የአበባ እርሻ የሚያስከትለው ጉዳት በገለልተኛ አካል ተጠንቶ እንዲቀርብ ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ

አዲስ አበባ፡- ግብርና ሚኒስቴር የአበባ እርሻ ልማት በአካባቢ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በገለልተኛ ቡድን አስጠንቶ እንዲያቀርብ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በግብርና ሚኒስቴር የአበባ እርሻ ልማት ምርታማነትና የአካባቢ አያያዝ ሥርዓት ውጤታማነትን በተመለከተ የ2014/2015 በጀት ዓመት ክዋኔ ኦዲት ግኝት ላይ ውይይት አድርጓል፡፡

በወቅቱ የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ አራሬ ሞሲሳ እንደገለጹት፤ የአበባ ልማት በሀገሪቱ ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ ዘርፍ ቢሆንም የራሱ የአሠራር መመሪያ የለውም።

ከአበባ እርሻ ልማት ጋር ተያይዞ በአካባቢ ላይ የደረሰው ጉዳት በገለልተኛ አካላት ማስጠናት እንደሚገባ ጠቁመው፤ ይህ መሆኑ ተጓዳኝ ችግሮችን ማወቅና የመፍትሄ ርምጃ ለመውሰድ ያግዛል ሲሉ አስረድተዋል።

የአበባ ልማት ያስከተለው ጉዳት በገለልተኛ ቡድን ተጠንቶ ሪፖርቱ እንዲደርሰን እንፈልጋለን ያሉት ምክትል ሰብሳቢዋ፤ ተቋሙ የድርጊት መርሀ ግብሩንም እስከ ህዳር 30 ለቋሚ ኮሚቴውና ለሚመለከታቸው አካላት መላክ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የአበባ ልማት ሥራው የዜጎችን ደህንነት በጠበቀ መልኩ እንዲሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ያለውን ግንኙነት በደንብ በማጠናከር የክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም የተጠያቂነት ሥርዓት ሊኖር እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡

ምክትል ሰብሳቢዋ እንዳመላከቱት፤ ለአበባ ልማቱ ፖሊሲና ደንብ ሳይዘጋጅበት እየተሠራ በመሆኑ ዘርፉን ለመምራት የሚያስችል ደንብና አሠራር መዘርጋት ይገባል፡፡

በዘርፉ እየተዘጋጀ ያለው መመሪያ ጸድቆ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ለገንዘብ ሚኒስቴር፤ ለፌዴራል ኦዲት መስሪያ ቤት፤ ለምክር ቤቱ የግብርና ጉዳዮችና ለመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ እንዲቀርብ ሲሉ ተናግረዋል።

በፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው፤ ከ2012 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ በግብርና ሚኒስቴር የአካባቢ እርሻ ልማት አምስት ባለድርሻ አካላትን እና 11 የአበባ እርሻ ድርጅቶች ላይ ትኩረት ያደረገ የኦዲት ክንዋኔ መቅረቡን አመላክተዋል።

በኦዲት ግኝቱ መሰረት ለአበባ እርሻ ልማት የሚገዙ ኬሚካሎች በተገቢው መጠን መግዛት እንደሚገባ እና የአበባ እርሻዎች ሌላ ምርት እንዲለማባቸው ሲደረግ በገለልተኛ አካል የኬሚካል ቅሪታቸው ጥናት መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በተጨማሪም የኬሚካል ማከማቸትና አወጋገድ ሂደቱ አካባቢን በማይጎዳ መልኩ ሊሆን ይገባል ሲሉ አስረድተው፤ በሰራተኞች ደህንነት፣ በአካባቢ ጥበቃና የመረጃ አደረጃጀቱን ማዘመን እንደሚገባ ተናግረዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የአበባ አልሚ ድርጅቶች የሚጠቀሟቸው ግብአቶችና ኬሚካሎች የሚያመጡትን ተጽዕኖ ለመከላከልና ተገቢ የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ሁኔታዎች እንዲኖሩ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛል።

በቋሚ ኮሚቴው በተሰጡ አስተያየቶች መሰረት ከሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመሆን በድርጊት መርሀ ግብሩና በኦዲት ግኝቱ መሰረት ለማስተካከል እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You