አንድ የሥራ ባልደረባዬ የነገረኝ የራሱ ገጠመኝ ነው። ጠዋት በታክሲ ወደ ሥራ ቦታ እየሄደ ነው። ለትራንስፖርት ከከፈለው ውስጥ የ5 ብር መልስ አለው። ቢጠብቅ ቢጠብቅ መልስ ረዳቱ አልሰጠውም። መውረጃው ሲደርስ ከታክሲው እየወረደ ‹‹መልስ ስጠኝ›› አለው። ረዳቱም ‹‹ይሄውልህ አህያ!›› ብሎ አምስት ብሩን ሰጠው። ይሄኔ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ ረዳቱን አነቀው። ሌሎች ተሳፋሪዎች መካክረውና ገላግለዋቸው ነገሩ በዚሁ አለቀ።
እግዲህ አስቡት! ‹‹መልስ ስጠኝ›› ከማለት ውጭ ምንም የተነጋገሩት መጥፎ ነገር የለም። ከዚያ በፊትም አይተዋወቁም፤ ያገናኛቸው ይሄ ሥራ ብቻ ነው። በዚያች ቅጽበት፣ በአንዲት ቃል ነው ረዳቱ አፉ እንደለመደ ያንን ነውር ስድብ የተሳደበው።
‹‹እንዴት ከታክሲ ረዳት ጋር ትጣላለህ?›› ስለው ‹‹እኔም በኋላ ያናደደኝ ከታክሲ ረዳት ጋር መሆኑ ነው›› አለኝ። ለመጣላትም አቻ ሳያስፈልግ አይቀርም፤ እነዚህ ልጆች (የታክሲ ረዳቶች) ስድብን መደበኛ ሥራቸው አድርገውታል። ሁሉም ናቸው ለማለት ባያስችል እንኳን በጣም ሲበዛ ባለጌዎች ናቸው። ለመሳደብ በማያደርስ ሁኔታ ዝም ብለው ከስድብ ይጀምራሉ። ትልልቅ ሰዎች ደግሞ ክብራቸው ሲነካ አይወዱም። ክብሩን ጠብቆ፣ በጨዋነትና በትህትና የሚስተናገድ ሰው ማንም ዝም ብሎ ስድ ባደገ አፍ ሲሰድቡት መናደዱ አይቀርም።
የታክሲውን መነሻ ያደረኩት በቅርብ ከሰማሁት ገጠመኝ ልነሳ ብየ እንጂ ስድብ በታክሲ ረዳቶችና ሾፌሮች የተገደበ አይደለም። እንዲያውም የጠቅላላ ሾፌሮች መገለጫ እስከሚመስል ድረስ አንገታቸውን አሾልከው ሲሰዳደቡ ነው የምናየው። ‹‹ከመንጃ ፈቃድ ጋር ስድብ አብሮ ነው እንዴ የሚሰጣቸው!›› እየተባለ ሁሉ ይቀለዳል።
እንደ አጠቃላይ መሳደብ የኋላቀርነት፣ የሞራለቢስነት እና የፈሪነት ምልክት ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ የሚያናድድ ነገር ሲፈጠር ሊያጋጥም ይችላል እንበል። ዳሩ ግን ምንም በሌለበት፣ በጨዋነት እየተስተናገደ ያለውን የሠለጠነ ሰው ብድግ ብለው የሚሳደቡ አሉ። ሰው አንዳንድ ጊዜ በሁኔታዎች ስሜታዊ ሊሆን ይችላል። ዳሩ ግን ከሳቅና ፈገግታ ሁነት ላይ ተነስተው አንድን ነገር ለመጠየቅ በስድብ የሚጀምሩ አሉ። ይሄ ለሚሰደበው ሰው ምን ያህል እንደሚያናድድ አይገባቸውም።
ልክ ነው ልክ አይደለም የሚለውን እንተወውና አንዳንድ ጊዜ በጓደኝነት (በትውውቅ) የፍቅር መሰዳደቢያዎች አሉ። ይህን አውቃለሁ። ይህ የሚሆነው ግን ለሚተዋወቁና ለሚግባቡ ሰዎች ብቻ ነው። የምሩን ተኮሳትሮና ተናዶ፤ የማያውቀውን ሰው የሚሳደብ ግን ኋላቀር የሆነ ሰው ብቻ ነው።
በወጣቶች ዘንድ፣ በልጆች ዘንድ፣ እንዲሁም በታክሲ ረዳቶች ዘንድ ብቻ የተገደበ ቢሆን አይደንቀኝም ነበር፤ ጉዳይ ሊሆንም አይችልም ነበር። ዳሩ ግን እንደ ማኅበረሰብ ምን ያህል ብዙ እንደሚቀረን የሚያሳየን እና ጉዳዩን አሳሳቢ የሚያደርገው፤ የሞራል እና የሥልጣኔ ምሳሌ መሆን በሚገባቸው የተማሩ ሰዎች ላይ በስፋት የሚስተዋል መሆኑ ነው። ውድ መኪና ይዘው፣ ውድ ልብሶችን ለብሰው፣ ትልቅ ቦታ ላይ ያሉ ሆነው፣ በእግረኛ መንገድ ላይ እየሄደ ያለ ሰው የሚሳደቡ አሉ። በተቋማት ውስጥ ለተለያየ ጉዳይ የመጣ ሰው ትንሽ ነገር ሲሳሳት ከማስረዳት ይልቅ የሚሳደቡ አሉ። እነዚህ ሁሉ ለምን ሆኑ ከተባለ መሠልጠን ገና ብዙ ስለሚቀረን ነው።
በተደጋጋሚ እንደምለው የሠለጠኑ ናቸው የሚባሉ ሀገራት ሠለጠኑ የተባለው በቴክኖሎጂ እና በመሠረተ ልማት ባላቸው ምጥቀት ብቻ አይደለም። የሠለጠኑ ናቸው የተባሉት አዕምሯቸው የሠለጠነ ስለሆነ ነው። የሞራል ከፍታ ስላላቸው ነው። ሰው ብቻ ሳይሆን ሌሎች ፍጥረታት ሁሉ ስለሚከበሩ ነው። ነውር የሆኑ ነገሮችን ስለማያደርጉ ነው፡፡
ምንም እንኳን የሞራል እና በጎ እሴቶች ባለቤት ብንሆንም በዚያው ልክ ግን ብዙ ነውር የሆኑ ነገሮችን እናደርጋለን። ከመሬት ተነስቶ የአንድን ሰው ክብር መንካት ነውር ብቻ ሳይሆን ወንጀልም ጭምር ነው። ብዙ የክብር መገለጫ የሆኑ እሴቶች እንዳሉን ሁሉ፣ ብዙ ክብረ ነክ የሆኑ ድርጊቶችና ንግግሮችም አሉን። አሳዛኙ ነገር ግን እነዚህ ነውር ነገሮች የተማሩ በሚባሉ እና የመሠልጠን አርዓያ ሊሆኑ በሚገባቸው ሰዎች የሚባሉ መሆናቸው ነው፡፡
ለመሆኑ ግን ስድብ የጀግንነት መግለጫ ነው ወይስ የፍርሃት?
ስድብን ባሕል ያደረግነው ሁሉ ይመስላል። ምክንያቱም ተሳዳቢ ሰዎችን እንደ ደፋርና ጀግና የሚቆጥሩም አሉ። ተሰዳቢውን እንደ ተዋረደ አድርገው ሰዳቢውን እንደ ደፋር የሚቆጥሩ ሰዎች አሉ። የተዋረደው ግን ሰዳቢው ነው። መሳደብ ጀግንነት ሳይሆን ፍርሃት ነው። ማስተዋል የማይችሉ ሰዎች መገለጫ ነው። የሆነ ነገር ይመጣብኛል ብሎ የሚፈራ ሰው ነው የሚሳደብ።
መሳደብ በራስ ያለመተማመን ምልክት ነው። አንድ ሰው ትሑትና ትዕግስተኛ የሚሆነው በራሱ ሲተማመን ነው። በአንፃሩ ግልፍተኛና ወፈፌ የሚሆነው ደግሞ ተጠራጣሪ ሲሆን ነው። በትንሽ ነገር የበታችነት ስሜት ስለሚሰማው ነው። የሚሳደቡ ሰዎች ምናልባትም በውስጣቸው የሚረበሹበት ነገር ስላለ ነው። በውስጣቸው ቁስል ሲኖር ነው።
በአንፃሩ ትዕግስተኛ፣ አስተዋይና በሀሳብ የሚያምኑ ሰዎች ደግሞ በራሳቸው የሚተማመኑ ሲሆኑ ነው። ስቀው ሊያልፉት ሁሉ ይችላሉ። ስቆ ለማለፍ ደግሞ በጣም የተረጋጋ አሳቢነት ይጠይቃል። ያ የተሰደበበት ነገር እንደማይወክለው፣ ተሳዳቢው በራሱ ችግር የተሳደበ መሆኑን ያውቃል ማለት ነው። እንዲያውም ለተሳዳቢው ሰውየ ስብዕና ሊያዝን ይችላል። ‹‹ምን ሆኖ ይሆን?›› በሚል ለሕይወቱ ሊያዝንለት ይችላል። ምክንያቱም ዝም ብሎ ከመሬት ተነስቶ የሚሳደብ ሰው የሆነ ችግር አለበት ማለት ነው፡፡
በእንዲህ አይነት ማኅበረሰብ ውስጥ የሚያሳዝኑኝ ቀድመው የነቁና የሠለጠኑ ሰዎች ናቸው። የራሳቸውንም የሌላውንም ክብር ጠብቀው እየተንቀሳቀሱ ሳለ በአንዳንድ ባለጌዎች ግን ሊሰደቡ ይችላሉ። በዚህም ምክንያት የማያምኑበትን መደባደብም ሊገቡበት ይችላሉ ማለት ነው። በሥነ ሥርዓት የተቀመጠውን ሰው በስድብ ‹‹ወዲህ ጠጋ በል፣ ወዲያ ዞር በል….›› የሚል ይኖራል። በተለይም ሕጋዊ ያልሆነ አሠራርን የሚከተሉ ሰዎች ‹‹ለምን?›› ተብለን እንጠየቃለን ብለው ስለሚፈሩ በቁጣ እና በስድብ ይጀምራሉ።
በአንዳንድ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች የምታዘበው ነገር ደግሞ፤ አንዳንድ ባለጉዳይ ሆን ብሎም ይሁን ባለማወቅ አሠራሩ ከሚፈቅደው ውጭ አገልግሎት ለማግኘት ይጠይቅ ይሆናል። በዚህን ጊዜ አገልግሎት ማግኘት እንደማይችል በትሕትና መንገር ሲቻል በቁጣ እና በስድብ የሚናገሩ አሉ። ለምሳሌ ሰዓት አሳልፎ የመጣ ሰው፤ ሰዓቱ እንዳለፈና እንደማይቻል መንገር ሲቻል ‹‹የታባክ ቆይተህ ነው›› በሚል ስድብ እና ቁጣ ያመናጭቁታል። መከልከልንም እኮ በትሕትና መንገር ይቻላል፡፡
ይሄ ነገር ልማድ ከመሆኑ የተነሳ ባለጉዳዩም በትሕትና ካናገሩት ፊት የሰጡት ይመስለውና ከሕግና አሠራሩ ውጭ አገልግሎት ማግኘት ይጓጓል። እንደማይቻል በትሕትና ከነገሩት ለልመና ምቹ የሆኑ ይመስለዋል። ስለዚህ ቁርጡን እንዲያውቅ በቁጣ ይከለክሉታል ማለት ነው። ስለዚህ የሁሉም ችግር ነው፡፡
ስድብ የኋላቀርነት መገለጫ ነው! መሠልጠንን አለባበስ ላይ ብቻ አናድርገው! የሞራል እሴቶቻችንን እንጠቀም!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም