አሁን ያለንበት ዘመን ድንቃ ድንቅ ነገሮች ያሳየን ጀምሯል፡፡ አስደናቂ ታሪኮች፣ በዝና የምናውቃቸው እውነታዎች ፣ ክፉና በጎ ጉዳዮች ሁሉ ዛሬ ለጆሮና ዓይናችን ብርቅ አልሆኑም፡፡ ሁሉም በሚባልበት አግባብ ወደ እኛው ፈጥነው ይደርሳሉ፡፡ ዓለማችንን በአንድ መስኮት እያስተያየት ከአንድ ቤት ማዋል ማሳደር የጀመረው ደግሞ የቴክኖሎጂው ዕድገት ስለመሆኑ መካድ አይቻልም፡፡
ለጊዜው ሥልጣኔ ምስጋና ይግባውና ዛሬ ላይ በየትኛውም ዓለም ‹‹ኮሽ›› ያለ ነገር ሁሉ በአብዛኛው ሰው ጆሮ ሳይሰማ አያድርም፡፡ ሰላምና ጦርነቱ፣ ስፖርትና መዝናኛው፣ ሲኒማና ሙዚቃው ፣ አደጋው፣ ርሃቡ፣ ችግርና ደስታው ሁሉ የት ነው ሳይባል ለሁሉም ይታያል፣ ይሰማል። አሁንም ለቴክኖሎጂው ምስጋና ይድረስና እስከዛሬ ሳናይ ሳንሰማው ያለፈን የዓለማችን ሁነት የለም ለማለት ያስደፍራል፡፡
ይህን የዓለም ገጽታ በቅብብሎሽ እያዳረሱ ወደእኛ ከሚያካፍሉን የቴክኖሎጂ እጆች መሃል ብዘዎችን መጥራትና መዘርዘር ይቻላል፡፡ ከጥንት እስከዛሬ ከእኛው ጋር ያሉትን የቴሌቪዥን፣ የጋዜጣና የሬዲዮ አውታሮችን ጨምሮ የሌሎችም ውለታ በዋዛ የሚረሳ አይሆንም፡፡
ዛሬ ላይ በዘመናችን መረጃን በወቅቱና በጊዜው፣ በአፍታ ፍጥነት እያጣደፉ ለጆሯችን የሚያደርሱን በእጅጉ በርክተዋል፡፡ እንዲህ መሆኑ ስለምንም ጉዳይ ባዕድ እንዳንሆን የሚያሰላን ነውና አስፈለጊነቱ አጠያያቂ አይሆንም፡፡ ስለ መረጃ መጋቢዎቻችን ጉዳይ ስናነሳ ደግሞ አንድ ሁለት ብለን የምንዘረዝራቸው ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
እዚህ ላይ የመረጃ አውታሮቻችን ብዛትና አይነት እንዳለ ሆኖ ለማየትና ለመስማት የምንመርጣቸውን መለየቱ አንድም ብልህነት ሌላም ደግሞ ዕውቀት መሆኑን መጠቆም ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ቆም ብለን ማሰባችን ለሁላችንም ቢጠቅም እንጂ አይጎዳም፡፡
ስለምርጫ ጉዳይ ስናነሳ ነገሬ ብለን ስለምንከተላቸው የመረጃ ምንጮቻችን መነጋገሩ ይበጅ ይመስለኛል፡፡ አሁን ላይ በፌስ ቡክ፣ በቲክ ቶክና በዩ ቲዩብ ዕለት በዕለት የሚደርሱ መረጃዎች በርክተዋል፡፡ እነዚህ መረጃዎች በተንቀሳቃሽ ምስልና ድምጽ ታጅበው የሚቀርቡ ናቸውና በቀላሉ ዓይንና ጆሮን መማረካቸው አያጠያይቅም፡፡
ጠቃሚና አስፈላጊ የሚባሉ ጉዳዮችን የሚያስተላልፉት እንዳሉ ሆነው ከበጎነታቸው ጉዳታቸው የሚያመዝኑትም የበርካቶችን አእምሮ ለመቆጣጠር ጉልበቱ ተችሯቸዋል። ከሁሉም የሚገርመው ግን የእነሱ አጉል መረጃ መራገቡ ብቻ አይደለም፡፡ አስደናቂው ጉዳይ የወሬ ጫፋቸውን ይዘው ወሬውን የዱላ ቅብብሎሽ የሚያደርጉ ተከታዮቻቸው ልማድ እንጂ፡፡
እንዲህ አይነቶቹ የማህበራዊ ሚዲያ ተከታዮች የተላለፈውን መረጃ በወጉ የመመርመር ልምዱ ያላቸው አይመስልም፡፡ ጉዳዩ በርከት ያለ ተመልካች እንዳለው ሲያውቁ ተጨማሪ በመሆን ቁጥር ያበራክታሉ፡፡
በማህበራዊ ሚዲያው ተሞክሮ ፣ አንድን ጉዳይ መውደድ፣ የወደደዱትን ለሌሎች ማጋራትና ያጋሩትንም በራስ ገጽ ላይ መልሶ መለጠፍ የተለመደ ነው፡፡ አንድ ሰው ይህን ሁሉ መንገድ ሲያልፍ ግን እንዲህ ለማድረጉ የራሱ ምክንያትና መነሻ ይኖረዋል፡፡ የተላለፈው መልዕክትና፣ ምስል፣ አልያም ሙዚቃ በውስጡ የተለየ ትርጉም አስቀምጧል ማለት ነው፡፡
እንዲህ ባይሆን ከራሱ አልፎ ሌሎች እሱ ያየውን እንዲያዩለት፣ የተረዳውን እንዲረዱለት ባልፈለገ ነበር፡፡ ይህ እውነታ ግን በሁሉም የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ ይሠራል ማለት አይደለም፡፡ አንዳንዶች ጉዳዩን ብዙዎች መወደዳቸውን በመመልከት ብቻ የሌሎችን ጅራት የሚከተሉ ናቸው፡፡
እንዲህ አይነቶቹ የማህበራዊ ሚዲያው ሱሰኞች ስለሚለቀቁት መረጃዎች ጥቅምና ጉዳት የሚረዱ አይደሉም። ብዙዎች ‹‹ዕልል…›› ባሉበት ጉዳይ ድምቀት በመሆን የሚያጨበጭቡና ለሌሎች ዓላማ ግብ የሚሆኑ ናቸው። አብዛኞች አንድን መረጃ ሲያስተላልፉ በበቂ ምክንያት ነው፡፡ ለማን ፣ ለምንና እንዴት እንደሚያደርጉት ጭምር አይጠፋቸውም፡፡
እነሱን እንከተልን ባዮቹ ግን ጉዳዩን ከመውደድና ከማጋራት ባለፈ ስር የያዘ ዓላማ ላይኖራቸው ይችላል። አንዳንዴ በማህበራዊ ሚዲያው ሰፈር የሚያስደንቅ አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡ ድንገት አንዱ ይነሳና በሰውኛ ሀገር የእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፈ አንድ መልዕክት ይለጥፋል፡፡
ሃሳቡ ‹‹ገብቶናል ተረድተነዋል›› የሚሉ ጓደኞች እንደተለመደው ላይክ፣ ይሉትን ምልክት ይነኩለታል፡፡ የምልክቱን መደጋገም የሚያስተውሉ ሌሎች ደግሞ እነሱ ስላደረጉት ብቻ ከኋላ ይከተላሉ፡፡ በዚህ ብቻ አይበቃም። ከላይኩ ጀርባ ሼሩ ፣ ፖስቱ ሰብስክራይቡ ይግተለተላል። ኮሜንቱም አንዱ የሌላውን እየተከተለ ይዥጎደጎዳል፡፡
ይህ መልዕክት ምናልባትም የባለ ጉዳዩን ዓላማ ብቻ መሠረት ያደረገ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህን ጉዳይ በወጉ ተረድተው መሆን የሚገባውን የሚያደርጉት ግን በጣም ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡
በሌላ ጊዜ ደግሞ አንድ ሙዚቃ በጥቂት ሰዎች መራጭነት ተለይቶ ይለቀቃል፡፡ የዚህ ሙዚቃ ግጥም ሁሉም በእኩል በማይግባባበት ቋንቋ የተዘጋጀ ነው። የዜማው ስልት ግን ብዙሃኑን አድማጭ ከመቀጫው እያስነሳ ላስጨፍር ፣ ላወዛውዝ ይላል፡፡
ይህ ሙዚቃ ባጋጣሚ ጆሯቸው የደረሰ በእጅጉ ይወዱታል ፣ ይማረኩበታል፡፡ አንዳቸውም ግን የዘፈኑን የግጥም ይዘት አያውቁትም፡፡ ከማራኪ ዜማው የዘለለ አዝማቹን ፣ መልዕክቱን ፣ የእያንዳንዱን የስንኝ ትርጓሜ አይረዱትም፡፡ እንዲያም ሆኖ አብሮ መጫወት የፈለገ ጫፉን ይዞ ያንጎራጉራል፣ ይዘፍናል፡፡
አስገራሚው ጉዳይ እንዲህ መሆኑ ላይ አይደለም፡፡ የዘፈኑ ትርጓሜ ምን አልባትም ሰዎችን ነጥሎ የሚያነውር፣ ሀገርን የሚበጣብጥ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህን ሙዚቃ አብዝተን ወደድን የሚሉቱ አንዳንዶች ግን እንደለመዱት ፈጥነው በገጻቸው ላይ ይለጥፉታል፡፡
ሁኔታው የገባቸው ፣ ትርጉሙን የሚያውቁት በሁኔታው መገረማቸው አይቀርምና እንዴት? ብለው ይጠይቃሉ፡፡ የአድናቂ ነን ባዮቹ ምላሽ ግን እንደተለመደው ውሃ አያነሳም። ትርጉሙን ሳይሆን ሙዚቃውን ስለመውደዳቸው ብቻ እየዘረዘሩ ሊያስረዱ ይሞክራሉ፡፡
ምንግዜም ቢሆን እንዲህ አይነቶቹ የማህበራዊ ሚዲያው ልማደኞች ሳሩን አይቶ ገደሉን እንደረሳው ምስኪን በሬ መመሰላቸው አይቀሬ ነው፡፡ እንደነዷቸው ይነዳሉ፡፡ እንዳሏቸውም ይሰማሉ፡፡ ብዙዎቹ ሲያደርጉት እንደሚስተዋለው በሚዲያው ታዋቂ ናቸው የሚባሉ ሰዎችን በማየት ብቻ የሚከተሉ ናቸው፡፡
ታዋቂዎቹ ምንም ይበሉ ምን ለእነሱ ሁሌም ትክክል ናቸው፡፡ አንደበታቸው አይስትም፣ ቃላቸው አይሳሳትም። ምንጊዜም ከእነዚህ ሰዎች የሚተላለፈውን ቃል ፣ አልያም ጽሁፍ እስከ መጨረሻው ታግሰው አያዩትም።ወዳጆቻቸው ብቅ ባሉ ቁጥር የለመዱትን ላይክና ሼር ያንበሻብሿቸዋል፡፡
እርግጥ ነው የማህበራዊ ሚዲያውን ለበጎ ዓላማ ማዋል ለብዙሃኖቻችን ጠቃሚ ነው፡፡ ትናንትናን ከዓለማችን የቴክኖሎጂ መንገድ ርቀን ቆይተናልና ዛሬን በአንድ መስኮት መጋራታችን ‹‹እሰየው›› ያስብላል፡፡ እንዲህ ስንል ግን ያየን የሰማነውን ሁሉ እንዳሻን እናድርገው ማለታችን አይደለም፡፡
‹‹አንገት የተሠራው ዞሮ ለማየት ነው›› እንዲሉ ከድርጊት በፊት ማስተዋልና አርቆ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ያብረቀረቀ ሁሉ ወርቅ እንደማይሆን ተረድቶም ጣፋጩን ከመራሩ ሬት መለየት ግድ ይላል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያውን በወጉ መጠቀም አንድ ነገር ሆኖ ማንን እንደምንከተል፣ የቱን እንደምንመርጥ መለየት አዋቂነት ነው፡፡ ከሆነ በኋላ ‹‹አላወኩም ነበር ማለቱ ከትዝብትና ወቀሳ አያድንምና።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 17 ቀን 2016 ዓ.ም