የፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ ቅድመ ዝግጅትን በሚመለከት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴርን ያገለለ ሥራ እያከናወነ መሆኑ ተጠቁሟል። የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በበኩሉ መንግሥት ያላወቀውን ሥራ እያከናወነ አለመሆኑን ገልጿል።
ፈረንሳይ በታሪኳ ለሦስተኛ ጊዜ የምታዘጋጀው የ2024ቱ ኦሊምፒክ ሊካሄድ ወራት ብቻ እንደሚቀሩት ይታወቃል። ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከዓመት አስቀድሞ የተለያዩ ዝግጅቶች መጀመሩን እንዲሁም በአውሮፓ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በማሰባሰብ ረገድ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። ይሁን እንጂ ኮሚቴው እያከናወነ ያለውን ተግባር የኢትዮጵያን ስፖርት በበላይነት የሚመራው የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እንደማያውቀው ገልጿል። ሰሞኑን ለ27ኛ ጊዜ በመቀሌ በተካሄደው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት የመንግሥትን አቅጣጫ በገለፁበት ወቅት ‹‹የፓሪስ ኦሊምፒክን ቅድመ ዝግጅት በሚመለከት ኮሚቴው እቅዱን እንዲያቀርብ ቢጠየቅም በቂ ምላሽ ካለመስጠቱም በላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና ክልሎችን ብቻ ነጥሎ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን በማግለል ከአዲስ አበባ እስከ ፓሪስ የሚል እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል›› ብለዋል።
ይህም አካሄድ ተገቢነት የሌለውና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ኃላፊነትና ስልጣን ያላካተተ መንግሥትም በመጨረሻ ‹‹ሀብት አምጣና ውድድሩ ላይ እንካፈል›› ቢባል መልስ ሊሰጥበት የማይችለው አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ መሆኑን አስገንዝበዋል። በዚህ ሁኔታ የሚዘልቅ ከሆነም የ2024 ኦሊምፒክ እንደባለፈው ኦሊምፒክ ችግር ውስጥ ሊጥል እንደሚችል ስጋታቸውን ገልፀዋል። ኦሊምፒክ የሀገራት የሰንደቅ ዓላማ እና ተሳትፎ ጉዳይ በመሆኑ የትኞቹም ሀገራት በብሄራዊ ደረጃ በማቀድና በመመካከር ይሰራሉ። ይህ ካልሆነ ግን በ2020 ኦሊምፒክ ያጋጠመው ችግር እንዳይደገም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴም ሆነ አብረውት እየሰሩ የሚገኙት አካላት ከወዲሁ በጉዳዩ ላይ ግልጽ አቅጣጫ ይዘው እንዲሄዱ አሳስበዋል። ከእዚህ ውጪ የሆኑ አካሄዶች ግን በየትኛውም መንገድ ተቀባይነት የሌላቸውና መንግሥት ያስቀመጠውን ፖሊሲ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤት ያገለለ ሥራ ተቀባይነት እንደማይኖረው ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ተወካይ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ፣ በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ለተነሳው ጉዳይ ምላሽ ሰጥተዋል። በዚህም ኮሚቴው መንግሥትን ያገለለ ሥራ አለማከናወኑን የጠቀሱት ተወካዩ፤ ኮሚቴው የቅድመ ዝግጅት ሥራውን እያከናወነ ያለው ከመንግሥት ጋር መሆኑን ገልጸዋል። በ2024 ኦሊምፒክ መንግሥትም ሆነ ህዝቡ ትልቅ ነገር የሚጠብቅ እንደመሆኑ የኮሚቴውን እንቅስቃሴ መንግሥት እየደገፈው እንደሚገኝ አስረድተዋል። ‹‹የፓሪስ 2024 ኦሊምፒክን በሚመለከት ከፈረንሳይ ኤምባሲ ጋር ስንነጋገር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳያውቅ አልሰራንም›› ያሉት አቶ ገዛኸኝ፣ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋርም በመነጋገር እየተሰራ መሆኑንና ከዚህ ባለፈ የሚከሰቱ ችግሮችን ግን በውይይትና በመነጋገር መፍታት አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል። “ህዝቡን ተስፋ የሚያስቆርጥ ንግግር አስፈላጊ አይደለም “ ሲሉ አቶ ገዛኸኝ አክለዋል።
የኦሊምፒክ ቅድመ ዝግጅቱን አስመልክቶም የኮሚቴውና የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚዎች ከወራት በፊት ተገናኝተው ባደረጉት ውይይት ስራቸውን መጀመራቸውን ጠቅሰዋል። በዚህም መሰረት በ2020 ኦሊምፒክ የተፈጠሩ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል እቅድ በማውጣት ከአምና ጀምሮ እየሰራ ሲሆን፤ በተለይም በአውሮፓ የሚገኙ በርካታ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በማነቃነቅ በገንዘብም ሆነ በሞራል እገዛ በማድረግ ውጤት ማምጣትና ሀገርን ማስጠራት ላይ ያተኮረ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በፓሪስ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት ከተደረገም በኋላ በተደረገው እንቅስቃሴ ከፓሪስ ወጣ ብሎ በሚገኝ ከተማ ኦሊምፒኩ ሊካሄድ ጥቂት ወራት ሲቀሩ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድን ዝግጅት ሊያደርግ የሚችልበትን ሁኔታ በማመቻቸት ስምምነት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል። በዚህም መሰረት ቡድኑ 42 ኪሎ ሜትር የሚሆን ርቀት ነጻ የመለማመጃ ጎዳና እንዲሁም ዘመናዊ የስልጠና አካዳሚ ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል ብለዋል። ይህም የኢትዮጵያን በጎ ገጽታ ለመገንባት የሚደረግ ጥረት እንደሆነ ነው ተወካዩ ያስረዱት።
በመጨረሻም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ከ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ በኋላ አመርቂ ውጤት ቢያስመዘግብም ህዝቡ ከሚጠብቀው ውጤት አንጻር ማሳካት ያልቻለው በምን ምክንያት ነው ሚለውን መገምገም፣ የአመራሩ የእርስ በእርስ ግንኙነት ምን እንደሚመስል እንዲሁም ከተቋማት ጋር ያለው ግንኙነት ሰላማዊና ተቋማዊ መሆኑን በግልጽ እንዲመለከትና ለኦሊምፒኩ ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደርግ ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ህዳር 18/2016