ሰሞኑን ከአንድ የሀገራችን ታዋቂ የቴሌቪዥን ጣቢያ አንድን ጉዳይ ስታዘብ ከረምኩ፡፡ በዚህ ጣቢያ የተላለፈው ዝግጅት ጊዜው የራቀ አይደለምና በርካቶች ያስታውሱታል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ሁሌም በጣቢያው በተለመደ ሰዓት የሚቀርበው ሳምንታዊ ዝግጅት በአብዛኛው ችግሮችን በግልጽ አሳይቶ መፍትሄ መሻት ላይ የሚያተኩር ነው፡፡
እስካሁን በተላለፉ ፕሮግራሞችም ይህንኑ በግልጽ ስናስተውል ቆይተናል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም አዕምሯችን ጥቂት የማይባሉ ሰዎችን አሳዛኝ ታሪኮች ከትቦ አስቀርቷል። እንደተመልካች እኛም በልብ ሰባሪ ታሪኮቻቸው እኩል አንብተናል፣ ከልብ አዝነናል፡፡ መለስ ብለንም ዕንባቸው ሲታበስ አይተን በተለወጠ ሕይወታቸው ተደስተናል፡፡
በአጠቃላይ ይህ የቴሌቪዥን ዝግጅት ቁምነገር አዘል ነውና የበርካታ ተመልካቾች ምርጫ ነው ማለት ያስደፍራል፡፡ ከሰሞኑም የእነዚህን ዓይነት ታሪኮች የሚጋራ አንድ ሰው በዚሁ የቴሌቪዥን ዝግጅት ብቅ ብሎ አሳዛኝ ታሪኩን አውግቶናል፡፡
የዚህ መሰናዶ እንግዶች ችግሮቻቸው በርካታ ነው፡፡ ሁሌም በታሪኮቻቸው መሀል ሀዘንና ለቅሶ ይስተዋላል፡፡ የዝግጅቱ ዋና ዓላማም የሰዎችን ችግር አሳይቶ መተው አይደለም ፡፡ ይልቁንም ያዘኑ፣ ያለቀሱ ምስኪኖችን ዕንባ ማበስ ነው፡፡ በተቻለ አቅም ጎዶሏቸው ሞልቶ ቀና ይሉ ዘንድ መቋቋሚያ ድጋፍን እነሆ! ማለትም ለምዷል፡፡
ታሪኩን የሚመለከት ታዳሚ ታዲያ በሚያየውም በሚሰማውም እውነት ማዘንና መጨነቁ አይቀርም፡፡ እንዲያም ሆኖ ከዚህ ሀቅ በስተጀርባ የሚገኘውን መልካም ውጤት መጠበቁ የግድ ነው፡፡ መጨረሻው በጎ ሲሆን ታዲያ በርካቶች ከባለጉዳዮቹ እኩል ፊታቸው ይፈካል፡፡
አስቀድሜ ወደጠቆምኳችሁ ባለታሪክ ልለፍ፡፡ በቅርቡ በዚሁ የቴሌቪዥን ጣቢያ እንግዳ ሆኖ የቀረበ ወጣት ነው፡፡ የዚህ ሰው የሕይወት ፈተና ከገጠር ኑሮው ይጀምራል፡፡ ገና በልጅነት ዕድሜው ወላጅ እናቱን በሞት ያጣው ይህ ወጣት ከእሱ በታች ያሉትን ሁለት እህቶችና ወንድሙን ለማሳደግ ቀላል የማይባል ዋጋ ከፍሏል፡፡
ባለታሪኩ ሲናገር እንደተሰማው የወላጅ እናቱ የሞት መንስኤ የኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ ነው፡፡ በወቅቱ ከሕመሙ ጋር ተያይዞ የነበረው አድልኦና መገለል የከፋ በመሆኑም የእናት ሕመም ምስጢር ሆኖ ነው የዘለቀው። ምስጢሩ እንዳይዛመት ማሳመኛው ደግሞ የአባወራው ከቫይረሱ ነጻ መሆን ነበር፡፡
የመገለሉ ጉዳይ እንዲህ ቢቃለልም ዳሩ ከሁለቱ ሕጻናት የትልቋ ልጅ ከቫይረሱ አለማምለጥ ደግሞ ለቤተሰቡ ከባድ የሚባል ሀዘን ማትረፉ አልቀረም፡፡ ይህ እውነት እንደታወቀ ሕይወቷን ለመታደግ የጸበልና የሕክምና ትግሉ አልተቋረጠም፡፡ አባት ባለቤታቸውን በሞት ካጡ ወዲህ ልጆቻቸውን ለማሳደግ ብዙ ደክመዋል። ሌላ ሚስት ላለማግባት ወስነውም በብቸኝነት ዓመታትን ቆጥረዋል፡፡
የዚህ ቤተሰብ ሌላው ፈተና ደግሞ የትንሹ ልጅ ጤና ማጣት ነበር፡፡ ይህ ልጅ እናቱ ከሞቱ በኋላ በነበረ ጥርጣሬ በተደጋጋሚ የኤች አይ ቪ ምርመራ ተደርጎለታል። አንድም ውጤት ግን በደሙ ቫይረሱ እንደሚገኝ አልጠቆመም። የምርመራው ውጤት ይህን ያመላክት እንጂ ልጁ ግን ጤና ይሉት የለውም፡፡ በሰውነቱ የወጣው ቁስል የዘወትር ሕመም ሆኖ ያሰቃየዋል፡፡ ከሕክምናው በላይ ባህላዊ ልማድን የመረጡት ቤተሰቦች ለመዳኑ መፍትሔ ያደረጉት በጋለ ብረት አካሉን ማስተኮስ ነበር፡፡
እንግዳው ዛሬ ላይ ሆኖ በወቅቱ የነበረውን ወንድሙን ስቃይ በተለየ ስሜት ያስታውሰዋል፡፡ ያልበረታው የሕጻን ገላው ከአንድ አይሉት በሁለት ሰዎች እጅ በጋለ ብረት ተተኩሷል፡፡ ዕባጩን ለማፍረጥ በሚደረገው ጥረት ሁሉ ሰውነቱ በፍም ግሎ በሚወጣ ብረት ጋይቷል፡፡ ነፍስና ሥጋው እየተጨነቀ ቆዳው እንደ ጨርቅ ሲጨስም ቆይቷል።፡
ይህ እውነት የባለታሪኩ አይረሴ የሕይወት ክፍል ነው፡፡ ምንጊዜም ያለፈውን ሲያነሳ ዓይኖቹ በእንባ ይሞላሉ፡፡ ካሳለፈው የመከራ ሕይወት ሁሉ ይሄኛው ሀቅ ሚዛን ደፍቶ ከልብ ያስለቅሰዋል፡፡ ይህ ወጣት ለሁለቱ ሕጻናት መኖር ብዙ ሆኗል፡፡
የተወለደበትን አካባቢ ትቶ ከወጣ በኋላም ስለእነሱ የሴት፣ የወንድ ሳይል ባገኘው ሥራ ታግሏል፡፡ በዚህ ገጽ ብቻ ተገልጾ በማያበቃው የሕይወት ውጣ ውረድ ተራምዶም የእህትና ወንድሙን እስትንፋስ አቆይቷል፡፡ ይህ የወጣቱ ታሪክም የቴሌቪዥን ጣቢያውን ትኩረት በመሳቡ ነው በእንግድነት ያስመረጠው፡፡
የእኔ የትዝብት ቅኝትም የሚዳስሰው የትንሹን ልጅ ታሪክ ነው፡፡ የቴሌቪዥኑ ብርቱ እንግዳ እንደነገረን ሁለቱን ልጆች እሱ ከሚኖርበት አዲስ አበባ ካመጣቸው ሰነባብቷል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ የአባቱ መቸገርና ወደ ጸበል መግባት ነው፡፡ ልጆቹ እሱ ዘንድ ከመጡ ጀምሮ ግን የትምህርት ዕድል አላገኙም፡፡ ቀናቸውን ቴሌቪዥን በማየት ሊገፉት ግድ ብሏል፡፡
ከጸበሉ ቆይታ በኋላ ጤናው ያልተመለሰው ትንሽ ልጅም ወደ ሕክምና ደርሶ በድጋሚ ምርመራ ይደረግለታል። ይህ አጋጣሚ ግን ታሪኩን እንዳልነበረ ቀየረው፡፡ እስከዛሬ ከቫይረሱ ነጻ ነው ሲባል የኖረው ሕመምተኛ በደሙ ኤች አይ ቪ መኖሩ ተረጋገጠ፡፡ ይህ እውነት ለባለታሪኩ ወጣት ሌላ ሸክም ሆኖ ሕይወቱን አከበደው፡፡ ሁለት ታናናሾቹ ከቫይረሱ ጋር እየኖሩ መሆኑን አምኖ ለመቀበል እስኪቸገር ተፈተነ፡፡
ይህን እውነታ በቴሌቪዥን ጣቢያው ቀርቦ የሚነግረን ወጣት አሁን ጭንቀቱ በእጥፍ ከብዷል፡፡ ስለ ሕይወት ሸክሙ መፍትሔ ለመሻትም በአደባባይ ወጥቶ እውነታውን አጋርቷል፡፡ ይህን ታሪክ ከሁሉም ለየት የሚያደርገው ደግሞ ትንሹ ልጅ ስለራሱ ማንነት ፈጽሞ ያለማወቁ ነው። የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ ትዝብትም በዚህ ጉዳይ ያተኩራል፡፡
ከታሪኩ ነገራ ለማወቅ እንደሚቻለው ልጆቹ ትምህርት ቤት ስለማይሄዱ ውሏቸውን ቴሌቪዥን በማየት ያሳልፋሉ።፡ ወጣቱ ደግሞ ትንሹ ልጅ ቫይረሱ እንዳለበት ፈጽሞ እንዲያውቅ አይፈልግም፡፡ እሱ ይህን ይበል እንጂ ሌሎች ሰዎችን ጨምሮ ታማሚው ያለማንም ነጋሪ የራሱን ታሪክ የሚያውቅበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡
እንዴት ከተባለ ደግሞ ይህ ታሪክ ለተመልካች ተደራሽ በሚሆነው የቴሌቪዥን ስርጭት ሲተላለፍ ውሎ አያድርምና ነው፡፡ እንደሚታወቀው በቴሌቪዥን የቀረበው ፕሮግራም የማን ታሪክ እንደሆነ ግልጽ ነው። ባለቤቱ ማንነቱን በይፋ ካስተዋወቀ ደግሞ ቤተሰቡንና ኑሮውን ለመለየት አይቸግርም፡፡ ይህ ሀቅ ባለበት ሁኔታም ጉዳዩን መስጥሮ ‹‹ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ›› ማድረጉ ትርጉሙን ያዛባዋል፡፡
የሚያስገርመው ጉዳይ ወጣቱ እውነታውን ለወንድሙ አልነግረውም ማለቱ ላይ አይደለም፡፡ የጣቢያው አዘጋጆች ብዙ እያወቁ ‹‹ንገረው፣ አትንገረው›› ከሚሉት ምክር መግባታቸው እንጂ፡፡ ወዳጆቼ! እስቲ እናንተም ቆም ብላችሁ አስቡት፡፡
ይህ ልጅ ታሪኩን የሚያወጋለት የራሱ ወንድም ነው። ተናጋሪው ደግሞ ፈጽሞ ራሱን ሊደብቅ አልሞከረም፡፡ ከመነሻው አንስቶ እየገለጸ የቀጠለው የመላውን ቤተሰብ ታሪክ ነበር፡፡ ስሙን አልጠራም እንጂ ስለማን እንደሚያወራ ግልጽ ሆኖ ተቀምጧል፡፡ ሁሉም ጉዳይ ለሁሉም እንዲህ ይፋ በሆነበት አጋጣሚ ‹‹በዕድሜ እስኪበስል ህመሙን ልነግረው አልፈልግም›› ማለቱ እንደኔ ጉዳዩን የሞኝ ተረት ከማድረግ አያንስም፡፡
ይህ ልጅ ዕለቱን ከቴሌቪዥን እይታ እንደማይርቅ እየታወቀ ሙሉውን ሃሳብ ሳይቆርጡ ማስተላለፍም ከተጠያቂነት አያድንም፡፡ ፕሮግራሙ አርታኢ (ኤዲተር) የለውም እንዴ? ሊያስብልም ይችላል፡፡ በእነሱ ቤት ይህ ልጅ ዕድሜው እስኪበስል አያውቅም፣ አይሰማም ማለት ነው።፡ የቴሌቪዥኑ ጉዳይስ? አንድ አበባል አለ ‹‹አትንገር ብዬ ብነግረው አትንገር ብሎ ነገረው›› ይሉት ተረት፡፡
እንዲህ ዓይነቱ ትንሽ የሚመስል ስህተት ሊያስከትል ከሚችል ድንገተኛ ድንጋጤ ባለፈ የሞራል ስብራቱ ይከፋል፡፡ እኔ ግን እላለሁ፤ ከመጣደፍ ይልቅ ቆም ብሎ ማሰብ ይቀድማል፡፡ ምክሬም ትዝብቴም ነው፡፡
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 24/2016