ባለፈው ሐሙስ ነው። ማታ 11፡50 አካባቢ የመንግሥት ሠራተኞች ማመላለሻ አውቶብስ (ፐብሊክ ሰርቪስ) ለመያዝ ወደ መቆሚያ ቦታው እየሄድኩ ነው። አራት ኪሎ የሚገኘው አራዳ ክፍለ ከተማ በር ላይ ባለው የአውቶብስ መቆሚያ ቦታ ላይ አንድ ዕድሜው በአሥራዎቹ መጀመሪያ ሊሆን የሚችል ልጅ የእግረኛ መንገዱ ላይ ወድቋል። ፖሊሶችን ጨምሮ ዙሪያውን በሰዎች ተከቧል።
አጠገቡ ስደርስ በአፍና አፍንጫው ደም የሚመስል ነገር ይወጣል። እኔም እንደማንኛውም ሰው እያዘንኩ ‹‹ምን ሆኖ ይሆን?›› እያልኩ ምን እንደማግዝ ግራ ገብቶኝ ሳለ፤ አንዲት ሴትዮ ከመጣሁበት ተቃራኒ አቅጣጫ በኩል ሰዎችን እየገፋፋች የወደቀው ልጅ ጋ ደረሰች። ወዲያውኑ ለተሰበሰበው ሰው ወደየጉዳያቸው እንዲሄዱ መናገር ጀመረች። በቁጣ እና በመሰላቸት ድምጸት ልጁ እንደዚያ የሚያደርገው አውቆ መሆኑን ተናገረች። ቃሉን በትክክል ባልሰማትም የሆነ የሚጠጡት ነገር መኖሩን ተናገረች፤ በአፋቸው የሚወጣው ደም እንዲመስል ማለት ነው። እንዲህ የሚያደርጉት ገንዘብ እንዲሰበሰብላቸው ነው እያለች ምክንያቱን ተናገረች።
እሷ እንደዚያ ስትናገር እኔ ተናደድኩ። እንዴት አይነት ጭካኔ ነው ልጁ እንዲህ ወድቆ፣ በአፍና አፍንጫው ደም እየወጣ ምንም ያልመሰላት? ብየ ተገረምኩ። የተሰበሰቡት ሰዎች እንዳይሸወዱ አስጠንቅቃ መንገዷን ቀጠለች። እኔም ግራ እየተጋባሁ ትንሽ አለፍ ብየ ቆምኩ። የሚሆነውን ነገር እያየሁ ሳለ ሰዎች አንድ አንድ እያሉ ሄደው አለቁ። የነበሩት ፖሊሶችም ሄዱ። ልጁ ብቻውን ተኝቶ ቀረ። አጠገቡ ደግሞ ቆማ የምትለምን ሌላ ልጅ አለች።
አሁንም ግራ እየተጋባሁ አንድ የማውቀው የሰርቪስ ተጠቃሚ መጣ። ያየሁትን ነገር ሳስረዳው ‹‹አጠገቡ ያለችው ልጅ ‹አውቆ ነው› እያለች ነበር›› አለኝ። ነገርየው መለመኛ ይሆን እንዴ? እያልኩ መጠራጠር ጀመርኩ። በዙሪያዬ ያሉ ሰዎችም እንዲህ አይነት ማጭበርበሪያዎች መኖራቸውን እየነገሩኝ የማታለል የልመና አይነቶች ላይ ስናወራ ቆየን።
በዚህ ሁኔታ ላይ እያለን ከቆምነው ውስጥ አንደኛው ‹‹እዩት እዩት እዩት ሲነሳ›› አለን። ዞር ብየ ሳይ ቀስ ብሎ ተነስቶ ተቀመጠ፣ አሁንም ቀስ ብሎ ተነሳ። ዙሪያ ገባውን አይቶ ወደ አስፋልቱ ገባ። እንደማንኛውም ሰው እየተራመደ አስፋልቱን ከተሻገረ በኋላ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ቅድስት ማርያም ወጣ።
እንዲህ አይነት ማጭበርበር በዓይኔ ሳይ የመጀመሪያዬ ነው። እግራቸውን፣ እጃቸውንና የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻቸውን እንደ ተዋናይ ‹‹ሜክ አፕ›› በመቀባት በአካል ጉዳተኛ ስም የሚያጭበረብሩ እንዳሉ ሰምቼ አውቃለሁ፤ በመገናኛ ብዙኃንም ዜና ተሰርቶበት ያውቃል። እንዲህ በዓይኔ ማየቴ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ስለሆነ ብዙ ሲያስገርመኝ ቆየ።
ወዲያውኑ ወደ አዕምሮዬ የመጣው በእነዚህ ሰዎች ምክንያት ልመና የማጭበርበር ብቻ ተደርጎ መታየቱ ነው። በትክክል ችግር ያጋጠማቸው ሰዎች አጋዥ ማጣታቸው ነው። አውቆ ነው ተብለው መታለፋቸው ነው። በእነዚህ አጭበርባሪዎች ምክንያት ሰብዓዊነት መጎዳቱ ነው። ሰዎችን ተጠራጣሪ እንዲሆኑ ማድረጉ ነው።
‹‹ልመና ከልክል›› የሚባል እናቶች ሲሉ የምሰማው አባባል አለ። ትልልቅ ሰዎች እገዛ ያስፈልጋቸዋል። አብሯቸው ወጣት ሰው ካለ የሚያግዛቸው ሌላ ሰው አይኖርም። ያ አብሯቸው ያለው ወጣት ሰው ሸክም ወይም ሌላ ነገር ካላገዛቸው ‹‹ልመና ከልክል›› ይሉታል። ምክንያቱም እሱ አለ በሚል ሌሎች ሰዎችን ‹‹አግዙኝ›› ብለው መለመን ሊቸገሩ ነው። በእነርሱ ዓውድ ልመና ማለት ‹‹በእንተ ስሟ ለማርያም›› እያሉ ምፅዋት መጠየቅ ብቻ አይደለም። እገዛ መጠየቅን ልመና ይሉታል። ለምሳሌ ሸክም አሸክሙኝ ለማለት ‹‹ለምኜ ነው ያሸከሙኝ›› ይላሉ። ሰዎችን የሆነ ነገር እንዳያደርጉ ለማባበል ‹‹እባክህ ልለምንህ›› ይላሉ።
እናም እነዚህ አጭበርባሪዎች እገዛና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ‹‹ልመና ከልክል›› ይሆናሉ። ሰዎች ለተቸገሩ ሰዎች ድጋፍ እንዳያደርጉ እየከለከሉ ነው። በእነዚህ አጭበርባሪዎች ምክንያት ተጠራጣሪ እንሆናለን።
እነዚህ አጭበርባሪ ለማኞች የደፈጣ ለማኝ ናቸው። የደፈጣ ውጊያ እንዳለ ሁሉ የደፈጣ ለማኝም ኖረ ማለት ነው። የደፈጣ ውጊያ ማለት የግድ ከወንዝ ወይም ከዛፍ ወይም ከድንጋይ በአጠቃላይ ከሆነ ነገር ሥር መደበቅ ማለት ብቻ አይደለም። የደፈጣ ውጊያ ማለት የማታለያና የማጭበርበሪያ መንገዶችንም መጠቀም ነው። ሴት (ንፁሃን) በመምሰል፣ ነፍሰ ጡር በመምሰል፣ አካል ጉዳተኛ በመምሰል በአጠቃላይ በብዙ ማታለያ መንገዶች ጠላት ላይ ጉዳት ያደርሳሉ።
ልክ እንደዚህ ሁሉ የደፈጣ ልመናም ተጀምሯል። በተለምዶ ‹‹ሿሿ›› የሚባለው ታክሲ ውስጥ የሚደረገው ማጭበርበር የዚህ አካል ነው። ሰውነትን የተለያየ አይነት ቀለም በመቀባት መለመን የደፈጣ ልመና መሆኑ ነው። እነዚህ ሰዎች ከማጭበርበራቸውም ባሻገር እገዛ በሚያስፈልጋቸው ሰዎች ላይ እምነት እንዲጠፋ እያደረጉ ነው። ምክንያቱም በትክክል ችግር አጋጥሟቸው መንገድ ላይ የሚወድቁ ሰዎችም አሉ።
የዚህኛው ገጠመኝ ተቃራኒ የሆነ ሌላ ገጠመኝ ልጨምር። እኔ ያጋጠመኝን የነገርኳት አንዲት የሥራ ባልደረባዬ ሌላ ገጠመኝ ነገረችኝ። ገጠመኙን ሳጠቃልለው የሚከተለው ነው።
አራት ኪሎ የሚገኘው ንብ ባንክ ሕንጻ ፊት ለፊት ካሉት ጁስ ቤቶች አጠገብ ነው። አንድ በወጣትነት ዕድሜ ላይ የሚገኝ ሰው ድንገት አዙሮት ተሽከርካሪዎች ከሚያልፉበት አፋልት ላይ ወደቀ። ከእጁ ላይ ሰነዶች ተበተኑ። ሰነዶችን ሰባስበው ሲያዩት የትምህርት ማስረጃዎች ናቸው። አራት ኪሎ አደባባዩ ጋ ከሚገኘው ክፍት የሥራ ማስታወቂያ ቦርድ ላይ ሥራ ሲፈልግ ቆይቶ እያለፈ ነበር። ልጁ የወደቀው ለረጅም ሰዓታት ምግብ ስላልበላ ከድካም ጋር ረሃብ ፀንቶበት ነው። ሲያነሱት ሰውነቱ ሁሉ ይንቀጠቀጣል። የአንደኛው ጁስ ቤት ባለቤቶች ወደ ውስጥ አስገብተው የሚበላ ነገር ሰጥተውት እየተሻለው ሄደ።
ይህ ክስተት ውስጥን ያላውሳል። ይህ በድካምና ረሃብ የወደቀ ልጅ በትክክልም እገዛ ያስፈልገዋል። እገዛ የተደረገለት ምናልባትም አጋዦች ችግሩ እውነተኛ መሆኑን ስላረጋገጡ ይሆናል፤ ምናልባትም አጭበርባሪዎች መኖራቸውን ስላላወቁ ይሆናል። የትምህርት ማስረጃዎቹን ስላዩ ሥራ ፈላጊ መሆኑ አሳዝኗቸው ይሆናል። ምንም ይሁን ምን ግን ያ ልጅ በዚያች ሰዓት እገዛ ያስፈልገዋል። ያ ልጅ ነገ ትልቅ ደረጃ ሊደርስ ይችላል፤ ምናልባትም በዚች ሀገር ላይ ትልቅ ሚና የሚኖረው ሊሆን ይችላል።
የተቸገረውም አጋዥ ቤተሰብ የሌለው ስለሆነ ብቻ ላይሆን ይችላል። በአጭሩ በዚያች ቅጽበት ተቸግሯል። ከሩቅ አካባቢ የመጣ ከሆነ ምግብ ሳይበላ ቆይቶ ይሆናል፤ ለታክሲ የተሰጠችውን ገንዘብ ምናልባትም ‹‹ሥራ እናስገኝልሃለን›› ለሚሉ አጭበርባሪ ደላላዎች ከፍሎት ይሆናል። ያም ሆነ ይህ ያ ልጅ በዚያች ቅጽበት እገዛ አስፈልጎት ከከፍተኛ ጉዳት ወይም ከሞት ዳነ ማለት ነው። ይህ የሆነው ሰብዓዊነት በተሰማቸው ሰዎች ነው።
የእነዚህ የደፈጣ ለማኞች ትልቅ ጉዳት እንዲህ አይነቱን የሰብዓዊነት መተጋገዝ ጥላሸት የሚቀባ መሆኑ ነው። መተማመን እንዳይኖር ማድረጉ ነው። ተጠራጣሪ እንዲንሆን ማድረጉ ነው። መቼም ድጋፍ ለማድረግ የጤና ምርመራ ልናደርግለት አንችልም።
ምንም እንኳን አጭበርባሪዎች በዚህ ትዝብት ተፀፅተው ይተውታል ባይባልም በእነርሱ ምክንያት ግን ሰብዓዊነታችን እንዳይጎድፍ። የተደረሰባቸውንም መቀጣጫ ማድረግና ማጋለጥ ይለመድ። ዋናው ነገር ግን በአጭበርባሪዎች ምክንያት የተቸገሩትን እንዳናልፍ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2016