ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችና የአፍሪካ ተጠቃሚነት ኢትዮጵያን እንደማሳያ

እ.አ.አ በያዝነው 2023 የአፍሪካ ህዝብ ብዛት ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን በላይ መድረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የዓለምን ሁለት በመቶ አካባቢ ሕዝብ የያዘችው አፍሪካ፤ በዓለም ላይ የሕዝብ ብዛቷን ጨምሮ ያላት የተፈጥሮ ሃብት እና ሌሎችም የተለያዩ ፖለቲካዊ ምክንያቶች ከምንጊዜውም በላይ አህጉሪቷን ተፈላጊ አድርገዋታል፡፡ ይህን ተከትሎ የተለያዩ ሀገሮች መንገዶችን እየፈለጉ ሀገሪቱን ወደራሳቸው ለመሳብ እየሞከሩ ይገኛሉ።

አፍሪካን የፈለጉ ሀገሮች አህጉሪቷን ከሚስቡባቸው መንገዶች መካከል የጋራ ጉባኤ በማዘጋጀት ትስስር መፍጠር አንደኛው ነው፡፡ ይህንን አሜሪካ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ፣ ቱርክ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ጀርመን ከአፍሪካ ጋር የሚያስተሳስሩ ጉባኤዎችን አካሂደዋል። ቀጥታ ከአፍሪካ ጋር ብቻ ሳይሆን ከራሳቸው የቅርብ ቡድኖች ጋር በሚያካሒዱት ጉባኤ ላይም የአፍሪካን መሪዎች በመጋበዝ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ጥረት ያደርጋሉ። አሁን ኦስትሪያ 20ኛውን የተባበሩት መንግሥታት ኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ጉባኤ በማካሔድ ላይ ሲሆን፤ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተጋብዘዋል፡፡ የጉባዔው የክብር እንግዳ ጠቅላይ ሚኒስትር በጉባኤው ንግግር እንደሚያደርጉ እና ይህም በአፍሪካዋ ኢትዮጵያ እና በኦስትሪያ መካከል ያለውን ግንኙነት በተሻለ መልኩ እንደሚያሳድገው ይጠበቃል።

ባለፈው ሳምንት በጀርመን በተካሔደው የጂ20 ‘ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ’ (CWA) በተሰኘው ለውጥ ተኮር በሆነው ጉባኤ ላይ የአፍሪካ ሀገራት እና የተለያዩ አጋሮች ንግግር አድርገዋል፡፡ በዚህ የትብብር መድረክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢኮኖሚ ትብብር እና የግሉን ዘርፍ ማጠናከር በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በተካሔደው ውይይት ላይ ተሳትፈዋል:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጎን ለጎን ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ተገናኝተው መወያየታቸውንም በማህበራዊ የትስስር ገፅ ተጠቁሟል። “የተጠናከረው ግንኙነታችን እና ዘርፈ ብዙ ትብብራችን በመተማመን እና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ እና ዘላቂ ልማት ላይ ያተኮረ ነው” ሲሉ ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ጽፈዋል።

ከኦስትሪያ እና ከጀርመን በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሳዑዲ አረቢያም አቅንተው ነበር። በዓለም ላይ ጠንካራ ኢኮኖሚ እየገነቡ ካሉ ሀገራት መካከል ተጠቃሽ መሆን የጀመረችው ሳዑዲ አረቢያ፤ የ”ሳዑዲ-አፍሪካ” የመሪዎች ጉባኤን ለመጀመሪያ ጊዜ አዘጋጅታለች።

እንደሌሎቹ ጉባኤዎች ሁሉ የ”ሳዑዲ-አፍሪካ” የመሪዎች ጉባኤም በአፍሪካ ሀገራት እና በሳዑዲ አረቢያ መንግሥት መካከል ያለውን ትብብር ለማሳደግ ያለመ መሆኑን የሳዑዲ አረቢያ መገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ጠቁመዋል። በሳዑዲ አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ከተሳተፉ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛኒያ እና ሌሎችም ሀገሮች በመሪዎቻቸው አማካኝነት ታድመዋል።

የአረብ ኒውስ ልዑሉን ጠቅሶ እንደጠቆመው፤ ትብብርን፣ አጋርነትን እና የንግድ ግንኙነቶችን ለማዳበር ባላቸው ጉጉት የ”ሳዑዲ-አፍሪካ” የመሪዎች ጉባኤን እንዳዘጋጁ ተናግረዋል፡፡ ይህ ጉባኤ የንጉስ ሳልማን የልማት ተነሳሽነት በአፍሪካ መጀመሩን የሚያበስር መሆኑንም በአረብ ኒውስ ተጠቁሟል።

አረብ ኒውስ በዘገባው እንዳብራራው፤ የሳዑዲ- አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ፤ የፖለቲካ ቅንጅቶችን ለማጎልበት፣ ቀጣናዊ የጸጥታ ስጋቶችን ለመፍታት፣ በጥናት እና በሀገር ውስጥ አዳዲስ የኃይል መፍትሄዎችን ለመፍጠር እና የኢንቨስትመንት ትብብርን ለማጎልበት እንዲሁም የኢኮኖሚ አቅምን ለማስተዋወቅ ያስቻለ እንደነበር ተነግሮለታል።

የጉባኤው ቀዳሚ ትኩረት በሳዑዲ እና በአፍሪካ መካከል የፖለቲካ፣ የክልላዊ ደህንነት እና የኢኮኖሚ አጋርነት ዙሪያ ትብብር እና ቅንጅት ማጠናከር ነው የተባለ ሲሆን፤ የአህጉሪቱ ሀገራት በጉባኤው ሃሳባቸውን እና ፍላጎታቸውን በመሪዎቻቸው አማካኝነት አንፀባርቀዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በ”ሳውዲ አፍሪካ” የመሪዎች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በኢትዮጵያ እና በሳዑዲ መካከል ያለው ግንኙነት ታሪካዊ እና ሥር የሰደደ መሆኑን በማስታወስ፤ እንዲህ ዓይነት ጉባኤ እጅግ በሚያነቃቃ መልኩ ግንኙነትን ለማደስ ይረዳል፤ ግንኙነታችንን ማደስ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ሳዑዲ እና ኢትዮጵያ ግንኙነታቸውን ማደስ እንዳለባቸው ከማስታወስ ባሻገር፤ አፍሪካ እና ሳዑዲ ያላቸው ጂኦግራፊያዊ ተቀራራቢነትን በመጥቀስ፤ እነሳዑዲ ከእንግዳ ተቀባዩ የአፍሪካ ሕዝብ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ከምንጊዜውም በላይ አሁን ማሳደግ እና መቅረብ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ይህ በልዩ ሁኔታ በሳዑዲ እና በአፍሪካ መካከል እየታደሰ ያለው ግንኙነት አፍሪካ ያላትን ዕምቅ አቅም ለማንፀባረቅ የሚረዳ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ የሳዑዲ እና የአፍሪካ ግንኙነት መጠናከር በአህጉራዊ ደረጃ ተቀባይነት ባገኘው የልማት ዕቅድ የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063፣ የተባበሩት መንግሥታት የዘላቂ ልማት ግቦች እና የሳዑዲ የ2030 ራዕይ እንዲሳካ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል።

እነዚህን ራዕዮች እውን ለማድረግ የሁለቱንም የኢኮኖሚ ዕድገት እድሎች በመጠቀም የሳዑዲ-አፍሪካ ትብብርን ማጠናከር እና በተለይም የፋይናንስ ልማት ትብብርን ማሳደግ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ጠቁመዋል።

ከኢትዮጵያ ጋር ባላት ግንኙነት ሳዑዲ የታዳሽ ኃይል፣ ጤና እና የትምህርት ዘርፍ ላይ ድጋፍ ማድረጓን በማስታወስ፤ በቀጣይ በጋራ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ትስስርን በማጠናከር የኢኮኖሚ ግንኙነት ላይ ሰፊ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አመላክተዋል፡፡

አህጉራዊ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥን በተመለከተ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ከኢትዮጵያ አምስቱ የፖሊሲ ዋልታዎች መካከል ግብርና ዋነኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በዓመት ሁለት ጊዜ እየተመረተ መሆኑን፤ ከ6 ሚሊዮን ሔክታር ያላነሰ መሬት በእርሻ እየለመ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ የከተማ ግብርናን በማበረታታት የጓሮ አትክልት እና የእንስሳት እርባታ ላይ ሰፋፊ ሥራዎች በመሠራት ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

በግብርናው ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ሀብት በመመደብ በኢትዮጵያ ቢሳተፉ አፍሪካን ከማሳደግ ባሻገር የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡ ጨምረውም ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት አረንጓዴ ልማት ላይ በስፋት እየተንቀሳቀሰች እንደምትገኝ አብራርተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ልማት ስኬትን በተመለከተ በሰፊው የተናገሩ ሲሆን፤ የሳዑዲ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ተሳታፊዎች በተለይም የመካከለኛው ምስራቅ ተዋናዮች ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። እ.ኤ.አ. ከ2019 ጀምሮ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል፤ ከ25 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን በየዓመቱ በሚያንቀሳቅሰው ግዙፍ የደን ልማት መርሀ ግብር ተግባራዊ እርምጃዎችን እየወሰደች ነው ብለዋል። ሀገሪቱ 32 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን መትከሏንም ተናግረዋል።

እ.ኤ.አ. በ2026 መጨረሻ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ሥራዋን በማጠናከር፤ በአጠቃላይ 50 ቢሊዮን ዛፎች ትተክላለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ ለአንድ ዓመት ሙሉ በ64 ሚሊዮን ቤንዚን የሚንቀሳቀሱ መኪኖችን ከመንገድ ከማስወገድ ጋር ሊመሳሰል የሚችል መሆኑን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሳዑዲ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ከሳዑዲ አረቢያ አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን ጋር የሁለቱን ሀገራት ሁለገብ ግንኙነት እና አጋርነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ተወያይተዋል። በተጨማሪ ከጂቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ እና ከሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

የሳዑዲ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ የፖለቲካ ቅንጅቶችን ለማጎልበት፣ የአካባቢውን የጸጥታ ስጋቶች ለመቅረፍ እና በጥናት እና በአካባቢው አዳዲስ የኃይል መፍትሔዎችን በማጎልበት ኢኮኖሚያዊ ለውጥን ለማስተዋወቅ ያለመ እንደሆነ ተጠቁሟል።

የሳዑዲ የዜና አገልግሎት ዘገባ እንዳመለከተው፤ በሳዑዲ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ በኩል ሳዑዲ አረቢያ የአፍሪካ አህጉር ሀብቷን እና ውስጣዊ አቅሟን ለመጠቀም የሚያስችሏትን አዳዲስ መፍትሄዎችን ለማግኘት ዓለም አቀፍ ጥረቶችን ለማጠናከር ያስችላታል ብሏል፡፡ ይህም የሳዑዲ መንግሥት ኢንቨስትመንት እና የልማት ፕሮጀክቶች በአፍሪካ ሀገራት በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ለመተሳሰር እንደሚያግዝ ዘገባው አብራርቷል፡፡

ሳዑዲ አረቢያ በቀጣይም ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር፣ ወደ ሰፊ አድማስ ለማስፋት እና በተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ልማታዊ ዘርፎች ፍሬያማ አጋርነት ለመመስረት እንደምትፈልግ የሳዑዲ የዜና አገልግሎት ዘግቧል።

ይህ የመሪዎች ጉባኤ በክልላዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የመንግሥቱ አመራር ሚና እና በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ የሚመራ ሌላኛው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በሪያድ በሳዑዲ አረቢያ-አፍሪካ ኢኮኖሚ ኮንፈረንስ ላይ መሳተፉን አስታውሶ፤ ከኮንፈረንሱ ጎን ለጎን ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከሳዑዲ አረቢያ አቻቸው መሀመድ አል ጃዳን ጋር ተወያይተዋል። በውይይታቸው ወቅት ሁለቱም ሚኒስትሮች በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ በልማት ሥራዎች እና የዕዳ ማሻሻያ ሥራዎች ላይ ተወያይተዋል።

በዚህ ጉዳይ የሳዑዲ ዓረቢያ የገንዘብ ሚኒስትር መሐመድ አል ጃዳን መንግሥታቸው በኢትዮጵያ እየተካሄደ ላለው የልማት እንቅስቃሴ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ እና ሳውዲ አረቢያ በፔትሮሊየም እና ኢነርጂ ዘርፎች በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል። የትብብር ስምምነቱን በገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ እና በሳዑዲ አረቢያ የኢነርጂ ሚኒስትር አብዱላዚዝ ቢን ሳልማን አል ሳዑድ መካከል ተካሂዷል።

ስምምነቱ በሪያድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንደተገለጸው፤ ሁለቱ ሀገራት በነዳጅ አቅርቦት፣ በኃይል ቴክኖሎጂ ሽግግር እና በኃይል ኢንቨስትመንት መስኮች በትብብር ለመስራት ያስችላል ተብሎለታል። የመግባቢያ ሰነዱ በኃይል መስክ የሚደረጉ የልማት ሥራዎችን እና የነዳጅ አቅርቦትን ለኢትዮጵያ ለማረጋገጥ እንደሚያበረታታ ተጠቁሟል።

የፖለቲካ ተንታኞች ሳውዲ አረቢያ ከምንጊዜውም በላይ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ጠንካራ የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ግንኙነት ለመፍጠር በንቃት እየሰራች ነው ያሉ ሲሆን፤ ስብሰባው በሳይንስ፣ በትምህርት፣ በኢኮኖሚ፣ በባህልና በሌሎችም ቁልፍ ዘርፎች ትብብር እንደሚያሳድግ ጠቁመዋል።

ከመሪዎቹ ጉባዔ ጎን ለጎን የሁለቱም ወገኖች 25 ወጣት ልኡካን የሚወክሉበት የሳዑዲ-አፍሪካ ወጣቶች ፎረምም ተካሂዷል።ፎረሙም የአፍሪካ ወጣቶች ልዑካን በሳይንስ ዘርፍ ያላቸውን ዓለም አቀፍ ብቃታቸውን እንዲያሳድጉ ያስችላል ተብሏል። ከጉባዔው ጋር ተያይዞ የሳዑዲ አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን በአፍሪካ የንጉስ ሳልማን የልማት ተነሳሽነት መጀመሩን እና በአህጉሪቱ በ10 ዓመታት ውስጥ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚሸፍኑ ልማታዊ ፕሮጀክቶችን እና ፕሮግራሞችን ይፋ አድርገዋል።

ኢትዮጵያና ሳዑዲ አረቢያ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በሌሎች ዘርፎች ጠንካራ ትብብር ያላቸው ሲሆን፤ የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በ1948 የጀመረ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። ሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ ከከፈቱ ከመጀመሪያዎቹ የአረብ ሀገራት ተርታ መመዝገቧን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ሳዑዲ በሰፊው ከአፍሪካም ሆነ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ጥረት ያደረገች የዘመኑ የመጀመሪያዋ ሀገር አይደለችም፡፡ የኢትዮጵያን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የ49 ሀገራት መሪዎች የተሳተፉበት ሁለተኛው የአሜሪካ- አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤም አሜሪካን አካሂዳለች። በቀጣይ ወር ታኅሳስ ላይ ይኸው የአሜሪካ- አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ለሦስተኛ ጊዜ ይካሔዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በሁለተኛው የአሜሪካ- አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ዓለማችንን እየፈተኗት ያሉ ተግዳሮቶች የአየር ንብረት ቀውስ፣ መልካም አስተዳደር፣ የምግብ ዋስትና እና የዓለም ጤናን የሚጨምር ሲሆን፤ እንዲሁም የአሜሪካ-አፍሪካ የንግድ እና የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማጠናከር ላይ ያተኮረ እንደነበር ተዘግቧል።

ጉባዔው አፍሪካ ቁልፍ የጂኦፖለቲካል ተጫዋች እንደሆነች ዕውቅና በመስጠት ላይ የተመሠረተ እንደነበር የተጠቀሰ ሲሆን፤ በመድረኩ ላይ አህጉሪቱ የአፍሪካን ህዝቦች ብቻ ሳይሆን የዓለምን የወደፊት ሁኔታ የምትቀርፅ መሆኑም ተዘግቧል።

በአሜሪካ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ለአፍሪካ ከተሰጠው ዕውቅና ባሻገር፤ አፍሪካ በቡድን 20 ውስጥ የአፍሪካ ኅብረት ቋሚ ቦታ የሚያገኝበትን ሁኔታ በተመለከተ መክረው ሕብረቱን አባል አድርገዋል። በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ ከአፍሪካ ሀገራት መካከል ቋሚ አባል እንዲያካትት ተነጋግረዋል።

ይህ ሁሉ ሀገራት አፍሪካን ለመሳብ የሚያደርጉት ጥረት ሲሆን፤ በቀጣይም አሜሪካን ጨምሮ ሌሎችም ሀገሮች ጉባኤ በማዘጋጀት እና ከሀገራቱ መሪዎች ጋር በመወያየት፣ በትብብር በመስራት ግንኙነታቸውን ይበልጥ እንደሚያጠናክሩ ይጠበቃል፡፡

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ህዳር 18/2016

Recommended For You