ባለፈው ዓርብ ጠዋት ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በር ላይ ከሚገኙ ጫማ ከሚያጸዱ ልጆች ከአንደኛው ጋ ጫማዬን ለማስጠረግ ልቀመጥ ስል መንገድ የሚያጸዱ ሴቶች አካባቢውን በአቧራ ጉም አስመሰሉት፡፡ እያጨሱት ጫማ የሚያጸዱት ልጆች ጋ ደረሱ፡፡ ልጆቹ ተነስተው አቧራው ወደማይጨስበት ቦታ ራቅ አሉ፡፡ እኔም ተከትዬ አብሬያቸው ቆምኩ፡፡
ይሄኔ አንደኛው ልጅ እየተናደደ ‹‹በጠዋት አያጸዱም እንዴ!፤ በጠዋት እኮ ነው ማለቅ ያለበት›› ሲል ሌላኛው ደግሞ ‹‹አቧራ እኮ ነው ግን ምኑን ይጠርጉታል? በእጅ የሚነሳውን ብቻ አንስተው ለምን አይሄዱም? ይሄ እርሻ የሆነ መንገድ ምኑ ይጠረጋል?›› ሲል ብሶቱንም ግርምቱንም ገለጸ፡፡
ልጁ እንደዚያ ሲል ነው እኔም ልብ ብዬ ማስተዋል የጀመርኩት፡፡ የሚጠረገው መንገድ የተቆፋፈረ አቧራ ነው። የተቆፈረ መሬት ላይ ያለ አቧራ ደግሞ ተጠርጎ አያልቅም፡፡ የሚጠረገው አስፋልት ሲሆን ነው፡፡ አስፋልት ከሥር አቧራ ስለማያወጣ ከላይ ያለውን ሲጠርጉት ይጸዳል፡፡ የተቆፋፈረ መንገድ ግን መሬቱን የቱንም ያህል ቢጠርጉት አፈር ከሥር እየወጣ ይሄዳል። ሲጠረግም እየጨሰ ሌሎች አካባቢዎችን ጭምር ይበክላል እንጂ አይጸዳም፡፡ እንዲያውም አቧራ የሌለውን አስፋልት እንደገና አቧራ መጨመር ነው፡፡
ይህ ሁሉ የሆነው ግን በጽዳት ሠራተኞች ችግር አይደለም፡፡ የእነርሱ ችግር ምናልባትም ከጠዋት 1፡00 በፊት ጨርሱ ተብለው በራሳቸው ድክመት መንገደኛ እስከሚበዛ አስረፍደውት ከሆነ ነው፡፡ መንገደኛ ሲበዛ ለእነርሱም ለመጥረግ ያስቸግራል፡፡ ከዚያ ውጭ ግን ችግሩ መንገዱን ያፈረሰው አካል ነው፡፡ ይህ ችግር በተደጋጋሚ ቢጮህበትም አሁንም ችግሩ ሊቀረፍ አልቻለም፡፡
የእግረኛ መንገዶች የሚፈርሱበት የራሱ ምክንያት ይኖረዋል፡፡ ያንን ምክንያት ግን አብዛኛው ነዋሪ አያውቅም። ነዋሪው የሚያውቀው ለጥገና የሚፈርስ መንገድ ሊሰራ እንደሚችል ነው፡፡ አፍርሶ የሚተውበትን ምክንያት የሚያውቀው አፍራሹ (ሰሪው) አካል ብቻ ነው፡፡ በመሃል ግን መንገደኛ ይጉላላል፤ የከተማዋ ውበትም ይበላሻል፡፡ ዝናብ ሲዘንብ ጭቃ፣ ፀሐይ ሲወጣ አቧራ ይሆናል፡፡ በዝናብ ወቅት የመንገድ ጠርዝ ላይ በመንጠልጠል ሰርከስ የምንሰራ መስለን ነው የምንሄደው፡፡ እንዲህ የበጋ ወቅት ሲመጣ ደግሞ አቧራው አካባቢውን የእርሻ ማሳ ነው የሚያስመስለው፡፡
ቀደም ሲል እንዳልኩት አንድ መንገድ ሲፈርስ የራሱ ምክንያት ይኖረዋል፡፡ የተሻለ አድርጎ ለመሥራት (ለማደስ)፣ ወይም ሌሎች የሚጨመሩ ነገሮች ሲኖሩ ማፍረስ ያለ ነው። ዳሩ ግን መንገዱን ማፍረስ ሲጀመር የሚጠናቀቅበት ጊዜ አብሮ አይታቀድም ወይ? አንዳንድ መንገዶች በአንድ ጀንበር ፈርሰው እናገኛቸዋለን፤ ለመሥራት ግን በጋ እና ክረምት ሲፈራረቅባቸው እናያለን። እግረኛና ተሽከርካሪ ይደባለቅባቸዋል፡፡ ተሽከርካሪዎች ተደርድረው መሃል ከተማ ላይ የደረቅ ወደብ ማራገፊያ ይመስላል፡፡
በዚሁ እግረ መንገድ አንድ ትዝብት ልጨምር። አንዳንድ የእግረኛ መንገዶች ለዕድሳት ተብለው እንደገና ይሰራሉ፡፡ ለምሳሌ ኮንክሪት የነበረው ቴራዞን ይደረጋል። የሚነጠፈው ቴራዞን በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚነቃነቅ ይሆናል፡፡ ዝናብ ሲዘንብ በውስጡ ውሃ ይይዛል፤ ከዚያም ከአንደኛው ጫፍ ላይ ሲረግጡት ከዚያኛው ጫፍ ወደላይ ይነሳል፤ ከውስጡ ያለው ውሃ ልብሳችን ላይ ይረጫል ማለት ነው፡፡
ከምንም በላይ ግን አስቸጋሪ የሚሆኑት ተቆፋፍረው የሚረሱ መንገዶች ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ የመንገድ መቆፋፈር ቅሬታ የሚነሳው የክረምት መግቢያ ላይ ነው፤ አቧራ እንደ ችግር አይታይም፡፡ ከጭቃ በላይ ግን አደገኛ የሚሆነው አቧራ ነው፡፡ ጭቃ በዓይን የሚታይ ስለሆነ እንጸየፈው ይሆናል፡፡ አቧራ ግን በዓይን የማይታዩ ባዕድ ነገሮች አሉበት፤ ለበሽታ ይዳርጋል ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳን አቧራ መሆኑ ችግር የለውም ተብሎ ነው ያልተሰራው ባይባልም ትኩረት ሊሰጠው ግን ይገባል፡፡
በነገራችን ላይ እነዚህን የተቆፋፈሩ መንገዶች ቶሎ መላ እንዲደረግላቸው አሳሰብኩ እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አዲስ አበባ ውስጥ በእግር መሄድ የሚመረጥባቸው ብዙ ለዓይን ማራኪ የሆኑ የእግረኛ መንገዶችን እያየን ነው። ለምሳሌ፤ ከአራት ኪሎ ወደ ካዛንቺስ በታክሲ ከሄድኩ ይቆጨኛል፡፡ ብዙ ጊዜ አስቸኳይ ጉዳይ (ሥራ) ካልሆነ በስተቀር ካዛንቺስ የምሄደው በእግሬ ነው። ምክንያቱም ከወዳጅነት ፓርክ አንስቶ እስከ ሳይንስ ሙዚዬም ድረስ ያለው የእግረኛ መንገድ አውሮፓ ውስጥ በተንቀሳቃሽ ምስል የምናያቸውን የሰለጠኑ ከተሞች ነው የሚመስል፡፡ ይህ መንገድ ከዓመታት በፊት የቆርቆሮ አጥር እየታከክን፣ ከተቃራኒ አቅጣጫ የሚመጣ ሰው ቆመን እያሳለፍን፣ የተከማቹ የውሃ ኩሬዎችን እየዘለልን የምናልፍበት ነበር፡፡
ሌላው በዚሁ እግረ መንገድ ማንሳት የምፈልገው ደግሞ በብዙ ቦታዎች ላይ የተሰሩ የመንገደኛ ማረፊያዎች ናቸው፡፡ ከቅርቤ ልጀምርና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በር ላይ ግራና ቀኝ ማረፊያዎች አሉ። ከአጠገቡ ደግሞ ታሪካዊ ክስተቶችን የያዙ ጋዜጦች ፎቶዎች አሉ፡፡ ብዙ መንገደኞች ሥራዬ ብለው ከዋናው መንገድ ገንጠል ብለው ገብተው ያዩታል፡፡ አንዳንዶቹ በከፍተኛ ተመስጦ አንድ በአንድ እየዞሩ ያዩታል፡፡ አሻግረው ደግሞ ከተቋሙ ሕንጻ ላይ ያሉትን የኢትዮጵያ መሪዎች ያያሉ፡፡ ይህን በሌላ ቀን እመለስበታለሁ፡፡
ይህ የመንገደኞች ማረፊያ ለብዙዎች እረፍት ማድረጊያ ነው፡፡ መመሰጫ ነው፣ መጠባበቂያ ነው። እንዲህ አይነት የመንገደኞች ማረፊያዎች በተቋማት አካባቢዎች ሊሰሩ ይገባል፡፡
በአውቶብስ ማቆሚያዎች ላይ የመንገደኞች መጠበቂያ ማረፊያዎች ተሰርተዋል፤ ችግሩ ግን መሰልጠን ገና ብዙ ስለሚቀረን አብዛኞቹ ተነቃቅለዋል። የሚሰጡትን ጥቅም በማየት ጥበቃ ልናደርግላቸው ይገባል፡፡ ከአውቶብስ መጠበቂያዎች በተጨማሪ ደግሞ በብዙ አካባቢዎች ለመንገደኞች ማረፊያ የተዘጋጁ አግዳሚ ወንበሮች አሉ። እነዚህ የመንገደኞች ማረፊያዎች የተሰሩት ጥሩ የእግረኛ መንገድ ባሉባቸው አካባቢዎች ነው፡፡
እንግዲህ እነዚህ የመንገደኞች ማረፊያዎችና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተሰሩ የሚያማምሩ የእግረኛ መንገዶች የፈጠሩት ስሜት ይመስላል በአንዳንድ የተቆፋፈሩ መንገዶች እንድንማረር አድርጎናል፡፡ አንዳንዱ ሲያሳምር አንዳንዱ ማበላሸት የተለመደ ነው።
የመንገዶች ተቆፋፍሮ መቅረት ላይ አንድ የማይገባኝ ነገር አለ፡፡ ነገሮች እንደታሰበው እንደማይሄዱ ይታወቃል። ይጠናቀቃል በተባለበት ጊዜም ላይጠናቀቅ ይችላል፡፡ ዳሩ ግን የሚጀመርበት ጊዜ (አስቻይ ሁኔታ) ሳይታወቅ ለምን ማፍረስ ላይ ይቸኮላል? ሥራው የሚጀመርበት ጊዜ ሲታወቅ ማፍረስ አይሻልም? ምክንያቱም አንድ የተቆፋፈረ መንገድ ምንም ነገር ሲሰራበት ሳናይ ለረጅም ጊዜ ይቆያል፡፡ ታዳጊ ሀገር ነንና ሁሉም ነገር ይፋጠን ለማለት ሁኔታዎች አይፈቅዱም። ዳሩ ግን ቢያንስ በተለመደው እንኳን እንድንቆይ የሚሰራበት ሁኔታ እስከሚመቻች የማፍረሱ ነገር ባይጣደፍ ይሻላል!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26 ቀን 2016 ዓ.ም