ነውርነት – በሕጋዊነት

ምሳ ሰአት ነው። በርካታ ታዳሚ ከምግብ ቤቱ ቅጥር ተገኝቷል። ወጪ ገቢው በሚተራመስበት ሰፊ አጸድ ቦታ ይዘው የሚመገቡ ፣ ያዘዙትን ምግብ በተስፋ የሚጠብቁ ብዙ ናቸው። ከእነሱ ጠረጴዛ የቅርብ ርቀት የሚገኘው የእጅ መታጠቢያ እንደልማዱ በሰዎች አጀብ ተከቧል። በልተው የጨረሱና ገና ለመብላት ያሰቡ ተመጋቢዎች ፊትና ኋላ ተሰልፈውበታል ።

በልተው ከጨረሱት አብዛኞቹ እጃቸውን እየታጠቡ ለሌሎቹ ይለቃሉ። አንዳንዶች ግን ከኋላቸው የቆሙትን ፍጹም የረሱ ይመስላል። እጃቸውን ቀስ እያሉ ያሻሉ ። ውሃ እየጨመሩ መልሰው መላልሰው ይታጠባሉ ። ጠባቂዎቹ አሁንም እንደቆሙ ናቸው።

እጅ ታጣቢዎቹ ጨርሰዋል ሲባል ደግመው ሳሙና ያነሳሉ። ውሀውን እየጨመሩ፣ በዝግታ እየታጠቡ ይቆያሉ። አንዳንዱ በትዕግስት ይጠብቃል። ሌላው በንዴት ይቁነጠነጣል ። እነሱ ግን የማንም ስሜት ምናቸውም አይደለም ። ይባስ ካቀረቀሩበት ቀና ብለው ከፊት ለፊታቸው መስታወት መልካቸውን አየት፣ ጸጉራቸውን ነካ፣ነካ እያደረጉ በዝግታ ይጎነበሳሉ።

ይህን ሁሉ ጨርሰው መለስ ባሉ ጊዜ ከኋላቸው የተሰለፈውን ወረፋ ጠባቂ ማየታቸው አይቀርም። እነሱ ግን ድንጋጤና ሀፍረት አይነካቸውም። ከበባውን ጥሰው ፣ ሰልፉን አቋርጠው እየነጠሩ ይሄዳሉ ።

ወዳጆቼ ! አሁንም ከምግብ ቤቱ ሰፊ ግቢ አልወጣሁም ። ‹‹ዓይን አያሳየው የለም ›› እንዲሉ ሆኖ በየቀኑ የማስተውለን ጉዳይ ዛሬም እንዲሁ እየታዘብኩ ነው ። ሰውዬው ምሳውን በልቶ እንደጨረሰ ወደ እጅ መታጠቢያው አምርቷል። ውሀውን ከፍቶ እጆቹን ከታጠበ በኋላ በዛ መከረኛ መስታወት ፊቱን አየት አድርጎ መልሶ አቀርቅሯል ።

ዛሬም በግቢው ዙሪያ የተሰበሰቡ በርካታ እንግዶች የምሳ ገበታ ይዘዋል። አዲስ የሚገቡ ደንበኞችም የሚያሻቸውን አዘው በመጠባበቅ ላይ ናቸው። የሰውዬው ወደ መታጠቢያው ማቀርቀር ለእጅ ጽዳት ብቻ አልሆነም። ውሀ በአፉ ሞልቶ ጉሮሮውን ለማጽዳት እየሞከረ ነው።

ይህን እንደጨረሰ ከአፉ የቀረውን የምግብ ቅንጣት በጣቶቹ እያጸዳ አፍንጫውን ይናፈጣል። መናፈጥ ሲባል እንዲህ በዋዛ አይምሰላችሁ ። ‹‹ እንፍ፣ እንፍ ፣ እንፍ….. ›› እየደጋገመ ። ወዲያው በእጁ የያዘውን ነውር ከፊት መታጠቢያው አዝረክርኮ መልሶ ጉሮሮውን ያፀዳል።

ደረቱን ይዞ ወደ አፍንጫው የሚስበው ትንፋሽ ታዲያ በዝምታ የሚወጣ አይደለም። ደጋግሞ ‹‹አክ አክ ..›› ሲለው ለተመጋቢው ጆሮ ፈጥኖ የመድረስ ኃይል አለው ። ድርጊቱን አስተውለው ሁኔታው ያልተመቻቸው እንግዶች ፊታቸው ሲኮሳተር ይታያሉ። የዓይናቸውን እውነት በትዝብት ብቻ ማለፍ የማይሹት መብላት የጀመሩትን ከእጃቸው ጥለው ቦታውን ለቀው ይሄዳሉ። ሰውዬው ግን ይቀጥላል። ‹‹እንፍ ፣ እንፍ፣ እንፍ ››

እንግዲህ ይህ የሚሆነው ሰዎች ምግብ በሚበሉበት ፣ የብዙኃን መገናኛ ውስጥ ነው ። እንዲህ አይነት ዓመለኞች ይህን ድርጊት ሲፈጽሙ ያሉበትን፣ የቆሙበትን ስፍራ የሚያስቡት አይመስልም ። ክፉ ልምዳቸውን ቀረብ ብሎ የሚነግራቸው ስለማይኖርም በስህተት መንገዳቸው ሲመላለሱ ይስተዋላል።

አንዳንዴ ደጋግመን የምንፈጽመው ልማድ ነውር መሆኑን የሚጠቁመን ከሌለ ትክክል ነን ብለን ልንቀጥልበት የሚያግደን የለም። አስተውላችሁ ከሆነ አንዳንድ የመስሪያ ቤት መጸዳጃዎች የስልክ መነጋገሪያ ቦታዎች እየሆኑ ነው ።

በተለይ እነዚህ ስፍራዎች ንጽህናቸው የተጠበቀ ከሆነ በእጃቸው ስልክ የያዙ ሰዎች ያዘወትሯቸዋል። እንዲህ መሆኑ ምናልባት የሌሎችን ሰራተኞች የሥራ መንፈስ ላለመረበሽ ይሆናል። አልያም ሚስጥር ነክ የሆኑ ጉዳዮችን አርቆ ለማውራት ጭምር ። እንዲህ ማሰቡ ጨርሶ አያስከፋም ። ለሥራ ባልደረቦች ሰላም ተጨንቆ አማራጭ መጠቀም የሚያስመሰግን ነው ።

ይህ እውነታ የሚደነቅ ሆኖ የመጠቀሚያ ቦታው ለዚህ ዓላማ አለመታሰቡ ደግሞ ሌሎችን እንዳይረብሽ ሊታሰብበት ይገባል ። እዚህ ላይ ‹‹ሌሎች›› የሚለው ቃል የመጸዳጃ ቤቱ ተጠቃሚዎች በሚል ይታሰብልኝ።

አዎ! በዚህ ስፍራ የመጀመሪያ መብት ያላቸው የመጸዳጃ ቤቱ ተጠቃሚዎች ናቸው። ስፍራውን ሊገለገሉበት ሲመጡ በዙሪያቸው ሰዎች መኖራቸውን አይተው ሊሸማቀቁ አይገባም። ግልጹን እናውራ ከተባለ ብዙ ጊዜ ስልክ የሚያወሩ ሰዎች መጸዳጃዎችን መምረጣቸው የተጠቃሚዎችን የቆይታ ጊዜ የሚያሻማ ነው።

እንደ እኔ ዕምነት ስልኩን የሚያወራው ወይም በዝምታ የሚያዳምጠው ሰው ‹‹ሄደ አልሄደ›› በሚል ተጠቃሚው መሳቀቅ አይገባውም። በመጸዳጃው እንዳሻው የመጣበትን ፈጽሞ ለመውጣት ነጻነቱ ሊኖረው ይገባል እንጂ ።

የመጸዳጃ ቤቱን ጉዳይ ካነሳነው አይቀር የጥቂት ጽዳት ሰራተኞችን ልማድም ጠቆም ማድረጉ አይከፋም። የጽዳት ሰራተኞች ሁሌም የመጸዳጃ ቤቶችን ንጽህና ለመጠበቅ በእጅጉ የሚተጉ ናቸው። የእንጀራ ጉዳይ ሆኖባቸው እንጂ የአንዳንድ ተጠቃሚዎች ያልተገባ ልማድ ከእነሱ አልፎ ለሌሎች ጭምር እንደሚያበሽቅ አናጣውም። እነሱ ሁሌም ግዴታቸውን ለመወጣት የሚያደርጉት ጥረት በእጅጉ ያስመሰግናቸዋል።

አንዳንዴ ግን አንዳንድ የጽዳት ሰራተኞች ስራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ከስፍራው መራቅን አይሹም። በየአፍታው ለማጽዳት እንዲያመቻቸው ይመስላል የመጸዳጃ ቤቶቹን የመግቢያ በሮች አይለቁም። እንደውም አንዳንዴ ጥሩ ወንበር ይዘው ከበራፉ ተቀምጠው መዋል ምርጫቸው ይሆናል ።

ችግር የሚሆነው የእነሱ ተቀምጦ መታየት አይደለም። አሁንም መጸዳጃውን መጠቀም የሚሻ ሰው ቢኖር እነሱን አልፎ ለመግባት ይቸገራል። ከዚህ ባለፈ ወደ ውስጥ ዘልቆ የልቡን መሻት ለመከወን ሙከራው ነውር መስሎ ሊታየው ሁሉ ይችላል። ተጠቃሚው ለጊዜው ‹‹ይቅርብኝ›› ብሎ ቢተወው እንኳን ሰራተኞቹ ለአፍታ ከስፍራው ዞር ካላሉ ተቸግሮ መዋሉ አይቀሬ ይሆናል ።

እንግዲህ እንዲህ አይነቶቹ ልማዶች ቀላል የሚመስሉንና በየዕለቱ የምናያቸው ስህተቶች ናቸው። ልማዶቹ ከዚህም ባለፈ ነውር ብለን ስያሜ ብንሰጣቸው የሚበዛባቸው አይሆንም። እነዚህ አጓጉል ጉዳዮች በአንድም በሌላም በሌሎች የሚፈጸሙ አልያም እኛው የምናደርጋቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ነውር መሆናቸውን ልቦናችን ቢያውቅም ደፍረን እንደምንፈጽመው ሁሉ ቆርጠን ለመተው የምንቸገርባቸው ይሆናሉ።

መቼም ከእስከዛሬው ልምዳችን በማህበረሰቡ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የትኛው በጎና ነውር መሆኑ አይጠፋንም ። ብዙ ጊዜ በቸልተኝነት ንቅን የምንተዋቸው ድርጊቶች ግን ከመተዛዘብ አልፎ የሌሎችን ሥነ ልቦና እስከ መጉዳት ይሄዳሉ።

ነውርነትን ህጋዊ ባደረግነው ቁጥር ትክክል የሆንን መስሎን ለሌሎች ክፉ አርአያ እንሆናለን። እንዲህ በሆነ ጊዜ ራስ ወዳድነት ይበረታል። ስህተቶች ሳይታረሙ እንዲጓዙ ያስገድዳል ። ይህ እንዳይሆን ከድርጊት በፊት ቆም ብለን ማሰቡ አይከፋም። አስቀድሞ ማሰብ መተሳሰቡ ለሁላችንም ይበጃልና አበቃሁ !

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 3/2016

Recommended For You