በገበያ ትስስርና የገጽታ ግንባታ አላማውን ያሳካው ጉባኤ

የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማሕበር ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በቅርቡ ለ12ኛ ጊዜ ዓለም አቀፍ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ጉባኤ አካሂዷል። ጉባኤው በርካታ የዘርፉ ተዋናዮች ተሳትፈዋል። ጉባኤው ዘርፉን ለማሳደግ፣ የገበያ ትስስር ለመፍጠር፣ ምርቶቹን ለማስተዋወቅና የገጽታ ግንባታ ለመፍጠር በእጅጉ እንደሚያግዝ አስቀድሞም እንደታመነበት ሁሉ፣ ስኬታማ መሆኑን የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማሕበር ጉባኤው ገልጿል።

“ኢትዮጵያ ለግብርና ምርት ፍላጎት አስተማማኝ ምንጭ” በሚል መሪ ሀሳብ የተካሄደው ይህ ጉባኤ አገሪቱ ለወጪ ንግዱ ያላትን እምቅ ሀብት ለዓለም በማስተዋወቅ የውጭ ምንዛሪ ግኝቷን ማሳደግ እንድትችልና ባለሀብቶችንም በመሳብ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱ ተገልጿል። ከዚህ ባለፈም ዘርፉ የሚጠበቅበትን እንዲወጣና በመንግሥት የተያዘው የወጪ ንግድ እቅድ እንዲሳካ ለማድረግና የጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎች እና ቅመማቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማሕበርም በዘርፉ እያበረከተ ያለውን የሥራ እንቅስቃሴ ለማስተዋወቅ ጉባኤው የላቀ ድርሻ ማበርከቱም ተጠቁሟል።

12ኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ጉባኤ በኢትዮጵያ መካሄዱ በዘርፉ ያለውን የገበያ ትስስር ለማጠናከርና የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለማስተዋወቅ ማስቻሉን የጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎች እና ቅመማቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማሕበር ገልጿል፤ ማሕበሩ ዓላማውን ማሳካት የቻለ ጉባኤም ብሎታል። በጉባኤው በአገሪቱ የሚገኙ ላኪዎች፣ ግብዓት አቅራቢዎች፣ አገልግሎት ሰጭዎችና ገዥዎችን በአንድ መድረክ ማገናኘት መቻሉን ማሕበሩ ጠቅሶ፣ እነዚህ አካላት የንግድ ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል ብሏል። በተለይም በጉባኤው የተገኙ አምራቾች፣ ላኪዎችና አቅራቢዎች አዳዲስ የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ ማስቻሉንም አስታውቋል።

ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው የግብርና ምርቶች መካከል የጥራጥሬና ቅባት እህሎች በውጭ ምንዛሪ ግኝት ከፍተኛ አቅም እንዳላቸው የጠቀሱት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ሲሳይ አስማረ፣ ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ጉልህ አበርክቶ ያላቸውን እነዚህን ምርቶች በጥራት አምርቶ ለገበያ ማቅረብ ተገቢ መሆኑንም አመልክተዋል። ለዚህም ለዘርፉ ዕድገት ማነቆ የሆኑ ችግሮችን መፍታት ቀዳሚው ሥራ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

‹‹ለዘርፉ ዕድገት ማነቆ ከሆኑ ችግሮች መካከል የፀጥታ እጦት፣ የኮንትሮባንድ ንግድና የምርት ጥራት ችግር ተጠቃሽ ናቸው›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ችግሩን ለመፍታት ከመንግሥትና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ እንደሆነም ተናግረዋል። በቀጣይም ዘርፉን በማሳደግ አገሪቱ በሚፈለገው ደረጃ የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ ለማድረግ የምርት ጥራትን በማሻሻልና የገበያ መዳረሻ ሀገራትን በማስፋፋት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት፤ በወጪ ንግድ ሰፊ ድርሻ ካላቸውና ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ የግብርና ምርቶች መካከል የላቀ ድርሻ ያላቸው የቅባትና ጥራጥሬ ሰብሎች በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ገብተው ተወዳደሪ መሆን እንዲችሉ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው። ከሥራዎቹ መካከልም በየዓመቱ የሚዘጋጁ ጉባኤዎች ይጠቀሳሉ። በቅርቡ የተካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባኤም የግብይት ሰንሰለትን የሚዳስሱ፣ የአቅርቦትና የገበያ ሁኔታን የሚመለከቱ፣ የዓለም ገበያው ያለበትን ሁኔታ ለሀገር ውስጥ ላኪዎች ሊያስረዱ የሚችሉ ከ14 በላይ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበውበታል።

ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ጉባኤዎች ይልቅ በቅርቡ የተካሄደው 12ኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬ እና ቅባት እህሎች ጉባኤ በርካታ ተሳታፊዎችን ማስተናገድ የቻለ ሲሆን፤ በዚህም ጥሩና አበረታች ውጤት ተመዝግቧል። በቀረቡት ጽሁፎች ዙሪያ ጥያቄዎች ቀርበው ተገቢ ምላሾች ከመድረኩ ተሰጥቶባቸዋል።

በጉባኤው ላይ የአገር ውስጥ እንዲሁም የተለያዩ አገራት እንግዶች ተገኝተዋል፤ ከእነሱም መካከል ላኪዎች፣ ገዥዎች፣ የእርሻ ግብዓት አቅራቢዎች፣ የእርሻ ማሽን አቅራቢዎች፣ ተጋባዥ እንግዶች ከተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ ኤምባሲዎች፣ የልማት አጋር ድርጅቶች እና መገናኛ ብዙሃን ተጠቃሾች ናቸው።

በጉባኤው የተገኙት አጠቃላይ ተሳታፊዎች 482 ሲሆኑ፤ ከእነዚህ መካከልም የአገር ውስጥ ተሳታፊዎች 292 ናቸው። ከ19 የተለያዩ አገራት የመጡ የውጭ አገር ተሳታፊዎች ደግሞ 70 ይደርሳሉ። በጉባኤው ከተሳተፉ ሀገሮች መካከል ቤልጂየም፣ ቡርኪናፋሶ፣ ቻይና፣ ግብጽ፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ፣ ሕንድ፣ እስራኤል፣ ጃፓን፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን፣ ናይጄሪያ፣ ፓኪስታን፣ ሳውዲአረቢያ፣ ታንዛንያ፣ ሱዳን፣ ቱርክ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ዩክሬንና ሲንጋፖር ይገኙበታል።

ከኤምባሲዎች የተገኙት ተጋባዥ እንግዶች፣ ከመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ከግሉ ዘርፍ፣ ከልማትና አጋር ድርጅቶች እንዲሁም የሚዲያ ባለሙያዎች በአጠቃላይ 120 እንደሚደርሱም ማህበሩ ጠቅሷል። ከተሳታፊዎች መካከል በተለይም አምራችና ላኪዎች ከገዢ አገራት ጋር ስኬታማ የሆነ የንግድ ለንግድ የአቻ ውይይቶችን ማካሄድ ችለዋል።

በተፈጠረው የገበያ ትስስር የንግድ ለንግድ አቻ ውይይትም 20 በመቶ የሚሆኑ ላኪዎች በቀጣይ ምርቶቻቸውን መላክ የሚያስችላቸውን ስምምነት መፈረም እንደቻሉ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ ይህ ከገዥ አገራት ጋር የተደረገ ስምምነት ውጤታማ እንደነበርም አስታውቀዋል። በተጨማሪም የዓለም አቀፍ ምርት ፍላጎት መጠን እና የዋጋ አዝማሚያ መረጃዎችን ማግኘት መቻሉንም ገልጸዋል። ይህንንም ከተሳታፊዎቹ ባገኙት ግብረመልስም ማረጋገጥ እንደቻሉ ተናግረዋል።

በጉባኤው የሽልማት ፕሮግራም እንደተካሄደም የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ በጥራጥሬ እና ቅባት እህሎች ዘርፍ ከፍተኛ አፈጻጸም ላሳዩ ስድስት ድርጅቶች የዋንጫ እና የምስክር ወረቀት መሰጠቱን ገልጸዋል። በተለይም በጥራጥሬ እና በቅባት እህሎች ዘርፍ ከፍተኛ ዕውቅና ባገኙ 12 ባለሙያዎች ጠቃሚና ተገቢ መረጃ መቅረቡንም አመላክተዋል። ከ12ቱ ባለሙያዎች ሁለቱ የአገር ውስጥ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ አስሩ ደግሞ የውጭ አገር መሆናቸውን አመልክተዋል። የዘርፉ ባለሙያዎች ያቀረቧቸው ጥናታዊ ጽሁፎች፤ የገበያ መረጃዎች፣ የምርት አቅርቦት እና የዋጋ አዝማሚያዎች ትንተናዎች እና ትንበያዎችን ያካተቱ ጽሁፎች እንደነበሩም ጠቁመዋል።

12ኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ጉባኤ ዋና ዓላማ አድርጎ የተነሳው አባላት ወይም የኢትዮጵያ ላኪዎች ከገዢዎች ጋር ግንኙነት ማድረግ እንዲችሉ መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ሌላው የጉባኤው ዓላማ በዚሁ አጋጣሚ የአገሪቱን መልካም ገጽታ ማስተዋወቅ እንደሆነና ይህንንም ማሳካት እንደተቻለ ነው ያመላከቱት።

እሳቸው እንዳሉት፤ ከዚህ ቀደም የተካሄዱ ዓለም አቀፍ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ጉባኤ ኢትዮጵያ በቅባት እህሎችና በጥራጥሬ ምርት አቅርቦት ቀዳሚውን ስፍራ እንድትይዝ አድርገዋል። በመሆኑም በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ በጥራጥሬና የቅባት እህል አቅራቢዎች ሰሌዳ ላይ የተቀመጠች አገር መሆን ችላለች። በተለይም ጥራት ያላቸውና ስም ያላቸው ምርቶች ማለትም እንደ ሁመራ ሰሊጥ የመሰለ ምርት ኢትዮጵያ በዓለም ስሟ እንዲጠራ አድርጓል። ለዚህም ላኪዎችና ማሕበሩ ትልቅ ድርሻ የነበራቸው መሆኑን ነው የጠቀሱት።

በቀጣይም ኢትዮጵያ በግብርና ምርት ያላትን እምቅ ሃብት ተጠቅማ ኢኮኖሚዋን ማሳደግ እንድትችል እንዲህ አይነት ጉባኤዎች ወሳኝ ናቸው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የግብርና ምርት ለኢትዮጵያውያን እንጀራ በመሆኑ በዘርፉ ሰፊ የሆነ የእሴት ሰንሰለት ስለመኖሩ አስረድተው ምርቱን በሌሎች ዓለማት የማስተዋወቅ ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመላክተዋል።

12ኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ጉባኤ የተካሄደበት ወቅት አዳዲስ ምርቶች ወደ ገበያ እየገቡ ያሉበት መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰው፣ ገዢዎች ወደ አገሪቷ መጥተው ፋብሪካዎችን መጎብኘት መቻላቸው ውጤታማ አድርጎናል ነው ያሉት። በዚህ ረገድም ሰፊ ሥራ እየተሰራ እንደሆነ አመላክተው፣ ላኪዎች እስከታች ወርደው አርሶ አደሩ ምርቱን እንዲያወጣ በማድረግ በተለይም ኢትዮጵያ የምትታወቅበትን የሰሊጥ ምርት በጥራት ሰብስቦ ወደ ገበያ ለማቅረብ ሰፊ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ያለው ሁኔታ ምርት ለማንቀሳቀስ ምቹ መሆኑን አቶ ሲሳይ ጠቅሰው፣ የሰላሙ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ ይህ ዓመት ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት ማግኘት እንደሚቻልም ተናግረዋል።

ለውጭ ገበያ በሚቀርቡ ምርቶች ላይ እሴት ከመጨመር ጋር ተያይዞ ማሕበሩ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ፤ ለእዚህም ከአኩሪ አተርና ከመሳሰሉት ዘይት ለማምረት የተደረጉ ሙከራዎች መኖራቸውንም በአብነት ጠቅሰዋል። በአገሪቱ ከምርት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ፋብሪካዎች በሚፈለገው መጠን ጥሬ ዕቃዎችን እያገኙ እንዳልሆነም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

ማሕበሩ ምርቶቹን በጥሬው ብቻ ለውጭ ገበያ ከማቅረብ ይልቅ እሴት ጨምሮ ለመላክ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ያጋጠሙ ችግሮችን አንድ በአንድ በጥናት በመለየት ለሚመለከተው አካል በማቅረብ መፍትሔ የማምጣት ሥራ እየተሰራ ነውም ብለዋል። ለአብነትም ከችግሮቹ መካከል ተጠቃሽ የሆነውን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ሰፊ መሬት የሌላቸው አርሶ አደሮች በኮንትራት እርሻ በስፋት እንዲያመርቱ የማድረግ ሥራ መሰራቱን አስታውቀዋል። በቀጣይም ይህ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠው፣ አገሪቷ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንድትችል እንደሚሠራ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረቱት የጥራጥሬና የቅባት እህሎች በዓለም ላይ እጅግ ተወዳዳሪና ተፈላጊ ናቸው። የአገሪቷ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ለብዙ የዓለም አገራት ቅርብ እና አመቺ መሆን ለእዚህ አንዱ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል። ይህንኑ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ምርቱን በጥራት በማምረት በተቀላጠፈ መንገድ ለዓለም ገበያ ማቅረብና ኢኮኖሚያዊ አበርክቶውን ከፍ ለማድረግ ማሕበሩ ትልቅ ድርሻ አለው።

ለእዚህም ምርቶቹን በጥራት ለዓለም ገበያ ለማቅረብ የማስተዋወቅ ሥራ መሥራት አንዱና ዋነኛው ሥራ መሆኑንም አስታውቀዋል። በአፍሪካ ኢትዮጵያን የሚያህል ሰፊ መሬት ያለውና በግብርና ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ያለው አገር የለም ሲሉ ጠቅሰው፣ ይህን በተቻለ መጠን ወደ ማዕከል አምጥቶ ለዓለም ገበያ ለማስተዋወቅ የቅንጅት ሥራ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። በእዚህ በኩል ማሕበሩ ከመንግሥት ጋር እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በአብዛኛው ምርቶቿን ወደ ኤዥያ፣ መካከለኛው ምስራቅ፣ አሜሪካና አውሮፓ ስትልክ መቆየቷን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ምርቶቹ ለአፍሪካ አገራት በተለይም ጎረቤት ከሆኑ አገራት ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠር ወደ ኬንያ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ እየተላኩ መሆናቸውን አመልክተዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ይህም ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ያላትን የንግድ ቁርኝት በማጠናከር በኩል ያለው አበርክቶ ጉልህ ነው። በጉባኤው ላይም የጉባኤው ተሳታፊ በርካታ ገዢዎች ከአምራችና ላኪዎች ጋር የተዋወቁበትና አዳዲስ የገበያ ዕድሎችም የተገኙበት ሁኔታ ታይቷል።

በ2015 በጀት ዓመት 147 ሺህ 205 ቶን የሚደርሱ የቅባት እህሎች ለውጭ ገበያ ቀርበው 253 ሚሊዮን 344 ሺህ 754 የአሜሪካ ዶላር ገቢ ተገኝቷል። ለውጭ ገበያ ከተላኩ 377 ሺህ 261 ቶን የጥራጥሬ ምርቶችም እንዲሁ 310 ሚሊዮን 568 ሺህ 278 የአሜሪካ ዶላር ገቢ ተገኝቷል።

በ2016 በጀት ዓመት ከቅባት እህሎችና ከጥራጥሬ ሰብሎች ወጪ ንግድ 593 ሚሊዮን 300 ሺህ ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ሲሆን፤ በሩብ ዓመቱም ከ117 ሚሊዮን 769 ሺህ ዶላር በላይ ተገኝቷል።

በጉባኤው የተገኙ የተለያዩ የውጭ ዜጎች ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን እምቅ ሃብት የመረዳት ዕድል ያገኙ ሲሆን፤ ለንግድ አመቺ መሆኗን ጭምር መገንዘብ ችለዋል። ደንበኞች በጉባኤው የገቡት ውል ተፈጻሚ እንደሚሆንም አስታውቀዋል፤ የውል መቋረጥም ሆነ የጭነት መስተጓጎል ሊገጥማቸው እንደማይችል ፕሬዚዳንቱ አረጋግጠዋል። በአጠቃላይ ጉባኤው የንግድ ልውውጥና የገበያ ማስፋት ሥራ የተሠራበት ብቻ ሳይሆን አገራዊ የገጽታ ግንባታ መፍጠር የተቻለበትና ስኬታማ መሆን የቻለ እንደነበር አስታውቀዋል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You