ነጣቂው

ገዳም ሰፈር በአዲስ አበባ ከተማ በመሃል አራዳ ውስጥ የሚገኝ ጥንታዊ ሰፈር ነው። ገዳም ሰፈር ስያሜውንም ያገኘው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦት ጋር በመጡ ቄሳውስት ነው። ምንም እንኳን ሰያሜው የተረጋጋና ፀጥታ የሞላበተ ሰፈር እንደሆነ ቢያመላክተንም ሰፈሩ ግን በተቃራኒው የመጠጥ ቤቶች፤ የመዝናኛ ብዛት የሞላበት ምሽቱ ከቀኑ የበለጠ የሚደምቅበት ገዳምነቱን የረሳ ሰፈር ሆኗል።

ሰፈሩ ጥንታዊ እንደመሆኑ የጥንት ሰፈሮች አይነት መልካም ማህበራዊ ግንኙነት ያለው ትንሽ ትልቁ ተጋግዞ የሚኖርበት ደመቅ ያለ ሰፈር ነው። በእለቱ ከሰፈሩ የመዝናኛ ቤቶች መካከል በቅርቡ የተከፈተ አንድ አዲሰ ሆቴል በመኖሩ ነበር አቶ ብስራት መረሳና ባለቤታቸው ወይዘሮ ቀፀላ ጊዮርጊስ ወደ ሰፈሩ ያቀኑት።

ከመኖሪያ ሰፈራቸው ሰሚት ሰባ ሁለት ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ተነስተው በእለቱ የሚመረቀውን የወዳጃቸውን የወይዘሮ አፀዱ ሙላትን ሆቴል ምርቃት ለመታደምና የባለቤታቸው እህት ልጅ ምርቃት ላይ ለመገኘት ከቤታቸው አምሮባቸው የክት ልብሳቸውን ለባብሰው ነበር የወጡት።

በእለቱ ለተመራቂዋ ስጦታ ለመግዛትና በሆቴሉ ምርቃት ላይ የሚያወጡትን ገንዘብ አስራ አንድ ሺ ብር ይዘው ነበር። ሁሉንም ጉዳያቸውን አጠናቀው ወደ ቤት ለመነሳት በተሰናዱበት ወቅት አቶ አስማረ ትንሽ ማምሸት ስለፈልጉ ባለቤታቸውንና ሌሎች የፕሮግራሙን ታዳሚዎቸ በወንድማቸው መኪና ሸኝተው ወደ አንድ ግሮሰሪ ለመዝናናት ይገባሉ።

ከባለቤታቸው ከተለዩበት ከምሽቱ አንድ ሰአት አካባቢ ጀምሮ እስከ ምሽቱ አራት ሰአት ድረስ በሰላም ሲዘናኑ ከቆዩ በኋላ ከጓደኞቻቸው ጋር ተለያይተው ላዳ ታከሲ ይዘው ወደ ቤታቸው ለመሄድ በተዘጋጁበት ወቅት ነበር ያላሰቡት ውርጅብኝ የወረደባቸው።

ወደ ታሪኩ ከመግባታችን በፊት የዚህን ታሪክ መነሻ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መዝገብ የተመለከትኩት ሲሆን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት ስለአደረጉልን ቀና ትበብር ከልቤ ማመስገን እወዳለሁ።

ያላሰቡት ውርጅብኝ የወረደባቸው አባት

ነገሩ እንዲህ ነው ባለታሪካችን አቶ ብስራት አስማረ መረሳ ይባላሉ። ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ናቸው። ቤተሰባቸውን አክባሪ ለፍቶ አዳሪ የሚባሉ አባት ናቸው። ለወትሮው ብዙ የማይስቁ ጭምት ያሉ ትሁት የሚባሉ አይነት ሰው ናቸው። ልክ መጠጥ ሲቀማምሱ ግን ያ ዝም ያደረጋቸው አይነጥላ ይገፈፍና ተጫዋች ሳቂታ ፈገግታቸው የማይጠገብ አይነት ሰው ይሆናሉ።

ይህን የሚያውቁትም ቤተሰቦቻቸው ከእለታት አንድ ቀን የምትታይ ፈገግታቸውን በመናፈቅ ወጣ ዘና ልበል ሲሉ በሙሉ ፈቃደኝነት ነው የሚስማሙት። በእለቱ በነበሩት የሆቴል ምርቃትም ሆነ የባለቤታቸው እህት ልጅ ምርቃት ላይ መጠጥ የቀረበ ቢሆንም በይሉንታ ተይዘው የፈለጉትን ያህል ስላልጠጡ ነበር ከቤተሰባቸው ኋላ ቆየት ብለው ወደ መጠጥ ቤት የገቡት።

በገቡበት መጠጥ ቤት እየተጫወቱ ሲጠጡና ሲከፍሉ ከፊት ለፊታቸው ተቀምጠው የነበሩ ወጣቶች በትኩረት ሲከታተሏቸው ነበር።

ልክ ጨርሰው መውጣታቸውንና ከጓደኞቻ ቸው መለያየታቸውን ሲመለከቱ ተከትለዋቸው ወጡ። ሰአቱ መምሸቱና እግረኛ መንገዱ ላይ አለመኖሩን ከተመለከቱ በኋላ ከኋላቸው በማነቅ መንገድ ላይ ይጥሏቸዋል። ሰውየውም ራሳቸውን ለመከላከል ባደረጉት ሙከራ ላይ ሶሰቱ ወጣቶች ተረባርበው ይደበድባቸዋል። አኚህ የማይበገሩ አባት የሞት ሽረት ትግላቸውን ሲያካሂዱ አንዱ ወጣት በጎኑ የሻጠውን ጩቤ በማውጣት አንገታቸው ላይ ይሰካዋል።

ልክ ወጣቱ በያዘው ስለት ወግቶ እንዳደከማቸው የተገነዘቡት ሌሎቹ ወጣቶች በአቶ ብስራት ኪስ ያገኙትን ገንዘብ ዘርፈው ሊያመልጡ ሲሞከሩ የተመለከተች በአካባቢው የነበረች አንድ ሴተኛ አዳሪ ባሰማችው ጩኸት ተደናግጠው ወደ ተለያየ አቅጣጫ ተበተኑ።

የሴትዮዋን ጩኸት የሰሙት ሰዎች ወደ ቦታው ሲደርሱ አቶ ብስራት አንገታቸው ላይ ተውግተው ከሞት ጋር ትንቅንቅ ገጥመው ነበር። ይህንን የተመለከቱት ሰዎች የተጠቂውን ነፍስ ለማትረፍ በፍጥነት ወደ የካቲት አስራ ሁለት ሆስፒታል ቢያደርሷቸወም ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል።

ቤታቸው የፈረሰው የሟች ባለቤት

የሟች ብስራት አስማረ መረሳ ባለቤት ወይዘሮ ቀፀላ ጊዮርጊስ ደስታ ሀገር ሰላም ብለው በሀገር ልብሳቸው አሸብረቀው የክት ሽቷቸውን ከደበቁበት አውጥተው እሳቸውን ባላቸውንም ቀብተው በፈገግታ ነበር ከቤታቸው የወጡት። ከዛ ጉዳያቸወን ፈጽመው ለመመለስ ሲሹ አቶ በስራት ማምሸት በመፈለጋቸው እሳቸው ቀድመው ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ።

ቤት ገብተው ቡና አቀራርበው ቤቱን ሞቀ ሞቅ አድርገው የባለቤታቸውን መምጣት ቢጠባበቁም ትንሽ ቆይቼ እመጣለሁ ያሉት ባላቸው የውሃ ሽታ ሆነው ይቀራሉ። ግራ የተጋቡት እኚህ ሴት የባለቤታቸው ስልክ ላይ ቢሞክሩም ስልኩ ዝግ በመሆኑ የተነሳ በጭንቀት ወደ ሌሎች በአካባቢው ይገኛሉ ወዳሉት ሰው ሁሉ ይደውላሉ።

የተለያየ ቦታ ስልክ ቢሞክሩም ያልተ ሳካላቸው እናት ቁጭ ብለው ደጅ ደጁን እያዩ እኩለ ሌሊት ተቃረበ። ይሄን ጊዜ ነው እንግዲህ የእጅ ስልካቸው ጠርቶ የባለቤታቸውን ማረፍ የተረዱት።

ወይዘሮ ቀፀላ “መጀመሪያ ጉዳዩን ስሰማ ሰማይ ምድሩ ነበር የተደበላለቀብኝ ሀምሌ አራት ሁለት ሺ አስራ አራት ዓመተ ምህረት በሰላም ከመኖሪያ ሰፈራችን ሰሚት ወደ ገዳም ሰፈር የመጣነው። የአንድ ወዳጃችን የሆኑ ወይዘሮ አፀዱ ሙላት ደስታ የሆቴል ምርቃት ላይ ለመታደም ሲሆን እግረ መንገድ የእህቴን የመፅሄት ልጅ ምርቃት ተካፋይ በመሆን አምሽተን እኔና የወንድሜ ሚስት አንድ ሰአት ከሃያ ሶስት አካባቢ በባለቤቴ ወንድም በሄኖክ መኪና ወደ ቤት ሄድን” “በእለቱ ባለቤቴ አስራ አንድ ሺ ብር ይዞ ነበር። ምነው ብሩን ወስደው እሱን በተውልኝ ነበር? ምነው ቤቴን ከሚያፈርሱ አባ ወራዬን ከሚቀሙኝ የያዘውን ወስደው ቢምሩልኝ ?̋ ̋ ብለዋል ሳግ በቆራረጠው አንደበት።

የፖሊስ ምርመራ

የድረሱልኝ ጥሪን ሰምተው ተጎጂውን ወደ ሆስፒታል ያደረሱት ሰዎች የሞከሩት ነፍስ የማዳን ጥረት ሳይሰካላቸው በመቅረቱ የተነሳ ለፖሊስ ያመለክታሉ። ፖሊስም ጥቆማውን በመቀበል ወንጀሉ ወደተፈፀመበት አካባቢ ሲያቀኑ ተጎጂው የተወጋበትን ስለት ያገኛሉ። ከዚህም በተጨማሪ የአይን እማኝዋን ምስክርነት በመቀበል አንደኛ ተጠረጣሪን ለመያዝ እንቀስቃሴ ያደርጋሉ።

በእለቱ አንደኛ ተጠርጣሪ የሆነውን ሚካኤል ሳምሶን ለማግኘት ብዙም ሳይቸገሩ የዘረፈውን ሰባት ሺ ብር እንደያዘ ይይዙታል። ተጠትጣሪውን በቁጥጥር ስር ካዋሉ በኋላ ገብረ አበሮቹን አንድ በአንድ እንዲጠቁም በማድረግ ሶሰቱንም ወንጀል ፈፃሚዎችን በቁጥጥር ስር አውለዋል።

የወንጀሉ አይነት ከባድ የውንብድና ወንጀል ሲሆን አንደኛ ተከሳሽ ሚካኤል ሳምሶን ፤ ሁለተኛ ተከሳሽ ተክለ ኃይማኖት ወንዴ ፤ ሶስተኛ ተከሳሽ እዮብ የሻነው የተባሉ ወንጀል ፈፃሚዎች የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ አድርጓል።

የወንጀለኞቹ የእምነት ክህደት ቃል

አንደኛ ተከሳሽ ሚካኤል ሳምሶን ፤ ሁለተኛ ተከሳሽ ተክለ ኃይማኖት ወንዴ ፤ ሶስተኛ ተከሳሽ እዮብ የሻነው ተወልደው ያደጉት እዛው ገዳም ሰፈር አካባቢ ነው። ከልጅነት እስከ እውቀት የሚተዋወቁት እነዚህ ጓደኛሞች በትምህርትም ፊደል ከመቁጠር የዘለለ ብዙም የገፉ አልነበሩም። ወጣቶቹ ቀን ጫት ቤት መሽገው በመዋል ሲመሽ ስራዬ ብለው የያዙትን የንጥቂያ ተግባር ለመፈፀም ከዋሉበት ጉሬ ብቅ ብቅ ይላሉ።

በየእለቱ ባይሳካላቸውም ለሱሳቸው ማስታገሻ የሚሆን ያህል ግን ሳይነጥቁ አይውሉም ነበር። በእለቱም ለሰፈሩ እንግዳ የሆኑት አቶ ብስራት አስማረ ላይ ዓይናቸውን ጥለው ሲከታተሏቸው እንዳመሹ ይናገራሉ።

“በእለቱ ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ወደ ግሮሰሪው ሲገቡ ነበር ያየናቸው። ባለቤታቸው ጮክ ብለው ‘ራስህን ጠብቅ ‘ ሲሏቸው ነበር ተከትለናቸው ወደ መጠጥ ቤት የገባነው። እዛ ሰዎች አግኝተው ሲጨዋወቱ ካመሹ በኋላ ሲወጡ ተከትለናቸው በመውጣት በቀላሉ የያዙትን ተቀብለን ልንሸኛቸው አስበን ነበር። እሳቸው ግን በጣም ሊታገሉን ሲሞከሩ ነበረ በያዝነው ስለት ወግተን የያዙትን ገንዘብ ዘርፈን ያመለጥናቸው ̋ በማለት የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

“ጥፋተኞች ነን ሱስ አስገድዶን ለሱሳችን ማስታገሻ ገንዘብ ልንዘርፍ አንጂ ልንገላቸው አላሰብንም ነበር” ብለዋል በተፀፀተ አንደበት።

ፖሊስ በቦታው የተገኘውን ማስረጃ፤ የሰው ምስክሮችን ቃል፤ የተጠርጣሪውን የእምነት ክህደት ቃል አንድ ላይ በማድረግ ወንጀሉ ከባድ የውንብደና ደንጀል ድርጊት እንደሆነ አመላክቶ ያጠናቀረውን መረጃ በኢትዮጵያ የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፍትህ ሚኒስቴር ጠቅላላ አቃቤ ሕግ ልኳል።

 ውሳኔ

 አቃቤ ሕጉም በመሠረተው ክስ መሠረት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ሁለተኛ ምድብ ችሎት ጉዳዩን ተመልክቶ ውሳኔ ለመስጠት ለመጋቢት ሃያ ስምንት ሁለት ሺ አስራ አምስት ዓመተ ምህረት ይቀጥራል።

ወንጀል ፈፃሚዎቹ በተከሰሱበት ከባድ የውንብድና ወንጀል በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ሶስተኛ ምደብ ችሎት በ28/7/2015 ዓ.ም በዋለው ችሎት ክስና ማስረጃውን ከሕግ ጋር አገናዝቦ ይህንን ውሳኔ አስተላልፏል።

1ኛ ተከሳሽ በአስራ አራት ዓመት ፅኑ አስራት

2ኛ ተከሳሽ በአስር ዓመት ፅኑ አስራት

3ኛ ተከሳሽ በስድስት ዓመት ፅኑ አስራት እንዲቀጡ ተወስኗል።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You