ክፍት የሥራ ቀያሪ ማስታወቂያዎች

በ2010 ዓ.ም የለውጡ ሰሞን ይመስለኛል። በወቅቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮምኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር የነበሩት፤ በኋላም የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው የነበሩት ዶክተር ጌታቸው ድንቁ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሁኔታ ላይ ጽሑፍ አቅርበው ነበር፡፡ በቅርስ ጥናት ጥበቃ ባለሥልጣን አዳራሽ በተደረገው በዚያ ውይይት ብዙ ሀሳቦች የተነሱ ቢሆንም፤ ዶክተር ጌታቸው ያነሱት አንድ ነጥብ ግን አሁን ድረስ አይረሳኝም፡፡

የዶክተር ጌታቸው ሀሳብ ሲጠቃለል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ ችግር የባለሙያዎች አንድ ተቋም ውስጥ አለመቆየት ነው፡፡ ከዚህም ሲከፋ ደግሞ ሙያቸውን ቀይረው በሌላ የተሻለ ቢዝነስ ሊያስገኝ በሚችል ነገር የሚሰማሩ መሆናቸው ነው፡፡ የትኛው የተሻለ ይከፍላል በሚል ከተቋም ተቋም መዘዋወር የተለመደ እና መደበኛ አሰራር ሆኗል፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ሙያው ተገቢውን ክብር አያገኝም፤ የባለሙያዎቹ ፍላጎትም ከሙያው ይልቅ የተሻለ ክፍያ ማግኘትን ነው፡፡

እርሳቸው ምሳሌ አድርገው የጠቀሱት የጋዜጠኝነትን ሙያ ነው፡፡ የሠለጠኑ አገራት ውስጥ ያሉ ዓለም አቀፍ ዝና ያላቸውን የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ጋዜጠኞችን ምሳሌ ሲጠቅሱ፤ ከ30 ዓመት በታች የሆነ ጋዜጠኛ አይገኝም፡፡ በአንድ መገናኛ ብዙኃን ውስጥ ለረጅም ዓመታት ይቆያሉ፡፡ በአንድ በሆነ ነገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከታወቁ በዚያው ነው የሚቀጥሉት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ከ30 ዓመት በላይ የሆኑ ጋዜጠኞችን ማግኘት ዕድሉ ጠባብ ነው፤ ምክንያቱም በሙያው ትንሽ ከሰሩ ወደሌላ ዘርፍ

 ይሄዳሉ፤ ቢዝነስ የሚያስገኝ ነገር ፍለጋ ይሄዳሉ፡፡

የዶክተር ጌታቸውን ጥናታዊ ጽሑፍ ምሳሌ ያነሳሁት ለአንድ ሙያ ብቻ ነው፡፡ በዚህ መሰረት ከሄድን ኢትዮጵያ ውስጥ በብዙ ሙያዎች ውስጥ ተመሳሳይ ችግር ነው ያለው፡፡ ከተቋም ተቋም፣ ከሙያ ሙያ መቀያየር የተለመደ ነው፡፡ እንዲያውም አንድ መስሪያ ቤት ውስጥ መቆየት እንደ ስንፍና ነው የሚታየው፡፡ እየቀያየሩ ማየት እንደ ፋሽን ተደርጓል፡፡ ይሄ ማለት ዋናው ጉዳይ የሙያው ሳይሆን ባለሙያው የሚያገኘው ገንዘብ ሆኗል ማለት ነው፡፡

የሚወጡ ክፍት የሥራ ማስታወቂያዎችን ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፡፡ ለሥራ ፈላጊዎች ሳይሆን ለሥራ ቀያሪዎች የሚወጡ ናቸው፡፡ ክፍት የሥራ ማስታወቂያው ላይ የሚገለጹት ክፍት የሥራ መደቦች በመካከለኛ እና በከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው። ይሄ ማለት ክፍት የሥራ ማስታወቂያውን ካወጣው ተቋም ውስጥ በዚያ መደብ የለቀቁ ሠራተኞች አሉ ማለት ነው፡፡ ከተቋም ወደ ተቋም እንዲህ አይነት ዝውውር ሲበዛ ሁሉም ተቋማት ለክፍት የሥራ መደቦች ማስታወቂያ ያወጣሉ ማለት ነው፡፡

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሥራ ቀያሪዎች ራሱ ይጸጸታሉ፡፡ አንድ ተቋም ደሞዝ ጨመረ ሲባል ወደዚያ ተቋም ይሄዳሉ፡፡ ልክ ሄደው እንደተቀጠሩ ያ የለቀቁት ተቋም ደግሞ አዲስ ከገቡበት የተሻለ አድርጎ ይጨምራል፤ ደግሞ እንደገና ቀልባቸው ወደዚያ ያማትራል፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ የባለሙያው ትኩረት ሙያው ላይ ሳይሆን የተቋማትን የደሞዝና ጥቅማጥቅም ስኬል ማጥናት ይሆናል ማለት ነው። በዚህ ሁሉ ውስጥ ሥራ እና ሙያ ይበደላል ማለት ነው፡፡ ሥራ እና ሙያ እንዴት እንደሚበደል ማሳያዎችን እንጥቀስ፡፡ ይህን ለመታዘብ በተለይም የጋዜጠኝነት ሙያ ምቹ ነው፡፡

ወደ አንድ ተቋም መረጃ ለማግኘት እንደውላለን፡፡ ጉዳዩ ይመለከተዋል የሚባለውን ባለሙያ ያገናኙናል። ባለሙያው ሲጠየቁ፤ ‹‹አዲስ የገባሁ ስለሆንኩ ገና ነኝ›› ይላሉ፡፡ ይለምዳሉ ተብሎ ሲጠበቅ ደግሞ፤ ምናልባትም ተቀይረው ይገኙ ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በአንድ ተቋም ውስጥ የሆነ ዘርፍ ላይ ባለሙያ አሉ እንበል፡፡ ባለሙያው በአንድ ወቅት መረጃ ይሰጣሉ፡፡ ያንኑ ጉዳይ ምን ላይ እንደደረሰ ለመጠየቅ ሲደወል ‹‹እኔ አይደለሁም! ሌላ ሰው ነው!›› በማለት ከዚያ ሙያ እንደለቀቁ ይናገራሉ።አዲስ የገባው ደግሞ ገና አልተላመደምና መረጃው የለኝም ሊል ይችላል፡፡

ይሄ ነገር ከታች ባሉ ባለሙያዎች ብቻ የሚታይ ችግር አይደለም፡፡ በከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ላይ ራሱ በተደጋጋሚ የምናየው ነው፡፡ በሌሎች አገራት የአንድ ሚኒስትር ስም ከአገሪቱ ጋር ብራንድ መስሎ ይቆያል፡፡ ለምሳሌ የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲባል ሰርጌይ ላቭሮቭ የሚለው ቃል ቶሎ ወደ አዕምሮ ይመጣል፡፡ የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲባል ሳሚ ሹክሪህ የሚለው ስም ቶሎ ይታወሳል፡፡ በእርግጥ ይህ የሆነው ለረጅም ዓመታት መቆየታቸው ብቻ ሳይሆን ስማቸው የሚጠራበት አጋጣሚ ብዙ ስለሆነ ነው፡፡

እንደ ቢቢሲ፣ አልጀዚራ፣ ሲ ኤን ኤን፣ ፍራንስ 24… የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን ልብ ብላችሁ ይሆናል፡፡ ጋዜጠኞቻቸው ከረጅም ዓመታት በፊት የነበሩ ናቸው፡፡ በዚያ ሙያ ላይ ልምድና በርካታ ገጠመኞችን አካብተዋል፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች ብዙ ልምድ ስላላቸው ለተቋሙም ሆነ ለአገራቸው ትልቅ አስተዋፅዖ ያበረክታሉ ማለት ነው፡፡

ለረጅም ዓመታት የሚቆይባቸው ሙያዎች ምናልባት መምሕርነት እና ሕክምና ይመስሉኛል። መምሕርነትም ቢሆን ከግል ወደ መንግሥት፣ ከመንግሥት ወደ ግል ትምህርት ቤቶች መቀያየር አለበት፡፡ ከዚያ ውጭ ያሉት ሙያዎች ግን መቀያየር ዋና መገለጫቸው ሆኗል፡፡ እንዲያውም ጓደኛሞች ሲገናኙ ‹‹አሁን የት ነህ?›› ተባብለው ይጠያየቃሉ፡፡ መቀየር እንዳለበት ይታመናል ማለት ነው፡፡ ‹‹አሁንም እዚያው ነህ?›› በማለት አለመቀየሬን በግርምት ይታዘባሉ፡፡ ይሄ ነገር ልማድ ሆነና አለመቀየር እንዲያውም እንደ ስንፍና ሊታይ ነው፡፡

በእርግጥ እነዚህ ነገሮች የሆኑበት ምክንያት የኑሮ ጉዳይ ነው፡፡ እንደሚታወቀው አገራችን አሁንም ድሃ ናት፡፡ ተቋማት ለባለሙያዎቻቸው በቂ የሚባል ደሞዝና ጥቅማጥቅም ሊከፍሉ አይችሉም፡፡ በዚያ ላይ ተመሳሳይ የሆነ አሰራር የለም፡፡ በተመሳሳይ ሙያ የተለያየ ክፍያ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ባለሙያው ያንኑ ሥራ እየሰራ ከሙያ እኩዮቹ በታች ሲከፈለው ቅያሪ መፈለጉ አይቀሬ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ እየሰራ ያለበት ሙያው ለመኖር በቂ የሆነ ክፍያ የማያገኝበት ከሆነ ሌላ የቢዝነስ ሥራ ይሰራል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ጎበዝ የሚባል እና ተማሪዎች የሚወዱት የፊዚክስ መምህር አለ እንበል፡፡ ይህ መምህር በሚከፈለው ደሞዝ ቤተሰቡን ማስተዳደር ካልቻለ እና ሌላ የቢዝነስ አማራጭ ካገኘ መምህርነቱን ይተወዋል። አለበለዚያ ደግሞ ከመምህርነቱ ጋር ለማስኬድ ይሞክራል፤ ይህ ደግሞ ሙያውን ይበድላል ማለት ነው፡፡

ይህ የባለሙያ መሥሪያ ቤት መቀያየር ሙያን መበደል ነው፡፡ ሥራን እና ደንበኛን ማጉላላት ነው። ስለዚህ እንደ ባለሙያም፣ እንደ ዜጋም፣ እንደ መንግሥትም ሊታሰብበት ይገባል!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2016

Recommended For You