ሀገራዊ ምክክሩ እና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች

ሀገራዊ ምክክር የግጭት መንስኤዎች ላይ ትርጉም ባለው መልኩ ውይይት ለማድረግ እና የሚያጋጩ ጉዳዮች ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ ለመፍታት ምርጥ መንገድ ስለመሆኑ ዓለም አቀፍ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ነገር ግን የየሀገራቱ ባሕል፣ ማሕበረሰባዊ ቅንጅትና ታሪካዊ አመሠራረታቸው የተለያየ መሆን ለሁሉም ሀገራት አንድ ወጥ የሆነ ሳይንሳዊ ቀመር ያለው የምክክር አጀንዳ ማዘጋጀት እንዳይቻል አድርጎታል።

እንደ አንድ የማሕበረሰብን ፖለቲካዊና ማሕበረሰባዊ ቀውሶች መፍቻ ዘዴ፤ በማሕበረሰብ ሳይንስ ጠቢባን የተጠናበትና አንድ ወጥ ትርጉም የተሰጠበት ባለመሆኑ፤ ሀገራዊ ምክክር ለሁሉም የሚስማማ ሞዴል የለውም፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ ግልጽ የትግበራ እቅድ እና የአሰራር ደንቦችን ከተከተለ እንዲሁም ሀገራዊ ጉዳዮች በጥልቀት ከተመረመሩ እና በዛ መሠረት ላይ ከቆሙ የስኬት እድሉ ከፍ ያለ እንደሚሆን ይገመታል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ በዓለም ላይ ተወዳጅ መሳሪያነቱ እየጨመረ የመጣው ይኸው ሀገራዊ ምክክር፤ ባለፉት በርካታ ዓመታት በተለያዩ ሀገሮች እና ሁኔታዎች ውስጥ ተካሂዷል፡፡ በዚህም ለግጭት አፈታት እና ለፖለቲካዊ ለውጦች ፍቱን መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ከተለመደው የልሂቃን ውሳኔ ሰጪነት በላይ ብዙዎችን የሚያሳትፍ በመሆኑ፤ የአንድ ሀገር ሰላማዊ አቅጣጫን ለማስቀመጥ ያመቻል እየተባለለት ይገኛል፡፡ ነገር ግን መሪዎች ዳግሞ ሥልጣናቸውን ለማጠናከር አላግባብ የሚጠቀሙበት ሁኔታ ሲያጋጥም እና አንዳንድ ከሀገር ውጭ ያሉ ኃይሎች ጣልቃ ሲገቡ እንደሚከሽፍም የሀገራት ተሞክሮ ያመለክታል፡፡

ሀገራዊ ምክክር በተካሄደባቸው ሀገራት አንዳንዶቹ ስኬትን ሌሎች ደግሞ ውድቀትን አስመዝግበዋል። ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ፣ በላይቤሪያ፣ በቱኒዝያ እና በሊባኖስ የተካሔዱ ምክክሮች አንጻራዊ ስኬትን ሲያስመዘግቡ፣ በየመን የተደረገው ግን ሳይሳካ ቀርቷል። እነዚህ ሁሉ ምክክሮች ዋናው ግባቸው በማሕበረሰቡ ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ ሲተገበር የነበረው በዘር መድልኦ ላይ የተመሠረተው ጨቋኝና አግላይ ፖለቲካዊ አስተዳደራዊ ሥርዓትን ደምስሶ በምትኩ እኩልነትና ፍትሕ የተሞላበት ሥርዓት እንዲፈጠር ማድረግ ነው።በዚህ በኩል ደቡብ አፍሪካ ተጠቃሽ ናት፡፡

ለተከታታይ ዓመታት ትውልድን ባካተተው መልኩ የእርስ በእርስ ጦርነት በመካሔዱ ምክንያት ተበጣጥሶ የነበረውን ማሕበራዊ ትስስር እንደገና ለማገናኘትና አጠናክሮ ለመቀጠል ሊባኖስ እና ላይቤሪያ ላይ የተካሔዱትን ሀገራዊ ምክክሮች መጥቀስ ይቻላል።

መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ እነዚህ በየሀገሩ የተካሔዱ ምክክሮች አንድ የሚያገናኛቸው መሠረታዊ ዓላማ ቢኖር በተፎካካሪ ወገኖች መካከል፣ የሚያስማማ መፍትሔን በማምጣት፣ የሚያገዳድልና የሚያጠፋፋ ፉክክር ሳይሆን ሰላማዊና መደማመጥ፣ ብሎም ልዩነትን አቻችሎ፣ አቅም ያለው የፖለቲካ ሥልጣኑን ጨብጦ ሌላውን በጠላትነት ሳይኮንን ሁሉም የተስማሙበት የፖለቲካ መድረክ መፍጠር ነበር። ዞሮ ዞሮ በነዚህ ሀገራት የተደረጉት የብሔራዊ ምክክሮች ዓላማቸው የፖለቲካ ሥልጣንን ፍትሐዊና ሰላማዊ በሆነ ዘዴ ተከፋፈሎ ሰላምን ለማስፈን ነበር።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥም ግጭትን ተከትሎ የነበረው ቀውስ ለውጥ ያመጣ ሲሆን፤ ለውጡ እውን እንዲሆን ሀገራዊ ምክክር ያስፈልጋል የሚል ሃሳብ ተነስቷል፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ 1265/2014 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቋል፡፡ አዋጁ፤ ‹‹በሀገራችን በተለይም በፖለቲካ ልሂቃን መካከል በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እየተፈጠረና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ልዩነት መፍታት ለሀገራዊ አንድነት መሰረታዊ ነገር ነው። እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች በኢትዮጵያ ብቻ የተፈጠሩ ሳይሆኑ በሽግግር ላይ በነበሩ በርካታ ሀገራት ያጋጠሙ ችግሮች ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነት ፈተናዎችን አልፈው ስኬታማ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ያደረጉ ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው፤ አካታች ሀገራዊ ምክክሮችን ማድረግ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የተሻለ መግባባት እንዲኖር እና በሂደትም የመተማመን እና በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ የመሥራት ባህልን ለማጎልበት ጠቃሚ እንደሆነ ያረጋግጣል።›› ይላል፡፡

አካታች ሀገራዊ ውይይቶች በሀገራዊ ፖለቲካ ቀውስ ወቅት፣ ከጦርነት በኋላ ባሉ ሁኔታዎችና፣ መጠነ ሰፊ የፖለቲካ ሽግግሮች በሚደረግበት ጊዜ፣ በብዙ ባለ ድርሻ አካላት መካከል መግባባትንና ለችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለመፍጠር ያለሙ መድረኮች መሆናቸውን የሚያመለክተው ይኸው አዋጅ፤ እነዚህ መድረኮች በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር ተመራጭ መሆኑን ያትታል፡፡

ሀገራዊ ምክክሮች አካታች በሆነ መንገድ መካሄዳቸው የሀገሪቱን ችግሮች በመፍታት ዘላቂ ሰላም እንዲሁም ጠንካራና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ያስችላል፡፡ እንዲሁም ሰላም የሰፈነባት፣ እየዳበረ የሚሄድ፣ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለቤት የሆነች፣ ዘላቂ እና ፍትሃዊ እድገት የሚመዘገብባት ኢትዮጵያን የማየት ተስፋን እውን ለማድረግ ሀገራዊ ውይይት አስፈላጊ መሆኑ በአዋጁ ተብራርቷል።

ሀገራዊ ምክክር ግቡ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር እና ለማጎልበት እንዲሁም ሀገራዊ መግባባት ሊኖርባቸው በሚገቡ ጉዳዮች ላይ አካታች የምክክር እና የውይይት ሂደት በመፍጠር፤ ሰፊ መሠረት ያለው ስምምነት፣ መግባባት እና የጋራ አቋም እንዲኖር ማድረግ ነው። በተቻለ መጠን መሠረታዊ የሚባሉ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በተለያየ ጎራ የተሰለፉ የፖለቲካ ልሂቃንም ሆነ ምልዐተ ሕዝቡ ተቀራራቢ እና ለሀገራዊ አንድነት ገንቢ የሆነ አቋም እንዲይዙ ማድረግ የአካታች ሀገራዊ ምክክሩ ዋነኛ ግብ መሆኑ በአዋጁ ላይ ተመላክቷል።

አዋጁ በኢትዮጵያ ችግር መኖሩን ጠቅሶ፤ ሌሎች ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ ችግር የነበረባቸው ሀገሮች በሀገራዊ ምክክር ከህመማቸው መዳን መቻላቸውን ጠቁሟል፡፡ በዚህ ምክንያት በኢትዮጵያም ሀገራዊ ምክክር ያለውን ችግር ለመፍታት እንደሚያመች በመታመኑ አዋጁ መዘጋጀቱ ይጠቁማል፡፡

ስለሀገራዊ ምክክር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም የተናገሩትን የጠቆመው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳመለከተው፤ ሀገራዊ ምክክሩ በዜጎቿ ተሳትፎ የተሻለች ኢትዮጵያን በመገንባት ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ትልቅ እድል የሚፈጥር ነው ሲሉ መናገራቸውን ጠቁሞ፤ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አመራርና አባላት ጋር በአካሔዱት ውይይት፤ ኮሚሽኑ ለሚያከናውናቸው ተግባራት ስኬት መንግሥት የሚጠበቅበትን ድጋፍና እገዛ የሚያደርግ ብቻ መሆኑን ማረጋገጣቸውን ዘግቧል።

ከተቋቋመ አንድ ዓመት ከዘጠኝ ወር አካባቢ ያስቆጠረው ይኸው ኮሚሽን፤ የሀገራት ተሞክሮን እንዴት አይቷል? ስንል በሙያቸው የሰላምና ደኅንነት ተመራማሪ እና መምህር እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደኅንነት ጥናት ተቋምን በዳይሬክተርነት የመሩ፤ ትኩረታቸውን በሰላም ግንባታ፣ እንዲሁም በግጭት አፈታትና በደህንነት ላይ ያደረጉ ኮሚሽነር ዮናስ አደዬ (ዶ/ር) አነጋግረናል፡፡

ኮሚሽኑ ከተቋቋመ በኋላ ምንም እንኳ አስራ አንዱም በጋራ በአካል ለማየት የሄዱበት ሀገር ባይኖርም፤ ቀደም ሲል ብዙሃኑ የኮሚሽኑ አባላት በተለያየ ጊዜያት የተለያዩ ሀገራትን ተሞክሮ በአካል አይተዋል። በተጨማሪ የተለያዩ የዳሰሳ ጥናቶችን በማካሔድ እና በጉዳዩ ላይ በመነጋገር ሃሳብ መለዋወጣቸውንም ኮሚሽነር ዮናስ ዶ/ር ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽነር ዮናስ ዶ/ር እንደሚናገሩት፤ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን በእንግሊዝ በሰሩበት ወቅት በአካል ተገኝተው ሰሜን አየርላንድን አይተዋል፡፡ ሰሜን አየርላንድ ለብዙ ዘመን በከፍተኛ ግጭት ውስጥ የቆየች ሲሆን፤ በግጭቱ የተፈጠረው ቁስል ታክሞ ለመዳን የሚያስቸግር ነበር፡፡ ግጭቱ ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ሲሆን፤ በካቶሊክ እና በፕሮቴስታንት መካከል ነበር። ግጭቱ አንዱ የደገፈውን የእግር ኳስ ቡድን ሌላው አለመደገፍ ብቻ ሳይሆን፤ አንዱ ባለፈበት መንገድ ሌላው እንዲያልፍበት አይፈቀድም ነበር። በኋላም በሲቪክ ማህበራት እና በምሁራን ሀገራዊ ምክክር ተካሂዶ ችግሮች መፈታት ችለዋል፡፡

የኢትዮጵያ እንደ አየርላንድ የተጋነነ አይደለም ያሉት ኮሚሽነር ዮናስ (ዶ/ር)፤ ከዛ ትልቅ ነገር መማራቸውንም ያስታውሳሉ፡፡ የደቡብ አፍሪካውያን ሀገራዊ ምክክር ጉዳይን በማስታወስ፤ በአካልም ጭምር በደንብ እንደሚያውቁት ያብራራሉ፡፡ ኮሚሽነር ዮናስ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን በሰሩበት ብላክፎርድ ሴንተር፤ ዴዘሞን ቱቱ የራሳቸው ማዕከል በመኖሩ ትምህርቱን ሲያካፍሏቸው እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ‹‹በርግጥ የደቡብ አፍሪካው ከኢትዮጵያ ይለያል፤ የእነርሱ በነጭ እና በጥቁር መካከል ነበር፡፡ ነገር ግን የተሳካላቸው በመሆኑ ከደቡብ አፍሪካ የምንወስደው ትምህርት ይኖራል፡፡›› ብለዋል፡፡

ሌላው በአካል የኬንያንም እንዳዩ የሚናገሩት ዶክተር ዮናስ፤ የእነርሱ ከምርጫ ጋር የተያያዘ ሲሆን፤ ወደ አንድ ሺህ አምስት መቶ ሰዎች የሞቱበት እና በአፍሪካ አንድነት ድርጅት እና በጋናው ተወላጅ እና በቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን አደራዳሪነት የተፈታ ጉዳይ እንደነበር ያንንም በዝርዝር እንደሚያውቁት ይናገራሉ፡፡ በኬንያ በሀገር ደረጃ የተቋቋመው ሀገራዊ ምክክር እና የእርቅ ኮሚሽን የተሳካለት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

የሩዋንዳንም ማየታቸውን የሚናገሩት ኮሚሽነር ዮናስ ዶ/ር፤ ሀገር በቀል የመነጋገሪያ መድረኮች ምን ያህል አዋጪ መሆናቸውን እንዳረጋገጡበት ይጠቅሳሉ። ገቻቻ የሚባል የሩዋንዳውያንን ባህል በመጥቀስ፤ በኢትዮጵያም አፊን በሲዳማ፣ ገዳ በኦሮሞ፣ ሽምግልና በአማርኛ፣ በወላይተኛ ጉተራ በሌሎችም አካባቢዎች ያሉ የመወያያ እና የመነጋገሪያ አሠራሮች መኖራቸውን እንደተረዱም ይገልፃሉ፡፡

ሌላው ኮሚሽነሮች ጥናታዊ ወረቀቶችን አብረው እያዩ፤ ሃሳብ ሲለዋወጡ እንደነበር በማስታወስ፤ የሴራሊዮን እና የላይቤሪያን እንዲሁም የቤኒንን ሀገራዊ ምክክሮች ሲቃኙ፤ የተካሔዱ ጥናቶችን ማየታቸውን ይገልፃሉ፡፡ በግል ካዩዋቸው በተጨማሪ በጽሑፍ ሁላቸውም በጋራ ማየታቸውን ይጠቁማሉ፡፡ የተሳካላቸውን ቤኒን፣ ቱኒዚያን ብቻ ሳይሆን በአንፃሩ በከፊል ያልተሳካላቸውን የየመንን፣ የሱዳንን እና የደቡብ ሱዳንን ሀገራዊ ምክክር ተሞክሮዎችን አይተው ለኢትዮጵያ ሊሠራ የሚችለው የቱ ነው? ከእነዚህ የሚቀሰመው ትምህርት ምንድን ነው? የኢትዮጵያን አውድ በጥሩ ሁኔታ የሚያንፀባርቅ ለኢትዮጵያ የሚመቸው የቱ ነው? በሚል ውይይት በማካሔድ ትምህርት መውሰዳቸውን ይናገራሉ፡፡

ነገር ግን ማንም መረዳት እንዳለበት በየትኛውም ወንዝ ሁለት ጊዜ አንድ ዓይነት ውሃ መፍሰስ አይችልም። ምክንያቱም ቀደም ሲል የሄደው አሁን ካለው የተለየ ነው፡፡ በዚሁ ልክ የትኛውም አውድ ሙሉ ለሙሉ ሌላውን መምሰል አይችልም፡፡ ነገሮች ሁሉ በለውጥ ላይ ስላሉ እያንዳንዱ ዓውድ የራሱ ባህሪ አለው፡፡ የኢትዮጵያ ከአየር ላንድ የተለየ ነው፡፡ ነገር ግን አንዱ ከሌላው መማሩ የተፈጥሮ ሕግ ነው ብለዋል፡፡

እንደ ኮሚሽነር ዮናስ ዶ/ር ገለፃ፤ የወሰዷቸው ትምህርቶች ምክክር በሀገሪቱ ሕዝብ በባለቤትነት የሚወሰድ እና የሚመራ ሲሆን፤ እንደሚሳካ ማረጋገጥ ችለዋል፡፡ ሌላው ምክክሩ የተሳካ እንዲሆን ባለቤትነቱ የሀገሩ ሕዝብ ሲሆን፤ ሂደቱ ግልፅ፣ ተአማኒነት ያለው እና አካታች መሆኑ እንዲሁም ከውጭ ጣልቃ ገብነት ነፃ መሆን እንዳለበት አምነዋል፡፡

በሀገር ውስጥም የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ሲኖር፤ ወይም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ተፎካካሪም ሆነ ገዢ ፓርቲዎች ምክክሩን የራሳቸው እንደሆነ የሚወስዱት ከሆነ ላይሳካ እንደሚችል ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡ የሱዳንን ተሞክሮ ሲያዩ የፓርቲ ጣልቃ ገብነት እንዳይሳካ እንደሚያደርግ፤ የየመኑን ምክክርም ሲያዩ ያልተሳካው የውጭ ጣልቃ ገብነት በመኖሩ መሆኑን እንዳረጋገጡ ይናገራሉ፡፡

የቤኒን ልክ እንደ አየር ላንድ በሀገሩ ሕዝብ የሚመራ ግልፅ እና እዛው የሚወያዩትም ጠንካራ እና ብቃት ያላቸው፤ ተአማኒነት ያላቸው፤ በምርምር የታወቁ ከሆኑ ሊሳካ እንደሚችል አረጋግጠናል ይላሉ፡፡ እነዚህ የውጭ ተሞክሮዎች ከታዩ በኋላ፤ ለኢትዮጵያ የሚበጀውን አስበው እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በርግጥም ኮሚሽነሩ እንዳሉቱ ሁሉ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅም፤ ሀገራዊ ውይይቶች ወጤታማ እና ሰፊ ተቀባይነት ያላቸው እንዲሆኑ ግልፅ የሆነ መዋቅር ሊኖራቸው እንደሚገባ አስቀምጧል። የሂደቱ ተዓማኒነት በዋናነት ምክክሩን እንዲያሳልጥ እና እንዲመራ ወይም እንዲያካሂድ በሚሰየመው አካል ብቃት እና ገለልተኝነት ላይ እንደሚወሰንም ገልጸዋል። ይህን ሀገራዊ ምክክርን የሚያስተባብርና የሚመራ አካል በአብዛኞቹ ዜጎች ዘንድ ተዓማኒ የሆነ እና ቅቡልነት ያለው፣ ግልጽ የሆነ የጥቅም ግጭት የሚያመጣ የፖለቲካ ዝንባሌ ወይም ግብ የሌለውና በአብዛኛው የምክክሩ ተሳታፊዎች ዘንድ በገለልተኛነቱ የታመነበት መሆን ይኖርበታል ብሏል፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ ሥራውን የሚመራና የሚያስተባብር ተቋም ከማቋቋም ጀምሮ ሥራውን የሚመሩና የሚያስተባብሩ አካላት ግልጽ ሥርዓት በመዘርጋት ተመርጠዋል፡፡

በአዋጁ፣ በአስተያየት ሰጪው ኮሚሽነር ዮናስ (ዶ/ር) እና በዓለም አቀፍ ስኬታማ የሀገራት ምክክር ተሞክሮ አንፃር፤ ይህ ማህበረሰቡ በተለምዶ ይጠቀምበት ከነበረው የማሕበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶችን የመፍቻ ዘዴዎች ለየት ያለውና፣ መንግሥትን፣ ፖለቲካ ድርጅቶችን፣ የማሕበረሰብ ተቋማትና የማሕበረሰብ ተወካዮችን በአንድ የጋራ መድረክ ላይ በማምጣት ከተለመደው መንግሥታዊ ተቋማት አሠራር ውጭ፣ ግን ደግሞ በመንግሥት ድጋፍ የሚተገበረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር አዋጅ ከማውጣት እና በጥንቃቄ ሥራውን የሚመሩና የሚያስተባብሩ አካላትን ከመምረጥ ጀምሮ ተሳታፊዎችን የመለየት ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር መላውን ሕዝብ በቀጥታም ሆነ በተወካዮቻቸው በኩል በአንድ የጋራ መድረክ ላይ መጥተው የሚገናኙበት ይሆናል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ለዘመናት ነቀርሳ ሆነው የጋራ ማንነትና በጋራ መገለጫዎቹም ላይ መግባባት እንዳይኖርና፣ ብሎም ማሕበረሰቡን በመለያየት ብቻ ሳይሆን፣ በሀገሪቷም ሰላም፣ ፍትሕ፣ ዲሞክራሲና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዳይሰፍን ጠንቅ የሆኑትን ማኅበረሰባዊ ነቀርሳዎችን፣ ቅንነት በተሞላበት ሀገራዊ ውይይት አማካኝነት መፍትሔ ያስገኛል የሚል እምነት የተጣለበት ነው፡፡ በአጠቃላይ ምክክሩ ስለ ወደፊት የጋራ ማንነትና ብሩህ የጋራ ሕይወት የሚመከርበት ሁሉን አቀፍ የሆነ የጋራ ምክክር ይሆናል የሚል ተስፋ ተጥሏል።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/2016

Recommended For You