በዓለም ላይ ከአንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን በላይ የመገጣጠሚያ ቁርጥማት፣ በጡንቻ እና በተያያዥ ችግሮች (አርትራይተስ) የተያዙ ሰዎች መኖራቸውን የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል። ምንም እንኳን በሀገራችን ያለው ታማሚ ይህ ያህል ነው ብሎ ለመናገር ጥናቶች ባይደረጉም ቁጥሩ ቀላል እንዳልሆነ ግን ይገመታል።
አርትራይተስ በመገጣጠሚያ አካል ውስጥ የሚፈጠር ብግነት(የጉልበት አንጓ) ሲሆን፤ መገለጫዎቹም፣ ሕመም መሰማት፣ እብጠት እና ተፈጥሮአዊ ቅርጽን ማጣት (Deformity) ናቸው። ከዚሁ ችግር ጋር ተያይዞም በመገጣጠሚያዎች ውስጥ ያሉትን አጥንቶች፣ ካርቲሌጅ ወይም ደጋፊ ቲሹዎች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ከአንድ መቶ በላይ የአርትራይተስ (ቁርጥማት) ዓይነቶች ያሉ ሲሆን ፤በሦስት ዋና ምድቦች ይከፈላሉ። እነርሱም በበሽታ አምጪ ተህዋስ የሚከሰቱ፣ ብግነታዊ አርትራይተስ ወይም ቁርጥማት እና ጫናዊ አርትራይስ ናቸው። እነዚህም በውስጣቸው ብዙ ዓይነት የቁርጥማት አይነቶችን ይይዛሉ። በጣም የተለመደው የአርትራይተስ አይነት፤ ጫናዊ አርትራይተስ ነው። ሉፕስ፣ሪህ እና ሩማቶይድ አርትራተስ ተጨማሪ የተለመዱ የቁርጥማት አይነቶች ናቸው።
ስለዚህም ታካሚዎች ማድረግ ከሚጠበቅባቸው ነገሮች መካከል፤ በሐኪም የታዘዙ መድኃኒቶችን በአግባቡ መውሰድ፣ እንደ ፋይበር ያሉ ፀረ ብግነት ምግቦችን የያዙ የተመጣጠነ አመጋገብ መከተል፣ የመገጣጠሚያ ሕመም ከመቀነስ ባሻገር ጤናማ ክብደት እንዲኖር ይረዳሉ። ሌላው መፍትሔ ከታሸጉ ምግቦች፣ ከመጠን በላይ የሆነ ስኳር እና የጨው መጠን አለመጠቀም ነው። እንዲሁም ሲጋራ ከማጨስ እና አልኮል መጠጣት መቆጠብም ያስፈልጋል። ከነዚህ ጎን ለጎንም መገጣጠሚያዎች ላይ ያለውን ጫና ለማቃለል ጤናማ ክብደት እንዲኖር መጣር ይገባል።
በተቻለ መጠንም ዘወትር የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በማድረግ ወይም ደግሞ ከተቻለ በቀን 15 ደቂቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን መከወን፤ በጡንቻዎች ውስጥ ያለው የእንቅስቃሴ መጠን ያሻሽላል። በተጨማሪም ለእጅ አንጓ፣ ለክርን፣ ለዳሌ እና ለጉልበቶች ቀላል እንቅስቃሴ ማድረግ ብሎም ሁል ጊዜ ለስላሳ እና ምቹ ጨማዎችን ማድረግ፣ ብስክሌት መንዳት፣ ዋና እና የእግር ጉዞ ማድረግም ለመገጣጠሚያ እና ተያያዥ የሆኑት ሕመሞችን ለመቀነስ እንደሚረዱ ይገለጻል።
የመገጣጠሚያ አያያዥ ጡንቻዎችን እና የኢሚዩኒቲ ችግሮች ምልክቶችን፣ አማራጭ የሕክምና አይነቶችን፣ በሰው ልጆች የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ላይ የሚያመጡት ተጽዕኖ ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ በጥቅምት ወር ይከበራል። ስለዚህም ስለ አርትራይተስ ግለሰቦችን በማስተማር፣ በሽታውን በጊዜ የማወቅ አስፈላጊነትን በማጉላት እና ውጤታማ አስተዳደርን ለመደገፍ አስተዋፅዖ ያደርጋል። ችግሮች በደንብ ወደሚታወቅበት፣ የተጎዱት ሕይወታቸውን በተሟላ ሁኔታ ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ እና እንክብካቤ ወደሚያገኙበት ሁኔታ አንድ እርምጃ ያቀርባል ተብሎ ይታመናል።
በየዓመቱ በፈረንጆቹ ኦክቶበር 12 የሚከበረው የአርትራይተርስ ቀን፤ ዘንድሮም ‹‹አርትራይተስን መረዳት፣ በጊዜ መታከም ፣ የተሻለ ሕይወት›› በሚል መሪ ቃል ተከብሮ አልፏል። ማክበር ያስፈለገበት ምክንያትም በሽታው በሁሉም እድሜ ክልል ያለ የማኅበረሰብ ክፍልን እንደሚያጠቃ እና በጊዜ ወደ ሕክምና ቦታ በማቅናት በበሽታው የተያዙ ግለሰቦችን ሕይወት ለማሻሻል ወሳኝ እና አስፈላጊ እርምጃ መሆኑን ለማሳየት እንደሆነ ተጠቁሟል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የመገጣጠሚያ ቁርጥማት፣ የጡንቻ እና የኢሚዩኒቲ ችግሮችን የሚያክም ‹‹ሩሁም የሩማቶሎጂ እና የውስጥ ደዌ ስፔሻሊቲ ክሊኒክ›› የተሰኘ ተቋም በይፋ በተመረቀበት ወቅት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ27 ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ‹የአርትራይተስ ቀን› ግንዛቤ ለመስጠት ተችሏል። በመርሐ ግብሩ ላይም የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ብርሃነ መስቀል ጠና፣ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሲሳይ ስርጉና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝዋል።
የክሊኒኩ መሥራች ዶክተር ብርሃኑ ደመላሽ እንደገለጹት ‹ሩሁም የሩማቶሎጂ እና የውስጥ ደዌ ስፔሻሊቲ ክሊኒክ› በሀገራችን ያለውን የመገጣጠሚያ፣ አያያዥ ጡንቻዎች እና ችግሮች ሕክምና ክፍተት የመሙላትን አላማ አንግቦ ወደ ሥራ ገብቷል። ክሊኒኩ “ጥራት እና ክብካቤ የተሞላበት ሕክምና” (Royalty Care) በሚል መርህ፤ ሳይንሳዊ መሠረት ያለው ሕክምናን በመስጠት፤ ወደ ፊት ሁሉም የሩማቶሎጂ ችግሮች በሀገር ውስጥ በተሟላ ሁኔታ ለመስጠት የተቋቋመ ሀገር በቀል የሕክምና ተቋም ለመሆን እንደሚሠራም አስታውቀዋል።
በተለይም ክሊኒኩ በጤና ዘርፉ ላይ የሚታየውን ሥራ አጥነት እና የልዩ ሕክምና አገልግሎት ተደራሽነት ውስንነት ለመፍታት እየሠራ እንደሚገኝ በመግለጽ፤ ከ20 በላይ ለሚሆኑ ቋሚና የትርፍ ሰዓት ሠራተኞች የሥራ እድል መፍጠር ችሏል። ምንም እንኳን በሽታው በሁሉም ሠው ላይ የሚከሰት ይሁን እንጂ በተለይም በወጣቶች ላይ ለሚከሰተው የቁርጥማት እና የሪህ በሽታ ለማከም ተቋሙ ዝግጅቱን አጠናቆ በይፋ ሥራ መጀመሩን ዶክተር ብርሃኑ አብራርተዋል።
የሩማቶሎጂ ባለሙያዎችን ለማፍራት የሰው ኃይል ላይ ከታች ጀምሮ እስካላይኛው መዋቅር መሠራት እንዳለበት ሩማሌቶሊጂስቱ ዶክተር ዘነበ መላኩ ይናገራሉ። ምናልባትም ይህንን ለማድረግ ዓመታትን ይፍጅ እንጂ መንግሥት፣ የግሉ ዘርፍ እና ሌሎችም በጥምረት መሥራት ከተቻለ ለውጦችን ማምጣት ይቻላል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ የሩማቶሎጂ ባለሙያ እና የታካሚዎች ቁጥር ፍጹም በሚባል ደረጃ የሚመጣጠን አይደለም። በኢትዮጵያ ብቻ ያሉት ባለሙያዎች ሦስት ብቻ ናቸው። በአሁን ወቅት ሕክምናው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ የሚሠጥ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ፤ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ሥራውን መሥራት ይገባል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም የሕክምናው ወድ መሆን እና ምርመራዎች ውደ ውጭ ተልከው የሚደረጉ መሆናቸውን ከግንዛቤ በማስገባት የዲያግኖስቲክ አገልግሎቶች መሻሻል እንዳለባቸው ይጠቁማሉ። ትልቅ ግብዓት የሚፈልግ በመሆኑም የጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ፋርማሲዩቲካል አገልግሎት እና መሠል ተቋማት ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩበት ይገባል። የግሉ ዘርፍም የበኩሉን አስተዋፅዖ ቢያደርግ ችግሩን ማቅለል ይቻላል። ‹‹እንደ ሀገር ትልቅ ተግዳሮት አለ። ›› ያሉት ዶክተር መላኩ፤ መድኃኒቶች እንደ ልብ እና በአይነት የመገኘታቸው ነገር አናሳ በመሆኑ ለታካሚዎች ይህንን ያገናዘበ ሥራ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 8 ቀን 2016 ዓ.ም