መጪውን ጊዜ የሚወስነው አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የሰውን አእምሮ ማለትም ችግር የመፍታት እና ውሳኔ የመስጠት ችሎታዎችን ይዞ ሰውን ተክቶ ሥራዎችን ማከናወን ማስቻል መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ አሁን ላይ በኢትዮጵያም ሥራ ላይ እየዋለ፤ ምርምር እየተካሔደበት ያለው አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ምንድን ነው? ስንል ባለሙያዎችን አነጋግረናል፡፡

የኢቲስዊች ፕሮግራም ቢሮ ዳይሬክተር አቶ አቤኔዘር ወንድወሰን እንደሚናገሩት፤ ቀደም ባሉት ዓመታት ኮምፒውተርም ሆነ ሌሎች ቴክኖሎጂዎች ሰውን ተክተው የመሥራት አቅም አልነበራቸውም፡፡ አሁን ግን የተለያዩ አልጎሪዝሞች ማለትም በፊት ከነበረው በላይ ለኮምፒውተሩ ብዙ መረጃ በመሥጠት፤ በተሠጠው መረጃ ልክ እንደሰው ማሰብ እንዲሞክር እና ውሳኔ እንዲሠጥ ማስቻል አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የሚባለውን አዲስ ቴክኖሎጂ አስተዋውቋል፡፡

ይህ ቴክኖሎጂ የተገኘው ሰው የተለያዩ መረጃዎችን ይዞ እንዴት እንደሚወስን በማስተማር እና ኮምፒውተሩ ያንን መረጃ ይዞ የሚጠየቀውን ጥያቄ እንዲመልስ ለማስቻል በተሠራው ሥራ ነው፡፡ በተዘዋዋሪ የኮምፒውተር ሥርዓት ላይ ሰው የሚሠራቸውን ሥራዎች እንዲሠራ ለማሻሻል በተካሔደው ሙከራ፤ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ተፈጠረ ማለት ነው፡፡ ይህ እንደሰው በምክንያታዊነት ማሰብን እና መሥራትን ያካተተ ሥርዓት መሆኑን አቶ አቤኔዘር ያስረዳሉ፡፡

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አንድ ነገር ብቻ አለመሆኑን ሲያስረዱ፤ አንደኛው ማሽንን ማስተማር ነው፡፡ ማሽን ወይም ኮምፒውተር ሲማር ከሚሰጠው መረጃ ተነስቶ ምላሽ እንደሚሠጠው ሁሉ፤ ይሄኛውም ማለትም አርቴፊሻል ኢንተለጀንሱ ተምሮ ዕውቀት እንዲያካብት ይደረጋል ይላሉ፡፡

ሌላኛው አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ጥልቅ ማስተማር ነው፡፡ ይህ ማሽኑ በጣም ብዙ መረጃ ተሸክሞ ለምሳሌ ምስሎችን፣ የንግግር ድምፆችን እና ሌሎችንም መለየት የሚችል ሲሆን፤ ይሄኛው በሁለተኛ ደረጃነት ተቀምጦ እንደሚገኝ ያብራራሉ፡፡

ተፈጥሯዊ የቋንቋ ሂደት ወይም ተፈጥሯዊ ንግግርን ለኮምፒውተሩ ማሳየት፣ ማስተማር እና ማስተርጎም የሚቻልበት ሁኔታም አለ፡፡ ይሄ ማሽኑ እንደሰው ማውራት እንዲችል ማድረግ ነው፡፡ ከዛ ውስጥ ለምሳሌ በአገልግሎት መስጫዎች ሰዎች ሳይኖሩ የደንበኞችን ጥያቄዎች ልክ እንደሰው ሆኖ መመለስ እና ድምፅ እየሠሙ ቋንቋን መተርጎምም በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መፈፀም ተችሏል ሲሉ አቶ አቤኔዘር አርቴፊሻል ኢንተለጀስን የደረሰበትን ደረጃ ያብራራሉ፡፡

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የሚያየውን ወይም የተሠጠውን ምስል እና ቪዲዮ በመተርጎም ማወቅ የሚችልበት ሁኔታ መኖሩን አመልክተው፤ ለምሳሌ አንድ ሰው ቤት ለመግባት የአንድ ሰው ፊት የቤቱ መግቢያ ቁልፍ ማድረግ እንደሚቻል አብራርተዋል፡፡ ይሄ የሆነው ማሽኑ ከዚህ በፊት የተመዘገበ ነው ብሎ የሰውን ፊት እንዲለይ ፕሮግራም በመደረጉ መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡

እንደ አቶ አቤኔዘር ገለፃ፤ ከላይ የተገለፁትን ሥርዓቶች አንድ ላይ በማድረግ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን ለተለያዩ ጉዳዮች መጠቀም ይቻላል፡፡ ይሄን ለምሳሌ በጤና፣ በፋይናንስ ሥራዎች በተለይም በባንክ አገልግሎት፣ በትምህርት እና በመዝናኛ ላይ ትልቅ ለውጥ እያመጣ ነው፡፡

በአጠቃላይ ግን አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የተፈጠረበት ምክንያት ሰዎች በሚያስፈልጉበት ቦታ ሁሉ ገብቶ በመሥራት የሰዎች ድካም ለመቀነስ መሆኑን በማመላከት፤ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ሰዎችን ተክቶ እየሠራ መሆኑ ለአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ሃሳብ እንደምሶሶ የሚወሰድ ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በመኖሩ ሥራዎች የሚከናወኑበት ጊዜ እጅግ ያጠሩ እንደሚሆኑ፤ አርቴፊሻል ኢንተለጀንሱም ተንትኖ እና ተርጉሞ በሰከንዶች ምላሽ መስጠቱ ሕይወትን እንደሚያቀል አብራርተዋል፡፡ በባንክ የገንዘብ ልውውጥ ላይ እየተሠራ ያለውን ጠቅሰው፤ የመጀመሪያው ጥቅም የክፍያ ማጭበርበሮችን መለየት እንዲችል ተደርጎ ተሠርቷል፤ በዚህም ብዙ ውጤት መጥቷል ብለዋል፡፡

አርቴፊሻል ኢንተለጀንሱ ደንበኛው ከቀን ወደ ቀን እንዴት አድርጎ ገንዘብ እንደሚያዘዋውር በማጥናት ያ ደንበኛ ከሚሳየው የአጠቃቀም ልምድ ወጣ ሲል ወዲያውኑ በመለየት ያ ደንበኛ ራሱ ላይሆን እንደሚችል አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ምልክት በመሥጠቱ ደንበኞች እንዳይጭበርበሩ ሰዎችን እና ተቋማትንም እየጠበቀ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በደህንነት ጥበቃ በኩልም ትልቅ ሥራ እየሠራ መሆኑን በማስታወስ፤ ዐሻራን አንብቦ በር መክፈት የእዚሁ ቴክኖሎጂ ውጤት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አሁን ላይ በየቦታው ፊትን እና ዐሻራን የሚለየው አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሆኑን ተናግረዋል። በደንበኞች አገልግሎት ላይም በዚሁ ቴክኖሎጂ የታገዘ የጥሪ ማዕከል አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን በመጥቀስ፤ ለደንበኞች የተለያዩ መረጃዎችን፣ ግላዊ ምክረ ሃሳቦችን የመሥጠት ሥራ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አማካኝነት እየተካሔደ ነው ብለዋል፡፡

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የሚይዘው መረጃ የብዙዎችን በመሆኑ የአንድ ተቋም ደንበኛ ምን እንደሚፈልግ በመገመት ለደንበኞቹ መሠጠት ያለበትን አገልግሎት ቀድሞ ተረድቶ በተቋሙ የሚሰጠው አገልግሎት እንዲያሻሽል መረጃ ይሰጣል ብለዋል፡፡

አንድ ተቋም ከደንበኞች ባህሪ እና ፍላጎት በመነሳት ምን ዓይነት ዕቃ ላቅርብ ወይም ምን ዓይነት አገልግሎት ልስጥ የሚለውን በመተንተን ምን ዓይነት አገልግሎቶችን በቀላሉ ቀድሞ በመረዳት ብዙ ተቋማት ማቅረብ እንዲችሉ አስችሏቸዋል፡፡

እንደ አቶ አቤኔዘር ገለፃ፤ በጤና ዘርፍ ላይ ልክ እንደ ሕክምና ባለሙያ ሆኖ ምክረ ሃሳቦችን ሁሉ የመስጠት ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ ኤክስሬ፣ ኤም አር አይ እና ሲቲ ስካን በማንበብ አንድ ታካሚ የት ቦታ ላይ ምን እንዳመመው በቀላሉ በሰው ዓይን ተነበው ሊለዩ የማይችሉትን በሙሉ በመለየት የተሻለ የሕክምና አገልግሎት እንዲኖር አስችሏል፡፡

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የታካሚውን ያለፈ የሕክምና መረጃን ስለሚይዝ ቀጣይነት ያለው ሕክምናዎችን ለምሳሌ እጅ ላይ የሚታሰር ነገር በማድረግ የታካሚውን የጤና ሁኔታ የሕክምና ባለሙያዎች መከታተል እንዲችሉ የሚያግዝበት ሁኔታ ላይ መደረሱንም አብራርተዋል፡፡

የተለያዩ መረጃዎችን በመተንተን እና በመተንበይ በምርምር የተሻለ መድኃኒት እንዲኖር የተሻለ አስተዋፅኦ ያደርጋል ያሉት አቶ አቤኔዘር፤ በትምህርት ላይም የተሻለ አገልግሎት እንዲገኝ ያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በአንድ ክፍል ውስጥ ግላዊ የማስተማሪያ ማለትም የተማሪውን አቅም በማጥናት የተመቸ የማስተማሪያ መንገድ በመቅረፅ ዕገዛ እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

የፈተና ውጤትን ወዲያውኑ አርሞ በደቂቃ ውጤቱን የማሳወቅ እና አስጠኚ ሆኖ የማገልገል እንዲሁም ለተማሪዎች የመለማመጃ ጥያቄዎችን የመሥጠት ሥራ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እየተሠራ መሆኑን ነው ያመላከቱት፡፡

በአጠቃላይ በቤት ውስጥ የተሻለ ሕይወት እንዲኖር፣ የኃይል አጠቃቀም ላይ እንዳይባክን የማገዝ፣ የደህንነት ካሜራ እንዲኖር የማድረግ እና አኗኗራችን ምርጥ እንዲሆን የማገዝ ሥራንም ያከናውናል ብለዋል፡፡

የቤት ውስጥ ዕቃዎች ሲበላሹ ቶሎ ከመለየት ጀምሮ መኪናዎች ያለ አሽከርካሪ መነዳት የሚችሉበትን ሁኔታ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አማካኝነት ማከናወን መቻሉንም አመላክተዋል፡፡

በዓለም አቀፉ የግሎባል ቴክኖሎጂ ኤንድ ዲጂታል ሶልዩሽን የሚሠሩት አቶ አበበ በቀለ በበኩላቸው፤ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በቀላል አገላለፅ ሰው ሠራሽ የማሰብ ችሎታ ማለት ነው ይላሉ፡፡ ሰው ያስባል፣ ይሠራል፡፡ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስም እንደሰው ሆኖ አስቦ አንድ ሰው ሊያከናውነው የሚችለውን ውስብስብ ሥራዎች ያካሂዳል፡፡ ምናልባት ማመዛዘን እና ውሳኔ እስከ መስጠት የዘለቀ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ጥቅምን አስመልክቶ ሲያስረዱ፤ በጦር ቴክኖሎጂ እና በሌሎችም በተለያዩ ዘርፎች ላይ እጅግ የተወሳሰቡ ሥራዎች በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አማካኝነት በመሠራት ላይ ናቸው ብለዋል፡፡ የሰው ልጅ ጉልበት ውስን በመሆኑ አንድን ሥራ የሚሰራበት ሰዓትም ውስን ነው፡፡ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ያለ ምንም ድካም ከሰው በላይ እየሠራው መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

ሰው ለረዥም ሰዓት ሊሠራው የማይችለው ጉልበቱ ወይም አዕምሮውን የሚደክመውን አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በቀላሉ ይሰራዋል ሲባል፤ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች አካባቢ፣ የአየር ትራንስፖርት በሚሰጥበት አካባቢ፣ የባቡር መስመሮች፣ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በሌሎችም ከፍተኛ የሰው አቅም የሚጠይቁ ብልሽት ሲያጋጥም ጀምሮ ያሉ ሥራዎችን ለማከናወን አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ፕሮግራም በተደረገው ልክ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በርግጥ ሰዎችን ተክቶ ሲሠራ ሥራ አጥነት ሊፈጠር እንደሚችል እና ከማሰብ አንፃር ሲታይ የሰዎች የመሥራት እና የማሰብ አቅምን በመንጠቅ የሚገባቸውን እንዳይሠሩ የማድረግ እና የምርምር ሥራዎች ላይ ብዙ ድጋፍ በማድረግ የማሰላሰል ችሎታ ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥር ይችላል ተብሎ ይገመታልም ብለዋል፡፡

ነገር ግን ከሚያስከትለው ጉዳት ይልቅ ያለው ጠቀሜታ ብዙ በመሆኑ፤ ቴክኖሎጂውን መጠቀም የተሻለ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ መረሳት የሌለበት ሰዎች እንሥራ ቢሉም የማይሠሩትን እና የማይወስኑትን ውሳኔ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ይሠራል፡፡

አቶ አቤኔዘር እንደ አቶ አበበ ሁሉ፤ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ከቁጥጥር ውጭ ይሆናል የሚል ስጋት መኖሩን ይጠቁማሉ፡፡ ቴክኖሎጂው በጣም ምጡቅ በመሆኑ፤ ከሰዎች ቁጥጥር ውጭ ከሆነ አደጋው የከፋ ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡ በተቃራኒው ሰዎች በቀናት እና በሰዓታት የሚሠሩትን ሥራ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በሰከንዶች መሥራቱ የሥራ ዕድልን ይሻማል የሚለው ግን እርሳቸው አያምኑበትም፡፡

አንድ ሰው ቀኑን ሙሉ የሚሠራውን ሥራ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በሰከንዶች ቢሠራው፤ ያ ሰው በሌላ አምራች በሚያደርገው ሥራ ላይ እንዲያተኩር ያግዘዋል እንጂ ሰዎች የሥራ ዕድል እንዳይኖራቸው አያደርግም ብለዋል፡፡

በርግጥ በዓለም ላይ አሁን ያለው የፀሐፊዎችን ሥራ ሙሉ ለሙሉ ይቀንሳል የሚለው ስጋት መኖሩን አመልክተው፤ የፀሐፊዎችን ሥራ ተክቶ ኢሜል መያዝ፣ ደብዳቤ መፃፍ እና ፕሮግራም ማውጣት በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እየተከናወነ በመሆኑ፤ በቀጣዩ አንድ ዓመት ሙሉ ለሙሉ የፀሐፊዎች ሥራ ይጠፋል ተብሎ ይፈራል ብለዋል፡፡ አቶ አቤኔዘር እንዳመለከቱት፤ ይህ ቢሆንም ትኩረትን አንድ ሥራ ላይ ከማድረግ ይልቅ ሌሎች አማራጮችንም ለማየት እንዲቻል መንገድ ይፈጥራል ብለዋል፡፡

ሁሉንም ነገር አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ከሠራው ሰዎች ብዙ እንዳያስቡ እና እንዳያሰላስሉ ያግዳል የሚለውንም ሃሳብ የሚቃወሙት አቶ አቤኔዘር፤ እንደውም የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መምጣት ሰዎች ብዙ እንዲያነቡ እና ብዙ እንዲያውቁ ያግዛል ብለዋል፡፡ በፊትም በጎግል ፍለጋ ተካሂዶ ለማንበብ ይመጣ የነበረው ውጤት፤ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በጣም ፈጣን እና ብዙ መረጃ በአንድ ጊዜ የሚገኝበት ሁኔታ መኖሩ እንደውም የሰዎች ዕውቀት የበለጠ በንባብ እንዲያድግ ያግዛል ብለዋል፡፡ ዋናው ነገር ቴክኖሎጂ ሲመጣ መልካም ጎን ቢኖረውም በተቃራኒው ጉዳት አይኖረውም ማለት አይቻልም፡፡ ሙሉ ለሙሉ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ላይ ጥገኛ መሆን ጥሩ ባይሆንም በጥንቃቄ በመያዝ ቴክኖሎጂውን መጠቀም የግድ ነው ብለዋል፡፡

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ከኢትዮጵያ አንፃር ተለይቶ ሲታይ፤ ቴክኖሎጂዎችን በመኮረጅ የመሥራት ተነሳሽነት አለ፡፡ አጠቃላይ ከኢትዮጵያ ስትራቴጂ እና ከኢኮኖሚው ጋር የማያያዝ ብዙ ተነሳሽነቶች ታይተዋል ያሉት አቶ አቤኔዘር፤ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረት ላይ እየተገነቡ ያሉ ጅምር የቴክኖሎጂ እንቅስቃሴዎች እና ብዙ ጥናቶችን እየተካሔዱ መሆናቸው ፤ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ፕሮግራሞች ተቀርፀው በየዩኒቨርሲቲው ትምህርቶች መሠጠት መጀመራቸው ተገቢ እና ትክክለኛ ርምጃ ነው ብለዋል፡፡ ዓለም ወደፊት ሲሔድ ወደኋላ መቅረት ሁልጊዜም እንደ ሀገርም እንደ ግለሰብም ተጎጂ እንደሚያደርግ አመልክተው፤ ኢትዮጵያም አምናበት ከጊዜው ጋር ለመሔድ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ብዙ እንቅስቃሴዎች ማድረጓን አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት አመላክተዋል፡፡

አሁን ኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን ተግባራዊ ማድረጓ በብዙ መልኩ የሚጠቅማት መሆኑን አቶ አበበም የተናገሩ ሲሆን፤ ለሰላም፣ ለኢኮኖሚ በአጠቃላይ ተዘርዝረው ለማያልቁ ጉዳዮች ጥቅም ያለው በመሆኑ ኢትዮጵያም በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ላይ የምትሠራውን ሥራ አጠናክራ መቀጠል አለባት ብለዋል።

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በተመራማሪዎች ብቅ ያለው በ1950ዎቹ ነበር፡፡ መነሻው በፈላስፋው በአለን ቱሪንግ ስም የተሰየመው የቱሪንግ ፈተና ፕሮግራም ነው። አንድ ማሽን ከሰው ባህሪ ጋር ምን ያህል ሊጣጣም እንደሚችል ለማወቅ በ1950 ቱሪንግ ፈተና አከናወነ፡፡ በመቀጠል በ1956 ዓ.ም የሒሳብ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ጀን ማካርት ስለሰው ሰራሽ ማሽን የማሰብ ችሎታ ጉዳይ አነሱ፡፡ በመቀጠል አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ ደረሰ፡፡

ምሁራኖቹ የወደፊቱን አስመልክቶ ሲናገሩ፤ ኢትዮጵያ ዓለም የደረሰበት ደረጃ ላይ ደርሳ፤ እየታዩ ያሉ ትልልቅ ለውጦች ይበልጥ ያድጋሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ደረጃ አሁን ጅምር ቢሆንም፤ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ትልቅ ለውጥ ይመጣል፡፡ በሰዎች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሻሻሎች ይኖራሉ፤ ግብርና፣ ትምህርት እና ጤና ላይ ትልልቅ መሻሻሎች ይመጣሉ ብለዋል፡፡ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን መሠረት ያደረጉ ምርትን ለማሳደግ የሚረዱ ብዙ ምርምሮች ሊካሔዱ እና በዛም ውጤት ሊገኝ ይችላል፡፡ ግን ይሄን ሲባል ሊመጣ የሚችለውንም ጉዳት በጥንቃቄ እየተከታተሉ ማለፍ ያስፈልጋል ብለዋል።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You