ታህሳስ 17 ቀን 1980 ዓ.ም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ልዩ ቀን ሆና ትታወሳለች። ከዛሬ 36 ዓመት በፊት ልክ በዛሬዋ ዕለት ኢትዮጵያ ባዘጋጀችው የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪቃ የእግር ኳስ ዋንጫ (ሴካፋ) ዚምባብዌን በፍጹም ቅጣት ምት በማሸነፍ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫውን ከፍ ያደረገችበት ዕለት ነበር።
ይህች ልዩ ቀን በተለይም የፍፃሜውን ጨዋታ በቀጥታ ሲያስተላልፍ በነበረው አንጋፋው የስፖርት ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ ዛሬም ድረስ ትታወሳለች። ‹‹ … ወይኔ! ወይኔ! ወይኔ ገብሬ! ገብሬ የመታውን የዚምባብዌው 2 ቁጥር በራሱ ግብ ላይ … በራሱ ግብ ላይ ከመረብ አሳረፈ … በራሱ ግብ ላይ ከመረብ አሳረፈ …
ዋንጫውን ለብሔራዊ ቡድኑ አምበልና ለአሁኑ የዋልያዎቹ አሠልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ የሰጡት የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) ፕሬዚዳንት፣ መንግሥቱ ኃይለማርያም ሲሆኑ፣ የተሰማቸውን ደስታ የገለጹት 100 ሺ ተመልካች የሚይዝ ስታዲየም ለመሥራት ቃል በመግባት ነበር።
በ1980 ኢትዮጵያ ያስተናገደችው ይህ የሴካፋ ውድድር በብዙ ነገሮች ተወጥራ የነበረችውን ሀገር በአንድነት ያቆመ እንደነበር ይነገራል። ኢትዮጵያ ከብቸኛው የአፍሪካ ዋንጫ ድሏ 26 ዓመታት በኋላ ያነሳችው የመጀመሪያ የሴካፋ ዋንጫ በወቅቱ ወግ አጥባቂ ሶሻሊስቶች ሳይቀሩ ያወጁትን ሰዓት እላፊ ረስተው በደስታ የዘለሉበት ነበር።
ውድድሩ በሁለት ምድብ ተከፍሎ የተካሄደ ሲሆን ኢትዮጵያ ከኬንያ ፣ ታንዛንያ እና ዛንዚባር ጋር በምድብ አንድ ተደልድላ ጨዋታዎቿን በአዲስ አበባ አድርጋለች። በአመዛኙ አዲስ ትውልድ ይዛ የቀረበችው ኢትዮጵያ የመክፈቻ ጨዋታዋን ከታንዛንያ ጋር አድርጋ ባዶ ለባዶ አጠናቀቀች። በሁለተኛ ጨዋታም በተመሳሳይ ከዛንዚባር ጋር በተመሳሳይ ያለ ጎል ተለያይታ ከብዙዎች የዋንጫ ግምት ውጭ ሆነች። ሆኖም በሦስተኛው ጨዋታ ጠንካራዋ ኬንያን ሁለት ለአንድ በማሸነፍ በአምስት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጣ ዛንዚባርን ተከትላ ወደ ቀጣይ ዙር አለፈች።
በመቀጠል በግማሽ ፍፃሜው የወቅቱ ስመ ገናና ቡድን ዛምቢያን አራት ለባዶ አሸንፋ የመጣችው የውድድሩ ቁንጮ ዩጋንዳን ሦስት ለባዶ በመርታት ወደ ፍፃሜ አለፈች። በፍፃሜው ጨዋታም ዚምባብዌን ገጥማ እስከ ተጨማሪ ደቂቃ ስትመራ ብትቆይም የወቅቱ ድንቅ አጥቂ ገብረመድኅን ኃይሌ በመጨረሻዎቹ ሽርፍራፊ ደቂቃዎች ባስቆጠራት ግብ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ። ጨዋታው በተጨማሪ ደቂቃዎች ቀጥሎ ሁለቱም ቡድኖች ግብ ባለማስቆጠራቸው ወደ መለያ ምት አምርተው ጨዋታው በድራማዊ ትዕይንቶች ታጅቦ በኢትዮጵያ አሸናፊነት ተጠናቀቀ።
በውድድሩ ድባብ እና ጨዋታውን በቴሌቪዥን ሲያስተላልፍ የነበረው ደምሴ ዳምጤ የሚታወሱ ገለፃዎች አሁንም ድረስ ከኢትዮጵያውያን አዕምሮ ስላልወጣው ውድድር የወቅቱ የቡድኑ አምበል የነበረው እና ወሳኟን የፍፃሜ ግብ ያስቆጠረው እንዲሁም ውድድሩን በተጫዋችነት እና ኋላ ላይ ደግሞ በረዳት አሰልጣኝነት ያሸነፈው ገብረመድኅን ኃይሌ ትውስታውን በተለያዩ አጋጣሚዎች ገልጿል።
ገብሬ በአንድ ወቅት ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ እንዲህ በማለት ነበር ትውስታውን ያጋራው፤
“ ወቅቱ ትልቅ ሀገራዊ አንድነት ያስገኘ ውድድር ነበር፤ ቡድናችን ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች አቻ ተለያይቶ ነበር ውድድሩን የጀመረው። ሴካፋ ዋንጫ እንደ አሁኑ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን ብቻ ሳይሆን የመካከለኛ እና ደቡብ አፍሪካ ሀገራትን ያካተተ ጠንካራ ፉክክር የሚደረግበት ነበር። በውድድሩ ጅማሮ ነጥቦች ጥለን ነበር፤ ከዛ ግን ተከታታይ ጨዋታዎች አሸንፈን ወደ ጥሩ መንፈስ የመጣንበት ውድድር ነበር።
“የፍፃሜው ጨዋታ ብዙ ድራማዎች ነበሩት። አንዱ በጨዋታው የነበረው እንቅስቃሴ፣ የደጋፊያችን ጉጉት እና በጨዋታ መሐል የነበረው ተጫዋቾቻችን ጉዳት እና ድካም ነበር። ብዙ ተሰላፊዎቻችን ደክመው መጠነኛ ጉዳታቸውን ተቋቁመው ነበር ጨዋታውን ያካሄዱት። ሌላው የማልረሳው ደግሞ ጎሏ የገባችበት መንገድ እና ደቂቃው ነው። ከመስመር የተሻማችው ኳስ በግምባር ለማስቆጠር ከሚያዳግት ቦታ ነበር ገጭቼ ያስቆጠርኳት። ሌላው ደቂቃው ነው፤ መደበኛ ሰዓት ተጠናቆ የተሰጠው ተጨማሪ ደቂቃ ሊያልቅ ሽርፍራፊ ደቂቃዎች ሲቀሩት ነበር ጎሉን አግብቼ አቻ የሆንነው። እንደውም ግቡ ካስቆጠርን በኋላ ደስታችን ገልፀን ልክ እንደገባን ነው የጨዋታው ማጠናቀቂያው ፊሽካ የተነፋው።
“በጣም የሚገርመው እና አጓጊ የነበረው ደግሞ የመለያ ምቱ ድራማ ነው። እኔ፣ ነጋሽ ተክሊት እና አማኑኤል ኢያሱ በተከታታይ መለያ ምቶቹን አስቆጠርንና እነሱ አንድ አስቆጥረው፤ ተካበ ሁለት መልሶ ሦስት ለአንድ መራን። ከዛ ቀጥሎ በቀለ ብርሃኑ ሳተ፤ በድጋሚ ዕድል ተሰጥቶትም ሳተውና እነሱ አገቡ። ከዛ በኋላ የነበረው አምስተኛ መቺው መንግሥቱ ሁሴን ቢያገባው እናሸንፍ ነበር፤ ሆኖም ሳተና ሦስት አቻ ሆን ውጥረት ውስጥ ገባን። ከዛ ግን ወደ ተጨማሪ ምት ተሸጋግረን የዚምባብዌ መቺ ሳተና እኛ በዳኛቸው ደምሴ አማካኝነት አስቆጥረን ጨዋታውን አሸነፍን።
“ከጨዋታው በኋላ የነበረው ደስታ ልዩ ነበር። የህዝቡ ስሜት በቃላት ለመግለፅ ይከብዳል። ጨዋታው ልክ እንደተጠናቀቀ ሕዝቡ ደስታውን መቆጣጠር አቅቶት ሜዳ ውስጥም ገብቶ ነበር። በዛን ወቅት የሰዓት እላፊ ነበር። ዋንጫውን ካነሳን በኋላ ግን በደስታ ብዛት ለቀናት የሰዓት እላፊው ተነስቶ ነበር። ሀገራዊ አንድነት እና ጥሩ የእግር ኳስ መነሳሳት የነበረበት ወቅት ነው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 21 ቀን 2016 ዓ.ም