የሀገር ተረካቢዎች ውጤት ምን ይነግረናል?

የትምህርት ሚኒስቴር ከትናንት በስቲያ የ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ተፈታኞችን ውጤት ይፋ አድርጓል። ውጤቱ አስደንጋጭ ነው። ከግማሽ በላይ (50 በመቶ) ያመጡት 3 ነጥብ 2 በመቶ ብቻ ናቸው ማለት እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም። ከተፈተኑት 845 ሺህ 188 ተማሪዎች ውስጥ ከ800 ሺህ በላይ የሚሆኑት የፈተናውን ግማሽ እንኳን አላመጡም የተባሉ ናቸው። ከግማሽ በላይ ያመጡት በቁጥር 27 ሺህ 267 ብቻ ናቸው ተብሏል።

በትምህርት ቤቶች ሲታይ ደግሞ፤ ፈተና ካስፈተኑ 3 ሺህ 106 ትምህርት ቤቶች ውስጥ አንድ ሺህ 328 ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ አላሳለፉም። በመቶኛ ሲታይ ፈተና ካስፈተኑ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 42 በመቶ ያህሉ አንድ እንኳን ተማሪ 50 በመቶ ማምጣት አልቻለም ማለት ነው። የማለፊያ ነጥብ ለጊዜው ባይወሰንም በግማሽ ቢያዝ (ምናልባትም ማለፊያው ይሄው ሊሆን ይችላል) ከአንድ ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች አንድ ተማሪ እንኳን አላሳለፉም ማለት ነው። ይህ ለምን ሆነ የሚለው በትልቁ ሊያሳስበን ይገባል።

አስታውሳለሁ ባለፈው ዓመት የትምህርት ሚኒስቴር መግለጫ ሲሰጥ በዚሁ ጉዳይ ላይ ትዝብት ጽፌ ነበር። የትዝብቴ ጥቅል ሃሳብ ትምህርት ሚኒስቴር የዘረዘራቸውን ምክንያቶች ትኩረት እንዲሰጣቸው ነበር። የተሻለ ውጤት ካስመዘገቡ ትምህርት ቤቶች ልምድ እንዲወሰድ ነበር። ምናልባት በአንድ ዓመት ሁሉም ነገር ላይሳካ ስለሚችል ለሚቀጥሉት ዓመታት ግን ልምድ ሊወሰድ ይገባል።

የዘንድሮው ውጤት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የመሻሻል ሳይሆን የመባባስ ምልክት ነው የታየው። ትምህርት ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ፤ በዜሮ ነጥብ ዜሮ አንድ በመቶም ቢሆን ማሽቆልቆል ነው የታየው። መሻሻል ሲገባን መባባስ እንዳይሆን አሁንም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። 97 በመቶ የሚሆን ተማሪ አላለፈም ብቻ ሳይሆን አብዛኞቹ ከመቶው ከ26 በታች ያመጡ ናቸው ተብሏል። እንግዲህ አስቡት! ብሔራዊ ፈተና የምርጫ ጥያቄ ነው፤ አንድ ምንም ያልተማረ ሰው ከመንገድ ላይ አስገብቶ ከአራቱ አማራጮች አንዱን አጥቁረው ተብሎ ቢሰጠው እንኳን ከመቶው 20 ምናምን ማግኘቱ አይቀርም። እንግዲህ እነዚህ ተማሪዎች ከዚህ አልተሻሉም ማለት ነው።

3 በመቶ ብቻ የሚሆን ተማሪ ከ50 በመቶ በላይ ያመጣው ለምንድነው? የሚለው ጥያቄ፤ እነዚህን ጥያቄዎች ይወልዳል።

ምናልባት ውጤት በዚህ መንገድ በዝርዝር መግለጽ ስለተጀመረ ይሆን? ከዚህ በፊት በነበረው አሰራር ጥቅል ውጤቱ ብቻ ይነገር ስለነበር ይሆን? ትምህርት ሚኒስቴር የፈተና ሥርቆትን ለማስቀረት በጀመረው አዲስ አሰራር ከአካባቢያቸው ርቀው በመሄዳቸው ተማሪዎች ተደናግጠው ይሆን? ከዚህ በፊት በነበረው አሰራር በፈተና ሥርቆትና በኩረጃ ብዙ ተማሪ ስለሚያልፍ እና አሁን ያ ልማድ ስለቀረ ይሆን? እንዲያ ከሆነ ብቃት ያላቸው ተማሪዎች ከዚህ በፊትም ቢሆን ምናልባትም ከ3 በመቶ አይበልጡም ነበር ማለት ነው።

ምናልባት ባለፉት ዓመታት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና በብዙ አካባቢዎች በነበሩ የፀጥታ ችግሮች የመማር ማስተማር ሂደት ስለተስተጓጎለ ይሆን? የ12ኛ ክፍል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና የሚወጣው በብዛት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቶችን በማጠቃለል ነው። ባለፉት ዓመታት ሁለተኛ ደረጃን በአግባቡ ያልተማሩ ስለሆኑ ይሆን?

ምናልባት ከዚህ በፊት በነበረው የትምህርት ሥርዓት ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ በሚገባ ስላልተማሩ ይሆን? አንድ ተማሪ ጎበዝ ተማሪ ሊሆን የሚችለው ከታች ጀምሮ በያዘው መሠረት ነው። በተለይም በገጠር አካባቢዎች የመዋዕለ ሕጻናት ትምህርት ቤቶች አልነበሩም። ተማሪዎች ፊደል መቁጠር የሚጀምሩት ከአንደኛ ክፍል ነው። ትምህርት ሚኒስቴር ከዚህ በፊት እንደገለጸው እስከ አራተኛ ክፍል ድረስ ምንም መጻፍና ማንበብ የማይችሉ ተማሪዎች አሉ። እንዲህ ዓይነት ተማሪዎች እንደምንም ተገፍተው 12ኛ ክፍል ሊደርሱ ይችላሉ። አንዳንዶቹም በተለመደው ኩረጃ እና ከ2008 ዓ.ም በኋላ ደግሞ ግልጽ በሆነ የፈተና ሥርቆት ያልፋሉ። እነዚያ አሰራሮች ስለቀሩ ሊሆን ይችላል እንዲህ አይነት አስደንጋጭ ውጤት መታየት የጀመረው።

ያም ሆነ ይህ የተመዘገበው ውጤት እንደ ዜጋ ትምህርት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ልንሰጥ እንደሚገባ የሚያሳይ ነው። አለበለዚያ ሥልጣኔን ማሰብ ከንቱ ነው የሚሆነው። የነገ የልጅ ልጆቻንን ኢትዮጵያ ማበላሸት ነው። የተማረ ዜጋ የሌላት ሀገር ልናስረክብ ነው። አሁን ላይ የምናያቸው ችግሮች የተፈጠሩት የሰለጠነ ዜጋ ባለመሆናችን መሆኑ በተደጋጋሚ የተወቀሰ ነው። በዚህ ሁኔታ በቀጣይም የተማረ ዜጋ የሌለባት ሀገር ልትሆን ነው ማለት ነው።

አሁናዊ ሁኔታችን ልብ ካልነው እንዲያውም ከዚህም የከፋ ሁኔታ ሊያጋጥመን ይችላል። ጭራሽ መጻፍና ማንበብ የማይችል ትውልድ ይኖረናል። በብዙ የሀገራችን አካባቢዎች በጦርነት እና በሰፈር ሽፍቶች ምክንያት ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል። ትምህርት ቤት መሆን የነበረባቸው ታዳጊዎች በከተሞች ግንብ እና አጥር ሥር ወዳድቀዋል። በየምግብ ቤቶች በር ላይ ፍርፋሪ ይለምናሉ። እነዚህ ልጆች የነገ ሀገር ተረካቢዎች ዜጎች ናቸው። በክፉም ይሁን በደግ በሀገሪቱ ሁኔታ ላይ የሚሳተፉ እነዚህ የዛሬ ልጆች የነገ ወጣቶችና ጎልማሶች ናቸው።

እንደ ዜጋ የትምህርት አመለካከት ላይ ችግር አለብን። ተማሪን ማብቃት የሚቻለው በትምህርት ቤት ብቻ አይደለም፤ ወላጆች ከፍተኛ ሚና አላቸው። ከዚህ በፊት በነበረን የትዝብት ጽሑፍ ‹‹ወላጆችም ይማሩ›› ብለን ነበር። ከትልልቅ ከተሞች ውጭ ባለው ማህበረሰብ ውስጥ አሁንም ለትምህርት ትኩረት የማይሰጥ አለ። ልጆች ከትምህርት ቤት መልስ በቂ የማንበቢያ ጊዜ እና ሁኔታ አያገኙም። እነዚህ ልጆች የሚወዳደሩት በቤታቸው ጭምር መምህር ከሚቀጠርላቸው ተማሪዎች ጋር ነው። ያንን ማድረግ ባይቻል እንኳን ልጆችን በሆነ ባልሆነው ከትምህርት ቤት ማስቀረትና የማንበቢያ ጊዜ አለመስጠት ዛሬም አለና ይህም ሊታሰብበት ይገባል።

በትምህርት ሚኒስቴር በኩልም መታሰብ ያለበት ነገር የትምህርት ጥራት በፈተና ብቻ አይመጣም። ብዙ ተማሪዎች ወደቁ ማለት የትምህርት ጥራት ተጠበቀ ማለት አይደለም፤ እንዲያ ከሆነ የትምህርት ጥራት ሳይሆን የፈተና ጥራት ነው። ትምህርቱን በጥራት ከተማሩ ሀገር አቀፍ ፈተናውን ባያልፉ እንኳን ትምህርት አላቸው። ስለዚህ ለፈተናው የተሰጠውን ትኩረት ያህል በቂ የትምህርት ዝግጅት ለማያገኙ አካባቢዎችም ትኩረት መሰጠት አለበት።

ቀጣይ ተፈታኝ ተማሪዎች ደግሞ ከዚህ መማር አለባቸው እንላለን። አብዛኞቹ ውጤቶች የሚገኙት በግል ጥረት ነው። የጦርነት ችግር ባለባቸው አካባቢዎችም የጥይት ድምጽ እየሰሙ ተፈትነው ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችም አሉና ከእነርሱም መማር ያስፈልጋል።

በአጠቃላይ፤ የተገኘው ውጤት እንደ ተማሪም፣ እንደ ወላጅም፣ እንደ መንግሥትም ትምህርት ላይ ብዙ መሥራት እንደሚገባ የሚያሳይ ነውና ይታሰብበት!

 ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን መስከረም 30/2016

Recommended For You