእከላት አሉት። በዲጂታል ቴክኖሎጂም በርካታ ተሞክሮዎች አሉት።
በዚህ ረገድ አዳዲስ ነገሮችን መፍጠር የሚችሉና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ሀገሪቱ የምትፈልገውን መፍትሄ ሊያመጡ የሚችሉ ተማሪዎችንም ይዟል። ከዚህ አኳያ እንዲህ አይነቱን ሀብት በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል የሚቻል ከሆነ የዲጂታል ቴክኖሎጂውን ወደፊት ማራመድ ይቻላል ።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥር 7/2016